በአማራ ክልል ከትምሕርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በኵር ጋዜጣ አማራጭ መፍትሔዎችን ስታመላክት ቆይታለች። በትምህርት ላይ ያሉትም የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችንም መዘገቧ ይታወሳል፡፡ በቀደሙት እትሞቻችንም በክልል ደረጃ የሚሰጡ የስምንተኛ እና ስድስተኛ ክፍል ተፈታኞችን ዝግጅት ዳሰናል፡፡ መምህራንም ለተማሪዎች የተሻለ ውጤት መመዝገብ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት በተጠናከረ ሁኔታ እየሰጡ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል
በዚህ ዕትም ደግሞ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኞችን ዝግጅት እንዳስሳለን፡፡ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ዐይናዲስ ጋሻው ትገኝበታለች፡፡ ዐይናዲስ እንደገለፀችው ዩኒቨርሲቲ መግባትን ቀዳሚ ዓላማዋ አድርጋለች፡፡ ዕቅዷን ለማሳካትም የጥናት ክፍለ ጊዜ አዘጋጅታ በዚያው እየተመራች ነው፡፡ ይህም በሥራ መደራረብ ምክንያት ከጥናት ውጪ እንዳትሆን አግዟታል፡፡
ዐይናዲስ ጸጥ ያለ ቦታ እና ሰዓትን ለጥናት ትመርጣለች፡፡ ይህም ቀልቧን ሰብስባ እንድታጠና በማድረግ ለተሻለ ውጤት መመዝገብ እርግጠኛ እንድትሆን ረድቷታል፡፡ ቤተ መጻሕፍትም አዘውትራ እየተጠቀመች መሆኑን ተናግራለች፡፡ ይህም አዳዲስ ዕውቀቶችን እንድታካብት ረድቷታል፡፡ እነዚህ ሁሉ የዝግጅት ሥራዎች ዓመቱን በድል እንደምታጠናቅቅ እርግጠኛ እንድትሆን ረድቷታል፡፡
በዓመቱ በባሕር ዳር ከተማ የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ስድስት ሺህ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ የቅድመ ዝግጅት ሥራው የተጀመረው ትምህርት እንደተጀመረ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ትበይን ባንቲሁን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ምክትል ኃላፊዋ ማብራሪያ የስድስተኛ፣ ስምተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች የሚወስዱ በመሆናቸው ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ መማር ማስተማሩ በተሻሉ መምህራን እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
ቤተ መጻሕፍት በሳምንቱ ሁሉም ቀናት ክፍት እንዲደረግ ተደርጓል፡፡ ተማሪዎች በፈለጉት ጊዜ የፈለጓቸውን መጻሕፍት አግኝተው በማንበብ የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንዲቀላቀሉ ለቅዳሜ እና እሁድ አስነባቢ ተቀጥሮ ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ትበይን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደረን ከሌሎች አካባቢዎች የለየው ብቸኛው ምክንያት የአዳር ጥናት አለመጀመሩ ነው፡፡ ለዚህም ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታውን ቀዳሚው ምክንያት አድርገው አንስተዋል፡፡ ሌላው ትምህርት ቤቶች የአዳር ጥናት በሚያከናውኑበት ወቅት አዳሪው አካል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል በጀት ማግኘት ባለመቻሉ ነው፡፡
የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት ግን በተለየ መንገድ እየተሠጠ መሆኑን ምክትል መምሪያ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ይህም የተሻለ ዕውቀት እና የማስተማር ሥነ ዘዴ ባላቸው መምህራን በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በማካካሻ እና በማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎችን ይበልጥ ለማብቃት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ቢሆንም ተማሪዎች በሚፈለገው ልክ እየመጡ እንዳልሆነ ወይዘሮ ትበይን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ብለው አብነት ያነሱት የባሕር ዳር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ነው፡፡ ተማሪዎች ለምን የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት ለመውሰድ ያላቸው ተነሳሽነት ቀዘቀዘ? የሚለውን ለመለየት ጥናት መደረጉን ጭምር ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲወስዱ የተደረገው ለመምህራን የታክሲ እና መሰል ወጪዎች ድጎማ የሚሆን ክፍያ በመፈጸም ነው፡፡ ይህም የድጎማ ክፍያ ከወላጅ ጋር በመነጋገር የተወሰነ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲደረግም አንድ ተማሪ 150 ብር እንዲከፍል ይጠበቅ ነበር፡፡ የተማሪዎች ተነሳሽነት እየተዳከመ መጣ፤ ከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች ተነሳሽነት መዳከም ዋናው ምክንያት ከክፍያ መብዛት ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል በሚል የ50 ብር ቅናሽ በማድረግ ክፍያውን ወደ 100 ብር ዝቅ እንዲል ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡
አሁንም ተማሪዎች በሚፈለገው ልክ አለመመለሳቸውን ወይዘሮ ትበይን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የመምህራንን ወጪ ሊሸፍን የሚችል ሌሎች አማራጮችን ተግባራዊ አድርጎ ተማሪዎች ከክፍያ ነጻ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም የትምህርት አይነት ይዘቶች በወቅቱ እና አግባቡ እንዲሸፈኑ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ፈተናው እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ሊሠሩ የሚችሉ የሥራ መርሀ ግብሮች ተለይተው ለተግባራዊነቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ብቁ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ውጤታማ እንዲሆን መምሪያው ባለሙያዎችን መድቦ እየተከታተለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለተማሪዎች የተሻለ ውጤት መመዝገብ ወላጅም የራሱን ሚና እንዲወጣ በየትምህርት ቤቶች የወላጆች ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች በወረቀት እና በኦንላይን አማራጮች ይሰጣል፡፡ የኦንላይን ፈተና የኮምፒውተር እጥረት ከነበረባቸው ትምህርት ቤት የሚመጡ እና በቂ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለሌላቸው ተፈታኞች ፈታኝ እንዳይሆን ቀድሞ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆኑን ወይዘሮ ትበይን አስታውቀዋል፡፡
ሁሉም ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር መማሪያ ክፍል አላቸው ያሉት ወይዘሮ ትበይን፣ ሁሉንም ተማሪዎች አንድ በአንድ ያስጠቅማሉ የሚለው ግን አሁንም ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ባለፈው ዓመት ከትምህርት ውጪ ሆነው የከረሙ ተማሪዎች ዘንድሮ በመሸኛ ወደ ባሕር ዳር መጥተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ እነዚህ እና ከዙሪያ ወረዳው ገጠራማ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች መሠረታዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ሊኖርባቸው ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ወይዘሮ ትበይን ያምናሉ፡፡
የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሁሉንም ተማሪዎች ተደራሽ ሊያደርግ የሚችል የኮምፒውተር አቅርቦት የላቸውም፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተፈታኞች ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች ይወስዳሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች እንዳላቸው የቴክኖሎጂ አቅርቦት ፈተናው በኦንላይን እና በወረቀት ይሰጣል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አሁናዊ የፈተና ቅድመ ዝግጅት ሁሉም ተማሪዎች በኦንላይን አማራጭ ፈተናውን እንደሚወስዱ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑን ወይዘሮ ትበይን አስታውቀዋል፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች ግን ሲያስተምሩ በከረሙበት ትምህርት ቤት ፈተናውን እንደሚሰጡ ወይዘሮ ትበይን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ትምህርት ቤቶቹ በሚያስፈትኗቸው ተማሪዎች ቁጥር ልክ ኮምፒውተር አሟልተው ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እንዲሠሩ መመሪያ መሠጠቱን አስታውሰዋል፡፡
የሥነ ልቦና ግንባታ እና የጥናት ሥነ ዘዴ ሥልጠና ለተማሪዎች እና መምህራን እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከሥነ ልቦና ግንባታ ሥልጠናው ጎን ለጎን የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ለተማሪዎች የማሳወቅ ሥራ መሠራቱን ምክትል መምሪያ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች እንዴት? መቼ? እና የት? ማጥናት እንዳለባቸው ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
መምህራንም በቀሪ ጊዜያት ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ ምን አይነት ይዘቶች ላይ አተኩረው ማስተማር እንዳለባቸው የሚጠቁም ስልጠና መሠጠቱንም ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ መሠረቱን አድርጎ የሚሠራው ስቱደንት ዶት ኮም (www. student.com) በድረ ገጹ ሁሉም ተፈታኝ ተማሪዎች ዓመቱን በድል እንዲያጠናቅቁ ለጊዜያቸው ልዩ ትርጉም ሊሰጡ እንደሚገባ አስፍሯል፡፡ የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት የጥናት ጊዜን መከፋፈል ደግሞ ለውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም መሰላል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህም ለጥናት፣ ለክለሳ፣ መልመጃዎችን ለመሥራት ሰፊ ጊዜን በመስጠት በትምህርት ውጤታማ ለመሆን ይረዳል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም