ሥርዓተ ምግብ ማለት የተመገብነው ምግብ በሥነ ሕይወታዊ ሂደቶች በማለፍ በአጠቃላይ በሰውነት ግንባታ ዙሪያ እድገት ማምጣት ነው:: ዋና ዋና ምግቦች የሚባሉት በብዛት ኀይል የሚሰጡ እና የተመገብነው ምግብ በሰውነታችን ውስጥ ሥርዓተ ኡደቱን ጠብቆ በትክክል እንዲሠራ የሚረዳ መሆኑን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሥርዓተ ምግብ ኦፊሰር አቶ ባይለየኝ ቢምረው ተናግረዋል::
ንዑስ ንጥረ ምግቦች የሚባሉት ደግሞ ስርዓተ ዑደቱ እንዲካሄድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን ሁለቱም ዓይነት ንጥረ ምግቦች ከአካባቢያችን በቅርብ የሚገኙ ናቸው::
በአጠቃላይ ጤናማ አመጋገብ የሚባለው ሰውነትን የሚገነቡ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው ከእንስሳት እና ከጥራጥሬ የሚካተቱት ስጋ፣ ዶሮ ፣ እንቁላል፣ የእናት ጡት ወተት፣ ባቄላ፣ ለውዝ፣ ምስር፣ ሽንብራ፣ አሳ፣ አይብ እና ወተት መመገብ ሲቻል ነው:: ዳቦ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ቆጮ ፣ ድንች ፣ ስኳር አገዳ፤ ማር፤ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች፣ ፓስታ፣ ማኮሮኒ እና ሽሮ ደግሞ ኀይል እና ሙቀት ሰጭ ምግቦች ውስጥ የሚካተቱት ናቸው::
ኦፊሰሩ እንደሚገልፁት ለሰውነት ጠቃሚ ምግቦችን አመጣጥኖ መውሰድ ጤናማ ቢያደርግም እንደ ሀገር ያለው የአመጋገብ ሥትዓት ግን ጤናማ የሚባል አደለም::
እንደ አቶ ቢምረው ማብራሪያ በልማድ ዘወትር በገበታችን የሚቀርብ ምግብ የተሰባጠረ ሳይሆን አንድ ዓይነት ነው:: በአሁን ወቅት ደግሞ በየሱቆች የሚገኙ በፋብሪካ የሚመረቱ የታሸጉ ምግቦች እና መጠጦች ናቸው:: እነዚህ የምርት ውጤቶች በተለይ ለሕፃናት እና ህሙማና ጭምር መሰጠቱ ደግሞ ሌላ የጤና ጉዳት እያስከተለ ነው:: ከዚህ መረዳት የሚቻለውም ሥለጤናማ አመጋገብ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ብዙ እንዳልተሠራ ነው::
የቫይታሚን እጥረትን ለመከላከል ጎመን እና ቆስጣ፣ ከፍራፍሬ ማንጎ ፣ብርቱካን እና ፓፓዬ መመገብ እንደሚገባም ኦፊሰሩ ጠቁመዋል:: በሽታን ለመከላከል ደግሞ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አሰባጥሮ መመገብ ሲቻል ነው:: ጮማ፣ ጨው እና ስኳር ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ከገበታ እንዲርቁ አልያም ቅባት ያለው ምግብን እንዲቀንሱ ይመከራል::
የሥርዓተ ምግብ ኦፊሰሩ ጤናማ የሆነ የፆም ወቅት አመጋገብን በተመለከተም ሲያብራሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች ከቅባት ርቀው እና ቀኑን ሙሉ ፆም ውለው ቀለል ያሉ ምግቦችን ሽሮ፣ አትክልት… ሲመገብ ነው የሚቆዩት:: ችግር የሚሆነው ታዲያ በፆም የቆየው አመጋገብ በዓል ሲመጣ ቀጥታ ወደ ቅባታማ ምግቦች ይገባል:: በዚህ ወቅት ጨጓራ ደግሞ ከቆየበት ልምድ አንፃር ቀስ በቀስ ስለሚሠራ ለመፍጨት ይቸገራል::
ጨጓራ ወደ ነበረበት ለመመለስ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል:: በዓል ሲመጣ ምግቡ ሁሉ ቅባት የበዛው ሚጠጣው ደግሞ በብዛት አልኮል ስለሚሆን ለጤና ችግር ያጋልጣል:: በዚህ ጊዜ ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየ ጨጓራ ለህመም የመዳረግ አጋጣሚው ከፍተኛ ይሆናል:: ይህ ሲሆን ጥንቃቄ የጎደለው አመጋገብ ይከሰታል:: ይህን ተከትሎም ሆድ መንፋት፣ ሆድ ቁርጠት፣ ጨጓራ ማቃጠል እና ሌሎችንም ህመሞች ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያው ገልፀዋል::
ከፍተኛ ስብ ያለባቸው ምግቦች የካሎሪ ክምችታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን በተደጋጋሚ ከተመገብናቸው ያልተፈለገ የስብ ክምችት/ /ኮሌስትሮል/ እንዲጨምር ያደርጋል:: ይህም የልብ ህመም እና ለሰውነት መዛል/ስትሮክ/ ተጋላጭነትን ይጨምራል። ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ስኳር በሽታም ያስከትላል።
በባእላት ወቅት የሚዘወተሩት ጥሬ ሥጋ እና ሌሎች ያልበሰሉ ምግቦች ደግሞ እንደ ኮሶ በሽታ ዓይነት ያስከትላሉ:: በተለይ ሥጋው የሚታረድበት አካባቢ በጤና የተረጋገጠ ካልሆነ ለበሽታ ያጋልጣልና ህብረተሰቡ የእርድ ከብቶችን ጤንነት በማረጋገጥ በቄራዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያሳርድ አሳስበዋል:: በመሆኑም በዓላትን የጤና መታወክ ሳያጋጥም ለማሳለፍ የሚዘጋጀው ምግብ በአግባቡ ንጽህናው የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ኦፊሰሩ መክረዋል::
በበዓል ወቅት በተለይ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በአንድ ጊዜ ብዙ ከመመገብ መቆጠብ እንደሚገባ አቶ ቢምረው መክረዋል:: ለአብነት ዶሮ ከበላን ዶሮ በተፈጥሮ ቅባት አለው:: ከዚህ በተጨማሪ ቅቤ ፣ እንቁላል ፣ ወተት ፣እርጎ ፣ጥሬ ሥጋ… በአንድ ጊዜ ባይወሰድ ለጤና ጥሩ ነው:: የግድ ከወሰዱም ደግሞ መጠናቸው በጣም ጥቂት መሆን እንደ ሚገባው ነው ባለሙያው የሚመክሩት ::
በአጠቃላይ በእለት ከእለት ምግብ አጠቃቀም ሁለንም ንጥረ ነገር ያቀናጀ ካልሆነ አንዱን አዘውትሮ የመመገብ ልምድ በጤና ላይ ችግር እንደሚያስከትል አምኖ ምግቦችን በየአይነቱ አሰባጥሮ መመገብ እንደሚገባም ነው ባለሙያው ያሳሰቡት::
ጤናማ የአመጋገብ ሥርአት የሚባለው የአትክልት እና ፍራፍሬ ስብጥር ሲኖር ነው:: ነገር ግን ከፀረ ተባይ መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ በተለይ ጎመን ፣ ቆስጣ፣ ቲማቲም የመሰሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ከገበታ የማራቅ ሁኔታ ይስተዋላል፤ ለዚህ መፍትሄው ምንድነው? ስንል ለኦፊሰሩ ጥያቄ አነሳን:: እንደ ሀገር አቀፍ ችግሩ ተነስቶ በተለያየ መድረክ ከግብርና ቢሮ ጋርም እየተነጋገሩ እንደሆነ አቶ ቢምረው ጠቁመዋል:: ይሁን እንጅ ወደ ፊት ይሻላል ተብሎ ቢጠበቅም በአሁኑ ወቅት ገና መፍትሄ ያልተቀመጠለት ነገር እንደሆነ ተናግረዋል::
የምግብ አለመመጣጠ ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላል:: በተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት ብቻ የመሄድ ነገር በመኖሩ ይህንን ለመቀየር በቀን ውስጥ ከአትክልትም ፣ከፍራፍሬም ፣ከጥራጥሬም እያሰባጠሩ የመመገብን ልምድ ሁሉም በየቤቱ ሊተገብር እንደሚገባው አሳስበዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም