ካለፈው የቀጠለ
በመጀመሪያው ክፍል ድምፃዊ ይሁኔ በላይ ወደ ባህላዊ ዘፋኝነት እንዴት እንደገባ፣ የግሽ ዓባይ የባህል ቡድንን እንዴት እንደተቀላቀለ አስነብበናል። ከስራዎቹ መካከልም የተወሰኑ ስንኞችን በመምዝ የያዙትን መልዕክት ለመተንተን ሞክረናል። ቀጣዩ የመጨረሻ ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።
“የልጅ ወዳጅ እና የጓሮ በርበሬ
ዓመት ይለቀማል ሳይሰማ ወሬ
አብከነከነችኝ አብከነከንኋት
እሷ ጀመረችኝ እኔ ጭረስኋት”
ይሁኔ በዚህ ዘፈን ተሳክቶለት፣ ክልከላውን አልፎ ከፍቅረኛው ሲመኘው የነበረውን አግኝቷል። ለዚያውም እሷ ጀምራ እሱ ጨራሽ ሆኖ። ለዚያውም ለረጅም ጊዜ ሲወዳት የነበረችውን የልጅነት ወዳጁን አግኝቷል። ክልከላውን ሲያደርጉበት የነበሩት ቤተሰቦቿም ሳይሰሙ በምስጢር የልቡን አድርሷል። ክልከላ እዚህ ላይ አልሰራም።
“አሎ ሉሎ” የልጅነት የባላገር ዘፈን ነው። እረኞች የሚተራረቡበት ዘፈን። ከብት እየጠበቁ ገሳ እና ደበሎ ለብሰው የሚቀላለዱበት የባላገር ዘፈን ነው። “አበረ ሸጋ ልጅ ነበር። ከብቶችን ሲጠብቅ ውኃ በልቶት ቀረ” እየተባለ ይዘፈናል። ይሁኔ ይህን ዘፈን ከፍ አድርጎ ለሰፊው ሕዝብ አቅርቦታል።
“ክምክሟን” በሚለው ዘፈን የሀገር ልጅ የማር እጅ ከሚለው አባባል ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ያለውን ዘፈን አቅርቧል። በባህል፣ ቋንቋ እና እምነት መመሳሰል ለፍቅር እና መግባባት መልካም ነገር ነው። ተጣጥሞ ለመኖር ፍቅር ከአካባቢ ልጅ ጋር ሲሆን ውጤቱ የሰመረ መሆኑ እሙን ነው። የወንዜን ልጅ ጥሯት ትደብቀው ጉዴን የሚለውም ለዚህ ነው።
“ዘገሊላ” ዘፈን ከይሁኔ በላይ ስም ጋር የተሳሰረ ዘፈን ሆኗል። ሀይማኖታዊ በዓላት ከትውፊት የተነጠሉ አይደሉም። የገና፣ ጥምቀት፣ ዘገሊላ እና አስተርእዮ ማርያም በዓላት ከሃይማኖታዊ ስርዓቶች በተጨማሪ ትውፊታዊ ስርዓቶችም ይስተዋሉባቸዋል። በእነዚህ በዓላት ሕዝብ ሲሰባሰብ ይጠያየቃል። ይዘፍናል፤ ይጨፍራል። ከዚህ አልፎም ይተጫጫል። ሴት ከወንድ ይገናኛል። ይህ ዘፈን በየዓመቱ ታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ በስፋት የሚደመጥ የይሁኔ የምንጊዜም ዘፈን ሆኗል።
ኪነ ጥበብ አንድ ባህሪ አለው፤ ኩሸት ወይም ግነት። የይሁኔ “ውዴን ይዘሽው” ሙዚቃም እንዲሁ አንዲትን ውብ ሴት በውበቷ በማግነን ያቀርባታል። በዓይኖቿ ብርሃን ፈንጥቃ ጨለማውን የምታሸንፍን ሴት ያዜምላታል። ከአሪቲ እና ጠጅ ሳር የበለጠ ሽታ፣ ከገነት የሚልቅ መዓዛ ያላት ሴት አፍቅሯል። ይህችን ሴት መውደድ በርግጥ እሰይ አበጀሁ እንጂ ምን ያስብላል።
“ለእናትሽ ለአባትሽ ሺህ ወቄት ሰፍሬ
አስጎትቼ ባዝራ ዝናር አሰግሬ
ለአንገትሽ ጠገራ ለእጅሽ አምባር ጥዬ
ፎክሬ ወሰድሁሽ ሆ ብዬ ሆ ብዬ”
ብሎ ተሳክቶለት ያዜማል። በማህበረሰባችን ነባሩ ባህል ሴት ልጅ በቤተሰቦቿ ፈቃድ ስር ናት። ጥሎሽ ተጥሎ ነው ወንዱ የሚያገባት። ሴቷ ከአንገቷ ጀምሮ የምታጌጥበትን ባሏ በክብር በወላጆቿ በኩል ያቀርብላታል። ጋብቻ የክብር መገለጫ ነው። ሠርግም ዋናው ቀዳሚ ሚናው በማህበረሰቡ የተገነባውን ክብር ለማስገኘት ነው። በሠርጓ ቀን ሙሽሪትም ወላጆችም ይከበራሉ። ደግሰው ያበላሉ። በበቅሎ እና በፈረስ ሙሽሪትን ይዞ መሄድ ትልቅ ክብር ነው። የማህበራዊ እርከን ማሳያም ጭምር ነው። በከተሞች ሙሽሪት በሊሞዚን መኪና ስትሄድ እንደምታስደምመው ሁሉ፣ በገጠርም እንዲሁ በበቅሎ እና በፈረስ ከወላጆች ቤት መውጣት ትልቅ ደስታ እና ክብር ነው።
“ዘይሪኝ” ይሁኔ በላይ ወሎን ከሰላምታ እና ምርቃቱ ባህል ጋር ያቀረበበት ምርጥ ሙዚቃው ነው። ሁሉም ባህላዊ ሙዚቃዎች ውስጥ አንድ እውነት አለ። ይህም እውነት መልካም ገጽታን መገንባት ነው። ማንኛውም ማህበረሰብ በሙዚቃ ክፉ እና ኮሳሳ ተደርጎ አልቀረበም። ወሎ በብዙ ሙዚቃዎች እንደምናውቀው የፍቅር እና የብዝኀነት ተምሳሌት ነው። ወሎ በምርቃቱ እና ፍቅር አሰጣጡ የሀገር ምልክት ነው። ይሁኔም ይህንን ነው የሚመሰክረው ዘይሪኝ ሲል።
“ከእንቅልፌ ስነሳ አማን አውለኝ ብዬ
ቀኝ እጅሽን ልሳን በአንቺው መጀን ብዬ
የሰላምታ ረህመት ስጪኝ ልቀበል
አንቺ እንደዘየርሽው ተከፍቶም አይውል
በረካ ሁን ብሎ ወሎ ሲመራረቅ
ያኔ ነው አድባሩ ከሰው የሚታረቅ”
የወሎ ምርቃት፣ መልካም ምኞቱ እድል ረድኤት እና በረከት ነው ይላል ይሁኔ።
“ኧረ በሬው ና እና ባለቀንጃው” በሚሉት ዘፈኖቹ ይሁኔ ያደገበትን ማህበረሰብ ባህል አሳይቷል። በባላገሩ ሕይወት ገበሬ ከበሬ የተነጠለ ሕልውና የለውም። አርሶ አደሩ በሬውን በግጥም፣ በሽለላ፣ በዘፈን፣ በቀረርቶ እንዳይደክምበት እያበረታ ያርሰዋል።
“ጽዋውን አጋጨ ማህበር ሊጠጣ
ማነው ባለሳምንት ጽጌ የሚያወጣ
ተመስገን ይለዋል ፈጣሪን ወደ ላይ
አጭዶና ከምሮ አድርሶት ከሰማይ
ልጆቹ ፈነጩ ከብቶቹ ቦረቁ
ምን እንበላ ብለው ቀረ መሳቀቁ
ጫነው በፈረሱ እህሉን ከተማ
ወገኑን አጥጋቢ ጠንክሮ እያለማ”
ባላገሩ ከተማ መጋቢ ነው። እሱ በፀሐይ እና ብርድ አዝምሮ ከተሞችን ይመግባል። በፈጣሪው አምኖ ሰብሉን ይዘራል። በሃይማኖታዊ በዓላት ፈጣሪውን ያመሰግነዋል። ጠንክሮ ሰርቶ ከራሱ አልፎ ከተማውን የሚመግበው አርሶ አደር አኗኗር በሙዚቃው ቀርቧል።
የባላገሩን ባህል በሚገባ የሚያሳይ ሌላው የይሁኔ ሙዚቃ “ገላጋይ” የሚለው ዘፈን ነው። አሸናፊዎች በሚኖሩበት ዓለም አትንኩኝ ባይነት እና ጉልበት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚያስከብር ጋሻ ነው። አንዳንዱ በገንዘቡ፣ ሌላው በጉልበቱ፣ ቀሪው በስልጣን እና ክብር ከማህበረሰቡ ጋር በፍቅር እና በመከበር ይኖራል። ጠብ እና ግጭት በገጠር ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የሚከሰት ነገር ነው። አኗኗሩ በራሱ የሚፈጥራቸው በርካታ የግጭት ዓይነቶች አሉ። ባላገሩ በርስቱ እና በሚስቱ ከመጡበት አይመለስም። ጥይት ፈርቶ አይመለስም። በዚህ ዘፈን ውስጥ ይሁኔ የጠብ አጫሪነት ሚና የለውም። አትንኩኝ ነው የሚለው። ራሱን እየተከላከለ ነው።
“ቆይማ ቆይማ ላሳየው ቆይማ
አንቺን ብሎ መጥቷል ነገር የተጠማ
ደግሞ ለወንድነት ድሮም አልታማ
ባንቺ ይፈትኑኝ ይታይ የኔ ግርማ”
ሚስቱን ሌላ ሰው ተመኝቶበታል። ለዚህ ነው ተው ሲል የምንሰማው። ግጭቶች ወንጀል ይምሰሉ እንጅ በክብር እና በሉዓላዊነት ላይ ሲሰነዘሩ ፍትሐዊ ይሆናሉ። ወንድነት በየ ቤቱ እና ሀገሩ አለ። ግን ለመኖር ሲባል ቀለል ተደርገው መታየታቸው ሐቅ ነው። የማይነካውን ድንበር ነክተውበታል። መሳሪያውን ብድግ አድርጎ የመጠቃት እና የመደፈር እልህ ይዞት ይነሳል። እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ።
“በፊት ይገለጣል በዓይን የማይገለጥ
እስኪ ገለል በሉ ወዲህ አለ ነገር
ከውጪ ወራጁ ብጫዎት ብስቅም
ባንቺ ከመጡብኝ እኔ ዋዛ አላውቅም”
ብሎ ይፎክራል። ሳቅና ጨዋታውን አይቶ ጅል ሰው በጅል ሚዛን ገምቶታል። በነብር ቁጣ እስኪ ገለል በሉማ ብሎ በእቃ እና በሰው ላይ ተራምዶ ይነሳል። ባላገሩ ፍቅሩ እና ጥላቻው አንድ ነው። ሁለቱም ሚዛናቸው አንድ ነው። ጥላቻ የሚያውቅ ሰው የፍቅርንም ጥግ በሚገባ ያውቃል። የሚሰማ ጠብ አጫሪ ተው ተብሎ በሽማግሌ ይመከራል፤ አልሰማ ብሎ ድንበር ካለፈ ደግሞ በሽመል ቅንድቡን ይባላል። በፍቅር የሚንከባከብ ሰው፤ ልኩን ሲያልፉበት ለመግደልም አይራራም። “በአንድ እግር ይበቅላል በትርና አበባ፤ በልምምጥ ባይሆን ለምጠኸው ግባ” የሚለው ስንኝ ፍቅር እና ጥላቻ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች መሆናቸውን ያሳያል። ፍቅርን ከልክ በላይ ግልብጥ ሲያደርጉት መራሩ ጥላቻ ነው።
“ቤት ለእንግዳ ብዬ መሶቤን ባጋራ
ልካፈልህ አለኝ አንቺን ባላጋራ
ሲያዩሽ ዝም አልኋቸው ዓይን አይታገድም
ኩራቴ ነሽና ሲነኩሽ አልወድም
አንቺን ብሎ ወጥቶ ጀግና እንዴት ይረታል
እንኳን ብትር ቀርቶ ሞገድ ይመከታል
እንደ ስመጥሩ እንደ አበጀ በለው
ትዕግስት ብቻ አይደለም ክንዴ ብርታት አለው”
ብዙ ትዕግስት የሚያደርጉ እና ፍትሐዊ ጦርነት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ሞራል፣ ሕግ እና ፖለቲካ ስለሚደግፋቸው የኋላ ኋላ ማሸነፋቸው አይቀሬ ነው። ይህን መታገሴን ብቻ አትይ ብሎ ለጠላት ይናገራል። የፍቅር እስከ መቃብሩን አበጀ በለውን ጠቅሶ የተጠራቀመ የትዕግስቱ በትር የተሰነዘረ ቀን ክፉኛ ጉዳት ሊያደርስበት እንደሚችል ያስጠነቅቀዋል። ተው እረፍ ድንበር አትለፍ የተነሳሁ ቀን አልምርህም የሚል ማንገራገሪያ ነው የሚያሰማው ለባላጋራው። ለሚስቱም አለሁልሽ አትፍሪ ማንም አይነካሽም፤ ለአንቺ እና ለሀገሬ ሞት አልፈራም ሲል ያረጋግጥላታል።
ይሁኔ በ2007 ዓ.ም ባወጣው “ጉዛራ” አልበሙ የአባይ ማዶ ሰው በሚለው ሙዚቃ ድጋሜ ሽንብራ የሚል ቃልን ከፍቅር ጋር አያይዞ ሲያዜም እንሰማዋለን።
“እየተግደረደርሽ አስቸግረሽኛል
አንድ እግር ሽንብራ እንግዳ ይሸኛል
አንቺ ወፍ ጠባቂ የመንደሬ ልጅ
መስኖ እሸት ፈልፍዬ ስመጣ ወደ አንቺ
ወርውረሽ የላክሽው ልቤን ልታገኝ
ምድረ ነጎድሽ ነው ለካስ የመታኝ
እኔስ ጡትሽ ጡትሽ ምድረ ነጎድሽ
ደርሶ ብቅ እያለ ከውድ ደረትሽ
ሽንፍንፍ ሽንፍንፍ አረገኝልሽ”
እንደ ሀገር ስለተቃራኒ ጾታ እና ፍቅር በግልጽ መነጋገር ነውር ተደርጎ ይታሰባል። ይሁኔም የሚጠቅሰው ይህንኑ ነው። እናም ማህበረሰባችን ፍቅር እና ስጋዊ ተራክቦን በቅኔ ለመግለጽ ተቸግሮ አያውቅም። እንዲያውም ይሁኔ ትንሽ አለፍ ብሎ ጡት የሚለውን አካል በግልጽ ይጠራዋል። የሴት ልጅ ጡት በበርካታ የኪነ ጥበብ ስራዎች በብዙ መልኩ ተገልጾ ሰምተነዋል። በነብር፣ በሎሚ፣ በቀስት፣ በጦር፣ በተራራ እና በሌሎችም ተመስሏል። በዚህ ዘፈን ውስጥ ሽንብራ ጾታዊ ግንኙነትን ወክሎ በቅኔ ቀርቧል። ጡት በልጅነት ወሲባዊ አካል ነው። በሒደት የምግብ እቃ ይሆናል። “ጡት እና መንግሥት መውደቁ አይቀርም” ያለው ማን ነበር? ጡት ትልቅ አስማታዊ መስህብነት አለው። ቀልብን የመሳብ ምትሐታዊ ኃይል አለው። ይሁኔም ተሸነፍሁልሽ እባክሽ የሚለው ለዚህ ነው።
ከአካላዊ ገለጻ ጋር በተገናኘ ሌላ የይሁኔ ዘፈን አለ። “ዘንገና” በሚለው አልበም ውስጥ ተካቷል። ምን አለብሽ ይላል ርእሱ።
“ዓይንሽም ልብሽም ተው ይላል ተው ይላል
ወትሮም ያልተያዘ ግልግል ይችላል
ኮለል ኮለል ስትል ከፊቴ ቀድመሽ
ይሄው ሲስማሙብኝ ሽንጥና ዳሌሽ”
ይሁኔ የልጅቱን አካላት እንደ ጠላት ወስዷል። እሱ አይሆንሽም ብለው አመጽ የከፈቱበት እየመሰለው በእኔ ቦታ በሆኑ ምነው ይላል። ዓይኗ፣ ልቧ፣ ዳሌ እና ሽንጧ ተው ይቅርብህ ብለውታል። ፈርቷቸዋል። በዚህም አያበቃም።
“ይከሰስ ይወቀስ መኪና ሰፊው
ደረቷን ሰንጥቆ ጡቷን አሳየው
አንተ ጡት አሳሳች የእጸ በለስ ፍሬ
ቀና ቀና አትበል ተኛልን ለዛሬ
ከላይ ታች አትንጠር እስኪ አደብ ግዛ
የዘመኑ ሸምጣጭ አይደለም የዋዛ”
ይሁኔ “የአባይ ማዶ ሰው” ከሚለው ሙዚቃው ጋር ተቀራራቢነት ያለው ገለጻን ሲጠቀም እንሰማዋለን። የሰውነት ክፍሎቿን ተጣልቶ ነበር። ይቀጥልና ፍርዱ በእነሱ አይደለም መኪና ሰፊው ነው ገላዋን አጋልጦ ያሳያት በሚል ወቀሳውን ያዞራል። ይሁኔ ይህን አሳሳች የሚለውን ጡት አላገኘውም። ልጅቱም ቢለምናት አልሰማችውም። እናም ጡቶቿን ንጥር ንጥር አትበሉ ብሎ ምክር በመለገስ ይቋጫል። ሌላ ሰው እንዲነካው አልፈለገም።
“ብብ ከፊላው” የጽሑፋችን መቋጫ ይሁን። ይሁኔ የባህል ሙዚቃዎችን በጭውውት እና በድራማ መልክ የመስራት ልምምድ ከግሽ ዓባይ የባህል ቡድን የጀመረ ነው፤ አንቱዬዋ በሚለው። ይህን ሙዚቃ አምስት ሆነው ነበር የሰሩት። በ1993 ዓ.ም የወጣው አልበም በእኔ ስሜት የምንጊዜም ምርጥ አልበሙ ነው እላለሁ። የአልበሙ መጠሪያ “ብብ” የገጠር ልጆች ተሰብስበው የሚያዜሙት ሀገረሰባዊ ዜማ ነው። በይሁኔ ፈጠራ አከልነት አድጓል። የባህል ሙዚቃዎች የባላገሩን አኗኗር የሚዳስሱ ናቸው። ብብ የሚለውም ዘፈን ውስጥ አብሮ አደጉን ያፈቀረ ወጣትን እናያለን። ወንዶች በአንድ በኩል፤ ሴቶች ደግሞ በሌላ ከኩል ሆነው ነው ይህን ሙዚቃ የሚያዜሙት። በፉጨት ይጠራታል። ጓደኛው ግጥሙን ይጀምራል ።
የአፍቃሪው ጓደኞች “ከወንዙ ዳር ቆሞ ቢጠራት በፉጨት፤ ትውት አርጋው ወጣች ማጀቱን ለድመት” ይላሉ።
የሴት ጓደኞች ደግሞ “እሽም አትለው፤ እምቢው አትለው እንደ ሰፌድ ቆሎ ሳታንጓለው” ብለው ይቀጥላሉ ። ወንዶች ጓደኛችንን ወደሽዋል አፍረሽ ነው እንጂ በፉጨቱ ቀልብሽን ስቦታል ነው የሚሉት። ሴቶችም እንዲሁ ወንዶች ጅሎች ናችሁ ፍቅር እና ንቀት አታውቁም ይላል። እንጉርጉሮው ይቀጥላል። ከፊላው ስር አይቻት በአንጀቴ ስር ገብታለች ብሎ ይሁኔ መዝፈን ይጀምራል።
“ከቤቴ ትይዩ ተሰርቶ ጎጆዋ
ስትወጣ ዓይኗ ታየኝ ስትገባ ዳሌዋ
አልደብቅ እያልሁኝ እኔ እሷን መውደዴን
ሊያጥሩብኝ ነው አሉ መሄጂያ መምጪየን”
እያለ የፍቅሩን መጠን ያዜማል። ከንፈሯን መሳም ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ከምኞት አያልፍም። “ተዋዶ መቅረት እየተያዩ ሞት ነው” ይላል ይሁኔ። የክፋቱ ክፋት ደግሞ የጎረቤት ልጅ መሆን ነው። በየጊዜው ያያታል። እንደወደዳት ያወቁት ሰዎች ደግሞ ማለፊያ ማግደሚያውን መንገድ ሊዘጉበት መሆናቸውን ማወቁ አሳስቦታል።
ጽጋዬ ደቦጭ፣ ይልማ ገብረአብ፣ አበበ ብርሀኔ፣ አስቻለው አየለ፣ ተዘራ ተችሎ፣ በእውቀቱ ስዩም፣ አቤል መልካሙ፣ ተስፋ ብርሃኔ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ታደሰ መንክር፣ አስማማው በለው እና ሌሎችም በግጥም እና ዜማ ስራዎቹ ተሳትፈዋል። ከሌሎች ብዙ ድምጻዊያን በተለዬ ይሁኔ በላይ በርከት ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን በመስራት ዘፍኗል። የይሁኔ ሙዚቃዎች ምናልባትም ለሌላ ማህበረሰብ ጥናት መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማኛል። አበቃሁ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም