የቀጠሉት፣ ግን ያልተሰሙት የሰላም ጥሪዎች

0
121

ባለፈው አንድ ዓመት የክልሉን ሰላም ለመመለስ መንግሥት ያደረጋቸው የሰላም ጥረቶች ክልሉን ወደ አንጻራዊ ሰላም እንደመለሱት በኩል ቢገለጽም በዓመቱ ያጋጠሙ በርካታ ስብራቶች ግን አሁንም ሳይጠገኑ ቀጥለዋል:: በክልሉ የትምህርት እንቅስቃሴ ላይ የደረሰው ጉዳት ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው:: በ2016 ዓ.ም ያጋጠመው ግጭት በክልሉ ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ተቋማት ያለ ተማሪ እና አስተማሪ እንዲከርሙ ማድረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ይጠቁማል:: በዚያውበዓመት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ተማሪዎች ከትምህርት እንደራቁም መረጃው ያሳያል:: የጸጥታ ችግሩ በዚህ ዓመትም በመቀጠሉ ምክንያት ክልሉ አሳካዋለሁ ብሎ የተነሳውን ሰባት ሚሊዮን የተማሪዎች ምዝገባ እስካሁን ማሳካት እንዳልቻለ አስታውቋል:: በዚህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ተቋማት ልዩ ከለላ እንዲደረግላቸው የሚያደርግ አስገዳጅ ሕግ ቢያወጣም፣ ትምህርት ከሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ቢደነግግም ዓለም ትኩረት የነፈገችው ግጭት በሀገራት ላይ እያስከተለ ባለው ውድመት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተገደዋል:: ይህ ለወደፊቱ የሚፈጠረው የትውልድ ክፍተት ከፍተኛ ነው::
ግጭቱ ያደረሰው እና እያደረሰ ያለው ጉዳት በትምህርት እንቅስቃሴው ላይ ብቻ ግን ተወስኖ አልቀረም:: መፍትሄ ርቆት የቀጠለው ግጭት በክልሉ ሕዝብ ላይ ሰብዓዊ ጉዳት አድርሷል። ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳቱም ከፍተኛ ነው። ማኅበራዊ ምስቅልቅሉ ቀላል አይደለም። የልማት ሥራዎች ተስተጓጉለዋል። መንገዶች በተደጋጋሚ ሲዘጉ ከርመዋል:: ይህም ሕዝቡ እንደ ጤና ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኝ ሆኗል፤ በሸቀጦች እና በምርት አቅርቦት ላይ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርጓል::
ግጭቱ እያደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመውጣት በአሁኑ ወቅት መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ መግባቱን የክልሉ ይታወቃል:: ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ የተገባዉ በ2016 ዓ.ም በመንግሥት በኩል የተደረጉ የሰላም ጥረቶች ለውጥ ባለማምጣታቸው እንደሆነ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን መግለጫ በሰጡበት ወቅት አስታውቀው ነበር::
ከሰሞኑ ደግሞ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የሰላም ውይይቶች እየተካሄዱ ነው:: በሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ወረዳ ነዋሪዎች በክልሉ የተፈጠረው እና ቀጥሎ እየተካሄደ ያለው ሰላምን የሚያውክ እንቅስቃሴ የአማራን ሕዝብ የማይመጥን እና ሊታረም የሚገባ አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል::
በሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በተደረጉ የውይይት መድረኮቹ የተገኙ ተሳታፊዎችም የሰላም እጦቱ ሕዝቡ በምጣኔ ሐብት፣ በልማት፣ በማኅበራዊ እና በሥነ ልቦና ክፉኛ እንዲጎዳ ማድረጉን አንስተዋል:: በተለይ ግጭቱ የታዳጊ ሕጻናትን የወደፊት ሕይወት በእጅጉ እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል:: በተለይ በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የነገዋን ሀገር በዕውቀት የሚመራ ትውልድ እንዳይኖር የማድረግ አጋጣሚው እንዲሰፋ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም እንዲቆም ጠይቀዋል::
በደሴ ከተማ ከመንግሠት ሠራተኞች ጋር በተደረገው ውይይት የተገኙት የመንግሥት ሠራተኞች በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ግጭቶች የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: በመሆኑም አዋጭ መንገዱ ሀገራዊ የጥል ምክንያቶችን መለየት እና በግልጽ ተነጋግሮ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ነው ብለዋል::
የመንግሥት ቀዳሚ ፍላጎት እና ዕቅድ ልዩነቶችን በሰላማዊ ንግግር መፍታት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ገልጸዋል:: እስካሁንም ተደጋጋሚ የሰላም የሰላም ጥሪዎች መደረጋቸውን አስታውሰዋል:: በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ጋርም ንግግር መኖሩን ገልጸዋል:: ይሁን እንጂ አሁንም በመንግሥት እና በታጣቂ ኅይሎች መካከል ተሰልፈው ጥረቱን የሚያሰናክሉ ኀይሎች መኖራቸውን አስታውቀዋል::
ያም ሆኖ መንግሥት አሁንም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ለመፍታት ከሚመጣ ኅይል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here