መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም
ይህ የአውሮፓ ግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ ነው፤በውስጥ ሊጎቻቸው ምርጥ የውድድር ጊዜን ያሳለፉት የኃያሎቹ ፍልሚያ መድረክ ነው። በመድረኩ መሳተፍ ደግሞ የበርካታ ተጫዋቾች እና ክለቦች ህልም ነው- የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ።
የውድድር መድረኩ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አማካኝነት የሚዘጋጅ ነው። ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተሻግሯል። እ.አ.አ 1955 በቀድሞ አጠራሩ “የአውሮፓ ዋንጫ” በሚል ስያሜ ነበር የተጀመረው። በ1992 እ.አ.አ ግን የቀድሞ ስያሜውን በመቀየር “የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ” ስያሜን በመያዝ ውድድሩ እየተከናወነ ይገኛል። ግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ ባለፉት 21 ዓመታት ሳይቋረጥ ተከናውኗል። ሪያል ማድሪድ 14 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ባለ ታሪክ ክለብ ነው። ኤስሚላን ሰባት ጊዜ፣ ሊቨርፑል እና ባየርሙኒክ ደግሞ እያንዳንዳቸው ስድስት ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል።
በመድረኩም 32 ክለቦች ይሳተፉበታል። የተሳታፊ ክለቦቹ ቁጥር ግን ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ወደ 36 ከፍ እንደሚል የአወዳዳሪው አካል መረጃ ያመለክታል። ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን የሚያገኝ፣ በበርካታ አጋር ድርጅቶች የሚታጀብ እና ከትኬት ሽያጭም ረብጣ ሚሊዮን ዩሮዎች የሚታፈስበት ውድድር በመሆኑ ተሳታፊ ክለቦች ባሳዩት አቋም ልክ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
ሩብ ፍጻሜውን ለሚቀላቀሉ እያንዳንዳቸው ክለቦች ዘጠና አንድ ሚሊዮን ዮሮ ገንዘብም ያገኛሉ። ዘንድሮ የዚህ ገንዘብ ተቋዳሽ የሆኑት ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ስምንቱ ክለቦችም ተለይተው ታውቀዋል።
ፓሪሰን ዠርመን ፣ ባየርሙኒክ ፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ሪያልማድሪድ፣ አርሰናል ፣ ባርሰሎና ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ቦርሲያ ዶርትሙንድ በሩብ ፍጻሜው ተፋላሚነታቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል፡፡
የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ የዚህ መድረክ ንጉሥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። መድረኩ በአዲስ መልኩ ከተደራጀበት እ.አ.አ 1992 ጀምሮ ለ14 ያህል ጊዜ በመንገስ ቀዳሚው ባለ ታሪክ ክለብ ነው ሪያል ማድሪድ። ለመጨረሻ ግዜ ዋንጫውን ያነሳውም ከሁለት ዓመታት በፊት ነው። ዘንድሮም አስራ አምስተኛ ዋንጫውን ለማንሳት እየተንደረደረ ይገኛል። ሎስብላንኮዎቹ የምድብ ሁሉንም ጨዋታዎችን በማሸነፍ ነበር ጥሎ ማለፍ የደረሱት። በጥሎ ማለፉ ደግሞ የጀርመኑን ክለብ አርቢ ላይብዚንግን በደርሶ መልስ ሁለት ለአንድ በመርታት ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል። በወጣት ኮከቦች የተሞላው ሪያል ማድሪድ ዘንድሮ በላሊጋውም አስደናቂ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል። አሁን እያሳየ ባለው አስደናቂ አቋምም ሩቅ ሊጓዙ ከሚችሉ ጥቂት ክለቦች መካክል ግምት ተሰጥቶታል።
የአምናው የመድረኩ አሸናፊ ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮም በተከታታይ ዋንጫውን ለማንሳት በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘ ይገኛል። የእንግሊዙ ክለብ ልክ እንደ ሪያል ማድሪድ ሁሉ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ማሸነፉ ይታወሳል። የፔፕ ጋርዲዮላው ክለብ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ መድረክም ለዋንጫ የታጨ ክለብ ነው። የላቀ ተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾች የሰበሰበው የማንቸስተሩ ከተማ ክለብ በጥሎ ማለፉ የዴንማርኩን ኮፐን ሀገንን በድምር ውጤት ስድስት ለሁለት በመርታት ነው በቀላሉ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው። ጉዳት ላይ ያሉት ኬቭን ዲብሮይንን፣ ጃክ ግሪልሺን የመሳሰሉት ተጫዋቾች መመለሳቸው ደግሞ ቡድኑን ይበልጥ አስፈሪ አድርጎታል። በእግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ 40 በመቶ ዋንጫውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት እንደተሰጠውም ዘ ቴሌግራፍ አስነብቧል።
እ.አ.አ በ2011 የኳታር ንጉሣዊያን ቤተሰቦች የፓሪሱን ክለብ ፓርሰን ዠርመንን ሲገዙ ዕቅዳቸው በአውሮፓ እግር ኳስ ተጽዕኖ ለመፍጠር አስበው እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ ደግሞ ባላፉት ጥቂት ዓመታት ታላላቅ የእግር ኳስ ጠበብቶችን ወደ ፓርክ ደ ፕሪንስ ማስኮብለል ችለዋል። ሊዮኔል ሜሲ ፣ ኔይማር ጁኔር እና ኬሊያን ምባፔን ማስፈረማቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ክለቡ የሀገር ውስጥ አንበሳ ብቻ ሆኖ ቀርቷል ማለት ይቻላል። ባለ ሀብቶቹ እና ደጋፊዎች የሚጓጉለትን እና የሚናፍቁትን የታላቁን መድረክ ዋንጫም ማሳካት አልቻሉም። የፓሪሱ ሀብታም ክለብ ዘንድሮም አዲስ ተስፋን ይዞ ሩብ ፍጻሜ ደርሷል። በምድብ ጨዋታዎች ቦርሲያ ዶርትሙንድን ተከትሎ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለው ክለብ፣ የእስካሁኑ ጉዞው አስከፊ የሚባል አይደለም። በጥሎ ማለፉ የስፔኑን ክለብ ሪያል ሶሲዳድን በድምር ውጤት አራት ለአንድ በማሸነፍ ነው ሩብ ፍጻሜ የደረሰው።
በአሰልጣኝ ሊዊስ ኢኔሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ በስብስብ ደረጃ ሁሌም የሚታማ ባይሆንም ለዚህ መድረክ ግን ሲበዛ አይናፋር ነው። በ2020 እ.አ.አ ፍጻሜ ደርሶ የነበረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዙ አይዘነጋም። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ጥሎ ማለፉን እንኳ መሻገር እንዳልቻለ የሚታወስ ነው።
የባቫሪያኑ ክለብ ባየርሙኒክ ዘንድሮ በቡንደስሊጋው እየተፈተነ መሆኑን ተመልክተናል። ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ሞገሱ ተገፏል። ምንም እንኳ በቡንደስሊጋው ደካማ አቋም ቢያሳይም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ ግን ብርቱ መሆኑን እስካሁን አሳይቷል። በምድብ ጨዋታዎች ካደረጋቸው ስድስት መርሐ ግብሮች አምስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል። በጥሎ ማለፉ ጨዋታ የጣሊያኑን ክለብ ላዚዮን ሦስት ለአንድ በሆነ ድምር ውጤት በመርታት ከስምንቱ ክለቦች አንዱ መሆን ችሏል። ያለፉትን የምድብ ጨዋታዎች ከኮፐን ሀገን፣ ከጋላታሳራይ እና ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያከናወኑት ባቫሪያኖቹ እስካሁን ብዙ አለመፈተናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይልቁንስ ከባዱን ፈተና የሚጀምሩት ከዚህ በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።
ባቫሪያኑ በሩብ ፍጻሜው ከሜዳቸው ውጪ የሚያከናውኑትን ጨዋታ ደጋፊዎቻቸው ስቴዲየም እንዳይገቡ መታገዳቸው ደግሞ ይበልጥ ፈተናው እንዲበዛባቸው ያደርጋል። በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከክለቡ ጋር የሚለያዩት አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ስንብታቸውን ለማሳመር ይህንን ዋንጫ ለደጋፊዎቹ ለማበርከት የቻሉትን ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍጻሜ ደርሷል። ለመጨረሻ ጊዜ እ.አ.አ በ2010 ነበር ሩብ ፍጻሜ የደረሰው። በስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመሩት ወጣት መድፈኞቹ ዘንድሮም በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ሆነዋል። በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም ረጅም ርቀት ለመጓዝ አልመዋል። በምድቡ መርሐ ግብር በቀላሉ በበላይነት በማጠናቀቅ ነበር ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉት። ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ግን በፖርቹጋሉ ክለብ ፖርቶ ተፈትኖ በመጨረሻ ተሳክቶለታል። ወደ ፖርቹጋል ተጉዘው አንድ ለ ባዶ ተሸንፈው የተመለሱት ወጣት መድፈኞቹ በሜዳቸው ኤምሬትስ ከ120 ደቂቃ ፍልሚያ በኋላ በተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል። ወደ መለያ ምት ያመራው ጨዋታም አርሴናል አራት ለሁለት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል። ከማንቸስተር ሲቲ እና ከሪያል ማድሪድ ቀጥሎ ዋንጫውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት የተሰጠው አርሴናል በፖርቶ በመፈተኑ ግን ጥያቄን አጭሯል። በመድረኩ ካልበረታ ጉዞው በአጭሩ ሊቋጭ እንደሚችልም መረጃዎች አስነብበዋል።
ሌላኛው የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ከአራት ዓመታት በኋላ ነው ሩብ ፍጻሜ መድረስ የቻለው።በአሰልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ የሚመራው ክለብ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ አቋሙ ወርዶ ተስተውሏል። በዚህ ምክንያትም በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከአሰልጣኙ ጋር ይለያያል። የካታላኑ ክለብ በላሊጋውም ከሪያል ማድሪድ ጋር ያላቸው ልዩነት ሰፍቷል። በታላቁ የአውሮፓ መድረክ ግን በእስካሁኑ ጉዞው ተወድሷል። ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀው ባርሴሎና ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ከጣሊያኑ ክለብ ናፖሊ ጋር 180 ደቂቃ ተፋልሞ በድል ተወጥቷል። ባርሴሎና የአምናውን የሴሪ ኤውን ክለብ ናፖሊን በድምር ውጤት አራት ለሁለት በማሸነፍ ነው ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለው። አምስት ጊዜ የመድረኩን ዋንጫ ያነሳው የስፔኑ ክለብ አሁን ላይ ዋንጫ ካነሳ ግን አስር ዓመታት ተቆጥሯል።
አትሌቲኮ ማድሪድም ሩብ ፍጻሜ የደረሰ ሦስተኛው የስፔን ክለብ ሆኗል። የዋና ከተማዋ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ የምድብ ጨዋታዎችን በበላይነት ጨርሶ ነበር ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለው። ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ከጣሊያኑ ክለብ ኢንተርሚላን ጋር ባደረገው ትንቅንቅም የመጀመሪያውን ዙር ከሜዳው ውጪ አንድ ለ ባዶ ተሸንፎ መመለሱ የሚታወስ ነው። በሜዳው ዋንዳ ሜትሮ ፖሊታኖ ስቴዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ ውጤቱን በመቀልበስ ሁለት ለአንድ አሸንፏል። ከ120 ደቂቃ ፍልሚያ በኋላም ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ አትሌቲኮ ማድሪድ ሦስት ለሁለት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግሯል። የአምናው የፍጻሜ ተፋላሚው ክለብ ኢንተርሚላን ዘንድሮ ግን ሩብ ፍጻሜ እንኳ ሳይደርስ ከመንገድ ቀርቷል። የመድረኩን ዋንጫ አንስቶ የማያውቀው የዲያጎ ሲሞኒው ክለብ ከዚህ በፊት በ1974 ፣2014 እና 2016 እ.አ.አ ፍጻሜ ደርሶ እንደነበረ አይዘነጋም። ምንም እንኳ ክለቡ በላሊጋው ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ቢሆንም በታላቁ መድረክ ግን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ ሦስተኛው የስፔን ክለብ ሆኗል።
ቦርሲያ ዶርትሙንድም በሻምፒዮንስ ሊጉ ስምንቱን ክለቦች የተቀላቀለ ሁለተኛው የጀርመን ክለብ መሆን ችሏል። ዶርትሙንድ ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው ዘንድሮ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው።ከፓሪሰን ዠርመን ፣ኤስሚላን እና ኒውካስትል ዩናይትድ ጋር አንድ ምድብ የነበረው ዶርትሙንድ ምድቡን በበላይነት ነበር የጨረሰው። ከኤርዲቪዚው ክለብ ፒኤስቪ አይንዶቨን ጋርም በጥሎ ማለፉ ተገናኝቷል። ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቶ አንድ አቻ ተለያይቶ የተመለሰው የጀርመኑ ክለብ በኢዱና ሲግናል ፓርክ ያደረገውን የመልስ ጨዋታ ግን ሁለት ለባዶ አሸንፏል። ብዙ ሳይቸገርም ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግሯል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እስካሁን 112 ጨዋታዎች ተደርገዋል። በአጠቃላይ 332 ግቦች ከመረብ ሲገናኙ በአማካኝ በየጨዋታው ከሁለት ግቦች በላይ ተቆጥረዋል። አንቷን ግሪዝማን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ፣ ኸርሊንግ ብራውት ሀላንድ ከማንቸስተር ሲቲ ፣ እና ኬሊያን ምባፔ ከፓርሰን ጀርመን በስድስት ግቦች ኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩት ነው።
በየጨዋታውም ከ50 ሺህ በላይ ተመልካቾች በቀጥታ ስቴዲየም ገብተው ተመልክተውታል። ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ የጣሊያን ክለቦች ዘንድሮ ሩብ ፍጻሜ እንኳ መድረስ አልቻሉም፡፡ የስፔን ሦስት ፣እንግሊዝ እና ጀርመን ሁለት እንዲሁም ከፈረንሳይ አንድ ክለብ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ሰፖርት እና ዘ ቴሌግራፍ ናቸው፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም