የተወለዱት በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር የጁ ውስጥ በነበረች ትንሽ መንደር ነው:: በልጅነታቸው ብዙ ችግር ማየታቸውን ይናገራሉ:: አባታቸውን እና ወንድሞቻቸውን በችግር አጥተዋል:: በአጋጣሚ ወደ ሳውዲ አረቢያ የማቅናት እድል አግኝተው ተጉዘዋል:: በዛውም የመደበኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀዋል:: የአንድ መምህራቸው ንግግር የኢትዮጵያን ታሪክ ለማጥናት እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል:: እኝህ ግለሰብ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው::
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከታሪክ ተመራማሪነታቸው ባሻገር ኢትዮጵያን በመወከል ለአረብ ሀገራት እና ለሚመለከታቸው ስለ አባይ ግድብ እንዲሁም አጠቃላይ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል:: ከእሳቸው ጋር ያረግንውን አጠር ያለ ቆይታ እነሆ::
የግብጽ ታሪካዊ ሴራ ምን ይመስላል?
የግብጽ የሥነ-መንግሥት መርህ ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖታዊ ካባ የደረበ ነው:: ይህ ካባ ግን ከዘመን ዘመን መልኩን እና ቅርጹን እንዳሻው የመለዋወጥ መብቱን አስከብሮ ኖሯል:: ግብጽ አብዛኛው ህዝቧ የክርስትና እምነት ተከታይ በነበረባቸው ዘመናት ሃይማኖታዊ ቀኖናን እንደደነገጉ የሚታመንባቸው አያሌ ሊቃውንትን በማሰማራት ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር አባዊ (Patriarchy) ሥልጣን መዘርጋቷ ይወሳል:: በዚህም የአባይን ወንዝ ማልማት እና መጠቀም እንዳይቻል የሚያደርጉ፣ የስራ ባህልን የሚያለዝቡ ቀኖናዎች እና ህጎችን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ማስረጻቸውን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ጨምሮ የታሪክ ተመራማሪዎች ገልጸዋል:: በኋላም ግብጽ አብዛኛው ህዝቧ የእስለምና እምነት ተከታይ ሲሆንም የኦርቶዶክስ ክርስትና አፍሪካዊ መዳረሻ መሆኗ ቀጥሎ ጳጳሳትን እየላከች ለተለያዩ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች መፍጠሪያ ትጠቀምባቸው ነበር:: ሀገራችንም የራሷን ጳጳሳት መሰየም እስከጀመረችበት የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ድረስ በዚሁ ሂደት ቆይታለች:: አባይን ያክል ሀብቷን እንዳትጠቀምም ግብጾች የተጠቀሙበት መንገድ ነበር::
የአባይን ወንዝ ወደ ግብጽ እንዳይፈስ ከማስፈራራት ያልዘለሉት ኢትዮጵያዊያን ነገስታት እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን በወንዙ የመጠቀም እንቅስቃሴ አላደረጉም:: የበረከቱን ፋይዳ አጉልቶ ለህዝቡም ሆነ ለነገስታት ያስረዳ እዲሁም ሀሳብ ያፈለቀ ምሁር በታሪክ አልተመዘገበም::
ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የዐባይን ወንዝ ግልጋሎት ላይ ለማዋል ሙከራ የጀመሩ ቀዳሚ መሪ መሆናቸው በታሪክ ተቀምጧል:: ንጉሡ በአሜሪካኖች ዲዛይን አሰርተው በአባይ ወንዝ ላይ የሀይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ሞክረዋል:: ይሁንና ግብጽ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎች ሴራዎችን በመጠቀም የንጉሡ ትልም እንዳይሳካ አድርጋለች:: የወቅቱ ያደጉ ሀገራትም እርዳታ ከመከልከል፣ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እስከማሳደር ደርሰዋል:: ዐፄ ኃይለ ሥላሴም “እኛ አባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም፤ የውጭ ሀገራት ደግሞ አባይን ለመገደብ እርዱን ብንል ግብጥን ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም:: ቀጣዩ ትውልድ ግን በራሱ ንዋይ (ገንዘብ) ይገነባዋል:: ጥናቱ በክብር ይቀመጥ!” በማለት ተናግረዋል::
አብዛኛው ግብጻዊ የዐባይ ወንዝ ሕይወቱ መሆኑን፣ መነሻው ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከግብጽ እደሆነ እንዲገነዘብ በትምህርት ስርዓት ሳይቀር ተካቶ ሲሰጥ ቆይቷል:: በተቃራኒው ኢትዮጵያዊያን በሀብታቸው የመጠቀም ዕውቀቱም፣ ዝንባሌውም ሆነ ፍላጎቱ ሳይኖራቸው ለዘመናት ኖረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ አስተሳሰብ በጥቂቱ መለወጡን ገልጸዋል::
የሀገራችን በአባይ ወንዙ ተጠቃሚነቷ ምን ይመስላል?
ግብፅ ቁልቁል የሚፈስላትን ሄያጅ ወንዝ ሁለት እጆቿን ዘርግታ እየተቀበለች በሲናይ በረሃ ላይ “የውኃ ባንክ” ከፍታ በማጠራቀም ከዓለም ቀዳሚ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብታም ለመሆን በቅታለች:: ይሁንና ለናይል ወንዝ አንድ ብርጭቆ የሚሞላ የውሀ አስተዋጽኦ እንኳን አታደርግም:: በተቃራኒው ኢትዮጵያ አንድ ብርጭቆ ውኃ እንኳን ቀድታ እንዳትጠጣ እድል ሳታገኝበት ግብፅ የአንበሳው ድርሻ በመውሰድ የናይል ወንዝ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች:: ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላት የበላይነትስ ከምን የመነጨ ነው ለሚለው ጥያቄ የጀርባ ምክንያቶችን ስንመለከት፤
አንደኛ ኢትዮጵያ በሀይድሮሎጂና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰለጠነ ባለሙያ አልነበራትም:: በውኃ ሕግ እንደ ግብፅ በአግባቡ የተማረ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ነበረባት፤ አሁንም ቢሆን በአንፃራዊነት የተሻለ ሁኔታ መኖሩን የማይካድ ቢሆንም በሚያስፈልገው ደረጃ ይህ ችግር ተቀርፏል ማለት አያስደፍርም::
ሁለተኛው በኢትዮጵያ የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገትና የፖለቲካ አስተዳደር አለመኖር ነው:: ከኢኮኖሚ አንጻር ስናየው ኢትዮጵያ ዜጎቿን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ስለሆነ ይህ አስከፊ የሆነ የዜጎች የድህነት ኑሮ ለማስወገድ በተለይም የዜጎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አሰልቺ ኑሮን ለማላቀቅ በትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ሳይሆን በጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተጠምዳ እንድትኖር አስገድዷታል:: በሌላ አነጋገር የአባይ ወንዝ የሚያክል ትልቅ ሀገራዊ የተፈጥሮ ኃብት ለማልማት የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም አልገነባችም::
ሦስተኛ ግብጽ በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ የበላይነትና የተሻለ ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተፅእኖ የመፍጠር አቅምን የሚመለከት ነው:: ይህ ወታደራዊ የበላይነትና ዓለምአቀፍ ፖለቲካዊ ተሰሚነት በናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተጽእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው:: ግብፅ በአረብ ሀገራት የአለቃነት ማእርግ ተሰጥቷት ይህን አለቃነቷን በምዕራባውያን ሀገራት ላይም የጠነከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት አስችሏታል:: ምዕራባውያን ሀገራትም ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ይልቅ በግብፅ ላይ የተሻለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም አላቸው::
ግብፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራትና ያላትን ተሰሚነትን እንደ መልካም አጋጣሚና እድል በመውሰድ የምእራባውያንና የአረብ ሀገራት ከጎኗ እንዲሰለፉ ከማድረጓ በላይ በአለም አቀፍ ተቋማት ላይ ለኢትዮጵያ ብድርና እርዳታ እንዳይሰጡ እንደ መሰናከል ሆና መቆየቷ እንረዳለን:: እነ አለም ባንክና አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ይቅርና እዚሁ በአፍሪካ የሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ እንኳን ብድር ከልክሎናል::
ይሁንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ ግዙፉ የአባይ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በመጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በይፋ እንዲጀመር አድርገዋል:: የግብጽ መሪዎች ግድቡ 40 በመቶ እስኪደርስ ድረስ መቼም አይጨርሱትም በሚል ተዝናንተው ነበር:: በኋላ አቅም መፈጠሩን ሲያውቁ ጩኸታቸውን ጀመሩ::
ግብጽ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ መብቶች የምትላቸውን ያብራሩልን?
ግብጽ የናይል ወንዝን ከአምስት ሺህ በላይ ዓመታት በቀደምትነት ስትጠቀምበት እንደቆየች የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ:: ኑሮዋን፣ ደህንነቷን፣ ጉሮሮዋና የህዝቧ ህልውና መሰረት ያደረገው በናይል ወንዝ ላይ ነው:: ሄሮዶቱስ የተባለ ግሪካዊ የጥንት ፀሃፊ ግብፅ የናይል ስጦታ ነች ብሎ ነበር፤ ግብፅም ይህን ትለዋለች:: ይህ ማለት ግን ናይል የግብፅ “የግል ስጦታ” ነው ማለት ባለመሆኑ ናይል የአስራ አንድ ተፋሰስ ሀገራት “የጋራ ስጦታ” መሆኑን ማመን ያስፈልጋል:: በ1855 ዓ.ም አካባቢ ኢስማኤል ፖሻ የተባለው የግብጽ ገዢም ‘ግብጽ አባይ ናት፣ አባይም ግብጽ ናት’ በሚል እሳቤ በአባይ ሸለቆና በቀይ ባህር አቅጣጫ የግብፅን ግዛት ለማስፋፋት ቢያቅድም በኢትዮጵያውያን ጎራዴ መክሸፉን በታሪክ ተመዝግቧል::
በሌላ በኩል ግብፅ በመጀመርያዎች 20ኛ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አከባቢ በናይል ወንዝ ላይ ከፍተኛ የእርሻ ስራዎች ማከናወን የጀመረችበት ጊዜ ስለነበር “በቀደምትነት የመጠቀም” ህጋዊና ታሪካዊ መብቷን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶችን ማደራጀት የጀመረችበት ነበር:: በተለያዩ ምክንያቶች በግብፅ ላይ ጂኦ-ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እያሳደጉ የመጡ የምዕራባውያን ሀገራትም ትኩረታቸውን በናይል ላይ ማድረግ ጀመሩና በአንድም በሌላ መንገድም ግብፅ የሚጠቅሙና ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን የሚጎዱ የተለያዩ ስምምነቶችን ፈፀሙ:: ግብጽም እነዚህን ስምምነቶችና ተራ የሆነ የንብረት ሕግ መሰረት በማድረግ ናይልን ቀድሜ የያዝኩትና ከጥንት ጀምሮ ስጠቀምበት ስለነበር አስቀድሜ ከያዝኩት ኮታ ከተነካብኝ ወዮላችሁ ማለት ጀመረች:: የግብፅ አቋም ፍጹማዊ የግዛት አንድነት ከሚል ኃልዮት ጋር የሚያያዝ ሲሆን በዚሁ መሰረትም የራስጌ ሀገራት የግብፅ የውሀ ድህንነትና በቀደምትነት የመጠቀም መብትን በሚነካ መልኩ የናይል ወንዝን ሊጠቀሙበት አይችሉም የሚል “አልቦ ድምር ጨዋታን”(Zero-Sum Game)ታቀነቅናለች:: የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶችንም እየመዘዘች እንደመከራከርያ ዱላ ትጠቀምባቸዋለች::
የኢትዮጵያ አቋምና አለም አቀፍ የሕግ ተቀባይነቱ? ስምምነቶቹና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው?
በሱዳን በኩል ያለው ችግርስ ምን ይመስላል?
የሱዳን መሪዎች ከሕዝባቸው ፍላጎት ውጭ በኢትዮጵያ ላይ የያዙት የተሳሳተ አቋም በኢትዮጵያ በኩል በጥልቅት ሊታሰብበት ይገባል:: የሱዳን መሪዎች ከሕዝቡ የገጠማቸውን ተቃውሞና ውስጣዊ ፈተና ለማርገብ ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸሙት ደባ እና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በግልጽ ይታወቃል:: የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት የዘለቀ መልከ-ብዙ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል:: ሁለቱ ሀገሮች ከአንድ ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር የሚጋሩ ሲሆን፤ ሕዝባቸውም በመልክ፣ በቋንቋና በባህል የተጋመደ ነው:: ሆኖም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሱዳን መሪዎች ከሕዝባቸው ፍላጎት ውጭ በኢትዮጵያ ላይ የማይገባ በደል ሲፈጽሙ ኖረዋል:: ለአብነት በአውሮፓዊያኑ 2010 በጃፋር ኒመሪ ዘመን ጄነራል ዑመር ጠይብ በተባለ ምክትላቸው ስምንት ሺህ ፈላሻዎችን ስምንት ሚሊየን ዶላር ጉቦ ተቀብለው ኢትዮጵያ ሳታውቅ በሙሴ ኦፕሬሽን ወደ እስራኤል ሼጠዋል::
በአዲስ አበባ በግብጹ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ላይ የተሞከረውን የግድያ ሴራም አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ እንዳትሆን በማሰብ የተሸረበ ሴራ ነው:: በዘመነ ደርግ በቀይ ሽብር መዘዝ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን ኤጀንሲዎችን በማቋቋም የስደተኞችን እርዳታ 50 በመቶ ተጠቅማለች፣ ስደተኞችን እንደገቢ ምንጭ በማድረግም ወደ ሰላጤው ሀገራትና ወደ አውሮፓ ይልኩ ነበር:: በኢትዮጵያ የተነሱ ተገንጣይ ቡድኖችንም ከምስረታ ጀምሮ በማስታጠቅ ኢትዮጵያን በእርስ በርስ ጦርነት እንድትታመስ የሱዳን መሪዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው::
ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ በሕወሓት ሲጠቃ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ የወረረበት አጋጣሚም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፤ የሱዳን መሪዎች ከሕዝባቸው ፍላጎት ውጭ ተቀባይነት የሌለው ሴራ እየፈጸሙ ይገኛሉ:: በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን ኢትዮጵያ የሱዳን ትልቅ ባለውለታ ናት፤ ከቅርብ ዓመታት በፊት ሱዳን ለገጠማት ችግር ኢትዮጵያ ሸምግላ በሰላም ባይፈታ ኖሮ የሀገሪቷ እጣ ፈንታ ከባድ ሁኔታ ላይ ይወድቅ ነበር::
የሱዳን መሪዎች ግን ከዚህ በተቃራኒ እየሠሩና አሁን ላይ ደግሞ የግብፅ መጠቀሚያ ሆነዋል:: በመሆኑም የሱዳን መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙት ተደጋጋሚ ደባ በኢትዮጵያ በኩል በጥልቅ ሊታሰብበት ይገባል:: ዶክተር አልፋቂህ የተባለ ግብጻዊ ምሁር “የህዳሴ ግድብን ሙሌት ማስቆም ስላልቻልን የኢትዮጵያን አንድነት ማፈራረስ አለብን “ በማለት ቅስቀሳ አድርጓል:: በዚህም ትግራይ ከኤርትራ፣ ጋምቤላን ከደቡብ ሱዳን፣ አፋርን ከጂቡቲ፣ ሶማሌን ከሶማሊያ በማቀናጀት የማፈራረስ ዕቅድ መያዙን መረዳት ይገባል:: በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው የንጹሃን ጭፍጨፋ የዚሁ እቅድ አካል ነው:: ይህን በመረዳት ኢትዮጵያን ከግጭትና መበታተን አደጋ ለመጠበቅ በጋራ መቆም አለብን::
ሀገራችን እና የባሕር በር ፍላጎቷን እንዲሁም አስፈላጊነቱን ይንገሩን?
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የአንድ መንግሥት አጀንዳ ሳይሆን የሕዝቦች በዘላቂነት የመልማት ፍላጎት ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ120 ሚሊዮን በላይ በመድረሱ የባህር በር አስፈላጊነት እንዲጨምር አድርጓል:: የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የአንድ መንግሥት አጀንዳ ሳይሆን የሕዝቦች በዘላቂነት የመልማት ፍላጎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል::
ኬንያን ሳይጨምር በአፍሪካ ቀንድ ካሉት ሀገራት ድምር የሕዝብ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ይበልጣል፤ የሕዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥር ሀገራዊ ልማትን ማጠናከርና ከቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ግንኙነት መመስረት የግድ ነው:: ለዚህም ኢትዮጵያ የባህር በርን የመጠቀም ታሪካዊ መብቷን ለማስከበር ያሉ ሰላማዊ አማራጮችን ሁሉ መጠቀም ይገባታል::
ኢትዮጵያ በቀደምት ዓመታት የባህር በርን ለንግድና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም በስፋት ትጠቀምበት ነበር፤ የነበራት እድገትና ኃያልነትም ከዚህ ጋር የተቆራኘ ነበር:: አሁንም የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንድትሆን ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብርና በመግባባት መሥራት ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ የውጭም የውስጥም ኃይሎች በጋራ ሀገሪቱን ለመበታተን ቆርጠው የተነሱበት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመገንዘብ አደጋውን በጋራ ክንድ ሊመክተው ይገባል ::
ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ከመከፋፈል ይልቅ ወደ አንድነት መምጣቷ ያሳሰባቸውና የሀገሪቱ መረጋጋት የቀጠናውን መረጋጋት እንደሚያመጣ የተረዱ ሀገራት እየተፈጠረ ያለውን ህብረትና አንድነት ለመበተን ቀን ከሌት እየሰሩ ነው:: የሀገሪቱ መጠናከር እንደፈለጉ እጃቸውን ለመስደድ ለሚፈልጉ ወገኖች አመቺ አለመሆኑ የተረዱ ወገኖች ላለፉት 30 ዓመታት ስንከተለው የነበረው የልዩነት ፖለቲካ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፤ አብሮ ከማደግ ይልቅ አብሮ መውደቅን የመረጠ ነበር፤ ይህ የፖለቲካ አካሄድ ሀገሪቱን ከውስጥ አልፎ ለውጭ ጠላቶች አሳልፎ ሰጥቷታል::
የኢትዮጵያን መጠንከር የማይሹና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድክመቷን ለሚመኙ አካላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸው ቆይቷል:: ቀደም ሲል ሊደፍሩን ወኔ የሌላቸው ሀገራት ጭምር ድንበራችንን በኃይል ለመውረር ችለዋል፤ አንዳንዶቹም ጭራሽ ሀገሪቱን ለማፈራረስ ቆርጠው ተነስተዋል:: ሄደው ሄደውም የህዳሴ ግድብ ያረፈበት የቤኒሻንጉል ክልል የእኛ ነው የሚሉ ወገኖች ብቅ ብለዋል፤ በርካታ የውጭ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸውም ኢትዮጵያን ለማዳከምና የተጀመረውን የአንድነት መንፈስ ለመበረዝ ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው::
Bekur /በኲር, [2/26/2024 4:32 PM]
ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት በሳል ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን መከተል እና ያሉትን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ አሟጦ መጠቀም ተገቢ ነው:: የባህር በር ለኢትዮጵያ ከውጭ ጉዳይ ባለፈ የደኅንነት እና የልማት ጉዳይ ነው:: ኢትዮጵያ የባህር በርን ይዛ በቆየችበት ወቅት የነበረችበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ በወደብ ጉዳይ ላይ መደራደር እና መወያየት እጅግ አስፈላጊ ነው::
የዓባይ ግድብን በኅብረት እንደሠራነው ሁሉ በወደብ ጉዳያችን ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል::
በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አረብኛ የሚችሉ፣ ዲፕሎማቶችን ማሰማራቱ እጅግ አስፈላጊ ነው:: ሁሉንም ሰላማዊ አማራጮች አሟጦ መጠቀም ዲፕሎማሲያዊ የበላይነትን ለማግኘትና ሌሎችንም ለማሳመን ይረዳል::
ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!
አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም