የእስራኤል እና የሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ድፍን አንድ ዓመት ሞልቶታል። ይህ ቀውስ የመካከለኛው ምሥራቅን ውጥረት ጨምሮ ሄዝቦላህን እና ኢራንንም ወደ ጦርነቱ አስገብቷቸዋል። ጦርነቱ ሶሪያ፣ የመን እና ኢራቅን ወደ መሳሰሉት ሌሎች የቀጣናው ሀገራት አድማሱን እንዳያሰፋ ስጋት አሳድሯል። እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት ተከትሎ ሀማስን የሚደግፉ የሀውቲ እና የሄዝቦላህ ታጣቂ ቡድኖች እስራኤል ላይ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ።
በተለይ የየመኑ የሀውቲ አማጺ ቡድን እስራኤልን ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚላቸውን የንግድ መርከቦች ላይ በቀይ ባሕር ጥቃት ማድረስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። አማጺ ቡድኑ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የጥቅምት ወር ብቻ ከ80 በላይ በሆኑ የንግድ መርከቦች ላይ በሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ማድረሱን አሶሼትድ ፕሬስ አስነብቧል።
በቅርቡም የላይቤሪያ ኬሚካል ጫኝ መርከብ ላይ ጉዳት ማድረሱን መረጃው አመልክቷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ሀንስ ግሩንድበርግ ለፀጥታው ምክርቤት እንደገለጹት የየመን የሀውቲ አማጺያን በቀይ ባሕር በሚያልፉት ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙ የአካባቢውን ቀውስ አባብሶታል።
የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ድርጅትም የሀውቲ ታጣቂዎች ምንም ዓይነት ወታደራዊ ተግባር በሌላቸው የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ወንጀል መሆኑን አስታውቋል። የቀይ ባሕር ቀውስ የጀመረው እ.አ.አ ጥቅምት 19 ቀን 2023 ነው። የሀውቲ ታጣቂዎች በኢራን የሚደገፉ ሲሆን፤ ከኢራንም የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ድጋፍ ይደረግላቸዋል። አሁን ደግሞ “ያክንሆት” የተሰኘውን ሚሳኤል ለአማጺ ቡድኑ ሩሲያ እንድትሰጥ ኢራን እያግባባቻት ነው ተብሏል።
አማጺው ቡድን ይህን የጦር መሳሪያ በእጁ የሚያስገባ ከሆነ በቀይ ባሕር የሚያልፉ የንግድ መርከቦች የበለጠ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ። እናም የአሜሪካ ባለስልጣናት ጉዳዩ በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። የየመንን መንግሥት የሚቃወሙት የሀውቲ አማጺያን እ.አ.አ 2014 ጀምሮ ነው በቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢ መንቀሳቀስ የጀመሩት።
ከጥር 2024 እ.አ.አ ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሀውቲን ጥቃት በማውገዝ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ጦር ለጥቃቱ ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ እና እንግሊዝ በሀውቲ አማጺያን ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ቢሰነዝሩም በቀይ ባሕር በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ግን አላቆመም። እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ አማጺ ቡድኑ በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንደማያቆም መግለጹን የዘገበው አልጀዚራ ነው።
ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ አሜሪካ የአማጺ ቡድኑን የምድር ውስጥ መሣሪያ ማከማቻዎችን ከሰሞኑ በቦንብ ደብድባለች፤ ዒላማ የተደረጉት ስፍራዎችም አማጺ ቡድኑ በቀይ ባሕር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች የተከማቹባቸው ናቸው ተብሏል::
አማጺ ቡድኑ በቀይ ባሕር ጥቃት ከፈጸመበት 2023 የጥቅምት ወር ጀምሮ በ193 የንግድ መርከቦች ላይ አንድ ሺህ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ተጠቅሟል። የየመን ሀውቲ አማጺ ቡድን መሪ አብደል ማሊክ አል ሀውቲ “ከፍልስጤም ጎን እንቆማለን፤ ታጣቂዎቻችን ጠላቶቻችን ከሆኑት እስራኤል፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በቀይ ባሕር የሚጓዙ የንግድ መርከቦች ላይ ጉዳት አድርሰናል” ብለዋል።
የሀውቲ አማጺያን አብዛኛውን የየመን ከተሞች እና ቦታዎች ተቆጣጥሯል። አሜሪካ እና እንግሊዝም የየመን ዋና ከተማን ጨምሮ የአል ማስሪህ ቴሌቭዥን ጣቢያን በሰው አልባ አውሮፕላን ደብድበውታል። የሀውቲ ታጣቂዎችን ጥቃት ሽሽት ከመቶ በላይ የሚሆኑ የንግድ መርከቦች ቀይ ባሕርን አልፈው በአፍሪካ ኬፕ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት ተገደዋል። በዚህ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ከመዳረሻቸው ለመድረስ ተጨማሪ 14 ቀናት ይወስድባቸዋል። ይህም የማጓጓዣ ወጪውን ከሦስት እጥፍ በላይ ያደርግባቸዋል። ችግሩ እልባት አለማግኝቱ ደግሞ የዓለም ኢኮኖሚን እያናጋ ነው።
ቀይ ባሕር ወደ አውሮፓ፣ መካክለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም እስያ ለሚላኩ ምርቶች ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ነው። የዓለማችን 14 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ይዘዋወርበታል። አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ስሜን አፍሪካ ወደ አህጉራቸው ከሚያስገቧቸው ምርቶች 15 በመቶ የሚሆነው በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፍ ነው።
በፈረንሳያዊው ፈርድናንድ ዴ ሌሴፕ ሀሳብ አመንጪነት የተሠራው የስዊዝ ቦይ የቀይ ባሕር እና የሜዲትራኒያንን ባሕር በማገናኝት ከእስያ ወደ አውሮፓ የሚወስደውን ጉዞ እንዲያጥር አድርጓል። የስዊዝ ቦይ ወደ እስያ እና አውሮፓ ለመጓዝ አነስተኛ ወጪ የሚያስወጣ መስመር ጭምር ነው። መስመሩም እጅግ አስፈላጊ የዓለማችን የልብ ምት ሆኗል።
ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ በሚያሻግረው ስዊዝ ቦይ እና ወደ ባብ ኤል ማንደብ ላይ ከፍተኛ ስጋቶች እንደነበሩ አይዘነጋም። በባል ኤል ማንደብ እና ስዊዝ ቦይ መተላለፊያዎች በዓመት ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ መርከቦች ይተላለፋሉ። 14 በመቶ የዓለም ንግድ፣ 15 በመቶ የዓለም ነዳጅ ምርት፣ 40 በመቶው የአውሮፓ እና የእስያ ንግድም በሁለቱ መስመሮች የሚተላለፍ ነው። አሁን ላይ ግን ከቀይ ባሕር ወደ ስዊዝ ቦይ የሚጓዙ መርከቦች ቁጥር ቀንሷል።
በዚህ ምክንያት ግብጽ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰባት መረጃዎች አስነብበዋል። ያም ሆኖ ግን ግብጽ የየመን አማጺ ቡድንን ለመዋጋት ከሌሎች ሀገራት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደለችም። የእስራኤል መከላክያ መጽሔትን ጠቅሶ ሚድል ኢስት ሞኒተር እንዳስነበበው ግብጽ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቷን በመግታት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በቀጣናው ውጥረቱ እንዳይባባስ፣ ከአረቡ ዓለም ጋር ባላት ፖለቲካዊ እና ሀይማኖታዊ ቅርበት ነው።
በቀይ ባሕር እየደረሰ ያለው ጥቃት እና አለመረጋጋት በሳውዲ አረቢያ፣ ሱዳን እና ሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይም ከባድ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ውጥረቱ እንዲጨምር አድርጓል።
(ስለሽ ተሾመ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም