በመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ስድስት ሀገራት ያዋስኑታል፤ አራት የአፍሪካ ሀገራት እና ሁለት የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት። አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የዓለም ንግድ የሚቀላጠፍበት፣ አምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት (ኃያላኑ) የጦር ሰፈር የገነቡበት፣ የኢትዮጵያም ዋነኛው የንግድ መስኮት ነው – ቀይ ባሕር። ስፍራው የዓለማችን የወታደራዊ እና የኢኮኖሚ ልብ በመሆኑ ኃያላን ሀገራት ትናንትም ዛሬም የሚርመሰመሱበት እና ለአፍታም ቢሆን ዓይናቸውን አይነቅሉበትም። ይህ ደግሞ የሽብር አደጋ ስጋት እና የባሕር ላይ ወንበዴዎች የማይጠፋበት ቦታ አድርጎታል።
ቀይ ባሕር ወደ አውሮፓ፣ መካክለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም እስያ ለሚላኩ ምርቶች ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ነው። የዓለማችን 12 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ይዘዋወርበታል። አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ እና ስሜን አፍሪካ ወደ አህጉራቸው ከሚያስገቧቸው ምርቶች 15 በመቶ የሚሆነው በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፍ ነው።
ካሳለፍነው ሕዳር ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በቀይ ባሕር የሚርመሰመሱ የንግድ መርከቦች ላይ በየመን የሀውቲ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት እየተስፋፋ መጥቷል። ይህም በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አደጋ ደቅኗል። በዚህ ችግር አፍሪካ፣ እስያ እና አውሮፓ በእጅጉ እየተፈተኑ ናቸው። ችግር ፈጣሪዎች ደግሞ በኢራን የሚደገፉት የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች መሆናቸውን ሮይተርስ አስነብቧል። የታጣቂ ቡድኑም ጥቃቶችን መሰንዘሩን በተደጋጋሚ አስታውቋል። በእስራኤል እና ሀማስ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሉ የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
አማፂያኑ በቅርቡ ባስወነጨፉት የባልስቲክ ሚሳኤል የፓናማ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበች በቀይ ባሕር ስትጓዝ የነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ አነስተኛ ጉዳት ማድረሱን ሲኤን ኤን ዘግቧል። ጥቃት የደረሰባት ይህቺ መርከብ አንድሮ ሜዳ ትሰኛለች። እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ የንግድ መርከቧ ከሩሲያ ተነስታ ወደ ህንድ በማቅናት ላይ ነበረች። ጥቃቱ የተፈጸመው ቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚገናኙበት የባብ ኤል ማንደብ የባሕር ወሽመጥ አቅራቢያ ነው።
የየመን ሀውቲ አማፂያን ከባለፈው ሕዳር ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአጠቃላይ በንግድ መርከቦች ላይ 50 ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ግዙፉ የአሜሪካ የባሕር ሎጅስቲክ አገልግሎት አስታውቋል። በዚህ ምክንያት የመርከቦች የመጫን አቅም ተገድቧል። ከ15 እስከ 20 በመቶ የመጫን አቅማቸው መቀነሱን መረጃው ያመለክታል።
ቀይ ባሕር የምድራችንን ከግማሽ በላይ ጉዞ ይቀንሳል። ይሁን እንጂ በቀይ ባሕር የሚንቀሳቀሱት የንግድ መርከቦች ከሀውቲ ታጣቂዎች ለማምለጥ ረጅሙን ጉዞ ለማድረግ ተገደዋል። የንግድ መርከቦቹ አፍሪካን ኬፕ ተብሎ የሚጠራውን መተላለፊያ እየተጠቀሙ ሲሆን ይህም ጊዜያቸውን ያባክናል፤ ለአላስፈላጊ ወጪም ይዳርጋቸዋል።
በዚህ የተማረሩት ታላላቅ የንግድ መርከብ ኩባንያዎች ከቀይ ባሕር እንደወጡም ተዘገቧል። ከታሕሳስ ዘጠኝ 2024 እ.አ.አ ጀምሮ የሀውቲ አማፂያን በተከታታይ ባደረሱት ጥቃት ምክንያት ከዓለማችን አምስቱ ዋና ዋና የመርከብ ኩባንያዎች አራቱ በቀይ ባሕር መንቀሳቀስ አቁመዋል። እንደ ብሪቲሽ ፔትሮሊየም (ቢፒ) ያሉ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች በቀይ ባሕር ማጓጓዛቸውን አቁመዋል። ይህ ደግሞ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ በሚያሻግረው ስዊዝ ቦይ እና ወደ ባብ ኤል ማንደብ ላይ ከፍተኛ ስጋቶች እንደነበሩ አይዘነጋም። በባል ኤል ማንደብ እና ስዊዝ ካናል መተላለፊያዎች በዓመት ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ መርከቦች ይተላለፋሉ። 12 በመቶ የዓለም ንግድ፣ 15 በመቶ የዓለም ነዳጅ ምርት፣ 40 በመቶው የአውሮፓ እና የእስያ ንግድም በሁለቱ መስመሮች የሚተላለፍ ነው።
አሁን ላይ በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል። ይህም እስራኤል በጋዛ ለምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ የበቀል እርምጃ እንደሆነ ተገልጿል። ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ አማፂያኑ አንድ መርከብ ያገቱ ሲሆን ሌላ አንድ መርከብ ላይ ደግሞ ጉዳት በማድረስ እንድትሰጥም አድርገዋል።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡና ንግድ የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ባደረሱት ጥቃት ለሦስት ቀናት ተስተጓጉሎ እንደነበር አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ የሚታወስ ነው። በቀጣይም የቡና ንግዱ ላይ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ችግሩ ሀገራችን ወደ አውሮፓ ገበያ በምትልከው የቡና መጠን ላይም ተጽዕኖ ፈጥሯል ነው የተባለው። አሁን ላይ ወደ ጀርመን ይላክ የነበረው የቡና መጠን በግማሽ መቀነሱን ደግሞ ዳይሬክተሩ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጥዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የአሜሪካ እና የእስራኤል ሎሌዎች ናቸው ብለው በሚኮንኗቸው የአረብ ባላንጣዎቻቸው፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ላይ የበላይነታቸውን ለማሳየት የሚወስዱት እርምጃ መሆኑ ጭምር ተሰምቷል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በኢራን አማካኝነት የታጠቁ እና ወታደራዊ ስልጠና ያገኙ ናቸው ተብሎ ይታመናል። የቡድን የጦር መሣሪያዎች፣ የባሕር ፈንጂዎች፣ የባልስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎች እንዲሁም ሰው አልባ ድሮኖች ከኢራን ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የንግድ መርከቦች ላይ ዒላማ ያደረገ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ፀረ መርከብ ሚሳኤሎችን እየተጠቀሙ ናቸው። በቅርቡ በእስራኤል ላይም የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ማስወንጨፋቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል። ጥቃቶቹ በእስራኤል ላይ ከባድ ስጋት መፍጠር ባይችሉም፤ የታጠቁት የጦር መሣሪያ በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች ላይ ግን ከፍተኛ ውድመት ያደርሳል ብሏል።
የእስራኤ እና ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የሀውቲ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ 200 የሚሆኑ ጥቃቶችን እንደከፈቱባት እስራኤል አስታውቃለች። ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም የሀውቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ቴል አቪቭን ደብድበዋል። የአንድ ሰው ህይወትም አልፏል። ሳይውል ሳያድር እስራኤል አማፂያን ቡድኑ ላይ የመጀመሪያውን ጥቃት አድርጋለች። እስራኤል በሰነዘረችው ጥቃትም የስድስት ሰው ህይወት ማለፉን ሮይተርስ አስነብቧል። ከእስራኤል በተጨማሪ አሜሪካ እና እንግሊዝም በኢራን በሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ወስደዋል።
በየመን 24 ሚሊዮን ሕዝብ ማለትም ከጠቅላላው 80 በመቶ የሚሆነው ሰብኣዊ እርዳታ የሚሻ ነው። ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዳሳወቀው 20 ሚሊዮኑ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል። የየመን 90 በመቶ የሚሆነው የምግብ ፍጆት ደግሞ ከውጪ የሚገባ በመሆኑ የየመን ነፃ አውጪ ነን የሚሉት የሀውቲ አማፂያን ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ እንቅፋት በመሆን ሕዝባቸውን ሳይቀር አደጋ ላይ ጥለዋል።
በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች ላይ የሚደረገው ጥቃት እስራኤልን እና አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ላይም ከባድ ሕመም ፈጥሯል። ይህም ሰፊ ቀጣናዊ ግጭት (ትርምስ) ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው አካባቢ ነው። ቀጣናው ሰፊ የባሕር መዳረሻ አለው፤ በቀይ ባሕር፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በህንድ ውቅያኖስ የተከበበ ነው። ይህም ቀጣናውን ቁልፍ ቦታ ያደርገዋል። አፍሪካን፣ አውሮፓን እና እስያን ያገናኛል። የጂኦ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታው ባለፉት ዐስርት ዓመታት የልዕለ ኃያላኑ የፍጥጫ መድረክ አድርጎታል።
በቀጣናው ግጭቶችን በማባባስ ረገድ የውጪ ኃይሎች ሚና የጎላ ነው። የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ቀይ ባሕር ውስጥ ያለውን ቀውስ አባብሶታል። የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ማለትም የዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ፣ የቱርክ፣ የኳታር፣ የሳውዲ አረቢያ እና የኢራን ጣልቃ ገብነቶች በአካባቢው የሚፈጠረውን ግጭት ለመፍታት አዳጋች አድርጎታል።
በቀጣናው የኃያላኑ ትኩረት ጨምሯል። ቻይና እና ጃፓን በጅቡቲ የጦር ሰፈር ገንብተዋል። በአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መካከል ፉክክሩ እና ውጥረቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አይሏል። ኃያላኖቹ በቀጣናው ተጽዕኗቸውን በማጠናከር የአፍሪካን ቀንድ የጦር አውድማ አድርገውታል። በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ አለመረጋግቶች እና ጦርነቶች መኖራቸው በቀይ ባሕር ለተፈጠረው ቀውስ አስተዋጽኦ ማድረጉን መረጃዎች አመልክተዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም