የቅርጫ ማህበራዊ ፋይዳ

0
150

በኢትዮጵያውያን ዘንድ  በበዓላት እና ከበአላት ውጭ ባሉ ጊዜያት እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች ከብት በጋራ ገዝቶ አርዶ ስጋ መከፋፈል  /ቅርምት፣ ቅርጫ/ የተለመደ ድርጊት ነው:: እኛም ቅርጫ ከሚፈፀምባቸው ባእላት አንዱ ልደት በመሆኑ  ትውልድ እና እድገታቸው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ አካባቢ ኑሯቸውን ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ያደረጉትን  አቶ ልንገር ክንዴን ቅርጫ የሚከናዎነው መቼ? እና እንዴት?… ነዉ? ስንል ጠየቅናቸው:: እርሳቸው እንዳሉን  በገጠር አካባቢ በበዓላት፣ ሰርግ ፣ ለቅሶ ወይም ትልቅ ድግስ ካልሆነ በስተቀር አንድ ከብት ብቻን አርዶ የማይጨረስ በመሆኑ ከብት በጋራ ተገዝቶ በመደብ በመከፋፈል አባላት እንደ አቅሙ ይከፋፈላል::

ባደጉበት በምሥራቅ ጎጃም አካባቢም ሰርግ ወይም ተዝካር ደጋሹን ለማገዝ በጋራ የመደገስ /ሌማት የመያዝ/ ልምድም አለ::  ለድግሱም  ባለሰርጉ በሬውን ገዝቶ  ሲታረድ ሌላው ባለሌማት ደግሞ እንደየ አቅሙ ሥጋውን በመከፋፈል ደጋሹ ያወጣውን በከፊል ይሸፍናል:: ከብት በጋራ ገዝቶ፣ አርዶ መከፋፈል/ቅርጫ ሥጋ፣ቅርምት)  ከበፊት ጀምሮ የመጣ ባህል መሆኑን አቶ ልንገር አስታውሰዋል::

በገጠሩ አካባቢ በሬ ገደል ገብቶ ሲወድቅም ከመሞቱ በፊት ታርዶ ባለንብረቱ  እንዳይጎዳ ብር አዋጥቶ በመስጠት በሬውን አርዶ ሥጋውን በመከፋፈል የሚደረገው እገዛ  ቅርጫ ይባላል:: ቅርጫ መቼ? እንዴት ተጀመረ? ለሚለው ግን በትክክል እንደማያውቁና ከአባቶቻቸው የመጣ ልማድ እንደሆነ ተናግረዋል::

ቅርጫ በድግስ ብቻ ሳይሆን በበዓላት ወቅት ሰንጋው ታርዶ  ቅርጫ ሲከፋፈል  በዓሉን የሚያደምቁና ከወዳጅ ፣ ዘመድ ፣ ቤተሰብ ጋር ተሰባስበው ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠብቁበት መንገድም   ሆኖ እስከዛሬ ዘልቋል::

ቅርጫ አንድ ማኅበር ወይም ቡድን፣ ጎረቤታሞች፣ ዘመዳሞች፣ ጓደኛሞች አሁን አሁን ደግሞ ከብት ገበያ አካባቢ  የማይተዋወቁ ሰዎች ሁሉ ሳይቀር ተሰባስበው አንዱን በሬ ወይም ላም በመግዛት ስጋዉን ለአራት፣ ለስድስት አሊያም ለስምንት   የሚካፈሉበት ሂደት ነው:: ድባቡም በሥራ፣ በቀልድ ፣ በጨዋታ እና ትኩስ ስጋ በመቀማመስ  የታጀበ በመሆኑ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት እና የማይረሳ ትዝታ ይፈጥራል::

ሌላው ሥለቅርጫ ያነጋገርናቸው አቶ ለገሰ አበራ እንደሚሉት ደግሞ  ከብት ገዝቶ እና አርዶ መከፋፈል አንዱ የበዓል ድምቀት እንደሆነ ያምናሉ:: ቅርጫ ከዚህ  ያለፈ ፋይዳ እና ቁርኝት እንዳለውም አቶ ለገሰ ተናግረዋል:: አብረው የሚሠሩ  ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሠራተኞች  የማይቋረጥ ወርሃዊ መዋጮ በማድረግ በዓሉ ሳይደርስ በሬውን  በዝቅተኛ ገንዘብ  ገዝተው  እንዲደልብ ካደረጉ በኋላ  በአል ሲደርስ ይከፋፈላሉ:: “ይህ ሲሆን”አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሀንስ አይሽረውም” እንደሚባለው ቅርጫ ሰዎችን  ከሥራ ባልደረባነት አልፎ  የሚፈጥረው ማህበራዊ  ግንኙነት በቀላሉ የሚቆረጥ አይሆንም::

አንዳንድ ሰዎች እንዳሉን ደግሞ  በቋሚነት በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ያለማቋረጥ የሚፈጽሙት የቅርጫ ማህበር አላቸው::  የቅርጫ ሥጋ መከፋፈል ከበዓሉ ድባብ ባሻገር የከብት ግዢና ዕርዱም ከተከናወነ በኋላ በቅርጫው ከሚሳተፉት ሰዎች ከአንዱ (በእድሜ ትልቁ)  ቤት ቅቤ ከበርበሬ ጋር ተመቶ፣ እንጀራ… ይቀርባል:: አራጁ ከምላስ እና ሰንበር ፣ከሥጋው እንዲሁም ከጉበቱ ቆራርጦ  በማዘጋጀት በጋራ ተሰብስበው ይበላሉ::

ጠላው፣ የአበሻ አረቄን ጨምሮ የተለያዩ መጠጦችም የቅርጫ ዝግጅት ማድመቂያዎች እንዲሆኑ አባላቱ ከየቤታቸው ያመጣሉ:: ታዲያ በሬውን የባረከው ሰው የበሬውን ሙሉ ልብ የመውሰድ ባህል የነበረ ሲሆን አሁን አሁን ግን አሱም አብሮ መከፋፈሉን አቶ ለገሰ ነግረውናል::

የበዓሉ ዋዜማ ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት የሚጀምረው ይህ የዕርድ ሥነ ሥርዓት አሁን አሁን አራጆች ለብዙ ሰዎች ለማረድ በሰዓት ቀጠሮ በመያዝ እርድ የሚጀመረው ከሌሊት ስድስት ሰዓት እንደሆነም አቶ ለገሰ አስረድተዋል:: ዕርዱ ግማሽ ከሆነ በኋላ ግማሹ ቅርጫውን ወደ ማከፋፈሉ፣ ግማሾቹ ደግሞ ከጉበት እና ምላስ የተዘጋጀውን ስጋ እየተቃመሱ ለአራጆችም እያጎረሱ የበዓሉን ጅማሮ ያበስራሉ::

በዚህ ሁኔታ የሚከናወነው የቅርጫ ሥጋ  እውቀት የሚጠይቅ ትልቅ ሙያ በመሆኑ ሁሉም ሰው የየራሱ ኃላፊነት መወጣት አለበት:: በቅርጫ ክፍፍል ወቅት የማኅበሩ ሰዎች በሁለት ቡድን በመከፋፈል  አንደኛው  ከአራጁ ጋር በመሆን ሥጋን በማመዛዘን ያስቀምጣል፤ በመደቡ ላይ ደግሞ የቆሙ ታዛቢዎች  “ይሄ በዝቷል ፣ ይሄ አንሷል” እያሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ:: በመጨረሻም ስማቸው በወረቀት ላይ ተጽፎ በተመደበው ሥጋ ላይ ይጣላል:: ከመደቡ ላይ ስማቸውን እያነበቡ የደረሳቸውን ይወስዳሉ:: በአንድ ሰው ላይ አነሰና በዛ የሚል ቅሬታ ሳይሰማ ቅርጫ ፍጻሜውን ያገኛል::

አብዛኛው ማኅበርተኛ እንዲሁም ብልት አውጪው ደስተኛ ሆነው እንዲሠሩ ከዕርዱ ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምግብ ቀርቦ በጋራ መመገቡ፣መጠጣቱ፣ሳቅ እናጨዋታው… እንደሚቀጥል አቶ ለገሰ ገልፀዋል::

በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የቅርጫ ክፍፍል በበዓላት  አሁንም  ያስቀጠሉ እንዳሉ ሁሉ የተውትም አልጠፉ:: ይህ ችግር የተፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት አንድም የከብት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች የሚያገኙት ገቢና አሁን ያለው የኑሮ ውድነት አለመጣጣም መሆኑን ነው የተናገሩት አቶ ለገሰ::

አቶ ለገሰ የቅርጫ ወቅት ትዝታም አላቸው፤ ከብት ገዝተው ዕርድ ለማከናወን ወደ ቦታው ሲያቀኑ ከብቱ መጥፋቱን፣ አራጅ ቀርቶ  ለማረድ ሲሞክሩ አንደኛው የማኅበሩ አባል በጉልበቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የተወሰኑ ሰዎች ዕርዱን ትተው   በሕክምና ተቋም እንዳሳለፉም ያስታውሳል::

የቅርጫ ሥጋ የመከፋፈል ባህል በተለይ በእድሜ የገፉ ሰዎች  የማይተው ባህል ነው::  ወጣቱም ይህንን ባህል ማስቀጠል እንደሚኖርበት አቶ ለገሰ  ይገልጻሉ::

በበአላትም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በአራጁ አጋዥነት የቅርጫ ክፍፍሉ ከተጠናቀቀ በኋላ እርስ በርስ በመመራረቅ ለቀጣይ ዓመት/ጊዜ/ እንዲያደርሳቸው መልካም ምኞታቸውን ተለዋውጠው ይለያያሉ::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የታኅሳስ 28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here