የበጋ መስኖ ስንዴ …

0
75

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ከፍተኛ ጥረት ከመኸር እርሻ ሥራ ባሻገር የመስኖ ልማትን ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።

ከክረምት ዝናብ ጥገኝነት ባለፈ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር የውኃ  ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ለማልማት ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ሆኖም ካላት ሰፊ መሬት እና የውኃ ሀብት አንጻር የሚጠበቀውን ሥራ አከናውናለች ለማለት አያስደፍርም።

በአማራ ክልል ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለመስኖ ልማት ምቹ ቢሆንም እስካሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው መሬት ግን ከ11 በመቶ እንደማይበልጥ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል። ለመስኖ ልማት ምቹ የሆነውን መሬት በሙሉ አቅም መጠቀም ካላስቻሉት ምክንያቶች የመስኖ መሠረተ ልማቶች አለመስፋፋት፣ የግንዛቤ እና የበጀት እጥረት፣ ዘመናዊ የመስኖ መሣሪያዎች አለመቅረብ እና ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው።

ቢሆንም ግን አርሶ አደሩ ከመኸር የግብርና ሥራው በተጨማሪ በመስኖ የተለያዩ ሰብሎችን እንዲያለማ ጥረት እየተደረገ ነው። አርሶ አደሮችም በየአካባቢያቸው የሚያገኙትን የውኃ ሀብት በመጠቀም የመስኖ ልማት እያከናወኑ መሆኑን ለበኩር ጋዜጣ ሐሳባቸውን በስልክ አጋርተዋል። አሁን ላይ በመስኖ የለሙ ሰብሎች እያሸቱ እና የደረሱት ደግሞ እየተሰበሰቡ መሆኑን ሐሳባቸውን አጋርተውናል።

አርሶ አደር በላይ ሺፈራው በሰሜን ሸዋ ዞን የሞጃና ወደራ ወረዳ የዙብአምባ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደርሩ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት በዓመት ሁለት ጊዜ ያመርታሉ። በመኸር እና በበጋ መስኖ ስንዴ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ።

አርሶ አደር በላይ አክለውም የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ በማከናወን በትንሽ መሬት ላይ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ቀድመው በመያዝም ሥራቸውን ያከናውናሉ። “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመስኖ ልማት ላይ በትኩረት በመሥራቴ የተሻለ ምርት እያገኘሁ ነው” ብለዋል።

በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አርሶ አደር በላይ ወደፊት መንግሥት በቂ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የተሻሻሉ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ቢያቀርብላቸው የተሻለ ምርት ማምረት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ሌላው ሐሳባቸውን ያካፈሉን በሰሜን ሸዋ ዞን የሞጃና ወደራ ወረዳ ከፊላገነት ቀበሌ ነዋሪው ቄስ አጥላው ሁሉምይፈር መስኖ በማልማት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደር ናቸው። ባለፈው ዓመት ስንዴ በማምረት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ሽያጭ አቅርበው የተሻለ ገቢ እንዳገኙ ነግረውናል። በዚህ ዓመትም በአራት ሄክታር መሬት ስንዴ እያለሙ እንደሆነ በስልክ ነግረውናል። የመሬት ልየታ፣ የማሳ ዝግጅት፣ ደጋግሞ ማረስ፣ የውኃ ጠለፋ፣ የግብዓት እና የዘር ዝግጅት የእርሳቸው ቅድመ ዝግጅቶች እንደነበሩ አስረድተዋል። አሁን ላይ የሰብሉ ቁመና ጥሩ እንደሆነ እና እያሸተ መሆኑን ነግረውናል።

አርሶ አደር ቄስ አጥላው ከዚህ ጎን ለጎን የመኸር እርሻ ዝግጅትም እያደረጉ ነው። ነዳጅ ለመስኖ ልማት (ለውኃ መሳቢያ ሞተር) በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ነዳጅ በበቂ  መጠን እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል። የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አጋጥሞ መጉላላት ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ ወረዳው ከዞኑ ጋር ተነጋግሮ ፈጣን ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል። የግብርና ባለሙያዎች ለሚያደርጉት ድጋፍ እና ክትትልም አመስግነዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የሞጃና ወደራ  ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ  መልከፃዲቅ ተክሉ ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት ወረዳው ለመስኖ ልማት ተስማሚ የአየር ንብረት እና የተሻለ አቅም አለው። አንድ ሺህ 861 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማ መሬት እንዳለውም አመላክተዋል። ከዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 529 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ  በዘር ለመሸፍን  ታቅዶ አንድ ሺህ 535 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል። ቀሪው 326 ሄክታር መሬት ደግሞ በአትክልት እና ፍራፍሬ እየለማ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በችግር ውስጥም ሆኖ ከዕቅድ በላይ በዘር መሸፈን ተችሏል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ሺህ 230 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ጥቅም ላይ ውሏል። የለማው ሰብልም በበሽታ እንዳይጠቃ ክትትል እየተደረገ ይገኛል። የውኃ ግድብን በመጠቀም በመስኖ እየለማ መሆኑን የተናገሩት አቶ መልከፃዲቅ ከ312 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተር እና 98 የሰብል መውቂያ ማሽኖች መኖራቸውንም አስረድተዋል።

