የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፎረም ጋር በመተባበር አራተኛ ዓለም አቀፍ የጤና ጥናትና ምርምር ጉባኤውን ከሕዳር 25 እስከ 26/2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል:: “ምርምርን ወደ ተግባር መቀየር፣ በችግር ውስጥ ሆኖ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓትን ማጠናከር” የጉባኤው መሪ ሐሳብ ነው::
በጥናትና ምርምር የተገኙ ውጤቶችን ለሕዝቡ ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ የጤና ሥርዓቱን ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ዕውቅና ኖሯቸው ለማይበገር የጤና ሥርዓት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ ደግሞ የጉባኤው ዓላማ ነው:: በክልሉ ያለውን የጤና ችግር በመፍታት በቀውስ ወቅትም የማይበገር የጤና ሥርዓትን መገንባት የዘንድሮው ጉባኤ ቀዳሚ ዓላማ ሲሆን በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችም ቀርበዋል::
በጤናው ዘርፍ ከተሰሩ ጥናቶች መካከል በቀውስ ወቅት እንዴት የጤና ሥትዓቱን ማጠናከርና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል የሚለው ጥናት ይገኝበታል። ጥናቱን በሰሜን ምእራብ አማራ ቀጠናን መነሻ ሲያደርግ በአራት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተጠናቀረ ነው። ጥናቱ በግጭት ወቅት የጤና ተቋማት ለጉዳት መዳረጋቸውን እና የአገልግሎት ተደራሽነት ፈተና ውስጥ መግባቱን፣ የጤና ባለሙያዎች እንደፈለገ ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን እንዳይሰሩ ማድረጉንም ጠቁሟል።
የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ፀሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) እንዳሉት ክልሉ በርካታ ምሁራን አሉት:: ይሁን እንጂ ችግሮችን ተጋፍጦ ለማኅበረሰብ ችግር ምላሽ ለመስጠት ውስንነቶች አሉ::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሉን ያጋጠሙት ችግሮች የጤና ተቋማት ሥራ እንዲያቆሙ፣ የግብዓት እጥረት ፈተና እንዲሆን፣ ፆታዊ ጥቃቶች እና ሌሎች ችግሮች የማኅበረሰብ ስጋት ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረጋቸውን ዶክተር ታፈረ ተናግረዋል:: እነዚህን ችግሮች በተመለከተም መረጃን አደራጅቶ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እና ዜጎች የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ከምሁራን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል:: ምርምሮች ችግር የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው በማንሳት በተለይም በቀውስ ወቅት ሁሉም ያለውን ዕውቀት እና ልምድ በመጠቀም ለኅብረተሰብ ጤና መጠናከር እና ለአገልግሎት መሻሻል መሥራትና እንደሚገባ አሳስበዋል::
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ለኅብረተሰብ ጤና ደህንነት መጠበቅ እና መሻሻል ምሁራን እና ሁሉም ባለድርዎች በመተባበር በክልሉ የተከሰቱ እና በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ሥጋቶችን በጥናትና ምርምር መፍታት እንደሚገባ ጠይቀዋል:: በጉባዔው የቀረቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶችም ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ዓላማ ያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል::
ችግሮችን በጥናት ለይቶ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለውሳኔ ሰጪ አካላት በማቅረብ ምርምሮች እውነተኛ የችግር መውጫ መንገድ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል::
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ችግርን መቋቋም የሚችል እና የማይስተጓጎል የጤና አገልግሎትን በመገንባት ጤናማ እና አምራች የሰው ኀይል ለመፍጠር ምርምርን ማጠናከር ወሳኝ ነው:: በተጨማሪም የጤና ሥርዓቱን በማጠናከር እና የጤና ግብዓትን ተደራሽ በማድረግ የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት፣ ማኅበራዊ ሥነ ልቦና እና ሥነ አዕምሮ ግንባታ ላይ በትኩረት ለመሥራት ምርምርና ፈጠራ ዋና መፍትሔም ነው::
በተለይ በችግር ወቅት ምርምር መፍትሔ (መውጫ መንገድ) ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች ጤና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አካላት ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስታወቁት::
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች የጤና ተደራሽነትን፣ ጥራትን፣ ፍትሐዊነትን እና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል:: በችግር ውስጥም የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወሳኝ ስለመሆናቸው አንስተዋል::
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ የአማራ ክልል ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ያጋጠሙት እና ዛሬም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች ከሌሎች የጤና ወረርሽኞች ጋር ተዳምረው የጤና ሥርዓቱን ሲፈትኑት ቆይተዋል፤ እፈተኑትም ነው:: ይህም ማኅበረሰቡን ለተለያዩ ችግሮች ዳርገውታል::
ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጉ፣ የጤና አገልግሎቶችን በተገቢው መንገድ ለመሥጠት የሚያግዙ የጤና መሠረተ ልማቶች ላይ ያጋጠሙ ጉዳቶች፣ በሕክምና መሣሪያዎች እና መድኃኒቶች ላይ ያጋጠመው ዘረፋ እና ውድመት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማድረጉ እንዲሁም የኅብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት እንዲደናቀፍ፣ ተደራሽነት እንዲገደብ ማድረጉ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ መረጃን መሠረት በማድረግ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት እና ጥራትን ለማሳደግ፣ የጤና መሠረተ ልማቶችንም መልሶ ለማቋቋም እና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ነው ያነሱት::
በጤና ሥርዓቱ ላይ እስካሁን ያጋጠሙ እና በቀጣይም ሊስተዋሉ የሚችሉ ችግሮችን ለይቶ ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ ጤና ቢሮ ከክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጋር ጥናት እና ምርምር ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል::
በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮች የማያስተጓጉሉት የጤና ሥርዓት ለመገንባት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው ጥናቶች በምክረ ሐሳብ ጠቁመዋል:: ማኅበረሰቡ የጤና ተቋማትን ባለቤት ሆኖ መጠበቅ እንደሚኖርበት፣ ስነ ልቦናውን የሚጎዱ ነገሮችንም ቀድሞ በውይይት መፍታት እንደሚገባ በመፍትሔነት ተለይተዋል::
በአጠቃላይ አሁን የተደረጉ ጥናቶች የተሻለ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል። በክልሉ ውስጥ ካለው ግጭት በተጨማሪ የበሽታ ወረርሽኞች ስጋት መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ጥናቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ስርጭትን ቀድሞ ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም አንስተዋል::
በጉባኤው ላይ የቀረቡ ጥናቶች በቅንጅት የተሠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አብዱልከሪም፣ ይህም ወደ ድርጊት ለመቀየር አጋዥ እንደሚሆን አስታውቀዋል:: ጤና ቢሮ መረጃን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን በመስጠት የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል:: በጥናት የተገኙ ውጤቶችን እና በተመራማሪዎች የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ነው ያሉት::
ጤና አዳም
የዐይን ዙርያ መጥቆር መንስኤዎች
በቂ እንቅልፍ አለመተኛት/እረፍት አለማድረግ
የቫይታሚን ሲ እና ኢ እጥረት
ተደጋጋሚ አይን ማሸት
ለጸሃይ ብርሃን መጋለጥ
በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ
የአይን ህመም/ኢንፌከሽን
የታይሮይድ ሆርሞን ችግር
ምልክቶች
የዐይን ስር ወይም ዙርያው ቀለም መቀየር
እብጠት
የዐይን መቅላት ይጀምርና ዙሪያው ይጠቁራል
ዐይን አካባቢ የህመም ስሜት መኖር
የዐይን እይታ መቀነስ
ቀለል ያለ ራስ ምታት ወይም የአንገት ህመም
የቤት ውስጥ ህክምና
በጥንቃቄ የበረዶ ፓክ ወይም በቀዝቃዛ ጨርቅ ከ 10 – 15 ደቂቃ ቦታው ላይ ማስቀመጥ
በቂ እረፍት መውሰድ፣ በቂ ፈሳሽ መውሰድ
ጭንቅላትን ቀና አድርጎ መተኛት
የታይሮይድ ሆርሞን መታየት
የደም ማነስ ካለ ያንን ማከም
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታህሣስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


