የቀጣዩ ትውልድ አርበኝነት

0
93

ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን አልፎ የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ጮራን የፈነጠቀው ድል ማነው? ቢሉ በዓለም ላይ ያለው ሁሉ በአንድነት የሚመልሰው “ዓድዋ!” በማለት ነው:: አፍሪካ የነጮች ቅርጫ ሆና በቅኝ ግዛት አሳሯን አይታለች:: ዜጎቿ የራሳቸው የሆነ ብሄራዊ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ እና ሥርዓት እንዳይኖራቸው ከማድረግም በላይ ለነጭ አገልጋይነት የታጩበት፤ ግን ደግሞ በዓድዋ የከሸፈበት የታሪክ ሁሉ ህያው መሠረት ነው::

የበርሊን ኮንፍረስ ኢትዮጵያን ለጣሊያን አሳልፎ ቢሰጥም የኢትዮጵያን “ወይ ፍንክች” ማለት ግን በተግባር ያረጋገጠ ነበር:: የነጭ የበላይነት አክትሞ ዓለም ሁሉንም በፍትሐዊነት የምታስተናግድ እንድትሆን ዓድዋ አደራ የሰጠበት ሆኖ ዛሬም ይታወሳል:: ድሉም በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን ታስቦ ይውላል::

ዛሬ ልናስነብባችሁ የፈለግነው ስለ ዓድዋ ድል አይደለም፤ ጣሊያን በኢትዮጵያ መሸነፏ አንገብግቧት በኢትዮጵያ ላይ ዳግም የበቀል በትሯን ስላሳረፈችበት የ1928 ዓ.ም ዳግም ጦርነት እና የአርበኞች ተጋድሎ እንጂ::

የኢትዮጵያ አርበኞች ድረ ገጽ (ethiopiapatriots.org) ጣሊያን ኢትዮጵያን ሳታንበረክክ አርፋ እንደማትቀመጥ የነበራትን ፍላጎት የቤኒቶ ሞሶሎኒ የአንድ ወቅት ንግግር ያስታውሳል:: “የዓለም ማኅበር (የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት) በኢትዮጵያ ላይ ያለውን መብታችንን በማወቅ ፋንታ እኛን ለመጨቆን ያስባል:: ነገር ግን ጨቋኞች ማኅበርተኞችን (ከተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ውስጥ) በፖለቲካም፣ በጦርነትም ቢመጡብን እንመልሳቸዋለን… ኢትዮጵያን 40 ዓመት ታገሥን፤ አሁን ግን በቃን! አስቀድመን ደኅና አድርገን ሳንዋጋ ወደ ኋላ ሊመልሰን የሚችል እንደሌለ ሁሉም ይወቅ!” በማለት የጣሊያንን ሕዝብ ከባሕር ማዶ ተጨማሪ መሬት ሊያወርስ ጦርነቱን በይፋ እንደጀመረ ታሪክ ያስረዳል::

የተለያዩ ጸሐፍት ስለ ጦርነቱ አጀማመር፣ ስላደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት እና ስለ ድሉ ምስጢር አውስተዋል:: የአምስት ዓመቱን የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት በተመለከተ ከጻፉ የታሪክ ምሁራን መካከል በእስራኤል ቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ሀጋይ ኤርሊህ ይገኙበታል::

ጣሊያን የተደራጀ የጦር መሳሪያን ይዛ ወደ ዓድዋ በመዝመት ኋላ ቀር የጦር መሳሪያ በታጠቁ ኢትዮጵያውያን የተከናነበችውን ሽንፈቷን በድል ለመመለስ ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ የበቀል ጦርነት እንደጎሰመች ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ:: በቀሉም በምድር እና በሰማይ በተደራጀ የጦር መሳሪያ ንጹሀንን ፈጅቷል:: እንደ ታሪክ ፕሮፌሰሩ ይህ ጦርነት ግን የኢትዮጵያውያን ጽናት፣ አልሸነፍ ባይነት እና አይበገሬነት በተግባር የተገለጠበት ነበር::

ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ማሳያ አድርገው የጻፉት “ንጉሣችን በሌሉበት አንዋጋም!” ብለው አለማፈግፈጋቸውን ነው:: ከጠላት ጋር የተመጣጠነ ትጥቅ እና ስንቅ አለመኖርም “ዝም ብለን እንቀመጥ፣ ጠላት ይግዛን… እንዲሉ እንዳላደረጋቸው ገልጸዋል:: በእነዚህ ምክንያቶች የአምስት ዓመቱ ጦርነት ድል ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ጽፈዋል::

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንዳስታወቁት ጣሊያን ከ40 ዓመታት ዝግጅት በኋላ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት ዳግም ያረጋገጠ ነው:: የአምስት ዓመቱ ጦርነት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ ማስመስከሪያ ሆኖ በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን ታስቦ እንደሚውል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል:: ይህ ቀን ንጉሠ ነገሥቱ ከአውሮፓ የተመለሱበት እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተውለበለበበት ቀን ነው::

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተሰልፎ ሀገሩን ከጠላት ወረራ በመከላከል ነጻነቱን ማረጋገጡንም ገልጸዋል:: እንደ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አገላለጽ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ እንደ ህዝብ ሁሉም አርበኛ ነው::

ልጅ ዳንኤል “የአርበኞችን ቀን አክብረን የምንውልበት ዋነኛው ምክንያት የቀድሞ ጠላቶቻችንን ጠባሳ እየነካካን ለማድማት ወይም ሕዝቡ ጥላቻን ይዞ እንዲጓዝ አይደለም:: ከውጭ የተሰነዘረብንን ጥቃት በጋራ መመከት የቻልን ሕዝብ መሆናችንን አዲሡ ትውልድ እንዲረዳው እና የራሱን አዲስ ታሪክ እንዲፈጥር ለማድረግ ነው” ብለዋል::

“የዓድዋን በዓል በታላቅ ድምቀት አክብረናል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የአርበኞችን ቀንም በእኩል ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: ምክንያቱም ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት መመከት ባይቻል ኖሮ ዓድዋን ማክበር አይቻልም ነበር ሲሉ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል:: ጣሊያን በመድፍ፣ በአውሮፕላን እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች በመታገዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ለመመከት አርበኛው ጊንጥ እና እባብን ትራሱ አድርጓል፤ የሚበላው እና የሚጠጣው አላሳሰበውም፤ በዚህም የተገኘው ድል በከፍተኛ ደረጃ መታየት እና መከበር እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል::

በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት በርካታ መንግሥታት ተለዋውጠዋል:: መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ሁሉም የየራሱን ርዕዮት ዓለም ማራመዱን ተከትሎ አርበኞች የሚገባቸውን ክብር አግኝተው ዘመናትን በክብር እንዲታወሱ አልተደረጉም ብለዋል:: ለዚህ አብነታቸው የአርበኞች ማኅበር በደርግ ዘመነ መንግሥት ፈርሶ የነበረ መሆኑን ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚመልሱ እና እርስ በእርስ የሚያስተሳስቡ የድሮ ታሪኮች በሥርዓት እንዲታወሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል:: የዘንድሮው መታሰቢያ ቀን በአዲስ አበባ የድል ሀውልት ሲከበር ብዙ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል:: የሀውልቱ መታደስ እና ዙሪያውን መቀመጫ መሠራቱ ለታሪኩ የተሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ይላሉ::

የአርበኞችን መታሰቢያ ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ ታሪኮች በመንግሥት ሥር ክብረ በዓላቸው ቢደረግ የሚል ምክረ ሐሳባቸውን አንስተዋል:: የአርበኞች ቀን ታስቦ የሚውለው በዋናነት በማኅበሩ አስተባባሪነት ነው:: ይህ ደግሞ በየአምስት ዓመቱ የሚቀያየር መሪ ባለበት  ሁኔታ ክብረ በዓሉ ወጥነት ያለው  እና አከባበሩም ፍጹም የደመቀ ሆኖ ዘመናትን እንዳይሻገር ሊያደርገው እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል::

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርቦኞች ቀዳሚ መልዕክት አዲሡ ትውልድ በሌላ አይነት ጀግንነት የራሱ የነገ አርበኛ እንዲፈጥር ነው:: በትምህርት፣ በሕክምና፣ በምህንድስና፣ በእርሻ እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከድኅነት በሚያወጣ ሥራ ላይ መሠማራት እና በትጋት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከሌላው ዓለም እኩል ተወዳዳሪ በሚያደርጉ የትምህርት ጥራት ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል:: አስተማማኝ ሰላም እና ፍትሕ እንዲሰፍን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርቦኞች ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል::

የዘንድሮው የአርበኞች የድል ቀን በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት ተከብሯል:: በዕለቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቦታው ተገኝቶ ማክበር ባይችልም በያለበት ታሪኩን ለልጆቹ እንዲያሳውቅ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል:: ፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here