አቶ መልከፃዲቅ እንደተናገሩት 740 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም (በክላስተር) እየለማ ይገኛል። በኩታ ገጠም መዘራቱ ለጥበቃ፣ ለክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም ግብዓቶችን ለማቅረብ አመቺ መሆኑን ጠቅሰዋል። ቀድመው የተዘሩ በቆላማ አካባቢዎች የሰብል ስብሰባ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 56 ሺህ 795 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በጋራ ወይም በደቦ በመሰብሰብ ከብክነት እና ከብልሽት እንዲከላከል ጽ/ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ልማት በትኩረት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች አንዱ ሰሜን ሸዋ ዞን ነው። በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ አግሮኖሚስት ባለሙያው አቶ ዘሩ ገረመው ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት በዞኑ የመስኖ ልማት በሦስት ዙር ይለማል። በአንደኛው ዙር 33 ሺህ 803 ሄክታር እና በሁለተኛው ዙር 15 ሺህ 272 ሄክታር መሬት መልማቱን  ተናግረዋል። በቀጣይ (በሦስተኛው ዙር) በሦስት ሺህ 107 ሄክታር ይለማል ብለዋል።

በአጠቃላይ ከመስኖ ልማቱ አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ 58 ሺህ 701 ኩንታል በአንደኛ ዙር እንዲሁም 23 ሺህ 580 ኩንታል በሁለተኛ ዙር የአፈር ማዳበሪያ  ጥቅም ላይ ውሏል። ለሦስተኛ ዙር ደግሞ 12 ሺህ ኩንታል ለማቅረብ ታቅዷል። የምርት መቀነስ እንዳይከሰትም የሰብል ተባይን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው።

የሰብል ስብሰባ በተለያዩ ወረዳዎች እንደጀመረም የተናገሩት አቶ ዘሩ ገረመው በበጋ መስኖ ከስንዴ በተጨማሪ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎች እየለሙ ነው ብለዋል። የደረሱ ሰብሎች በዝናብ እና መሠል ምክንያቶች እንዳይባክኑ በጥንቃቄ መሰብሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማዉ የእርሻ መሬት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸዉን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። በቢሮዉ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነዉ ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት በ2017 ዓ.ም 342 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነው። ከዚህ ዉስጥ 254 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በስንዴ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜም (ሚያዝያ 10 ቀን 2017 ዓ.ም) ድረስ በስንዴ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 202 ሺህ 795 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል። ምርታማነትን ለማሳደግም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የሰብል ልማቱ በኩታ ገጠም እንዲለማ ትኩረት ተሰጥቶም ተሠርቷል። ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 482 ሺህ 949 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመጠቀም ታቅዶ እስካሁን 494 ሺህ 150 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመላክቷል።

በተመሳሳይ 51 ሺህ 326 ሄክታር ሰብል መሰብሰቡን ያነሱት ዳይሬክተሩ እስካሁንም አንድ ሚሊዮን 257 ሺህ 898 ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል። በአማካኝ በሄክታር 37 ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በሚያዝያ ወር መጨረሻ የአንደኛ ዙር የሰብል ስብሰባ ይጠናቀቃል ያሉት ዳይሬክተሩ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም ባለሙያዎችን ቀድሞ በማግኘት የሙያ ስልጠና ተሰጥቷል፤ ክትትልና ድጋፍ በማድረግም ወደ ሥራው እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት። የመስኖ ቦይ (ካናል) የመጥረግና የመጠገን ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል። ከመኸር ልማት በተጨማሪ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማከናወን የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከግብርና ሚኒስትር የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here