ባሕል እና ታሪክ በቀለም አረዳድ እና ትርጉም አሰጣጣችን ላይ ያሳረፉት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ቀለም ከስሜት፣ ሁኔታ እና አካላዊ ምላሽ ጋር በቀጥታ ቁርኝት አለው። ሰውነታችን ለቀለማት ምላሽ ይሰጣል።
እ.አ.አ በ2020 ሰዎች ለቀለማት ያላቸው ስሜት ምን ይመስላል በሚል አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር። በሰላሳ የዓለም ሀገራት ውስጥ የሚገኙ 4,598 ሰዎች በዚህ ጥናት ተሳትፈው ነበር። በዚህም ጥናት ከተሳተፉት ሰዎች 51 በመቶ ያህሉ ጥቁር ቀለምን የፍርሀት እና የኀዘን ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ገልጸዋል።
43 በመቶ ያህሉ ደግሞ ነጭ ቀለምን የመረጋጋት ስሜት እንደሚፈጥርላቸው አስታውቀዋል። ቀይ ቀለምን 68 በመቶ ሰዎች የፍቅር ምልክት አድርገውታል። ሰማያዊ ቀለም ለ35 በመቶ ሰዎች የመረጋጋት ስሜት ፈጥሮላቸዋል። ቢጫ የደስታ፣ ብርቱካናማ የደስታ፣ ሐምራዊ የፍቅር፣ ቡናማ የቅያሜ፣ አረንጓዴ የመሙላት ምልክቶች ተደርገው በጥናቱ ቀርበዋል።
ይህ የቀለማት ከስሜት ጋር ትስስር ምርጫ ጥናት ውጤት ዓለም አቀፍ መልክ አለው ሲል ይገልጻል። የቀለማት አረዳድ በሰው ልጆች ተግባራት ላይ ቁልፍ ሚና እንዳለውም ያሳያል።
የቀለም ምርጫችን እና አረዳዳችን ከሕይወት ልምዳችን እና ከባህላችን ጋር የተቆራኘ ነው። በኢትዮጵያ ጥቁር ቀለም የኀዘን ምልክት ነው። በሕንድ ደግሞ ነጭ የኀዘን ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። በምእራባዊያን ሀገራት ነጭ ቀለም የንጽሕና እና ቅድስና ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል። በአንጻሩ በምስራቁ የዓለም ክፍል ነጭ ቀለም የኀዘን እና ለቅሶ መግለጫ ነው።
ክሮሞቴራፒ (የቀለም ሕክምና) በጥንት ግብጻውያን እና ቻይና ሰዎችን ከደዌያቸው ለመፈወስ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ቬሪ ዌል ማይንድ ድረገጽ እንደ ጥንቱ ሁሉ ዘንድሮም ሰዎችን በቀለም እና ብርሃን ማከም ተግባራዊ የሚደረግ ሳይንስ ስለመሆኑ አስነብቧል።
ቀይ ቀለም አካል እና አዕምሮ ያነቃቃል። የደም ዝውውርን ይጨምራል ብሏል። ቢጫ የስርዓተ ነርቭን ኡደት ያነቃቃል። ሰውነትን ያጸዳል፣ ያድሳል። ብርቱካናማ ቀለም ሳንባን ይፈውሳል፣ አቅምን ያሳድጋል። ሰማያዊ ሕመምን ያስታግሳል። ስቃይ ይቀንሳል።
ቀለማት በተማሪዎች የውጤት አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽዕኖ አላቸው። ቀይ አስፈሪ፣ ቀስቃሽ፣ አስደሳች ትርጉሞች ቢኖሩትም እንኳን በቀይ ቀለም ላይ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች የሚያስማሙ ወይም ስኬታማ የሚባሉ አይደሉም።
ከፈተና በፊት ለተማሪዎች ቀይ ቀለምን ማሳየት ወይም ለቀለሙ ዕይታ ማጋለጥ በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። ከዚህ ጋር የተገናኘ አንድ ጥናት በአሜሪካ ኮሌጆች ተደርጓል። ተማሪዎች የአምስት ደቂቃ ፈተና ሲወስዱ ጥያቄው በቀይ፣ ጥቁር እና አረንጓዴ ቀለማት ወረቀቶች ቀርቦላቸዋል። በቀይ ቀለም ወረቀት የተፈተኑት ተማሪዎች አረንጓዴ እና በጥቁር ቀለም ከተፈተኑት በ20 በመቶ ያነሰ ውጤት አስመዝግበዋል።
ቀለማት ከሸማቾች ግዢ አንጻርም ልዩነት ይፈጥራሉ። የምንለብሰው ልብስ እና የምንገዛው መኪና ቀለም ስለእኛ ባህሪ ብዙ ይናገራል። እድሜ፣ ጾታ እና ሌሎች ጉዳዮችም የቀለም ምርጫችን ይወስኑታል።
ነጭ ቀለምን የአዲስነት እና ንጹሕነት ምልክት የሚያደርጉት አሉ። የወጣትነት እና ዘመናዊነት ማሳያ ተደርጎም ይታሰባል።
ጥቁር የጥንካሬ ምልክት ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ብዙ የቅንጦት እቃዎች ቀለም ጥቁር ነው ይላል ሳይኮሎጂ ቱዴይ። ይህ ቀለም አማላይ፣ ኀይለኛ እና ምስጢራዊ ነው።
ቀይ ቀለም ደፋር እና ትኩረትን የሚስብ ቀለም ነው። ስለዚህ ይህን አይነት መኪና የሚመርጥ ሰው የኀይል፣ የተግባር እና የመተማመንን ምስል ለሰዎች ማሳየት ይፈልጋል ማለት ነው።
የቀለም ምርጫ በዋጋ እና ለነገሩ ባለን መውደድ ይወሰናል። እንዲሁም እድሜም የራሱ ሚና አለው። ወጣቶች አብረቅራቂ ቀለማትን አብዝተው ይወዳሉ። ደማቅ ቀለማትን ይመርጣሉ። በእድሜ ገፋ ያሉት ደግሞ ፈዛዛ ቀለማትን ይመርጣሉ። የቀለም ምርጫም ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ይወሰናል። ሞቃታማ ስፍራዎች የሚኖሩ ነጭ ቀለምን ይመርጣሉ። ጥቁር ቀለም የፀሐይ ብርሃንን ስለሚስብ ለሞቃታማ ስፍራ አይመረጥም። ነጭ ቀለም ደግሞ በርሃማዎች አካባቢ ይመረጣል። የፀሐይ ብርሃንን ስለሚመልስ ሙቀትን ይቀንሳል። በመኪናም ይሁን በአልባሳት ቅዝቃዜ ቦታዎች ጥቁር ቀለምን ይመርጣሉ። ሞቃታማ ቦታዎች ደግሞ ነጭ ቀለምን ያስቀድማሉ።
የኬሚካል መሐንዲሶች ቀለማት በስሜታችን፣ ከግላዊ ምርጫ፣ ባህል እና ሁኔታዎች የሚወሰኑ ቢሆኑም የቀለማት ስነ ልቦና ገና ያልተጠና እና ብዙ ምርምር የሚጠይቅ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።
ሳውዝ ቴራፒ ድረገጽ ዘረኝነት እና ቀለም በሚል ርዕስ ይዞት በወጣ ጽሑፍ ጥቁርነት እና ነጭነት በሚሉ ሁለት ዝርያዎች ላይ አተኩሮ ጽፏል። ነጭነት የተራማጅነት እና የበላይነት ምልክት ተደርገው መወሰዳቸውን ጽፏል። በአንጻሩ ጥቁርነት የበታችነት መገለጫ ሆኖ ተስሏል ሲል ይቀጥላል።
የምዕራባዊያን ነጮች ባህል ሁልጊዜ ምክንያታዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ብቁ፣ ዘመናዊ እና አዎንታዊ ተደርጎ መታየቱን በምሳሌነት ያነሳል። ይህም ሐሳብ ቀሪውን ዓለም በደካማነት የሚፈርጅ ምልከታ እንዳለው ይጠቅሳል። በዚህ ዕይታ ሌላኛው ዓለም ጥንታዊ፣ ኋላቀር፣ ምክንያታዊ ያልሆነ አድርጎ ያስቀምጣል።
የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ሲግመን ፍሩድ እና ካርል ዩንግ ጥቁር ቀለምን የኀይለኝነት እና ኋላቀርነር ምልክት አድርገው ማቅረባቸውን ይተቻል። ጥቁሮቹ ሰለጠኑ ከሚባሉት ነጮች ጋር ሲነፃፀሩ ዝቅተኛ የሰብዕና ደረጃ ያላቸው እና የሞራል ፍርድ እንደጎደላቸው ሆነው ቀርበዋል።
ጥቁር ቀለም በጥንታዊያን ግብጾች የመራባት እና የዓባይን ለም አፈር ይወክል ነበር። ሌሎች ሀገራት ደግሞ ጥቁርን የሞት እና የድብቅ ነገር ምሳሌ ያደርጉታል።
ቅኝ ግዛት በነጭ እና ጥቁር ቀለማት ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል። ሲሞን ማንዴዝ ዘ ሌተስት ድረገጽ ላይ በቀለማት ማግለል የጥቁር እና የነጭ ብቻ አይደለም ስትል ጽፋለች። የቀለም ጉዳይ ብዙዎችን ወደ ኋላ የሚጎትት ተጽዕኖ እንዳለውም ተናግራለች። “ጥቁሯ እናቴም ከጥቁር ይልቅ ነጻ ያለ ቀለምን ትመርጣለች” በማለት ለጥቁር ቀለም የሚሰጡ አሉታዊ ዕይታዎች ከራሳቸው ከጥቁሮች የሚነሱ መሆናቸውን ገልጻለች። የቀለም ምርጫ ትልቁ ጉዳት በጥቁሮች ላይ ነው።
አውሮፓን ማዕከል ያደረገው የውበት መለኪያ በማስታዎቂያ እና በሚዲያ ዘርፉ ጥቁር ቀለም ያላቸው ሰዎችን የማይፈለጉ እና ውበት የሌላቸው አድርጎ ይስላል። ጠይም እና ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች በመላው ዓለም በመጥፎ እና በጥፋት መልኩ ሲሳሉ መቀጠላቸውን ሲሞን ጽፋለች።
በብዙ የታሪክ፣ የእምነት፣ የልማድ፣ የአካባቢ፣ የዘመን ስብጥሮች ስንመለከተው ጥቁር ቀለም የተሰጠው ትርጓሜ፤ በቀጥታ ከጥቁር ሰዎች ጋርም ተያይዟል። ዛሬ ላይ ለጥቁር ቀለም የተሰጠው የተዛባ ትርጉም በአንድ አዳር የመጣ ጉዳይ አይደለም። ብዙ ሁኔታዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል። አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ጥቁሮችን እንደ ባሪያ ቆጥረው መመልከታቸው እና ለንግድ ማቅረባቸው ዛሬም ድረስ በአውሮፓ ሰዎች ዘንድ የነጭ የበላይነትን ፈጥሯል።
በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በመዝናኛው፣ በፖለቲካው ዘርፍ ጥቁሮች ዛሬም ከፊት አይደሉም። ጥቁሮች አቅመ ቢስ ሆነው ተስለዋል። የአሜሪካው ሆሊውድ ጥቁሮችን ከአስፈሪ፣ ሞት እና ኀዘን ጋር አያይዞ ማቅረቡ አልቀረም። የማይታወቁ እና አስደንጋጭ ነገሮች ከጥቁር ቀለም ጋር ይያያዛሉ። በልጅነታችን ስናድግ ጥቁር ቀለምን የሰይጣን፣ ጭራቅ እና አስፈሪ አውሬ ምልክት አድርገን አድገናል። ቅዱስ ሚካኤል የሚረግጠው ሰይጣን ምስል በጥቁር ቀለም መሳሉ ሁልጊዜም ሰይጣንን ጥቁር እና አስፈሪ አድርጌ እንዳስበው ያደርገኛል። እኔ ጥቁር ብሆንም እንኳን ሰይጣንን በጥቁር ቀለም ተስሎ በማየቴ ለቀለሙ ጥሩ ዕይታ አይኖረኝም።
ጥቁር ጨለማ ነው። ጥቁር አደጋ ነው። ጥቁር ምስጢር ነው። ጥቁር ባዶነት ነው። ጥቁር ጠብ አጫሪ እና ተንኮለኛ ነው። ጥቁር የግጭት ምንጭ ነው ተብሎ ስምምነት ተደርሷል።
ይህንን እውነት አሜሪካ ሆሊውድ ሳንሄድ በሀገራችን ሙዚቃዎች እና ፊልሞች ማየት በቂ ነው። ጥቁር ተዋንያን የሚሰጣቸው ሚና የተንኮል፣ የነገረኛነት እና አጥፊነት ሚና ነው። ወንዶች የትኛውንም ያህል ቆንጆ ቢሆኑ አማላይ አፍቃሪ ከመሆን ይልቅ የአቃጣሪነት እና የተደባዳቢ፣ ዘራፊ፣ ወንበዴነት ሚና ይሰጣቸዋል።
ሴትም ብትሆን ጠይም ወይም ጥቁር ከሆነች የሚሰጣት ሚና የቤት ሰራተኛነት ወይም አሉታዊ ተግባራት ላይ መሰማራት ነው። በሙዚቃዎች ውስጥም ቢሆን ጠይም ሴቶች እና ወንዶች ብዙ የተለመዱ አይደሉም። በአንጻሩ በሆሊውድ ፊልሞች ውስጥ ነጮች የበላይ ሆነው እንደሚታዩት ሁሉ በሀገራችንም ሚዲያ ቀይ ቀለም ያላቸው ሰዎች መሪ እና ተወዳጅ ናቸው።
የሚዲያ እና የቅኝ ግዛት ውጤት ሰዎችን ከራሳቸው ጋር አጣልቷቸዋል። ጠይም ነኝ ግን ቀይ ሰው እወዳለሁ። ልቦናዬ ተሰልቧል ልበል? ኢትዮጵያዊያን በጥቁርነታቸው አይኮሩም ወይም አይቀበሉትም የሚለው ሐሳብ ምንጩ ምንድን ነው?።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም