ወግ
ቡና በኢትዮጵያ ከፋ በሚባል አከባቢ የተገኘ ፍሬ ነው፤ “ኮፊ” የሚለውን የእንግሊዘኛ ስያሜ ያገኘውም ከዚሁ “ከፋ” ከሚለው የቡና መገኛ ሀገር ነው ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡
በኢትዮጵያ ሬዲዮ “የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና” ከሚለው ዝማሬ አንስቶ በቤታችን በማለዳው “ቡና ጠጡ” እስከሚለው ጥሪ ድረስ ቡና ለኛ ለኢትዮጵያውያን ቅርባችን የሆነ ፍሬ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን በቡና ሰበብ “ሥራ ፈቶች” የሚሉን ታዛቢዎች ቢኖሩብንም ቡናችን የልባችንን መወያያ መድረካችን መሆኑን የምናውቀው ግን እኛው ብቻ ነን፡፡ ቡና እየጠጣን ከቤታችን በመነሳት፣ ጎረቤቶቻችንን በማካለል፣ ቀበሌያችንን፣ ወረዳችንን፣ ዞናችንን… እያልን ስለ ሀገራችን የምንወያየውም የቡና ጀበናችን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ድረስ ተጥዶ እየወረደ ሲቀዳ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እኛ ከአቦል፣ ከቶና እና ከበረካ ብለን የምንጠጣውን ሦስት ስኒ ቡና በትልቅ ኩባያ አንድ ጊዜ በመጠጣት የሚበልጡን የብዙ ሀገራት ዜጎች እንዳሉ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ፡፡ ልዩነቱ እኛ ለሦስት ስኒ ቡና የምናባክነው ጊዜ መብዛቱ ላይ ነው፡፡
ቡናን ለቁም ነገር ውይይት ሳይሆን ለሀሜት ይጠቀሙበታል ተብለን የምንታማው እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ሀሜቱን የኛን የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ ስነ ልቦና ካልተረዱ ሰዎች የሚሰነዘር ጥቃት አድርገን መውሰዳችንም ስህተት አይሆንም፡፡ እኛ ለቡና ተጠራርተን ከምናደርገው ውይይት በተጨማሪ የቡና ቁርስ እያልን በጋራ የምንቋደሰው ጥራጥሬም ይሁን ሌላ ምግብ የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመዳችን እንደሆነ ያልተረዱልን ብዙ ሰዎች ስላሉ እነሱን በስኒ ዳር ጨዋታችን ወደፊትም ልናነሳቸው አንፈልግም፡፡
የኛ የኢትዮጵያውያን የቡና ሥርዓት በየትኛውም ዓለም የሌለ የኛነታችን መገለጫ እሴታችን ነው፡፡ ቡናው ተቆልቶ እንዳበቃ ብረት ምጣዱ ላይ እንዳለ ጢሱን ወደራሳችን የመውሰድ እና መልካም ነገርን መመኘታችን ከኛ ውጪ በማንም የማይደረግ ክዋኔያችን ነው፡፡ በስኒ ማስቀመጫ ረከቦት ዙሪያ የሚጎዘጎዘው ለምለም ሣር፣ በዕጣን ማጤሻው የሚትጎለጎለው ጢስ፣ የቡና ቁርሱ እና የቡና አፍይዎቹ አቀማመጥ ቡናችን ቡና ብቻ እንዳልሆነ ለማስረዳት ጥቂት አብነቶች ይሆኑናል፡፡
“ቡናስ ጥሩ ነበር፣ ለሱስ የሚበጅ
ቁርሱ የሰው ሥጋ፣ መሆኑ ከፋ እንጂ“
እያሉ ቡናችንን እንደ ሀሜት መሣሪያችን የሚቆጥሩት ሰዎች ራሳቸው ሀሜተኞች መሆናቸውን ሳንነግራቸው ማለፍ የለብንም፡፡
የጀበና ቡና ዛሬ ላይ “ስቲም” በሚባል የብረት ቡና ማፊያ ከፍተኛ ወረራ እየተካሄደበት ቢሆንም በብዙ ቤቶች አሁንም በከሰል ላይ የምትጣደው የሸክላ ጀበናችን የትላንታችን ማስታወሻ ሆና ቀጥላለች፡፡ በነገራችን ላይ የሸክላ ጀበናን ማሟሸት ወይም ቡናን ለማፍላት ዝግጁ ማድርግ ከኛ ሀገር ውጪ የሚታወቅ ጥበብ አይመስለኝም፡፡
የብዙ ችግሮቻችን መሠረቱስ እንደ ጀበናችን አለመሟሸቱ አይመስላችሁም? የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባታችን በፊት ወደ ግጭት የሚያስገቡንን ነገሮች ሰላም በሚባለው ማሟሻ ትንሽ ብናሟሸው ኖሮ እኮ…
ኢትዮጵያውያንን የአድዋው ድል፣ የሕዳሴው ግድብ፣ የአትሌቶቻችን ድል እና የጀበና ቡናችን አንድ ከሚያደርጉን ጥቂት ነገሮች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው ብልም “ተሳስተሃል!” የሚለኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእነዚህ ጥሩ ነገሮቻችን ጥሩነት የሚመነጨውም በኔ አመለካከት ከሙሽታቸው ነው፡፡
የጀበና ቡና አደባባይ ወጥቶ የብዙ ወጣቶች የገቢ ማግኛ ከመሆኑ በፊት የብዙ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ገቢ ማግኛም እንደሆነም የሚዘነጋው የለም፡፡ አረንጓዴ ወርቃችን በዓለም የቡና ገበያ ከብራዚሎቹ እየተከተልን ብዙ የውጪ ምንዛሬ የምናገኝበት ገራሚ ፍሬያችን ነው፡፡
ከሳሎን ወደ አደባባይ የወጣው የጀበና ቡናችን ምንም እንኳን ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድልን የፈጠረ ቢሆንም የብረት ቡና ማፍያው እየፈነዳ በብዙ ዜጎቻችን ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሷል፡፡እንደውም በአንድ አጋጣሚ ይኼው ስቲም የሚባለው የቡና ማፍያ እኔ በነበርኩበት ወቅት ፈንድቶ የለበስኩትን ነጭ ሸሚዝ ወደ ጥቁርና ነጭ ሸሚዝነት እንደቀየረብኝ ፈጽሞ አልዘነጋውም፡፡
ያን ዕለት የፈነዳው ስቲም የኔን ነጭ ሸሚዝ ማበላሸቱ ምንም ያልመሰለኝ የቡና አፍይዋን ቆንጆ መልክ ክፉኛ ማበላሸቱን ስላየሁኝ ነው፡፡ ያቺ ልጅ የቡና ከራማዋ በስቲሙ ተጣልቷት “ቡን” ካደረጋት ጊዜ አንስቶ በዚያ አከባቢ ዝር ብላ አላየኋትም፡፡ እኔም ከዚያ በኋላ “እባብ ያየ፣ በልጥ በረየ” እንዲሉ ዓይነት ሆኖብኝ የቡና ማፍያ ስቲም ካለበት አከባቢ ብዙ ሜትሮችን ርቆ መቀመጥን ልምዴ አድርጌዋለሁ፡፡
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ልበላችሁና አንድም ቀን የሸክላ ጀበና ፈንድቶ በሰው ላይ ጉዳት አደረሰ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፤ ባይሆን ፈላ አልፈላ እያልን ከአቦል እስከ ቶና እየተጠባበቅን ባለበት ወቅት የሸክላ ጀበናው ትርክክ ብሎ ቡናውም ሳይጠጣ፣ ከሰሉም ጠፍቶ፣ ሱሳችንን ያልተወጣንባቸው ብዙ ቀናት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በነገራችን ላይ ስለዚሁ ተዓምረኛ ፍሬያችን ተመራመርን የሚሉ ሳይንቲስቶች አንዴ ቡና ለጤና ተስማሚ ነው ሲሉን ይቆዩና ሌላ ጊዜ ደግሞ ቡና በጤና ላይ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች እያሉ ያልነገሩን ነገር የለም፡፡ እኔ ቡናን እየጠጣሁ ጥቅም እና ጉዳቱን ለመለየት በመጣር ላይ እገኛለሁ፤ እስካሁን ባለኝ የብዙ ጊዜ ምርምር ቡና ባልጠጣሁ ጊዜ ማፋሸክ አበዛለሁ፤ ያንጠራራኛል፤ ቀኔን በምቾት አላሳልፍም፤ በሥራዬም ደስተኛ አልሆንም፡፡ በጠጣሁ ቀን ደግሞ ሁሉም ነገሮች ጥሩ ይሆኑልኛል፡፡ ቡና ለጤና ጥቅም ይሰጣል የሚሉት ተመራማሪዎች ናሙናቸውን የወሰዱት ከኔ ዓይነት ሰዎች ላይ እንደሆነም እርግጠኛ ነኝ፡፡
በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ ወጌ “ነበር” ነበር ወደሚባል አፈ ታሪክ ሊሸጋገር ከጃማይካዊው ፈጣን ሯጭ ዩሴይን ቦልት በበለጠ ፍጥነት እየከነፈ ነው፡፡ እንዴት? ካላችሁኝ የዚህ ሁሉ ወጌ መንደርደሪያም ይሄንኑ ጉዳይ ለናንተ ለማካፈል ነው፡፡
ቡና ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት በወረቀት ተጠቅልሎ በ25 ሳንቲም (ስሙኒ) ይሸጥ ነበር፤ አሁን ግን እንኳንስ የ25 ሳንቲም ቡና ሊኖር ይቅርና ራሱ 25 ሳንቲምም እንደ ዳይኖሰርስ እየጠፋ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በአንድ ብር ቡና፣ ዕጣን፣ ሰንደል እና ስኳር እንድንገዛ የላኩን አያቶቻችን የብረቱም ይሁን የወረቀቱ አንድ ብር ምንም የማይገዛ ሲሆን በዓይናቸው ተመልክተዋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ “ቁጭ በሉና ቡና ይፈላላችሁ” የሚለው የክብር ግብዣም ከቀረ ሰነባብቷል፡፡
ቡና አፍልቶ ጎረቤትን መጥራት፣ በስኒዎች ዙሪያ ያንንም ይሄንንም እያነሱ መጨዋወት የጀበናን አንገት እየተናነቀ ልገፍል አትገንፍል የሚል ቡናን ማየት፣ “የቡና ስባቱ መፋጀቱ” እያሉ ቡናን በትኩስ በትኩሱ መጠጣቱ እና ሌሎችም የቡና ባህሪያት በቡና መወደድ ምክንያት ተቀያይረዋል፡፡
ድሮ ድሮ ቡና ተፈልቶ አቦሉ ላይ የደረሰ ሰው እንደ ጥሩ ሰው ይታይ እንዳልነበረ ሁሉ አሁን ላይ ቡና እየተፈላ አቦል ላይ ሰው ቢደርስ ያ ሰው በጣም እንደሚጠላ አይጠራጠሩ፤ እንደ ክፉ ቀላዋጭ መታየቱም የግድ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከአንድ ሺህ ብር እስከ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ብር በመድረሱ ነው፡፡
የወለጋ፣ የጅማ፣ የጋምቤላ፣ የሐረር፣ የዘጌ ወይም የሌላ እያልን አማርጠን የጠጣነው ቡና ዛሬ ላይ ኪሳችንን ቡን የሚያደርግ ፈንጂ ከሆነብን ሰነባብቷል፡፡ የጀበና፣ የማሽን፣ የስቲም እና የሌላ እያሉ አማርጦ መጠጣቱ ቀርቶ ገብስ ወይም ሌላ ባዕድ ነገር ያልተቀላቀለበት ቡና ማግኘትም እየቸገረን መጥቷል፡፡
እናንተዬ፣ ከኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበራት ቡና በዚህ ፍጥነት ከብዙ ደሃዎች ቤት ሳትሰናበተን ትወጣለች የሚል ግምቱ ፈጽሞ አልነበረኝም፡፡ በቀን አንድ ስኒ ቡና በ30 ብር እየገዙ ለመጠጣት በወር 900 ብር ማስፈለጉን ስታስቡት በጆሯችሁ ሽው የሚለው “ቡና ጤናን ይጎዳል” የሚለው የጤና ባለሙያዎች ምክር ነው፤ ምክንያቱም ቡናው ጤናችንን ባይጎዳው እንኳን 900 ብሩ ቀልባችንን መጉዳቱ አይቀርምና ነው፡፡
ሽንኩርት ሲገዙት እና ሲልጡት ሁለት ጊዜ ያስለቅሳል የሚሉንን አሽሙረኞች ሃሳብ ልዋስና ቡናም ሲገዙት እና ሲጠጡት ሁለት ጊዜ ጨጓራን ይልጣል ወደሚል ፈሊጥ ቀይሬዋለሁ፡፡ በሀምሳ ሳንቲም የጠጣነው አንድ ስኒ ቡና በዚህ ፍጥነት 30 ብር ሲገባ ማየት የምር ግን አልገረማችሁም?
ሀገር በቀል የሆነው ቡናችን ከሀገራችን አልፎ የውጪ ምንዛሪ በማስገኘቱ ደስተኞች ነበርን፤ ቡናን በመልቀም፣ በማጠብ፣ በመቁላት፣ በመፍጨት፣ በማሸግ እና በሌላም ቡና ነክ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው የሥራ ዕድል በተፈጠረላቸው ዜጎችም ደስተኞች ነበርን፤ በተለይም ቡናን በሚያለሙ አርሶ አደሮች የላባቸውን ማግኘት ላይ ደስታችን ወደር አልነበረውም፤ ቡናን አፍልተው በመሸጥ ራሳቸውን በሚረዱ ዜጎችም ደስተኞች ነበርን፤ ይሄ ሁሉ ደስታችን ቡን ብሎ የጠፋው ግን በራሳችን ወርቅ መድመቅ ባለመቻላችን ነው፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ከዚህ በኋላ ቡናን አረንጓዴ ወርቃችን እያልን የምናሞካሸው?
የብዙዎቻችን የነበረው ቡና የሀብታሞች ብቻ ሆኖ መቅረቱ የምር ያሳዝናል፡፡ “ሻይ ቡና እንባባል” የምትል አነስተኛ የግብዣ ጥያቄያችንም ከዚህ በኋላ ፈጽሞ ከከንፈራችን አትወጣም፡፡ የሻይ ቡና ግብዣችን እንደ መድኃኒት ልጆች በማይደርሱበት አካባቢ ይቀመጥ መባሉም ያሳዝናል፡፡ ቡናም እንደ ውስኪ እና ሌሎች የአልኮል መጠጦች የክት መጠጥ መሆኗም ያሳዝናል፡፡ ቡና መሸጫ ቦታዎችን ስናይም ባላየ ማለፋችን ያሳዝናል፡፡
በኔ በኩል፣ “ቡናስ ጥሩ ነበር፣ ለሱስ የሚበጅ
የገበያው ነገር፣ ኪስ ጎጂ ሆነ እንጂ”
እያልኩ ከቡና ልርቅ ነው፡፡ ወይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ቡና ወይ ደግሞ ከውጭ ሀገር እንደ ልባሽ ጨርቅ በርካሽ የሚሸጥ ቡና ካገኘሁኝ ለሱሴ ያህል እሱን እጠጣለሁ፡፡ እናንተስ?
ማረፊያ
የጥንት ዘመን የሹመት አሰጣጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለመጠሪያነት ሲውል
ባሕረ ነጋሽ – የኤርትራ
ራስ – ለትግራይ
ንቡረ ዕድ- ለአክሱም
ዋግሹም – ለዋግ ኸምራ
ፊት አውራሪ- ለወልቃይት
ደጅ አዝማች – ለቋራ
ጃንጥራር- ለአምባሰል
መርዕድ ዝማች- ለሸዋ
አዛዥ- ለአገው ምድር
ወሰን አዝማች- ለአማራ ሳይንት
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም