የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በያመቱ ህዳር 24 ቀን ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛ ምክንያት የአካል ጉዳተኞችን መብቶች እና ደህንነት ለማስጠበቅ፤ ማህበረሰባዊ ግንዛቤን ለማሳደግ፣በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ ለማበረታታት ነው፡፡. በዓሉ ሲከበር ለበዓሉ ታዳሚዎች የአካል ጉዳተኞችን ችሎታዎች እና አስተዋፅኦ ማሳየት ትኩረት ከሚሰጣቸው ቁም ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ይህ የትኩረት ነጥብ የተንጋደዱ አመለካከቶችን በመለወጥ አድልኦዎች እና መገለሎች እንዲወገዱ ያግዛል፡፡
አድሏዊ አሠራሮች እንዲሁም አነጋገሮች መስተካከላቸው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡ ልዩ ልዩ ስምምነቶች እና የሀገር ውስጥ ሕግጋት እንዲከበሩ መሠረት ይጥላል፡፡ ይህም መንግሥታት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የተዘረዘሩትን መብቶች እንዲተገብሩ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የሕጎች መከበር አካል ጉዳተኞች በሚፈልጉት እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የሚያስችሏቸውን ምቹ ሁኔታዎች ይፈጥርላቸዋል፡፡ ምቹ ሁኔታ ሲባልም የመንገዶች ምቹነት እና ተደራሽነት፤ የህንጻዎችን ምቹነት፤ የቴክኖሎጅ እንዲሁም የመረጃ ተደራሽነትን ያካትታል፡፡ የበዓሉ መከበርም የእነዚህ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት በአካል ጉዳተኞች መብቶች ላይ ምን ያክል ጫና እንደሚፈጥሩ በማሳየት ችግሮቹ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ያግዛል፡፡
የአካል ጉዳተኞች በዓል በያመቱ መከበሩ አካታች ማህበረሰብ የመፍጠርን አስፈላጊነት ያጎላል፡፡ በዓሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በአካል ጉዳተኝነት ጉዳይ እንዲወያዩ እና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ አዳዲስ ሕጎችን፣ ፖሊሲዎችን… እንዲያወጡ ያነሳሳል፡፡
እነዚህ የበዓሉ ዓላማዎች መልካም ቢሆኑም ስኬታማ ናቸው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም በዓሉ በሚከተሉት መንገዶች ቢከበር የታለመለትን ግብ ይመታል ባይ ነኝ፡፡ የአካል ጉዳተኞች ዓመታዊ በዓል ብዙ ወጭ ወጥቶበት ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም እዚህ ላይ የግንዛቤ መጨበጥ አለመጨበጥ መለኪያው ምን ይሆን? የበዓሉ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?… የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢነት ያለው ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት በዓሉን በያመቱ የሚያከብሩት የተለመዱ ድርጅቶች፣ የማህበራት ኃላፊዎች፣ የዞን እና የክልል ፌደሬሽን መሪዎች፣ በአብዛኛው በዓሉ በሚከበርበት ከተማ ያለው አካል ጉዳተኛ፣ የማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ… ባለሙያዎች ናቸው፡፡
በእርግጥ አካል ጉዳተኝነቱን አምኖ ያልተቀበለ አዳዲስ አካል ጉዳተኛ ሊኖር ስለሚችል እና መድረክ የሚያገኝባት ብቸኛዋ አጋጣሚ ይችው የበዓል ቀን ስለሆነች በበዓሉ የሚሳተፈው የአካል ጉዳተኛ ቁጥር መብዛቱ የሚደገፍ ነው፡፡ ችግር የሚሆነው በዞን፣ በክልል፣ በፌደራልም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር ባብዛኛው ተሳታፊ የሚሆኑት ከበቂ በላይ ግንዛቤ አላቸው ተብሎ የሚገመቱ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ በዓሉ በአግባቡ እንዲከበር ለማስተባበር የግድ መኖር ያለባቸው ሰዎች ካልሆኑ በቀር ድግግሞሽ እንዳይኖር በቂ መረጃ እየተያዘ ተሳታፊዎች ቢመረጡ መልካም ነው፡፡ ከዚህ በፊት የበዓሉ ተሳታፊ ያልሆኑ እና በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ አጋጣሚ ያላገኙ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ጉዳት አልባ ወገኖች የበዓሉ ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡ አንድ መቶ በቂ ግንዛቤ ያገኙ አካል ጉዳተኞች ከመሰብሰብ አሥር ግንዛቤ ያላገኙ እንዲሁም የመፍትሄ ሀሳብ አቅራቢ አካል ጉዳተኞች ችግር ፈቺ ከሆኑ አምስት መሪዎች ጋር ውይይት ቢያደርጉ ውጤታማ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡
በዓሉ የት ነው የሚከበረው? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ምላሹ ከዞን ከተሞች በአንዱ ወይም በክልሉ መዲና የሚል ይሆናል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው ችግሮች የሚያጋጥ ሟቸው በወረዳዎች እንዲሁም በቀበሌዎች የሚኖሩት አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር በዓሉ ዞን እና ክልል ላይ ተንጠልጥሎ ከሚቀር ወደ ወረዳዎች እንዲሁም ቀበሌዎች ወርዶ ሊከበር ይገባል፡፡
ሁሉም ቢሮዎች አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ እንዲያቅዱ እና እንዲተገብሩ መደረጉ መልካም ነገር ነው፡፡ በዕቅዱ መሠረትም በዓሉን ተቋማቱ በዙር እንዲያከብሩት ቢደረግ የተሻለ ይሆናል፡፡ በዓሉን የሚያከብረው ተረኛው ተቋም ኃላፊነት መድረኩን ማመቻቸት ነው የሚሆነው፡፡
መድረኩን ያመቻቸው ተቋም ኃላፊዎች በመድረኩ ተገኝተው በመሥሪያ ቤታቸው ስንት አካል ጉዳተኞች እንዳሉ፣ ምን እንደተሟላላቸው፣ ምን ችግር እንዳጋጠማቸው፣ ችግሩ በምን መልኩ እንደተፈታ፣ ካልተፈታም በምን ሁኔታ ሊፈታ እንደታሰበ፣ የችግሩ አለመፈታት በተቋሙ እና በሠራተኛው ላይ ምን ጫና እንዳስከተለ፣ መሥሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞችን በመቅጠሩ ምን ችግር እንዳጋጠመው፣ ምን መልካም ዕድል እንደነበረው፣ ተቋሙ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ምን ያህል አካታች እንደሆኑ… እንዲያብራሩ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህ የበዓል አከባበር ቢተገበር በበዓል አክባሪው መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ አካል ጉዳተኞች አጋጥመውናል የሚሏቸውን ችግሮች በግልጽ እና ሕጉን በጠበቀ መልኩ እንዲያነሱ፣ መልካም አሠራር ካለም በቀጥታ እንዲያመሰግኑ መልካም አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ መድረኩ መሥሪያ ቤቶቹ ባለጉዳይ አካል ጉዳተኞችንስ ያለአድልዎ እያገለገለ ነው ወይ? የሚለውን በተመለከተ የበዓሉ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች አስተያየት እንዲሰጡም ይረዳቸዋል፡፡ በዓሉ በየተቋሙ በዙር መከበሩ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሠራሮች እና መመሪያዎች አሏቸው ወይስ የሏቸውም? የሚለውን ለመፈተሽ ያስችላል ብየ አስባለሁ፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው ያሉት የቢሮዉ ጽ/ቤቶች ለአካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች እና ባለጉዳዮች አመች ካልሆኑ ህንጻቸውን አመቺ ማድረግ ይችሉ ዘንድ አስተያየት እንዲሰጣቸው ዕድል ይፈጥራል፡፡
በዓሉ በዚህ መልኩ የሚከበር ከሆነ ተረኛ መሥሪያ ቤቱ የሚገዛባቸው አዋጆች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች እና አሠራሮች ዕውቀቱ ባላቸው ባለሙያዎች ስለሚተቹ መሻሻል ሊመጣ ይችላል፡፡ በዓሉን የሚያከብረው ተቋም ቢያንስ በራሱ መድረክ ላለመወቀስ የአካል ጉዳተኞችን ችግር በማዳመጥ መፍትሄ የሚሰጥበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ መድረኩን በበጎ ዐይኑ ሊያየው የሚወድ ኃላፊ ካለም በዓሉን ራሱን ለማስተዋወቅ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ተረኛው በዓል አክባሪ ተቋም በዓሉን በስሩ ካሉት የዞን ወይም ወረዳ ጽ/ቤቶች ባንዱ ሲያከብር አዳዲስ አካል ጉዳተኞችን የበዓሉ ተሳታፊ የማድረግ ዕድል ያገኛል፡፡
ባንጻሩም በተመሳሳይ ቦታ እያከበርን በሚፈለገው ልክ ለውጥ አይመጣም፡፡ እኔ እንኳን ሳውቅ በተመሳሳይ ቦታ ለ20 ዓመታት በዓሉ ተከብሯል፡፡. በእርግጥ ምንም ለውጥ አልመጣም ማለት አይቻልም፡፡ ቢያንስ ያኔ ለመብቱ ይቆረቆር የነበረው እና ያኔ ሥራ ላይ የነበረው ራሱን የቻለው አካል ጉዳተኛ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ካለው አንጻር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛው በሚፈለገው ልክ መብቱን አውቋል፤ በሥራ ላይ ተሰማርቷል፤ እኩልነቱ ተረጋግጦለታል ማለት ግን አይቻልም፡፡
በዓሉ ተቋማት ያለባቸው ያሠራርም ሆነ የሕግ አወጣጥ፣ ተደራሽነታቸው እና ክፍተታቸው በግልጽ የሚነገርበት እንዲሁም ተቋማቱ ችግራቸውን ለይተው ለለውጥ የሚነሱበት መሆን አለበት፡፡ በጋራ በዓላችን ላይ ብሶታችንን ካልተናገርን መቸ ልንናገር ነው? በዓሉ ሲከበር ግልጽ የሆነ የቤት ሥራ የሚሰጥበት፣ ሥራውን ያልሠራ ተቋም በግልጽ ክፍተቱ የሚነገርበት መሆን ይኖርበታል፡፡
በዓሉ ሲከበር ከፍ ያለ ተጽዕኖ ያመጣሉ የሚባሉ ተቋማት ኃላፊዎች ተጠርተው አካል ጉዳተኛው ፊት ለፊት ሀሳቡን እንዲያቀርብ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው ይናገር ማለት ሳይሆን ሀሳቦች ዕውቀቱ ባላቸው ጥንቁቅ አካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች ተደራጅተው በአቋም ደረጃ ሊቀርቡ፣ ምላሽም ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ኃይለ ማርያም ፍስሀ ( ዳኛ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


