የቡድን ሃያ ጉዞ

0
25

እ.አ.አ በ1999 የእስያ የገንዘብ ቀውስን ተከትሎ የተመሠረተው ቡድን ሃያ (G20) የገንዘብ ሚኒሥትሮች እና የማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች መድረክ ሆኖ ነበር የተጀመረው።

በመቀጠልም እ.አ.አ ከ2007 እስከ 2009 በተፈጠረው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ ምክንያት ወደ መሪዎች ጉባኤ አድጓል:: ይህም አድማሱን በማስፋት እንደ ንግድ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ልማት፣ ጤና፣ ኢነርጂ፣ ግብርና እና ፀረ – ሙስና ባሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ማሳለፍ ቻለ::

ቡድን ሃያ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒሥትሮች ለሁለት ቀናት ያህል የዓለምን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የሚሞክሩበት መድረክ ነው:: ከሀገራት መሪዎች በተጨማሪ የገንዘብ ሚኒሥትሮች እና የማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች፣ የንግድ ተወካዮች እና ፀረ – ሙስና ላይ የሚሠሩ ቡድኖች በስብሰባዎች ይካፈላሉ::

እ.አ.አ በ2008 በዋሽንግተን ዲሲ ከተካሄደው የቡድን ሃያ የመሪዎች ስብሰባ በኋላ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲካሄድ ተወሰኖ ነበር:: ይህን ተከትሎም እ.አ.አ በ2009 በለንደን (እንግሊዝ) እና ሴንት ፒትስበርግ (ሩሲያ) እንዲሁም እ.አ.አ በ2010 በቶሮንቶ (ካናዳ) እና ሴኡል (ደቡብ ኮሪያ) ተካሂዷል:: እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ ጉባዔው   ዓመታዊ እንደሆነ ከዓለተደረገ ኢኮኖሚ ፎረም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል::

ቡድን ሃያ (G20) የማክሮ ኢኮኖሚ (የዋጋ ንረት፣ ጠቅላላ የምርት መጠን፣ ገቢ፣ የምንዛሪ ተመን፣ የገንዘብ አቅርቦት) ፖሊሲዎችን ለማስተባበር፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ መረጋጋትን ለማስፈን እና አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያሰባስብ ዓለም አቀፍ መድረክ ነው።

የቡድኑ አባላት በአጠቃላይ 85 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አቀፉን የሀገር ውስጥ ምርት፣ ከ75 በመቶ በላይ የዓለም ንግድን እና ከዓለም ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይወክላሉ። ቡድኑ 19 ሀገራትን እና ሁለት ሕብረቶችን ያጠቃልላል:: ቡድኑ ቋሚ ሴክሬታሪያት (ጸሐፊ) የሌለው ሲሆን በየዓመቱ በተለያዩ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ይመራል:: ፕሬዚደንት ሆኖ የሚመረጠው አጀንዳውን ያስተባብራል፤  ስብሰባዎችን ያስተናግዳል::

የቡድን ሃያ አባል ሀገራት  አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ተርኪዬ፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ጃፓን፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እንዲሁም  የአፍሪካ እና የአውሮፓ ሕብረቶች  ናቸው::

እ.አ.አ መስከረም 09 ቀን 2023 በኒው ዴሊሂ ሕንድ) በተካሄደው የቡድን ሃያ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረትን እንደ ቋሚ አባልነት በይፋ ተቀብሏል:: ይህም የቡድኑ ታሪካዊ ምዕራፍ ተብሏል::

የአፍሪካ ሕብረትን ማካተት አፍሪካ በዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊ አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ መደበኛ ውክልና እንዳላት ያረጋግጣል:: ይህም ዓለም አቀፍ ፖሊሲን የመቅረጽ አቅሟን በእጅጉ ያሳድጋል::

የዘንድሮው ጉባዔም ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ ኅዳር 22 እና 23/2025 (ኅዳር 13 እና 14 2018 ዓ.ም) ‘አንድነት፣ እኩልነት፣ ዘላቂነት’ በሚል መሪ ሐሳብ ነበር የተካሄደው:: የጉባዔው አጀንዳም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የአየር ንብረት ቀውሱን እንዲላመዱ፣ ወደ ንፁህ ኀይል እንዲሸጋገሩ እና ከመጠን በላይ ዕዳ እንዲቀንስላቸው በመርዳት ላይ አተኩሯል:: በዚህ ጉባዔ ከ42 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል::

በጉባዔው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በቁጥር ትንሽ የሆኑት ነጮች በደቡብ አፍሪካ  በከፍተኛ መጠን እየተገደሉ እና መሬታቸው እየተቀማ ነው” በማለት ስብሰባው ላይ አልተገኙም:: ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አሜሪካ በዋሺንግተን የነበሩትን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ማባረሯ የሚታወስ ነው:: የቻይና እና የሩሲያ መሪዎች ባይገኙም ነገር ግን ተወካዮቻቸው መገኘታቸውን ልብ ይሏል::

አሜሪካ ባትሳተፍበትም አባል ሀገራቱን ወክለው በሥፍራው የተገኙት መሪዎች ባለ 122 ነጥብ የአቋም መግለጫዎችን አጽድቀዋል:: መግለጫው ዓለም አቀፋዊ ፍትሐዊነትን፣ ባለብዙ ወገን ማሻሻያ እና ዘላቂ ልማትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው::

በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት (አብዛኛዎቹ አፍሪካ ውስጥ ያሉ) የብድር ወለድ ክፍያ እንዳይከብዳቸው ዓለም አቀፉን የብድር ሥርዓት ማሻሻል፣ ማዕድናት በወጡበት ሀገር ውስጥ ዕሴት እንዲጨምሩ በማድረግ አፍሪካ ከዓለም አቀፉ ኢነርጂ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል፣ ታዳጊ ኢኮኖሚዎችን በማይጎዳ መልኩ ለነዳጅ ቅነሳ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሆን የገንዘብ አቅርቦቶችን ማመቻቸት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም እና ዓለም አቀፍ ምላሽን ማጠናከር በሚሉት ላይም ትኩረቱን አድርጎ ነበር::

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡድኑ የመሪዎች ጉባዔ በመካሄዱ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን አጀንዳ በዓለም አቀፍ ውይይቶች በማቅረብ ግንባር ቀደም እንድትሆን አድርጓል:: እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የቡድን ሃያ አባልነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ታሪካዊ ክስተትም ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉባዔው በርካታ የዓለማችን ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሀገሮች  በተለይም የአሜሪካ፣ የቻይና እና የሩሲያ ከፍተኛ መሪዎች አለመገኘት በርካቶች የቡድኑ ፈተና አድርገው ቆጥረውታል::  አንዳንዶች ደግሞ የቡድን ሃያን የወደፊት አስፈላጊነት እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል::

ይህ ሁኔታ ቢከሰትም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአፍሪካዊው “ኡቡንቱ” ፍልስፍና በመመራት እርስ በርስ መተሳሰርን እና ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጉላት ነበር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት።

ሲሪል ራማፎሳ ጉባዔው በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ወቅቱ ለደቡብ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን እንደሚያመላክት ተናግረዋል። ጉባዔው የቡድን ሃያ (G20) የጆሃንስበርግ የመሪዎች መግለጫን በማጽደቅ ተጠናቋል።

መግለጫው ከቃላት ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን የሚጠቅሙ ተጨባጭ ተግባራትን በመፈጸም እና በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ ርምጃን በማመቻቸት የመድረኩን ጥቅም እንደሚያሳይ የጉባዔው ተሳታፊ ሀገራት መሪዎች ጠቁመዋል።

መሪዎቹ ባወጡት መግለጫ በሱዳን፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በፍልስጤም ግዛት እና በዩክሬን ያለውን ጦርነት  በማውገዝ “ፍትሐዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ” ሰላም ለማስፈን እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

መግለጫው ለፓሪስ ስምምነት ቁርጠኛ መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጧል:: የአየር ንብረት ፋይናንስን ማሳደግ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የኃይል ሽግግርን ማፋጠን አስፈላጊ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥቷል::

እ.አ.አ በ2030 ከሰሃራ በታች ያሉ 300 ሚሊዮን ሰዎችን ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ለማገናኘት እንደ “ሚሽን 300” ያሉ የዓለም ባንክ  እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሮጄክቶችን ለማሻሻል ቃል ገብቷል:: በረሃብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቁጥርን ለመቀነስ ክፍት የንግድ ፖሊሲዎችን እና አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች መደገፍን ጨምሮ ጠንካራ እና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል።

ጉባዔው የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ለዘላቂ ልማት ያላቸውን እምቅ አቅም አምኗል:: የኤ አይ ፎር አፍሪካ (AI for Africa) ተነሳሽነት መጀመሩን በመቀበል እና በ ኤ አይ አስተዳደር ላይ ዓለም አቀፍ ቅንጅት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት ለወቅቱ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት እና የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ ለማንፀባረቅ የተባበሩት መንግሥታት ማሻሻያ እንዲያደርግ መሪዎች ጠይቀዋል።

የቡድን ሃያ ውጤታማነት አከራካሪ ሲሆን ተቺዎች እንደ እኩልነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ የሥርዓታዊ ችግሮችን ለመፍታት አለመቻሉን ይገልጻሉ:: ውጤታማነቱ በአባላት ፍላጎቶች፣ በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች እና በአንዳንድ ሀገራት የበላይነት የሚፈተን ሲሆን ይህም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባትን እና እርምጃን ሊያደናቅፍ ይችላል ይላሉ።

ቡድኑን ውጤታማ አይደለም ከሚያስብሉት ምክንያቶች አንዱ የአባል ሀገራቱ ውሳኔዎች ፖለቲካዊ መግለጫዎች እንጂ በሕጋዊ መንገድ ተፈጻሚነት የላቸውም የሚለው ነው። የሚጸድቁ መግለጫዎችን ሀገራት ችላ ሊሏቸው ይችላሉ:: በአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መካከል ያሉ ግጭቶችም ስምምነቶችን ያቀዘቅዛሉ።

ቢቢሲ፣ አናዶሉ እና ወርልድ ኢኮኖሚ ፎረም የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሕዳር  22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here