የሽግግር ፍትሕ እንዴት ይተግበር?

0
161

ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት በተለይ አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን ክፉኛ ጎድቷል:: ይህን ክስተት ካውንስል ኦን ፎርይን ሪሌሽንስ  የተባለው ድረ ገጽ የክፍለ ዘመኑ አውዳሚ ጦርነት ሲልም ነው የገለጸው:: መረጃው አክሎም ጦርነቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አስነብቧል::

ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ነጥቋል፤ እጅግ ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመትንም አድርሷል:: ለአብትነትም አማራ ክልል ብቻ ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት እንደደረሰበት በጥናት ተረጋግጧል::

ይህን ተከትሎ ታዲያ ጦርነቱ በውይይት ከመጠናቀቁ ማግስት አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ  የሽግግር ፍትሕ እንደሚኖር ነው የተነገረው:: ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እየተሠራ መሆኑም በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል::

ጉዳዩን ለመተግበር ደግሞ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ በጥናት የተደገፈ ረቂቅ ማቅረቡ ይታወቃል፤  ቡድኑ ታዲያ የተጠያቂነት ጉዳይ በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ ለሚለው በሰጠው አስተያየት አሁን ባሉት ተቋማት ልዩ ችሎትም ሆነ አዲስ ፍርድ ቤት በማቋቋም የተጠያቂነትን ሥራ ማከናወን አዳጋች መሆኑን ጠቁሟል:: በመሆኑም አዲስ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል::

ይሁን እንጂ በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ መወሰኑን ሪፖርተር አስነብቧል::

እንደ ዘገባው ከሆነ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ባቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ የፍርድ ቤቶችን ሒደት በሚመለከት ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚለው ምክረ ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ፣ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ልዩ ችሎት በማቋቋም እንዲታይ ነው ውሳኔ የተላለፈው::

ይሄው ቡድን ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ልዩ ፍርድ ቤቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና መርሆዎችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሕጎችን እና አሠራሮችን ሊከተል ይገባል፤ ሥጋቶችን ለማስቀረት፣ ተጎጂዎች እና ተከሳሾች በሒደቱ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑንም አስታውቋል::

ረቂቅ ፖሊሲውንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ማፅደቁ ይታወሳል:: በሌላ በኩል የዳኞች አሿሿም፣ የሕዝብ ተሳታፊነት እና ገለልተኛነት የሚሉ ሐሳቦች በቡድኑ ምክረ ሐሳብ መሠረት ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሏል:: ከዚህ በተጨማሪም የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሒደቶችን የሚያከናውን ልዩ ነፃ እና ገለልተኛ የዐቃቤ ሕግ ተቋም መቋቋም አለበት የሚለው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን ጋዜጣው በዘገባው አክሏል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል:: በምክክሩ ወቅት ሐሳብ የሰጡት  የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ሥነ ሥርዓት አዋጅ አፈፃፀምን በተመለከተ በአዋጁ የተሰጡትን ኃላፊነቶች እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል:: ጎን ለጎንም በአዋጁ ተፈፃሚነት ላይ የክትትል ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ነው የተናገሩት::

ከፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሽግግሩ በፊት ለደረሱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሔ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል::

 

ዓለም አቀፍ ተሞክሮ

ከአንደኛው እና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ባሻገር በርካታ ሀገራት አውዳሚ ጦርነቶችን አካሂደዋል፤ ይሁን እንጂ በሽግግር ፍትሕ በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በደል የተሟላ መፍትሔ ለመስጠት እንዳስቻላቸው ታሪካቸው ያስረዳል:: ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ እና ጋምቢያ ደግሞ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸውን ከአፍሪካ ሕብረት ድረ ገጽ (የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ) ያገኘነው መረጃ ያብራራል::

እ.አ.አ. በ1994 በመቶ ቀናት ብቻ አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎቿን ያጣችው ሩዋንዳ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉት ሩዋንዳዊያን በጭካኔ ተግባሩ ተሳትፎ ነበራቸው በሚል ክስ በመመሥረት ፍትሕ ፊት እንዲቀርቡ አድርጋ ነበር። በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ በሀገር ውስጥ ችሎት እና በባሕላዊ መንገድም የዳኝነት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ማድረጓን ነው የመረጃ ምንጩ የሚያብራራው:: ይህም (የተወሰኑት በይቅርታ መታለፋቸውንም ልብ ይሏል) ሀገሪቱን በዴሞክራሲ እና በሰላም እንዲሁም በተሻለ የልማት መንገድ መራመድ አስችሏታል ነው ያለው።

በተመሳሳይ በትንሹ የ100 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው እ.አ.አ. ከ1991 አስከ 2002 በዘለቀው የሴራሊዮን የርስ በርስ ግጭት ለደረሰው ጥፋት በተቋቋመው የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን እንዲሁም ልዩ ችሎት አማካኝነት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ፍትሕን ማስፈን ችላለች:: የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን በተሰጠው ስልጣን መሠረት ተጎጂዎችን ከሰቆቃ በመታደግ ችግሩን በዕርቅ መፍታት፣ ብዙኃኑ ላይ ለደረሰው ግፍ ምላሽ መስጠት፣ ግፉ በቀጣይ እንዳይደገም መፍትሔ ማበጀት ላይ አተኩሮ ሠርቷል:: ሁሉንም የሚያስማማ ውሳኔ በመስጠትም ችግሩ ከቂም በቀል በፀዳ መልኩ መፍትሔ እንዲያገኝ አስችሏል።

በተመሳሳይ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውንና በጥቁሮች ላይ ያነጣጠረውን ጭፍጨፋ በይቅርታ እንደተሻገሩት የመረጃ ምንጩ አስታውሷል::

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here