ቀደም ባሉት ጊዜያት በባሕር ዳር ከተማ ዋናው ገበያ እና አካባቢው መንገድ ዳር ላይ ሠርተው መለወጥ የሚፈልጉ ወጣቶች አልባሳት፣ ጫማ፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች…ለመሸጥ ሲሞክሩ ከደምብ አስከባሪዎች ጋር ሲሯሯጡ ማየት የተለመደ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ንብረታቸው እየተንጠባጠበ ትርፉ ቀርቶ ለኪሳራ የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን በኲር መዘገቧ ይታወሳል፡፡
የሥራ ፍላጎት እያላቸው ሱቅ ተከራይተው የመነገድ አቅም የሌላቸው ወጣቶች ያነሱትን የመሸጫ ቦታ ጥያቄ አስመልክታም በኲር ከተማ አስተዳደሩን አነጋግራ ነበር፡፡ ወጣቶች እያከናወኑት ያለው የመንገድ ላይ ንገድ ሸማቹን ለወከባ የሚዳርግ፣ የከተማዋን ሰላም የሚያውክ…በመሆኑ ወደፊት ችግራቸው ታያቶ የእሁድ ገበያ ሊመቻችላቸው እንደሚችል ቃል ተገብቶ ነበር፡፡
አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ የገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረጉ በከተማዋ እምብርት ፓፒረስ ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ዋናው አስፋልት ለእሁድ ቀን መሸጫ /እሁድ ገበያ/ ፈቅዶላቸዋል፡፡ እኒያ ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ውስጥ ሆነው ደምብ አስከባሪዎች ሲመጡባቸው ለሸጡት እቃ እንኳን ብራቸውን ሳይቀበሉ ኋላቸውን እያዩ ይሮጡ የነበሩ ወጣቶች ዛሬ ተረጋግተው በመሸጥ ደንበኞቻቸውን ሆነ ራሳቸውን ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን በቦታው ተገኝተን አረጋግጠናል፡፡
“ካልሲ በ10 ብር…” እያሉ ገዥ የሚጠሩትን አልፈን ወደ ውስጥ እየዘለቅን ስንሄድ ደግሞ ጫማ፣ ቦርሳ ፣ ሻንጣ፣ አዳዲስ እና የተለበሱ አልባሳት ፣ የሕጻናት ልብስ፣ የቤት ቁሳቁሶች… በየዓይነቱ ተደርድረው አስተዋልን፡፡ ነጋዴው ለሽያጭ ያቀረበውን ቁሳቁስ ሲያዋድድ እና ሲያስተዋውቅ፣ በዋጋም ሆነ በጥራት የተሻለ የሚለውን ሲያቀርብ ሸማቹም በበኩሉ የሚፈልገውን መርጦ ለመውሰድ ላይ ታች ይላሉ፡፡
የገበያ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ሰለሞን ወርቄ አንዱ ነው፡፡ ሰለሞንን በቦታው ያገኘነው የቤት እቃዎችን ከፊቱ ገዥን በሚስብ መልኩ ደርድሮ ነው፡፡ በተደራጀ መልኩ ቦታ አግኝቶ ሥራውን ባይሠራም በፊት ቁሳቁሶችን በመያዣ ደርድሮ በአንገቱ አንግቦ /በሱቅ በደረቴ/ ይሠራ ነበር፡፡ ኋላም ሥራውን ለማሻሻል ቢያስብም ሱቅ መከራየት ግን ካለው ወረት(ካፒታል) ጋር ተመጣጣኝ ስላልነበር እየተዘዋወረ የሚሠራበት ካሬታ በመግዛት ቀጠለ፡፡
በ2014 ዓ.ም ሥራውን እንደጀመረ የሚገልፀው ሰለሞን በመጓጓዣ የሚሸጣቸው እቃዎች ተሰብረው እንዳያከስሩት የማይሰበሩ እቃዎችን ብቻ በመግዛት ሥራውን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በወቅቱም በየቦታው ሲጓጓዝ አንዳንድ ቦታ ላይ ግብር እና የሱቅ ኪራይ የሚከፍሉ ነጋዴዎች በአካባቢው ሲያዩት ስለማይፈቅዱ ለመሥራት ይቸገር እንደ ነበር ያስታውሳሉ፡፡
በመሥሪያ ቦታ እጦት ችግር ላይ የነበረው ሰለሞን አንድ ወቅት ጓደኛው ከሳምንት አንድ ቀን የእሁድ ገበያ /ሰንደይ ማርኬት/ መኖሩን ነገረው፡፡ አምጥቶም አሳየው፡፡ ወዲያውኑ ወጣቱ ቁሳቁሱን ከበፊቱ በተሻለ ዋጋ ተረጋግቶ በመሸጥ ደንበኛ የሚያፈራበት ዕድል በመፍጠሩ እሁድን በጉጉት እንደሚጠብቃት ይናገራል፡፡
“በእርግጥ አቅም ሲያድግ የራሴ የምለው ቦታ ይኖረኛል” የሚለው ሰለሞን ይህንን የመሥራት አቅም እስኪፈጥር ድረስ ግን በእሁድ ገበያ ከሚሳተፉ ጓደኞቹ ጋር ጥሩ ልምድ እና በርካታ ደንበኛ ማፍራት መቻሉን ሰለሞን ገልጾልናል፡፡ ወጣቱ እንደሚለው በየሳምንቱም የተሻለ ቁሳቁስ ለደንበኞቹ ለማቅረብ እና የለም ላለማለት የሚይዘውን ዕቃ ዓይነት በየጊዜው ይጨምራል፡፡ ለጀማሪ ሠራተኛም ጥሩ ዕድል ነው፡፡
መሠረት አታላይ የተባለች ወጣት ደግሞ ከዋናው ገበያ “መሥራት ያስከብራል” ከተሰኘው ሕንፃ በመከራየት የተመረጡ የቦንዳ /የተለበሱ/ ልብሶች ሽያጭ ለአንድ ዓመት ተኩል ሥትሠራ ቆይታለች፡፡ ድንገት በገጠማት ችግር አራት ወር ቆይታ ስትገባ ሥራዋ እንደነበረው መቀጠል ባለመቻሉ ሱቁን እንደዘጋችው ትናገራለች፡፡ ድጋሚ ሱቅ ተከራይቶ ለመሥራት አቅም ባይኖራትም ቀደም ያስረክቧት ከነበሩ ሰዎች ጥቂት ልብሶች ተረክቦ በእሁድ ገበያ በየሣምንቱ በመሸጥ ጥሪት ለመቋጠር ጥረት እያደረገች መሆኗን ነግራናለች፡፡
ሱቅ ተከራይቶ ለመሥራት ከሦስት እስከ ስድስት ወር ቅድሚያ ኪራይ መክፈል ግድ በመሆኑ የእሁድ ገበያ አቅም እንደሚፈጥር ወጣቷ ታምናለች፡፡ እናም እንደ እርሷ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም አቅማቸውን አጠናክረው ሱቅ የመከራየተ አቅም እስኪያገኙ በየቦታው የእሁድ ገበያ ቢቋቋም የተሻለ ነገን እንዲያስቡ እንደሚያደርግ መሠረት ጠይቃለች፡፡
ማታ ማታ መንገድ ዳር በመቀመጥ የሕጻናት አልባሳት እና ካልሲ የሚሸጠው ሽመልስ አዱኛው በበኩሉ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሞ ከማታው ገበያ ይልቅ ግን ከሳምንት አንድ ቀን የሚገበያዩበት የእሁድ ግብይት የተሻለ እንደሆነ ነው የገለፀልን፡፡
የገበያው መከፈት በርካታ ወጣቶች በደምብ አስከባሪዎች ይደርስባቸው የነበረ እንግልት ቀርቶ እቃዎችን ተረጋግተው እንዲሸጡ ማስቻሉን ሽመልስ ምስክር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የሱቅ ኪራይ ስለሌለባቸው የእቃውን ትርፍ ብቻ አስበው በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚሸጡ በርካታ ደምበኞች እንዲመጡ ማስቻሉን፣ እነሱንም ሸማቹንም ተጠቃሚ ማድረጉን እና ለሥራ አጥ ወጣቶች ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ንግድ መምሪያ ኃላፊ አቶ አደራው ጋሻው እንዳሉት ፓፒረስ አካባቢ የተፈቀደው የእሁድ ገበያ ወጣቶች በየመንገዱ ሲሸጥ በየጊዜው ከማባረር ሠርተው እንዲኖሩ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጐ የተቋቋመ ነው፡፡
በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ሰንሰለቱ ሲበዛ ተጐጂ የሚሆነው ሸማቹ ማህበረሰብ በመሆኑ ይህንን ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ አምራቹን ከሸማች የሚያገናኝ ቦታ የመፍጠርን ሥራ ሙከራዎችም እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከእሁድ ገበያ በተጨማሪ በግሽ አባይ እና በጣና ክፍለ ከተማ እንዲሁም ህዳሴ አካባቢ /ድንቄ ጀርባ/ የአምራችም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች መሀል ላይ ደላላ ሳይገባ አምራቾች ምርታቸውን የሚሸጡበት ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡
እንደ ኃላፊው እምነት ገበያው ሲቋቋም በየአካባቢው የመጓጓዣ ወጭ እና ድካምን ለመቀነስ፣ ለሻጭ ደግሞ በየመንገዱ ከመሸጥ ቦታ ይዘው ከሸማቹ ጋር መገናኘት የሚችልበት ዕድል መፍጠር ነው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም