የቁርጥ ቀን ወዳጃችን

0
13

በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በሀገሪቷ ስም ሰፈር እና አደባባይ ተሰይሟል፡፡ ኢትዮጵያም በዚች ሀገር መሃል ከተማ በስሟ ትምህርት ቤት እና አደባባይ ተሰይሞላታል፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር እስከ 2009 ድረስ በኢትዮጵያ ስም የሚጠራ የባቡር ጣቢያም ነበር (በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ምክንያት የኢትዮጵያ ስም ተነስቶ ነበር) የኢትዮጵያ ስም ሲፋቅ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለው ነገር አልነበረም፤ ይልቁንም በሀገሪቱ የሚኖሩ ራስ ተፈሪያዊያን ተከራክረው ባቡር ጣቢያውን በኢትዮጵያ ስም ዳግም አሰይመውታል፡፡ ይህች ሀገር የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ወዳጅ ናት፤ ይህንን ብዙ ሰው ላያውቀው ይችላል፡፡

ፋሽስት ጣሊያን በ1988 ዓ.ም በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መሪነት አድዋ ላይ ድል ከተደረገ በኋላ ለ40 ዓመታት ራሱን አዘጋጅቶ ዳግም ወረራ ፈጽሟል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሀገራቸውን ላለማስወረር የሚችሉትን ካደረጉ በኋላ ባለመሳካቱ ለዓለም አቤቱታ ለማሰማት ወደ ቤልጂየም ብራሰልስ አቅንተዋል፡፡ በዛውም ለዓለም ሕብረት አባል ሀገራት አቤት አሉ፡፡ ነገር ግን ከአብዛኛው አባል ሀገራት ስላቅ እና ሹፈት ነበር የደረሰባቸው፡፡ በዚህ ክፉ ወቅት ከተበዳይዋ ኢትዮጵያ ጎን ከቆሙ አምስት ብቻ ሀገራት ውስጥ የዛሬዋ የሽርሽር መዳረሻችን ሜክሲኮ አንዷ ነበረች፡፡ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን በተቃራኒው የቁርጥ ቀን ወዳጅ ሀገር ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

ሜክሲኮ  በሰሜን አሜሪካ  አህጉር ትገኛለች፡፡ አጠቃላይ ስፋቷም ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን  ስኩየር  ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ በሲአአይኤ  ካታሎግ  መረጃ መሠረት  የሕዝብ ብዛቷም  በ2025 እ.አ.አ 131 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 89 በመቶው የክርስትና ዕምነት ተከታይ ነው፡፡ የሜክሲኮ ዋና ከተማ ሜክሲኮ ሲቲ ትባላለች፡፡ የሜክሲኮ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን የነፍስ ወከፍ ገቢዋም 25 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ መገበያያዋም የሜክሲኮ ፔሶ ይባላል፡፡

ሜክሲኮ በዓለማችን ላይ በጥንት ዘመን ከፍተኛ ሥልጣኔ ላይ ደርሰው ነበር የሚባልላቸው የማያ እና የአዜቲክ ስልጣኔዎች ማዕከል ነበረች፡፡ ሜክሲኮ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ አሁን ያላትን ሁለት እጥፍ ስፋት ነበራት፡፡ ሆኖም ከአሜሪካ ጋር በተደረገ ጦርነት ተሸንፋ 55 በመቶ የሚሆነውን ግዛቷን አጣች፡፡ ተቆርጦ ወደ አሜሪካ የተቀላቀለው መሬት ስፋት ከኢትዮጵያ  ይበልጣል፡፡ አሜሪካ በወቅቱ 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከፍላ መሬቱን አጸናችው፡፡ ዛሬ ላይ ከሦስት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ከሚሰፋው የሁለቱ ሀገራት ድንበር ከአንድ ሺህ በላዩ በብረት ፍርግር እና ኤሌክትሪክ በተጠመደበት እሾህ ሽቦ የታጠረ ነው፡፡ ይህን ሁሉ መሰናክል እና የመግቢያ ክልከላ አልፈው በሕገ ወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሜክሲኮያዊያን አሜሪካ ውስጥ አሉ።

ዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ ደግሞ ከ700 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ጥንታዊ እና ውብ ከተማ ናት፡፡ ሜክሲኮ ሲቲ 22 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል፡፡ ከተማዋ በዓመት 22 ሴንቲ ሜትር ወደ ታች ትሰምጣለች፡፡ ባለፈው አንድ ክፍለ ዘመን ብቻ ዘጠኝ ሜትር ወደ ታች ሰምጣለች፤ የዚህ ምክንያቱም ከተማዋ ሐይቅ ላይ በመገንባቷ ነው፡፡

በመሃል ሜክሲኮ ሲቲ በጥቅጥቅ ጫካ የተሸፈነ ፓርክ ይገኛል፤ ስሙም ቦስኪዩ ዴ ቻፑልቴፔክ ይባላል፡፡ የዚህ ፓርክ ስፋት በኒው ዮርኩ ሴንትራል ፓርክ በእጥፍ እንደሚበልጥ የዎርልድስ ሞንመንተም ፈንድ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል፡፡ በመላው ላቲን አሜሪካ  ትልቁ ፓርክ  ሲሆን  ሦስት  የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ በውስጡም  የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የመመገቢያ ሬስቶራንቶች እና ሐይቅ  ይዟል፡፡

ሜክሲኮ ዘመናዊ እና ሰፋፊ የባቡር ጣቢያዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ከገነቡ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡ የባቡር ትራንስፖርት በእጅግ አነስተኛ ዋጋ መጠቀም የሚቻልባት ሀገርም ናት፡፡ በዚህም ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቀን ውስጥ ባቡርን በመጓጓዣነት ይጠቀማሉ፡፡ የምድር የባቡር ሥፍራዎቻቸው ከመጓጓዣነት ባለፈ የተለያዩ ኩነቶችንም ያስተናግዳሉ፤ ለአብነት አውደ ርዕዮች፣ ሙዚቃ ዝግጅቶች፣ ፊልም መመልከቻዎች፣ ቤተ መጻሕፍት እና ሌሎችም ግልጋሎቶች ይሰጡባቸዋል፡፡

ሜክሲኮ የጋራ መጓጓዣ መንግዶችን ሕዝቦቿ እንዲጠቀሙ ታበረታታለች፤ ለዚህም ሲባል አውቶብሶች ብቻ የሚጓዙባቸው ጎዳናዎች አሉ፡፡ ያለ ትራፊክ መጨናነቅ ሰዎች የፈለጉበት ቦታ በጊዜ ስለሚደርሱ የአውቶብሱን አማራጭ የበለጠ ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም ሀገሪቷ የነዳጅ ወጪን ቀነሰች የአካባቢ ብክለትንም ተከላከለች ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ኤሌክትሪክ መኪኖች፣ ብስክሌቶች እና የገመድ ላይ መጓጓዣዎች በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

ሜክሲኮ የምግብ ሀገር ናቸው ከሚባሉት ውስጥ ምትጠቀስ ናት፤ ታኮስ የሚባለው የምግብ ዓይነት ደግሞ ሀገሪቷ በዓለም የምትታወቅበት መለያዋ መሆኑን የከልቸርስ ትራቭልድ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል፡፡ ሜክሲኮ ገብቶ ታኮስን ሳይቀምሱ መውጣት ነውር ነው፡፡

ታኮስ በሜክሲኮ በስሙ ቀን ተሰይሞለታል፤ ይህም መጋቢት 30 ነው፡፡ አሜሪካዊያን በታኮስ ፍቅር ከመውደቅ አልፈው በየዓመቱ ጥቅምት አራትን የታኮስ ቀን በሚል ያከብሩታል፡፡ ታኮስ በዋናነት ትናንሽ ቂጣዎች፣ የተፈጨ ስጋ፣ አይብ፣ የተፈጨ አቮካዶ፣ አትክልት፣ ስልስ እና በሌሎች ግብዓቶች ይዘጋጃል፡፡ ተኪላ የተባለው አልኮል መጠጥም የሜክሲኮ መታወቂያ ነው፡፡ የቸኮሌት ሀገር በሚል በዓለም የምትታወቀው ስዊዘርላንድ ናት፤ ነገር ግን ቸኮሌትን ሠርታ ለዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀች ሜክሲኮ ናት፡፡

ሜክሲኮአውያን ከምዕራብ ዓለሙ በተለየ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከስፔን እና ከቀደምት ቀይ ሕንዳዊያን ጋር በዋነኛነት ስነ ሕይወታዊ ማንነታቸው የተሰናሰለ ነው፡፡ የስፓኒሽ ቋንቋም ከሀገር በቀል ዘየ ጋር ተቀላቅሎ ይነገራል፡፡ ሜክሲኮ በስነ ሕንጻ የታወቀች ናት፤ ጥንታዊ እና ዘመናዊ የኪነ ሕንጻ ተጽዕኖ ያረፈባቸው አያሌ የሚያማምሩ ሕንጻዎች አሏት፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቲውቲሁዋካንን የመሳሰሉ ሕንጻዎች በስፋት ይገኙባታል፡፡ ከባህር ዳርቻዋ፣ ታሪካዊ ቦታዎቿ እና ማራኪ መልክዓ ምድሯ እኩል ኪነ  ሕንጻዎቿ  የጎብኚዎች  መዳረሻዎች ናቸው፡፡ የሜክሲኮ  ሽርሽራችንን  እዚሁ ላይ አበቃን፤ ሰላም!

 

አጭር እውነታ

ሜክሲኮ

 

  • ሜክሲኮ በሰሜን አሜሪካ አህጉር ትገኛለች፡፡
  • አጠቃላይ ስፋቷም ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡
  • የሕዝብ ብዛቷም እ.አ.አ በ2025 131 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
  • የሜክሲኮ ዋና ከተማ ሜክሲኮ ሲቲ ትባላለች፡፡
  • የሜክሲኮ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ነው፡፡
  • የነብስ ወከፍ ገቢዋም 25 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡
  • መገበያያዋም የሜክሲኮ ፔሶ ይባላል፡፡
  • ሜክሲኮ ሲቲ 22 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል፡፡
  • ሜክሲኮ ዘመናዊ እና ሰፋፊ የባቡር ጣቢያዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ከገነቡ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡
  • ታኮስ የሚባለው የምግብ ዓይነት ሀገሪቷ በዓለም የምትታወቅበት ነው፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here