የበገና ዝማሬዎች

0
707

“እጄ አመድ አፋሽ ነው ሞት ያማኛል አሉ

ጨርሼ ሰጥቼው ዘመዶቼን ሁሉ፣

ወገኖቼን ሁሉ

ሞት እንዴት ሰነበትህ፣  እንዴት  ሰንበተሃል

እግዚአብሔር ይመስገን፣ ወዴት ታውቀኛለህ

ለምን አላውቅህም አውቅሀለሁ እንጂ

የእናቴን፣ የአባቴን ስትዘጋ ደጅ

አንት ሁልጊዜ እንግዳ ሰው አጥፊ ነህ እንጂ

ሞት ተመላለሰ መንገዱ አደረገኝ

ዳግመኛ ቢመጣ ካለኔም አያገኝ”

በገነኛው ደምሴ ደስታ ሞትን በሚመለከት ያቀረቡት የበገና ዝማሬ ግጥም ነው።

በገና በአስር አውታር ጅማት የሚሠራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለምስጋና እና ዝማሬ የሚውል መንፈሳዊ መሣሪያ ነው። በገነ፣ ደረደረ፣ መታ፣ አነዘረ የሚሉትን ቃላት በመውሰድ በገናን የሚተረጉሙት ሊቃውንት አሉ። ሲመቱት ድዝ፣ ጥዝ የሚል ወፍራም ባለ ግርማ  ድምጽ አለው። በገና አሠራሩ በሙሉ፣ የተሠራበት ቅርጽ እና ሌሎች ክፍሎቹ ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለው ነው። በአጭር አገላለጽ በገና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዝማሬ መሣሪያ ነው።

በገና መቼ እና እንዴት ተጀመረ የሚለውን ታሪክ በግልጽ ተጠቅሶ የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በዚህም መሠረት በገናን ለመጀመሪያ ጊዜ የደረደሩት የላሜህ ልጅ የዩባል (ኢዮቤል) ልጆች ነበሩ። በገና መደርደር የተጀመረውም በአዳም ዘጠነኛ ትውልድ በሆኑት የላሜህ ልጆች ነበር ሲሉ ሊቃውንተ ኦርቶዶክስ ይመሰክራሉ። በገና ቃለ ማኅዘኒ (የኅዘን ድምጽ መግለጫ) እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ። ቃየል ወንድሙ አቤልን መግደሉን፣ ቃየል ደግሞ በልጁ በላሜህ መገደሉን እያሰቡ የዩባል ልጆች የደረቀ እንጨት ጠርበው እና አለዝበው፣ ቆዳ ፍቀው፣ አድርቀው እና ዳምጠው፣ ጅማት እክርረው  እንዲሁም አበግነው በኀዘን ድምጽ ያንጎራጉሩ ነበር ሲሉ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያብራራሉ።

ይህንን ተከትሎ በገና የኀዘን፣ የንስሐ፣ የልመና እና የምስጋና ማቅረቢያ መንፈሳዊ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በመቀጠልም በገና በቅዱስ ዳዊት ለዝማሬ አገልግሏል። በኋላም ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይነገራል። በገና ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ ለዘፈን እና ሌሎች ዓለማዊ  ተግባራት ጥቅም ላይ አይውልም። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ  ከበገና ጋር ስማቸው ቀድሞ የሚጠሩት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ አንጋፋ እና ቀደምት ናቸው። የበገና አውታር አሥር የሆነው አሠርቱ ትዕዛዛትን  ለማሳየት፣ ሁለቱ ቋሚ አምዶች ደግሞ ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ገብርኤልን ለመግለጽ፣ ከላይ አውታሮች የታሰሩበት ግድም ደግሞ ፈጣሪ የሁሉ የበላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ከታች ያለው የድምጽ ሳጥን ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለመወከል የተሠራ ነው በማለት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በገና እንደ ንዋያተ ቅዱሳን ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ለዓለማዊ ሙዚቃዎች መጫዎቻነት አልተፈቀደም ነው የሚሉት።

የበገና ግጥሞች ታሪክ ይጠቅሳሉ፤ አገርን ያነሳሳሉ፤ ነገሥታትን እና ሥራዎቻቸውን ያስታውሳሉ። ዋናው ጉዳያቸው እና ሚናቸው ግን በሰም እና ወርቅ ታጅበው ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ ነው። በዚህ ውስጥ መደነቅ፣ መደሰት፣ መፀፀት፣ ንስሐ፣ ተስፋ እና እምነት ይገለጻሉ። መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ አጼ ቴዎድሮስን በሀገር ስሜት ውስጥ ያነሳሷቸዋል። አባ ግራኝ ሞተ ብለው ዝማሬውን ርዕስ ሰጥተውታል።

“አባ ግራኝ ሞተ የሆዴ ወዳጅ

የሚያበላኝ ጮማ የሚያጠጣኝ ጠጅ

እኔ መዩ ቱርክ ባይ

የምሸሽ ነኝ ወይ

ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም

ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም

እኔ መዩ ቱርክ ባይ

የምሸሽ ነኝ ወይ

አያችሁት ወይ የአንበሳውን ሞት

በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት

እርሳሱን እንደ ጠጅ ጎርሶ ሲጠጣት”

በዚህ የበገና ድርድር ውስጥ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ጀግንነት ጉልህ ቦታ ይዞ፣ ሀገራቸውን ቆመው ስትደፈር ላለማየት፣ ለጠላት እጅ ላለመስጠት በመቅደላ አምባ ሲሰዉ እናያለን።

ሲሳይ ደምሴ ደግሞ አይቀር ሞቱ የሚል ርዕስ በሰጡት ዝማሬያቸው ፈጣሪ የሰው ልጅን ለምን ፈጠረ ብለው ይጠይቃሉ፤ ምድር ለአምላክ ቃል ከመገዛት በቀር  ከንቱ መሆኗን ይገልጻሉ።

“በደመ ነፍስ ሕይወት ሰውን መፍጠርህ

እንዲጠራ እኮ ነው ቅዱሱ ስምህ

ቤት እሠራ ብዬ

አጣና ቆርጬ መሬቱን ደልድዬ

እሠራ  እሠራ ስል ደከመ ጉልበቴ

ዓለማገር ቀረች ወይ ቤቴ ወይ ቤቴ

እኔ መንገደኛ ተሸኝቶ አዳሪ

ምን ክፉ አናገረኝ እንግዲህ ከቀሪ

ጠማማውን እንጨት እየቆረጣችሁ

ይህም ሃገር ሆኖ ቤት ትሠራላችሁ”

የበገና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመክፈት የተዳከመውን የበገና ዝማሬ ዳግም እንዲያንሰራራ የሚሰሩት መምህር ሲሳይ ደምሴ የበገና መማሪያ በሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። “በገና እግዚአብሔርን በማመስገኛነት በክብር በቤተክህነት እና ቤተ መንግሥት ሥልጣን ባላቸው በነገሥታቱ እና መኳንንት ቤት አገልግሎት ይሰጥ ነበር” ይላሉ። ለዚህም በማሳያነት አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ እቴጌ ጣይቱ እና ራስ መኮንን በገና ደርዳሪዎች እንደነበሩ መምህር ሲሳይ  ጽፈዋል። በገናን መደርደር ባይችሉ እንኳን ሌሎች ደርዳሪዎች እንደነበሯቸውም ጨምረው ያስረዳሉ።

መምህር ሲሳይ በገናን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኩን፣ ክብሩን፣ ጥቅሙን እና አጠቃቀሙን ተረድተን በአጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቀናት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። በተለይም በዚህ ጭንቀት፣ ኀዘን፣ መከራ በበዛበት ዘመን በገናን መደርደር እና ራስን መፈወስ፣ ከፈጣሪ ጋር በተመስጦ መገናኝት ከጥቅሞቹ መካከል ይጠቀሳሉ። መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ “በገና በጾም ጊዜ ብቻ የሚሰማ አይደለም፤ የመጸለያ እና ማመስገኛ  መሣሪያ እስከሆነ ድረስ ፈጣሪን የምናመሰግነው፣ የምንጸልየው በጾም ወራት ብቻ አይደለም። እኛ የምንከተለው የቅዱስ ዳዊትን በገና ነውና ቅዱስ ዳዊት 150 መዝሙሮችን የደረሰ ነው፤ እነዚህ 150 መዝሙራት በበገናም ይዘመራሉ” በማለት ማብራሪያ ይሰጣሉ። በገና በጾም ወቅት ብቻ የሚደመጥ የመሰለው በቀዳማዊ አጼ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የበገና መዝሙሮች በብዛት በራዲዮ ይደመጡ ስለነበር ነው በማለት ይቀጥላሉ። በገና ከአምላክ ጋር መገናኛ፣ በተመስጦ ራስን ማድመጫም ነው ይላሉ። በዚህም በገና የሁልጊዜ የምስጋና መሣሪያ ነው ብለዋል።

በአሁኑ  ጊዜም በኢትዮጵያ የበገና ድርደራን እና ዝማሬን የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በስፋት ተከፍተዋል። ይህንንም ተከትሎ በገና በርካታ ዘማሪያንን አፍርቷል። አሁን ወቅቱ የዐቢይ ጾም በመሆኑ ለጾሙ ምክንያት የሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራት እና ገድሎችን በዘማሪያን አንደበት እንቃኛለን።

ዘማሪት ሶስና ገብረ ኢየሱስ “ስቀለው ስቀለው” በሚል ርዕስ የክርስቶስን መሰቀል በበገና ዘምራለች። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው ከበደል በቀር ምድር ላይ ሁሉንም ሆኗል። ተርቧል፣ ተጠምቷል። ወንዞችን የፈጠረ አምላክ በውኃ በተጠማ ጊዜ አይሁድ  ኮምጣጤ አጠጥተውታል። የሚያደርሱበትን  መከራ እና ግርፋት በምጸት “ማን ነው የመታህ?” እያሉ ያፌዙበት ነበር። እሱ ግን ሁሉንም በምክንያት አድርጎታልና ምንም አልተናገረም።

“ምራቅ እየተፉ ፊትህ ላይ

ሲመቱ ሲሰድቡህ ስትሰቃይ

ምንም ሳትመልስ በፍቅር አየሀቸው

በመስቀል ሰቀሉህ ወደህ ሞትክላቸው”

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ትሕትና እና ምግባርን  በምድር ተዘዋውሮ አስተምሯል። አይሁድ ጠልተውት ሲገርፉት፣ ሲተፉበት እና ሲሰቅሉት “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ  ከአብ ከአባቱ ምሕረትን ጠይቋል።

ሊቀ መዘምራን ይልማ ኀይሉ “በይስሐቅ ፋንታ” በሚል ባቀረቡት የበገና መዝሙር የኢየሱስን መሰቀል እናም ዓለምን ለማዳን የወደደበትን ምስጢር ያዜማሉ።

“በይስሐቅ ፋንታ ኢየሱስ ታረደ

ደሙን ከፈለና  አዳምን ታደገ

ተጨነቀ ጌታ ተሰቃዬ ጌታ

የኔ መድኀኔዓለም የአዳም ልጅ አለኝታ

እንደሚታረድ በግ ተነዳ ወደ ሞት

ንጹሁ ኢየሱስ በደል የሌለበት”

ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባው ቃል መሰረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በስደት አድጎ፣ ሕዝብን አስተምሮ፣ ብዙ ተዓምራትን ሠርቶ፣ መሰቀል ለነበረበት የሰው ልጅ ሲል ተሰቅሎ መሞቱን፣ በዚህም አዳም ከሲኦል መውጣቱን ያነሳል።

“እጁ የታሰረው ይስሐቅ ተፈታ

ኢየሱስ ቀረበ በሰው ልጆች ፋንታ

ንጹህ በግ ቀረበ በደል የሌለበት በደለኛ ሆኖ

ሲሰቀል ሲገደል በደለኛ ሆኖ”

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሕማም እና የበደል ደዌ ብሎ ያለበደሉ፤ ስልጣን እና ኀይል እያለው ተገርፎ፣ ተሰቅሎ፣ የሰው ልጅን ሲያድን ሰማያዊውን ዳኛ ከሰውታል፣ ፈርደውበታል ይላል መዝሙሩ። ዘማሪ ታደለ ገድፍ በመስቀል ተሰቅሎ በሚል ባቀረበው መዝሙር ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን እና የደረሰበትን መከራ በማሰብ በኀዘን ውስጥ ሆኖ ያዜማል።

“መከራውን ሳስብ ሳስታውስ ቀኑን

ይቆስላል ይደማል ልቤ በኀዘን

መች ለራሱ ነበር ይህ ሁሉ መከራ

መስቀል ተሸክሞ የወጣው ተራራ

ሲያጎርሱት ሚናከስ ሰው ክፉ ነውና

እውሩን ቢያበራ ጎባጣን ቢያቀና

ጌታዬ ሰቀሉህ አይሁድ ጨከኑና

ምነው አያሳዝን የአይሁድ ክፋት

የዝናቡን ጌታ ውኃ ሲነፍጉት”

አዳም የአምላኩ ትዕዛዝ  በመሻሩ ተፈርዶበት ከገነት ወጥቶ በስደት ይኖር ነበር። ፈጣሪም ቸር አምላክ ነውና እንደገና ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት። በፈጠረው የሰው ልጅ አምላክ ተገድሎ ሞተ። የሰው ልጆችን የዘላለም የሞት ዕዳ ሻረው። ዓለምን ከኀጢዓት ለማዳን ሲል የማይሞተው ሞቷል። ጌቴ ሰማኒ በተባለ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ እየተንገላታ፣ እየተፉበት፣ እየገረፉት ጸና። በጊዜው እናቱ ይህንን እያየች ነበር። ዘማሪ ታደለ ግድፍም ያንን ቅጽበት በበገና እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።

“ድንግል አልቻለችም እንባዋን ልትገታ

እያየች በመስቀል ልጇ ሲንገላት

በአምላክነቱ ሳይፈርድባቸው

እንዲህ ሲል ጸለየ አምላክ ሆይ ማራቸው”

ዘማሪ ታፈሰ ተስፋዬ በበገና መዝሙራቸው “እስኪ ላስታውስ የሕማማቱን ሳምንት የጌታዬን የክርስቶስን ስቅለት” ብለው ይጀምሩና  ከመስቀል ሐሳብ እስከ ትንሣኤው ድረስ ያስታውሱታል።

አይሁድም በምቀኝነት ተነስተው፣ ኢየሱስን ለመግደል መምከራቸውን፣ ከሐዋርያት አንዱን ይሁዳን ጠርተው በመሳም አሳልፎ እንዲሰጣቸው ማድረጋቸውን፣ ሠላሳ ብር የእጅ መንሻውን እንደሰጡት፣ በቃሉ መሠረት ይሁዳ ሊያሳያቸው ጌታውን ሄዶ መሳሙን፣ ጌታም አውቆ ምነው ነከስከኝ ስለማለቱ በዝማሬያቸው ይገረማሉ።

“ ይሁዳ እንዴት ያለው ሰው ነው

ፈጣሪውን በሠላሳ  ብር ሸጠው

እንዲህ ነበር የሕማማቱ ስቃይ

የሚያሰቅቅ በሰው አዕምሮ ሲታይ

ሰኞ መክረው ማክሰኞም ዋሉ ሲያሴሩ

ረቡዕም አጽንተው በጣም መከሩ

ኀሙስ ሌሊት ይዘው የፊጥኝ አስረው

አቀረቡት ፍርድ አደባባይ ወስደው

አስፈረዱ ሞት ይገባዋል ብለው”

ዝማሬው እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለውን የስቃይ ጊዜ ይተርካል።

መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ በበገናቸው የኢየሱስ ክርስቶስን መሰቀል በሚመለከት ዝማሪያቸውን አሰምተዋል። ስቅለቱን ተከትሎ አዳም ነጻ ወጥቷል፣ ለሰው ልጆች ትንሳኤ መሆኑን ዝማሬው ያነሳል።

“ምድረ ቀራኒዮ መስቀል መሠረቱ

ጌታችን ተነሳ በእለተ ሰንበት

መጎሳቆል ቀረ መጣ ጌትነቱ

ጽኑ ሽብር ሆነ አይሁድ ተጸጸቱ

ዲያብሎስ ድል ሆነ ከነሰራዊቱ”  በማለት አዳም ወደ ቀደመ የክብር ቦታው መመለሱን በመዝሙሩ ይናገራሉ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here