የሰው ልጅ ከፍራፍሬ ለቀማ እና አደን ተግባራት ወጥቶ የተረጋጋ የግብርና ሕይወቱን ሲጀምር በቋሚነት መስፈር እንደጀመረ ይነገራል። ከዚህም በመነሳት ነበር የጥንታዊ ስልጣኔዎች ወንዞችን ተከትለው የተመሰረቱት። ለአብነት በየሎው ወንዝ ላይ የተመሰረተው የጥንታዊው ቻይና ስልጣኔ፣ በኢንደስ ወንዝ ላይ የተመሰረተው የሕንድ ስልጣኔ፣ በትግሪስ እና ኤፍራተስ ወንዞች መካከል የበቀለው የሜሶፖታሚያ ስልጣኔ፣ እንዲሁም የግብፁ የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ ተጠቃሽ ናቸው።
የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ ያበበ፣ ከዓለም ጥንታዊ ከሚባሉ ስልጣኔዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን ግብፅ እና ኩሽ የተባሉ አፍሪካዊ ስልጣኔዎችን ያበቀለ ነበር። የእርሻ ስራ መጀመርን አስታከው በሸለቆው መሀል የሰፈሩት ሕዝቦች የየራሳቸውን ግን ተመጋጋቢ ስልጣኔዎች በመገንባት ለዓለማችን ስልጣኔ መሰረት የጣሉ ብርቱ፣ ጥበበኛ እና ስልጡን ሕዝቦች ነበሩ። እናም በኩር በታሪክ አምዷ የአባይ ሸለቆው ስልጣኔዎችን ዋና ዋና አበርክቶዎች በወፍ በረር ትቃኛለች፣ መልካም ንባብ!
ከቅድመ ዓለም በፊት ከ4000 እስከ 3000 ባሉት ጊዜያት በሸለቆው መሀል ካበቡት ስልጣኔዎች መካከል የአባይ ወንዝ ስጦታ የተባለላትን የጥንታዊት ግብፅ ስልጣኔን እናገኛለን። ግብፅ አባይ ከመነሻው ይዞላት በሚመጣው ውሃ እና ለም አፈር ሕልውናዋ የተመሰረተ ነገር ግን አባይን ለታላቅ ስልጣኔ የተጠቀመችበት ብቸኛ ሀገር ናት። ለዚህም ይመስላል ሄሮዶተስ ግብፅ “የአባይ ስጦታ ናት” ብሎ እስከመጥራት የተገደደው። ስለሆነም የጥንታዊት ግብፅ ስልጣኔን በመቃኘት ስንጀምር፣ አስገራሚውን የስልጣኔ ቱሩፋቶች እናገኛለን። የዚህ ስልጣኔ ባለቤት ሕዝብ የራሱ የሆነ ስነ ጥበብ፣ ኪነ ሕንፃ፣ ሀይማኖት እና የሕይወት ዘይቤ ያለው ውስብስብ ማህበረሰብ ፈጥሯል።
የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ በታሪክ ውስጥ በዓለም ጥንታዊ ከሚባሉ ሰልጣኔዎች መካከል አንዱ ነው። በታችኛው የአባይ ወንዝ አካባቢ በሱዳን ከ3200 ቅ.ዓ እስከ 1069 ቅ.ዓ ድረስ ያበበ ስልጣኔ ነው።
የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ በእርሻ ላይ የተመሰረተ እና ሕዝቦቹም መስኖን ለመጀመሪያ ጊዜ ለእርሻ የተጠቀሙ ናቸው። በተለይ ከወንዙ ግራ እና ቀኝ ከፍ ብሎ ያሉት ስፍራዎችን በመስኖ በማልማት የአባይን ትሩፋት ማግኘት ችለዋል። እነዚህ ብርቱ ሕዝቦች አባይን በመጠቀም በርሃውን ለውጠዋል። በሌላ በኩል ግብፅን በዓለም መድረክ እስከ ዛሬ እያስጠሯት ያሉትን ተዓምራዊ የፒራሚድ ስራዎች እናገኛለን። ጊዛ በሚባለው ስፍራ ፍርስራሻቸው ቆሞ የሚታዩ 35 የሚሆኑ ግዙፍ ፒራሚዶች አሉ፤ በተለይ ሦሥቱ ከሠባቱ የዓለም ድንቃ ድንቆች ውስጥ ተካትተው ይገኛሉ። ከሁሉ ትልቁ 140 ሜትር ከፍታ እንዳለው ይነገራል። ድንጋይን በመጠቀም እጅግ ለአእምሮ የሚከብዱ እነዚህ ስራዎች በዚያን ዘመን የነበሩት የግብፅ ትጉሃን ጥበበኞች መገንባት መቻላቸው ለአሁኑ ዘመን እንቆቅልሽ ነው።
በሌላ በኩል የግብፅ የስነ ፅሁፍ መነሻነትን የሚያሳይ ፅሁፍ ሲሆን ሂሮግሊፊክስ ይባላል ግብፅ በጅኦሜትሪ፣ በሕክምና ሳይንስ፣ በአስትሮኖሚ፣ በሒሳብ እንዲሁም በፍልስፍናው ዘርፎች ከፍተኛ አሻራ ለዓለም ስልጣኔ ያሳረፈች የአፍሪካ ተወካይ፣ ከዓለም የጥንት ስልጣኔዎች መካከል አንዷ የአባይ ሸለቆ የወለዳት እንቁ በመሆን እስከ ዛሬ በታሪክ ተታወሳለች።
ነገር ግን የግብፅ የኃያልነት ዘመኗ በምስራቅ በኩል አሶራውያን እና በደቡብ በኩል ኑብያውያን በ8ኛው ክፍለ ዘመን ያደረጉባትን ወረራዎች ተከትሎ ነበር የመዳከም እጣ የወደቀበት። የኑብያውያን ስልጣኔም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጎልቶ መውጣት ጀመረ። ጥንታዊው የኑብያ ስልጣኔ ሌላው የአባይ ሸለቆ ትሩፋት ሲሆን እንደ ግብፅ ሁሉ የአባይ ወንዝ ተፋሰስን ተከትሎ የተመሰረተ ስልጣኔ ነበር። አንዳንዶቹ የኩሽ ስልጣኔ ይሉታል። የተረጋጋ ሰፈራ በኑብያ እንደነበረ በ6000 ቅ.ዓ የተገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ። የመጀመሪያው የተደራጀ ጥንታዊ ስልጣኔ በኑብያ እንደ ጀመረ የሚነገረው ደግሞ የካርማ ስርዎ መንግስት በኑብያ ከጀመረበት 2500 እስከ 1500 ቅ.ዓ ወቅት ነበር።
ይህ ስልጣኔ ከኢትዮጵያ እስከ ሜሮይ ድረስ ያለውን ሰፊ ስፍራ የሚሸፍን ሲሆን በእርሻ ላይ የተመሰረተ ሕይወትን በመገንባት ለግብፁ የኪነ ሕንፃ እና ቅርፃ ቅርፅ አስደናቂ ስራዎች እንደ መነሻ የሚቆጠሩ የተለያዩ አበርክቶዎች እንደነበሯቸው ታሪክ ያስረዳል። ኑብያ ሰራሽ ፒራሚዶች እስካሁን በሱዳን አካባቢ ይታያሉ። የተለያዩ የድንጋይ ውጤት የሆኑ አስገራሚ ቤተ መንግሥቶች፣ ቤተ አምልኮዎች፣ የመቃብር ላይ ሀውልቶች እና ሌሎች ተመሳሳይ ትንግርቶች የተሰሩበት የስልጣኔ ዘመን ነበር። ከድንጋይ ስራዎች በተጨማሪ የብረት ቴክኖሎጅ የተስፋፋበት ዘመን እንደነበርም በታሪክ ተፅፏል። ስምንተኛው ክፍለ ዘመን (ቅድመ ዓለም) ጀምሮ የኑብያ መዲና ወደ ሜሮይ ሲዛወር ግብፅ ሙሉ በሙሉ በኩሽ ቁጥጥር ስር የገባችበት ዘመን ነበር። ይህ ዘመን የኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች ዘመን ተብሎ ይታወቃል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች በግብፅ ዙፋን ላይ ለ100 ዓመታት ያህል ነግሰውበታል። አብዛኛውን ፒራሚዶች በመገንባትም ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች አሻራቸውን ያሳረፉበት ታሪክ ተመዝግቧል። በተጨማሪም ከመናገሻው ሜሮይ ሴት ነገስታት ወይም ሕንደኬዎቹ ለረጅም ዘመን የግብፅን እና የኩሽን ስልጣኔዎች እንዳስተዳደሩ ታሪክ ይነግረናል።
በአጠቃላይ የአባይ ሸለቆ ስልጣኔዎች አባይን ተተርሰው በመመስረት ዘርፈ ብዙ የስልጣኔ አሻራዎችን ያበረከቱ የታላላቅ ሕዝቦች መገኛ ነበር። ትሩፋቶቹ እስከዛሬ በየአካባቢው ቆመው ሕያው ምስክር በመሆን ለምርምር እና ጥናት ዋነኛ መሰረት ሆነዋል። በቁፋሮ እየተገኙ ያሉ የምርምር ማስረጃዎች የጥንታዊውን ዘመን ትንግርት እያሳዩ ይገኛል። በአባይ ዙሪያ እና የውሃ ውዝግብ በተመለከተ በሌላ ጊዜ እንዳስሳለን ለአሁኑ በዚህ አበቃን።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም