የቆሙ ኳሶች

0
25

በዘመናዊ የእግር ኳስ ስፖርት ውበት የሚለካው በኳስ ቁጥጥር (Possession) እና በሚያማምሩ ቅብብሎች ብቻ መሆኑ ቀርቷል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አዲስ እና እጅግ ወሳኝ የሆነ የማይታይ ጦርነት እየተካሄደ ነው።  ጦርነቱ የሚከናወነውም ኳሱ ከቆመበት ቦታ ነው። የማዕዘን ምቶች፣ የቅጣት ምቶች እና የጎን ውርወራዎች አሁን የአሰልጣኞች  ፈተና እና የውጤት መለወጫ ዋነኛ መሳሪያዎች ሆነዋል።

በዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ሻምፒዮን ለመሆን በሚደረግ ፉክክር፣ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ለማግኘት በሚደረግ ትግል እና ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ክለቦች ለቆሙ ኳሶች (Set-pieces) ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ ሆኖባቸዋል። በፕሪምየር ሊጉ የቆሙ ኳሶች ጉዳይ ከአሁን በኋላ ዕድል ነው ተብሎ የሚተው አይደለም። ይልቁንስ ሳይንስ፣ ስነ-ልቦና እና ታክቲክ የተቀላቀለበት የጨዋታ ወሳኝ ክፍል ሆኗል።

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁሌም በታክቲክ ለውጦች ግንባር ቀደም ነው። ፔፕ ጋርዲዮላ ባርሴሎናን ይዞ ያስተዋወቀው እና ዓለምን የመራው የ”ቲኪ-ታካ” (ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት) ዘመን በ2025/2026 የውድድር ዘመን ቦታውን ለሌላ ታክቲክ የለቀቀ ይመስላል። አሁን ላይ ውበት ሳይሆን ውጤት፣ ቅብብል ሳይሆን ጉልበት ወሳኝ ሆኗል። ኳሷ በቆመችባቸው አጋጣሚዎች (Dead-ball situations) የሚቆጠሩ ግቦች የሊጉን አሸናፊ እየለዩ ነው። ይህ የቆመ ኳስ አብዮት አርሰናልን የመሳሰሉ ክለቦችን ወደ ሊጉ አናት ሲያደርስ  አንዳንዶቹን ደግሞ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል።

ጊቭ ሚ ስፖርት እና ኦፕታ (GiveMeSport & Opt) ያወጡት ቁጥራዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በፕሪምየር ሊጉ ከሚቆጠሩት አጠቃላይ ግቦች ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት መነሻቸው ከቆሙ ኳሶች ነው። ይህ ማለት በየጨዋታው ከሚቆጠሩት ሶስት ግቦች አንዱ የሚገኘው ከማዕዘን ወይም ከቅጣት ምት ነው።

ቡድኖች ይህንን ዕድል ለመጠቀም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት የቆሙ ኳሶች አሰልጣኝ (Set-piece Coach) እና የመረጃ ተንታኞችን እየቀጠሩ ነው። ዘርፉ ከአሁን በኋላ እንደ ተጨማሪ የሚታይ ሳይሆን  እንደ ዋና የግብ ማስገኛ መንገድ ተደርጎ እየተወሰደ ነው። ጨዋታው በቴክኒክ እና በታክቲክ እየጠነከረ ሲሄድ በክፍት ጨዋታ (Open Play) ተጋጣሚን መስበር እየከበደ መጥቷል። ስለዚህ የቆሙ ኳሶች ያንን የተጠቀጠቀ የኋላ ክፍል  ለመስበር ትልቁ አማራጭ ሆኖ ብቅ ብለዋል።

በዚህ ዓመት የቆመ ኳስ ሲነሳ የአርሰናልን ስም ሳይጠሩ ማለፍ አይቻልም። መድፈኞቹ በፕሪምየር ሊጉ የቆመ ኳስ ንጉሥ ለመሆን በቅተዋል። ለዚህ ስኬት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የሚኬል አርቴታ ረዳት የሆኑት ፈረንሳዊው የቆሙ ኳሶች አሰልጣኝ ኒኮላስ ጆቨር ናቸው። አርሰናል እንደ ጋብሪኤል ማጋሌስ፣ ዊሊያም ሳሊባ እና ካይ ሀቨርትዝ የመሳሰሉ ቁመታቸው ረጅም እና በአየር ላይ ጠንካራ የሆኑ ተጫዋቾችን በስብስቡ ይዟል። በተለይ ብራዚላዊው ተከላካይ ጋብርኤል ማጋሌስ ከማዕዘን ምት የሚሻሙ ኳሶችን ወደ ግብ በመቀየር ረገድ በሊጉ ተወዳዳሪ የለውም። አርሰናል የሚጠቀመው ዋና ታክቲክ የተጋጣሚን ግብ ጠባቂ ማጨናነቅ ነው ።

ዘ አትሌቲክ እንደዘገበው አርሰናል ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች በልምምድ ሜዳ ላይ ብዙ ጊዜ እንደሚሰጥ  አመልክቷል። እያንዳንዱ ተጫዋች ኳሱ ሲመታ የት መቆም እንዳለበት እና ምን ማድረግ እንዳለበት በሽርፍራፊ ሴኮንድ ስሌት ይረዳሉ። አርሰናል ለዋንጫ ሲፎካከር ይህንን መሳሪያ ሲጠቀም ሌሎች ክለቦች ደግሞ ለተለያየ ዓላማ ይጠቀሙበታል። ኤቨርተን በክፍት ጨዋታ ግብ የማስቆጠር ችግር ስላለበት እያንዳንዱን የማዕዘን ምት ወደ ግብ ለመቀየር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደርጋሉ። ለኤቨርተን  አንድ የማዕዘን ምት ከፍጹም ቅጣት ምት ያልተናነሰ ዋጋ አለው። ጄምስ ታርኮውስኪ፣  ጃራድ ብራንትዋይት እና ዲዋይት ማክኒል ከሚሻሙ ኳሶች የሚያገኙትን እድል ወደ ግብ ለመቀየር የቡድኑ ዋና መሳሪያዎች ናቸው።

የኡናይ ኤምሬው አስቶን ቪላ አካሄድ ደግሞ የተለየ ነው፤ የቡድኑ የቆሙ ኳሶች አሰልጣኝ አውስት ማክፊ (Austin MacPhee) እጅግ የተወሳሰቡ እና ፈጠራ የተሞላባቸው እንቅስቃሴዎችን ይተገብራሉ። ተጫዋቾች ተጋጣሚን ለማሳሳት ቦታ ይለዋወጣሉ (Screening) አጫጭር የማዕዘን ምቶችን ይጠቀማሉ፤ እንዲሁም ያልተጠበቁ ኳሶችን ወደ ሳጥን ይልካሉ። ቪላን ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመለሰ አንዱ ምክንያት ነው።

እንደ ጊቭ ሚ ሰፖርት መረጃ በሊጉ ውስጥ አዳዲስ እና ወጥ የሆኑ የታክቲክ ለውጦች እየታዩ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ብዙ ቡድኖች ኳሱን ከግብ ክልል ወደ ውጪ በማራቅ (Out-swinging) ማሻማትን ይመርጡ ነበር። አሁን ግን አዝማሚያው ተቀይሯል። እንደ ዴክላን ራይስ (አርሰናል)፣ ጄምስ ዋርድ-ፕራውዝ (ዌስትሃም) እና ፔድሮ ኔቶ (ቼልሲ) ያሉ ተጫዋቾች ኳሱን ወደ ግብ አቅጣጫ ያሻማሉ። እግር ኳስ የቅርጫት ኳስ አጨዋወት ስልቶችን እየቀዳ ነው። ተጫዋቾች ግብ ለማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የቡድን አጋሮቻቸውን ከተከላካይ ነጻ ለማድረግ ሲሉ ሁሉንም መንገዶችን ይዘጋሉ። ይህ ስልት በተለይ አንድ ለአንድ (Man-to-Man) በመከላከል ለሚጫወቱ ቡድኖች ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ክለቦች እንደ ስቶክ ሲቲው ሮሪ ዴላፕ ዘመን ረዣዥም የጎን ውርወራዎችን እና የማዕዘን ምቶችን እንደ ዋና የግብ ምንጭ እየተጠቀሙ ነው። ከዚህ ቀደም እነዚህን እድሎች እንደ ተጨማሪ አማራጭ ይመለከቱ የነበሩ ክለቦች አሁን እንደ ዋና ስትራቴጂ ወስደውታል።” የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች እና የስካይ ስፖርት ተንታኝ ጄሚ ካራገር “የሊቨርፑል ደጋፊ ብሆንም እውነቱን መናገር አለብኝ፤ አርሰናል ማዕዘን ምት ባገኘ ቁጥር ጭንቅላቴን በምሬት እይዛለሁ። እንደዚህ አይነት አስፈሪ ነገር በእግር ኳስ አይቼ አላውቅም። አሁን ላይ መላው የእግር ኳሱ ዓለም አርሰናል የማዕዘን ምት ካገኘ ግብ እንደሚያስቆጥር እርግጠኛ ሆኗል” ሲል ተደምጧል።

በቆመ ኳስ አብዮት የሊጉ ንጉሥ አርሰናል ነው። ሚኬል አርቴታ እና የእርሳቸው የቆመ ኳስ መሀንዲሱ  ኒኮላስ ጆቨር መድፈኞቹን ወደማይቆም ኃይል ቀይረዋቸዋል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ2025/26 የውድድር ዘመን ብቻ አርሰናል 12 ግቦችን ከቆመ ኳስ በማስቆጠር የሊጉን መሪነት ይዟል። የብራዚላዊው ተከላካይ ጋብሪኤል ማጋሌስ ጉልበት የዊሊያም ሳሊባ ቁመት እና የዴክላን ራይስ ወደ ውስጥ የሚታጠፉ (In-swinging) ኳሶች ለተጋጣሚዎች አስፈሪ  መሳሪያዎች ሆነዋል። አርሰናል  በክፍት እንቅስቃሴ (Open play) ግብ ማስቆጠር አልሳካ ካለው መፍትሄው በእጁ አለ – እሱም የማዕዘን ምት ነው። ከአርሰናል ባልተናነሰ መልኩ ሌሎች የለንደን ክለቦችም በቆመ ኳስ አስፈሪ  እየሆኑ መጥተዋል።

ቼልሲ 10 የቆሙ ግቦችን ከመረብ  አገናኝቷል። በአሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የሚመራው ቼልሲ በቆመ ኳስ በሊጉ ሁለተኛው ውጤታማ ቡድን ነው። የፔድሮ ኔቶ ግሩም የግራ እግር ቅጣት ምቶች እና የኮል ፓልመር ቴክኒክ ለሰማያዊዎቹ አዲስ ጉልበት ሆነዋል። በተለይም ኖቲንግሃም ፎረስት ላይ ኔቶ ያስቆጠራት የቅጣት ምት የቡድኑን ብቃት ማሳያ ተደርጋ ትወሰዳለች። በአሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ስር እንደገና የተወለዱት ክሪስታል ፓላሶች  የኤፍ.ኤ ዋንጫ ድላቸውን ተከትሎ በሊጉም ጠንካራ ሆነዋል። ክሪስታል ፓላስ  እስካሁን ዘጠኝ ግቦችን ከቆመ ኳስ አስቆጥሯል። ዣን ፊሊፕ ማቲታ፣ ኢስማኢላ ሳር እና ኤዲ ኒኬቲያህ ያላቸውን የአየር ላይ ብቃት በመጠቀም ሊቨርፑልን ሳይቀር አሸንፈዋል። የማርክ ጉዌሂ ረጅም የጎን ውርወራዎች የቡድኑ ሌላኛው አደጋ ፈጣሪ መሳሪያ ነው።

ሩበን አሞሪም ወደ ኦልድትራፎርድ ከመጡ በኋላ ዘንድሮ ማንቸስተር ዩናይትድ ዘጠኝ ግብ ከቆመ ኳስ አስቆጥሯል። አሰልጣኙ የሚከተሉት ሦስት ተከላካይ መስመር (Back-three system) እንደ ሃሪ ማጉዋየር ያሉ ረዣዥም ተከላካዮች ወደ ፊት ሄደው ግብ እንዲያስቆጥሩ እድል ፈጥሯል።ሌላው የዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ክስተት የሆኑ ክለቦች ሰንደርላንድ እና ብሬንትፎርድ ናቸው። ድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት “ጥቁር ድመቶቹ” ስምንት ግቦችን ከቆሙ ኳሶች አስቆጥረዋል። አርሰናል ላይ ያስቆጠሩት ግብም ከረጅም የቅጣት ምት የተገኘ ነበር። አዲሱ አሰልጣኝ ኪት አንድሪውስ የክለቡን የረዥም ውርወራ ባህል አስቀጥለዋል። እንዲሁም ብሬንትፎርድ በሊጉ የፍጹም ቅጣት ምት ንጉሥ ነው፤ አምስት  ፍጹም ቅጣት ምቶችን በማስቆጠር። ክለቡ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ስምንት ግቦችን ከቆመ ኳስ አስቆጥሯል።  ሲያን ዳይችም በኖቲንግሃም ፎረስት እንደ ክሪስ ውድ እና ኒኮላ ሚሌንኮቪች ያሉ ግዙፍ ተጫዋቾችን ይዘው የቆመ ኳስን ዋነኛ የማሸነፊያ መሳሪያ አድርገውታል።

ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ግን እስካሁን በቆመ ኳስ ደካማ ቁጥሮችን አስመዝግበዋል። ሁለቱም  ክለቦች ከቆመ ኳስ በተመሳሳይ ሦስት ግቦችን ነው ያስቆጠሩት:: ፔፕ ጋርዲዮላ አሁንም ኳስን በማንሸራሸር ማሸነፍን ይመርጣሉ። ወኃ ሰማያዊ ለባሾቹ ኤርሊንግ ሀላንድን የመሰለ አጥቂ ቢኖራቸውም ከቆመ ኳስ የሚያገኙት ግብ ግን እጅግ አናሳ ነው። ሀላንድ ራሱ ሊቨርፑል ላይ ፍጹም ቅጣት ምት መሳቱ አንደኛው የችግሩ ማሳያ ነው። በአርኔ ስሎት የሚመራው ሊቨርፑልም ተመሳሳይ ችግር አለበት። ቫን ዳይክን እና ሶቦስላይን የመሰሉ በቆመ ኳስ የተካኑ ተጫዋቾች ቢኖሩትም ቁጥራቸው ከሌሎቹ ክለቦች አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ኒውካስትል፣ ሊድስ እና ቦርንማውዝ እያንዳንዳቸው ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የ2025/2026 የእንግሊዝ የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን እግር ኳስ ውጤት ተኮር እና ታክቲካዊ የቆመ ኳስ አጠቃቀም ያዘነበለበት ሆኗል። ሜዳ ላይ ውብ እግር ኳስ መጫወት ብቻ ዋጋ እያጣ ነው፤ የማዕዘን ምቶችን ወደ ግብ የመቀየር ጥበብ የሻምፒዮንነት ሌላኛው ቁልፍ መንገድ ሆኗል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር  29  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here