የቁማር ሱስ

0
143

የሰው ልጅ ወደዚች ዓለም ሲቀላቀል ምንም አይነት ሃብት እና ንብረት ይዞ አይደለም። ባዶ እጁን ከተፈጠረ በኋላ ግን አንዱ ባለፀጋ ሌላው ድሃ ሆኖ ህይወት ይቀጥላል። ወደ ሃብት መድረሻ ማማዎቹም በርካታ ናቸው።

ከቤተሰብ በውርስ ሃብት ይገኛል። በትምህርት ሃብት ማፍራት ይቻላል። በተለያዩ የቢዝነስ መስመሮችም በርካታ የዓለማችን ቢሊየነሮች ተፈጥረዋል። በበርካታ ህገወጥ ዜዴዎችም ሚሊዬነር ይሆናል። መቸም ቢዘረዘር የሃብት መገናኛ መንገዱ የትየለሌ ነው።

በምንም ይሁን በምን የተገኘ ሃብት ሁሉ ለአንዳንዶች ዘላቂ መገለጫ ሆኖ ይቀጥላል። አንዳንዱ ሃብት ደግሞ ታይቶ ጠፊ ሲሆን ይታያል። ከበርካታ ምክንያቶች መካከል የቁማር ሱሰኝነት አንዱ መገለጫ ነው። ቁማር የሰው ሃብትን  ከመሻት ስግብግብነት ይመነጫል፤ ውጤቱ ግን በአብዛኛው የቁማር ሱሰኞችን ለዘርፈ ብዙ የህይወት ምስቅልቅል መዳረግ ነው።

የቁማር አጀማመር

ቁማር/Gambling/ መነሻ ታሪኩን አራት ሺህ ዓመት ወደኋላ ይቆጥራል። መዳረሻዎቹ ደግሞ ጥንታዊ ቻይና፣ ግብፅ፣ ግሪክ እና ሮም ናቸው። ቁማር በጥንታዊ ቻይና ልክ እንዳሁኑ ሎተሪ መንግሥት ለህዝብ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ማሰባሰቢያ በሚል አስጀመረው። በጥንታዊ ግሪክ ደግሞ የቁማር አጀማመር ከአማልክት ጋር ይያያዛል።

የቁማር ሱስ መንስኤዎች

የቁማር ሱስ የሚመነጨው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ኮንቲኔንታል ሆስፒታሊቲ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው የጄኔቲክ ቅድመ ዝንባሌ ቁማርን ጨምሮ፤ ዘረ መል ለሱስ ተጋላጭ ያደርጋል። በመሆኑም የቤተሰብ ሱስ ታሪክ ያላቸው ግለሰቦች በቁማር ሱስ የመያዝ እድላቸው ከፍ ሊል ይችላል።

በሳይኮሎጂካል መንስኤዎች ደግሞ እንደ ግትርነት፣ የደስታ ፍላጎት እና የሴሮቶኒን /Serotonin/ (የሃዘን፣ ተስፋ መቁረጥ እና ድብርት ስሜት) ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አንዳንድ የባህሪ መገለጫዎች ግለሰቦችን ወደ ቁማር ሱስ እንዲያመሩ ከሚያደርጉት መካከል ይጠቀሳሉ። በዚህ ምክንያት የሚከሰት የዝንባሌ መዛባትም፤ የቁማርተኛውን የአሸናፊነት ቅዠት ከፍ ያደርጋል። ይህ ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን ኪሳራን ያስከትላል፤ የቁማር ሱሱንም እንዲቀጥል ያስገድደዋል።

ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችም ግለሰቦች ወደ ቁማር ሱስ እንዲገቡ ያደርጋሉ። እዚህ ላይ በኛ ሃገር የሚዘወተረውን የድንኳን ቤት ቁማር ማንሳት ይቻላል። በማህበራዊ መስተጋብራችን በአንድ ቤት ሃዘን ሲከሰት ተሰባስቦ ማስተዛዘን ተለምዷዊ ነው። ይህን ተከትሎ የሚከናወነው የካርታ ቁማር ጭዋታ በማህበረሰባችን ቅቡልነት አግኝቷል። በዚህም የተነሳ ለማስተዛዘን በሚል በመጠነኛ ገንዘብ ቀን ላይ ይጀመራል፤ መሸት ሲል ደግሞ “በሴካ እና ጋፈፋ” በሚሉት ጨዋታዎች “ላጥ ላጥ” ወደሚባለው ፈጣን እና አክሳሪ የቁማር ጨዋታ ይቀየራል። ኪሳራን ያስከትላል፤ ጥልም የሃዘን ቤቱ ማሳረጊያ ሊሆን  ይችላል። በሀዘን ቤት ድንኳን የሚጀመር የቁማር ልምምድ አድገት እያሳዬ በርካቶችን የከፋ የቁማር ሱስ ያዋርሳል።

የቁማር ሱስ ምልክቶች

አንድ ሰው ወደ ቁማር ሱስ የገባ መሆኑን ከሚያመላክቱ መገለጫዎች መካከል ሱሰኛው ከቤተሰቡ እና ጓደኞቹ ተደብቆ ጊዜውን ያሳልፋል። ለዚህም ነው አንዳንዶች የቁማር ሱስን “ድብቁ ሱስ” እያሉ የሚገልጹት።

በአጉል ተስፋ ቁማር ተጫውቶ ሃብት ለማፍራት በሚደረግ ግብግብ፤ ለመጫወቻ የሚሆን ገንዘብ በተለያዬ መንገድ ለማግኘት መሻትም የቁማር ሱስ መገለጫ ምልክት ነው። የቁማር ኪሳራን /መሸነፍን/ ተከትሎ በሚፈጠር ስሜትም እረፍት ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥ እና ብስጭት የቁማር ሱሰኛነትን ያመላክታሉ። መደበኛ ሥራን በወቅቱ እና በሚፈለገው የቁጥር እና ጥራት መጠን መፈጸም አለመቻል፣ የመጠጥ እና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን በድብቅ አብዝቶ መጠቀም መጀመርም ለቁማር ሱስ ተጋላጭችነትን አመላካቾች ናቸው።

የቁማር ሱስ ጉዳቶች

የቁማር ሱስ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን ያስከትላል። በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚገባው በየትኛውም ሃይማኖት ዉጉዝ መሆኑ ነው። “ያንተ ያልሆነን አትመኝ” የሚለውን ትዕዛዝ ያስክዳል። ምክንያቱም በቁማር ጨዋታ የሚገኝ ሃብት፤ የራስ ያልሆነን ገንዘብ ከሌላ ሰው ለማግኘት መሻት እና ከተቻለም መውሰድ ነው።

ቁማር ማህበራዊ መስተጋብርን ያበላሻል። ቁማርተኛ ለቤተሰቡ፣ ዘመዶቹ እና ጓደኞቹ በቂ ጊዜ አይሰጥም፤ የቁማር ሱሱን ለማርካት ሲል በርካታውን ጊዜ በቁማር ቤቶች ተደብቆ እንዲያሳልፍ ይገደዳል። እንደየማህበረሰቡ ወግ በሚከናወኑ የደስታና የሃዘን ክንዋኔዎች በተገቢው ጊዜና ሁኔታ እንዳይሳተፍ ያደርገዋል።

የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ ሥራውን በአግባቡ እንዳይፈጽም ያደርገዋል። በግል በሚያከናውናቸው ሥራዎችም  የትርፋማነት እድሉን ነፍጎ ለኪሳራ ይዳርገዋል።

ሜዲኮቨር ሆስፒታልስ በድረ ገጹ እንደሚያስገነዝበው የቁማር ሱስ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች ላይ ጉልህ የአእምሮ ጤና ጉዳት አስከትሏል። የመንፈስ ጭንቀት እና የአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት አደጋዎችንም ያባብሳል። የቁማር ሱሰኛ የወደፊት የቁማር እንቅስቃሴዎችን በማሰብ አልያም ያለፉትን የቁማር ልምዶች በማሰብ የመንፈስ ጭንቀት ህመም ያድርበታል።

በቁማር ሱስ የተያዙ ሰዎች ለዕዳ ወይም ለኪሳራ ይዳረጋሉ። በቁማር ምክንያት የሚደርስ የፋይናንስ ተፅዕኖ የቁማር ሱስ አስከፊ ገፅታ ነው። ቁማርተኞች የነበራቸው ሀብት ሁሉ አጥፍተው በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋል። የገንዘብ ኪሳራ ችግርን ለመፍታት ሲሉም ህገወጥ ተግባራትን ለመፈፀም ይገደዳሉ።

ያጡትን ገንዘብ እመልሳለሁ በሚል ጉጉት ከሚቀርቧቸው ሰዎች ዘንድ የብድር ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። ዕዳውን መመለስ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱም፤ አታላይ ባህሪያቸው የነበራቸውን ጤናማ ወዳጅነት ያሳጣቸዋል። በመጨረሻም የቁማር ሱስ ራስን የማጥፋት ስሜት ፈጥሮ ህይወትን ይቀጥፋል።

ተጠቃሽ የቁማር ሱሰኞች

በዓለማችን የቁማር ሱሰኞች መዝገብ ከሚጠቀሱት መካከል ታዋቂው ሩሲያዊ ጸሐፊ ፊዮዶር ዶስቶየፍስኪ /Fyador Dostoyevsky/ አንዱ ነው። “ዘ ጋምብለር” በሚለው መፅሐፉ ስለቁማር ሱስ እና ስሜት የራሱን ህይወት መገለጫ አድርጎ አስነብቧል። ከዚህም በተጨማሪ ወንጀል እና ቅጣት /Crime and Punishment/፣ ስለ ንፁህነት እና ክፋት መጋጨት /Idiot/ … በሚሉት እና በሌሎችም ጽሑፎቹ ይታወቃል።

ፊዮዶር ዶስቶየፍስኪ በጸሐፊነቱ እና አስተሳሰብ ተመራማሪነቱ/Philosophical Novelist/ ብቻ አይደለም ዓለማችን ያጎላችው፤ እውቅ የቁማር ሱሰኛም ነበር። የቁማር ሱሱ ለከፋ የጤና እና የገንዘብ ችግር ዳርጎት፤ የህይወት ዘመኑ ተጠናቋል።

ቻርለስ ጄምስ ፎክስ/Charles James Fox/ የ18ኛው ክፍለ ዘመን እና የ19ኛው ዘመን መጀመሪያ ታላቅ የእንግሊዝ ፖለቲከኛ ነበር። እ.አ.አ ከ1749-1806 ኖሯል። አባቱ ሄንሪ ፎክስ ታዋቂ ፖለቲከኛ ስለነበሩ እሱም የፖለቲካውን ጎራ የተቀላቀለው በ19 ዓመቱ ነበር።

በእንግሊዝ የባሪያ ንግድ እንዲቀር የበኩሉን ጥረት አድርጓል። ለፍትህ እና ነፃነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይታገል ስለነበር “የነፃነት ድምፅ” እና “የህዝብ መብት አስተዋይ” በሚል የሚገልፁትም ነበሩ።

ታዋቂው እንግሊዛዊ ፖለቲከኛ ፎክስ ታዲያ በዚህ ብቻ አልነበረም የሚታወቀው፤ የቁማር ሱሰኛም ነበር። ወላጅ አባቱ ባለፀጋ ስለነበሩ ተዝናኖትን ባሻው መንገድ እንዲፈፅም ፈቀዱለት። ያገኘውን እድል ተጠቅሞ ቁማርን መዝናኛ አደረገ። በመጨረሻ ግን የተጠናወተው የቁማር ሱስ ለከፍተኛ የገንዘብ ችግር ዳረገው። ብድር ውስጥ ገባ፤ አንዳንድ ንብረቶችን ሸጠ። በዚህም የነበረውን ክብር እና ዝና አጣ።

የቁማር ሱስ በዓለማችን የበርካቶችን ሃብት እና ዝና አሳጥቷል። የቤተሰብ ህይወት አመሰቃቅሏ፤ ለከፋ ድህነት ዳርጓል፤ ስደትን አስከትሏል፤ የራስን ህይዎት እስከማስጠፋት አድርሷል።

ከቁማር ሱስ መውጫ መንገዶች

ለሁሉም የቁማር ሱሰኛ ተመሳሳይ መፍትሄ ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ግለሰብ ተኮር መፍትሄ ያስፈልጋል። ግለሰቡ የሚችል ከሆነ ባንዴ ቁርጥ አድርጎ ማቆም ውጤታማ ያደርጋል። ይህ ግን በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚያሳኩት ነው።

ከቁማር ሱስ ለመላቀቅ የመጀመሪያው እርምጃ ጠቃሚ እንዳልሆነ ተረድቶ፤ ቆራጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ ነው። በራስ ውሳኔ መፍትሄ ላይ መድረስ ካልተቻለ የህክምና እርዳታ ቀጣዩ የመፍትሄ ማግኛ ይሆናል። ከመልካም ሱስ /ልማድ/ (Positive Addictions) እና መልካም ሰዎች ጋር መወዳጀት ከቁማር ሱስ ለመላቀቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው።

ከቁማር ሱስ ለመላቀቅ፤ በህክምናው መስክ የግንዛቤ /ባህሪ ቴራፒ (ሲቢቲ) በጣም ውጤታማ ከሆኑ የህክምና ዘዴዎች አንዱ ነው። ይህም ከቁማር ጋር የተያያዙ ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦችን እና ባህሪዎችን ግለሰቦች እንዲለዩ እና እንዲቀይሩ ይረዳቸዋል። ውስጣዊ ተነሳሽነትን በማጎልበት ቁማርን ለማቆም መፍትሄን ያስገኛል።

የቁማር ሱስን ሊያነሳሱ ከሚችሉ ግለሰቦች እና አካባቢዎች መራቅ፤ ደስታን በሚሰጡ አማራጭ ተግባራት ውስጥ መሳተፍም በግል የሚወሰዱ የመፍትሄ አማራጮች ናቸው።

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here