እ.ኤ.አ 1949 ጀርመን አንዳች ታሪክ አስተናገደች፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ የናዚ ጀርመን ጦር በምዕራባዊያኑ ሰራዊት ድል ከሆነ ወዲህ ሀገሪቱ በምዕራባውያኑ እጅ ወደቀች፡፡ እስከ 1949 ዓ.ም ነበር ታዲያ በምዕራባዊያኑ ቁጥጥር ስር የወደቁት ሦስት የጀርመን ዞኖች የተዋሀዱት፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱን ለሁለት ከፈላት፡፡ የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ወይም ምዕራብ ጀርመን ተብለው ተሰየሙ’ አሜሪካዊያን ምዕራቡን ጀርመን፤ የሶቭዮቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ደግሞ በምሥራቃዊ በርሊን ይዞታውን የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ብሎ በማቋቋም ነበር ምላሽ የሰጠው፡፡ ምሥራቅ ጀርመን በሚለው በሰፊው ትታወሳለች፡፡
የአንድ ሀገር ሰዎች በታሪክ አጋጣሚ የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነዋል፡፡ አንደኛው ኮሚኒስት ሌላኛው ካፒታሊስት፡፡ በርሊኖች ለሁለት ተከፍለው ከአስፋልት ወዲያና ወዲህ እየተያዩ ወዳጅ ፣ ዘመድ፣ ወንድማማቾች ከተሰመረው መስመር ስንዝር መሻገር ተከልክለው እየተነፋፈቁ መኖር ግድ አላቸው፡፡
የምዕራብ ጀርመን ክልል ከምሥራቁ በጣም የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ በመጣበት አጋጣሚ ምሥራቅ ጀርመን ግን በኢኮኖሚ እድገት አላመጣም ነበር፡፡ እናም ዜጐች በመጠለያ፣ በምግብ ችግሮች ብሎም በዝቅተኛ ምንዳ መሰቃየት ሆነ እጣ ፋንታቸው፡፡ ይህ ደግሞ ምሥራቅ ጀርመኖች ምዕራቧ ጀርመን በመፍለስ የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ይሰደዱ ጀመር፡፡ እያደር የስደተኛው ቁጥር እየጨመረ ሄደ፡፡ እስከ 1961 ዓ.ም ድረስም ሦስት ሚሊዮን ምሥራቅ ጀርመኖች ወደ ምዕራብ ፈለሱ፡፡ ይህ በምዕራባዊያን ዘንድ ለኮሚኒዝም ውድቀት አመላካች እንደሆነ አድርገው ሩስያን ለማጣጣል ምቹ አጋጣሚ ነበር::
የበርሊን ግንብ የመልካምና የመጥፎ እሳቤዎች ግጭት የፈጠረው የቀዝቃዛው ጦርነት አንዱና ዋነኛው ታሪካዊ ክስትት ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከምዕራቡ ጥምር ሀገራት በተቃራኒው ከነበረው ጐራ ጦርነቱን ትመራው የነበረችው ናዚ ጀርመን በሁሉም ርብርብ ተንበረከከች፡፡ እናም በምዕራቡ ሀያላን እጅ ወደቀች፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የግንቡ ጉዳይ የሚጀምረው፡፡
ጀርመን ለሁለት ባእዳን ሀይሎች ተሸነሸነች፡፡ አሜሪካ ምዕራቡን ጀርመን፤ ሶቭየት (ሩሲያ) ደግሞ ምሥራቅ ጀርመንን ተከፋፍለው እንደ ርእዮተ ዓለማቸው ያስተዳድሯት ጀመር፡፡ የአንድ አፈር/ምድር ልጆች የሆኑት ጀርመናዊያን ለካፒታሊስት እና ኮሚኒስት ርዕዮቶች ሊገዙ ጎራቸውን ለዩ፡፡ ይህ ወዳጅ ዘመድን ለዓመታት አለያይቶ ከበርሊን ማዶ ለማዶ ባሻጋሪ እየተያዩ እንዲኖሩ ግድ ሆነባቸው፡፡ የሁለት ዓለም ሰዎች መሆናቸው አይደል?!፡፡
በሶቭየት ህብረት ኮሚኒስት አስተዳደር ሥር የወደቀችው የምሥራቅ ጀርመን ዜጎቿ ለኢኮኖሚ እና ተዛማጅ ችግሮች ተዳረጉ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የተሻለ ሕይወት በመፈለግ ወደ ተሻለው ምዕራብ ጀርመን የመሰደድ ዕጣ የደረሳቸው፡፡ እናም ወደ ምዕራብ ጀርመን የሚፈልሱ ጀርመናዊያን ቁጥር እያደገ መጣ- ለቁጥጥር እስኪከብድ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ታዲያ በ1961 ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ ጀርመናዊያን ድንበር እየጣሱ ምዕራብ ጀርመን ገብተዋል፡፡ በእንድ ጀንበርም 4ሺህ ምሥራቅ ጀርመናዊያን ወደ ምዕራብ ጀርመን በመሰደድ የፍልሰቱ ክበረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እ.ኤ.አ ነሀሴ 12 ቀን 1961 ታዲያ እንዲህ አይነቱን ግዙፍ ፍልሰት ዝም ብሎ ለማለፍ የኮሚኒስት ባላሥልጣናቱ ተዕግስታቸውን ያሟጠጡባቸው ይመስላል፤ እናም አንድ እልባት ወደመስጠት ወሰዳቸው፡፡ በመግስቱ /ረፋድ ላይ የምሥራቅ ጀርመንና ሩሲያዊያን ሰራተኞች በርሊንን ለሁለት የሚያለያይ የሽቦ አጥር በመትከል ድንበሩን ዘጉት፡፡ ምዕራብ ጀርመኖች በጧት የተመለከቱትን ነገር ማመን አቅቷቸው የሩሲያዊያንን ተግባር ቢቃወሙም የሰማቸው አልነበረም፡፡ የሽቦው አጥር ግን ከ3 ቀናት በላይ አልቆየም፡፡ ወዲያውኑ አጥሩ እየተወገደ በቦታው በኮንክሪት ብሎኬቶች ግንብ መተካት ተጀመረ፡፡
በቀናት ውስጥ አራት ሜትር ከፍታ ያለው 111 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ግንብ በበርሊን እንብርት ላይ ተገንብቶም አለቀ፡፡ ምን አልባት ግንቡን ዘለው የሚሄዱ ሰዎችን ለመቆጣጠር ደግሞ 3ዐዐ የመጠበቂያ ማማዎች ተሰሩለት፡፡ ምስኪን የምዕራብ እና የምሥራቅ በርሊን ወንድማማቾች ናፍቆታቸውን እንኳ እንዳይወጡ ተነፈጉ፡፡
የበርሊኑ ግንብ በነሐሴ መጨረሻ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከግንቡ ማዶ አቋርጦ መሄድ የማይታሰብ ሆነ በሁለቱ ወገኖች ፍቅር መካከል ባዕዳን ያቆሙት ጠብ አጫሪ ግድግዳ በእንዲህ አይነት ታሪካዊ አጋጣሚ የአንድ ሀገር ልጆችን የቅርብ እርቁ አድርጐ እንዳለያያቸው ሀያ ስምንት ዓመታትን ዘለቀ፡፡
ያም ሆኖ ግን የባሰባቸውን የምሥራቅ ጀርመን ሰዎች ግንቡን ለማለፍ ከመሞከር አልተቆጠቡም ነበር፡፡
በምሥራቅ በኩል ግንቡን ለማለፍ የሞከሩ 19ዐ ሰዎች ለጠባቂዎች ጥይት ቀለብ ሁነው የቀሩበት አሳዛኝ ክስተትም በታሪክ ተቀምጧል፡፡
የምሥራቅ ጀርመን ባለሥልጣናት ስላቆሙት ግምብ ማብራሪያ መስጠት ጀመሩ፡ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ምዕራብ በርሊንን እንደ ስለላ ማዕከል እየተጠቀመበት ነው፤ ስለዚህም ሰላዮችን ላለሙት አላማ ግንቡን እንዳቆሙት ለማስረዳት ሞከሩ፡፡ ግንቡን “የፀረ ፋሽስት መከላከያ አጥር” የሚል ስያሜም ሰጡት፡፡
ምዕራባዊያኑ ደግሞ “የሀፍረት፣ የገመና የአሣፋሪነት መደበቂያ ግድግዳ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ብሎም ግንቡ በሶቭየት ይዞታ የሚኖሩ ጀርመኖች በምዕራብ በርሊን ከሚኖሩት ዝቅተኛ ህይወት እየመሩ እንዳሉ ለበርሊን ነዋሪዎች እንደ ዋነኛ ምስጢር ነው ለማለት ነበር “አሳፋሪ ግምብ” ብለው የሰየሙት፡፡
ግንቡ ሲጀመር ማብቂያ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ግን የማያልፍ የለም እነዚያ መከፋፈያ የጀርመኖች ግን አሳቃቂ 28 ዓመታትን አሳለፈ፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የሩሲያ መዳከም ለጀርመን ግንብ መፍረስ ዋነኛ ምክንያት ሆነ፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቆሞ የነበረው ግንብ በመፍረሱ ሁለቱ ጀርመኖች ዳግም ለመዋሀድ በቁ፡፡ ቀኑም ጥቅምት 24 ቀን 1981 ዓ.ም ነበር፡፡
“ድንበሮቹ መከፈታቸው በይፋ ሲገለፅ እኔ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበርኩ፡፡ እናም ወዲያውኑ እያንዳንዱ ተማሪ በአውቶቡስ በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው የድንበር ማቋረጫ አቅጣጫ ነጎደ፡፡ የእንግሊዝ አየር ሀይል ኮማንደር ከምሥራቅ በርሊን አቋርጦ ወደ ምዕራቡ ይገሰግሥ ለነበረው ህዝብ ‘የምናድላቸው አበባ ይዘናል’ ሲል ተናግሮ ነበር፡፡
“እንደ እውነቱ ከሆነ ድንበሩን እየተሻገረ የነበረው አብዛኛው ህዝብ የትም ለመሄድ ሀሳብ አልነበረውም፡፡ ዋናው ፍላጐታቸው ድንበሩን ተሻግረው ሁኔታው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ነበር፡፡ እናም እኛ አበባ በምናድልበት ቦታ እንዲደርሱ አብዛኛው ህዝብ ጉዟቸውን ያቆሙ ነበር፡፡
አንድ ጀርመናዊ ሴት ትዝ ትለኛለች፡፡ አይኖቿ በእንባ ሟሙተው ሁላችንንም እያቀፈች ትስመን ነበር፡፡በጀርመንኛ ቋንቋም ትናገር ነበር፤ ለካ የምታለቅስበት ምክንያት የቤተሰቧ አባል ከአንድ ዓመት በፊት ከምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ጀርመን ለማለፍ ሲሞክር ተገድሎባታል፡፡ ያ የገባን መምህራችን ሲተረጉምልን ነበር፡፡
“በግራና በቀኝ ግንቡን የከበቡት ሰዎች ግንቡን በማፍረስ ላይ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ህፃን ነበርኩ፡፡ በዓለም ውሰጥ ካሉት ለምን አንድ ግንብ ከፍተኛ ችግር ሊሆን እንደሚችል ምንም ግንዛቤ ያልነበረኝ ህፃን ልጅ ብሆንም ግንቡን የማፍረሱን ተግባር ግን ትክክለኛ የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ ይገባኝ ነበር፡፡
“አሁን በእርግጥ ለዚያ እለት ልዩ ክብር አለን፡፡ በዛች ታሪካዊ ቀን መገኘቴን ሳስብ እድለኛ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ ያን የፍርሀት ምልክት ለማፍረስ የድርሻየን አግዣለሁ፡፡ የግንቡን ፍርስራሾች በደብተር ቦርሳየ እየተሸከምኩ በማስወገድ የድርሻየን ተባብሪያለሁ፡፡
“እንደማስበው አባቴ አብዛኛውን ፍርስራሽ ያስወግድ ነበር፤ እንዲያውም ‘ከፍርስሯሾች አንዱ የራስ ቅሌን ፈንክቶኝ ነበር፣ ጉዳቴ ብዙ ባይሆንም’ ሲል ያስታውሰዋል አክላስ ናውተን ከአሜሪካ በቅርቡ ለአንድ ድረ ገፅ ትውስታውን ሲጽፍ፡፡
ሳምንቱ በታሪክ
ዐፄ ምኒልክ በአንቶኖሊ እይታ
ሕዳር 4 ቀን 1868 ዓ.ም ልቼ ከተማ ውስጥ ሆኖ የጻፈው ደብዳቤ እስፒዲሲዮኒ ኢታሊያና በሚባል መጽሃፍ ውስጥ ታትሞ ስለ ዐፄ ምንሊክ የሚከተለውን መግለጫ አካትቷል …እድሜያቸው 32 ዓመት ይሆናል። የጢማቸውም ሆነ የራሳቸው ጠጉር ጥቁር ነው። ፊታቸው የደስ ደስ ያለው እና ልዩ ጠባይ የሚታይበት ነው። አልጋ ላይ ተቀምጠው ነበር። ራሳቸውን እና እግራቸው በምንም ያልተሸፈነ ባዶውን ነበር። ነጭ ሱሪ ታጥቀው በላዩ ላይ ቀይ ጥለት ያለው ሸማ ለብሰዋል።…ከትከሻቸው ላይ ልብሳቸው በመርፌ ቁልፍ ተይዟል። በጣም ጥሩ ሰው ናቸው። ለጦር መሳሪ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው።
ዴቪድ ሊቪንግስቶን ተገኘ
ህዳር 1 ቀን 1863 ዓ.ም ላይ ነበር በአፍሪካ ጫካዎች ደብዛው የጠፋባቸውን ሚስዮናዊ እንዲፈልግ ተልኮ የነበረው አሳሽ ሄነሪ ስታሊን ተፈላጊውን ዴቪድ ሊቪንግስቶንን ማግኘቱ ይፋ የሆነበት ቀን ነው። ስታንሊ ለዓመታት ያህል ጠፍቶ የነበረውን ሊቪንግስቶንን ፍለጋ የጀመረው ከአምስት ወራት በፊት ነበር። እናም ኡጂጂ በተባለችው የአፍሪካ ስፍራ ዳቪድ ሊቪንግስቶን አገኘው። ስታንሊ ሰውየውን እንዳገነው “ይመስለኛል፤ አንተ ዶክተር ሊቪንግስተን ነህ?” ብቻ ሲል ነበር በቀላሉ የጠየቀው። በነገራችን ላ ለዚህ አላማ የተላከው ስታንሊ ነበር ኮንጎን ለቤልጂየሙ ንጉሥ አሳልፎ በቅኝ ግዛትነት የሰጠ የታሪክ ተወቃሽ ነው።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


