የባቄላ መስጅድ

0
309

በዚህ ፅሁፋችን ኢትዮጵያ ከእነሙሉ ለዛዋ እና ውበቷ በምትታይባት፣ እስላም ክርስቲያኑ ተሳስቦ እና ተዋድዶ የሚኖርበትን የአንድነት ገመድ አጥብቆ የያዘ ደግ ሕዝብ በሚኖሩባት፣ እምዬ ምኒልክ “በጥቅምት እኩሌታ ከትተህ ላግኝህ!…” ብለው ለታላቁ የዓድዋ ድል ቀጠሮ በያዙባት… በቀጠሮው መሰረትም የኢትዮጵያ ጀግኖች ከአራቱም አቅጣጫ ተምመው በተቀጠረው ጊዜ በተገናኙባት፣ ተገናኝተውም የታላቁን የዓድዋ ጦርነት ለማድረግ በመከሩባት እና ስኬታማ የውጊያ እቅድ ነድፈው በተንቀሳቀሱባት በታሪካዊቷ የወሎ ምድር  በወረኢሉ ለማተኮር ወደድን። በዚህች ታሪካዊት ስፍራ የሚገኘው ጥንታዊው የባቄላ መስጅድ የሽርሽራችን መዳረሻ ነው፤

መልካም ንባብ!

ከወሎዋ መናገሻ ደሴ ከተማ ተነስተን ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ መጓዝ እንጀምር። የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን የገራዶን ረግረግ፣ ይቶ ወንዝን፣ የሳንጣን ዳገትን፣ የግራኝ ሜዳን… አግድመት አቋርጠን፣ ጠባሲትን አልፈን ጉጉፍቱ ስንደርስ በላይ ከባህር ጠለል በላይ ከ3 ሺህ 880 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን ማራኪውን ያየዋል ተራራን እናገኛለን። የወልደ ተራራን ወደ ቀኝ ትተን ቁልቁል ከወረድን በኋላ ካቤ ከምትባለው፣ በዘመነ መሳፍንት ወቅት ስመ ጥር ጀግኖችን ካፈራችው እጅ በሚያስቆረጥም የቋንጣ ፍርፍሯ በምትታወቀው አነስተኛ ከተማ እንደርሳለን። ጉዟችንን ስንቀጥል ሰኞ ወይም አራግፊኝ የምትባለውን ከተማ አግኝተን ተጨማሪ 91 ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዝን በኋላ ታሪካዊቷን ወረኢሉን እናገኛታለን።

ስጋ በኪሎ የማይሸጥባት፣ ልክ እንደ ጥንት አባቶቻችን ወግ በአይተሽ ተመድቦ ሁሉም እንዳቅሙ ስጋ በልቶ የሚጠግብባት አስገራሚዋ ወረኢሉ አንዴ ካዩአት ደጋግመው የሚናፍቋት ከተማ ናት። በውስጧ አያሌ ታሪካዊ ቅርሶችን አቅፋ የያዘች  የታሪክ መናኸሪያ ለመሆኗ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ከእነርሱ መካከልም አንዱ ባቄላ መስጅድ ነው። በእስልምና ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ይህ እድሜ ጠገብ መስጅድ በዐፄ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተመሰረተ ሲሆን ከአካባቢው ባለፈ በሀገር ደረጃ መተግበር የተገባቸው መልካም ሀይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ክዋኔዎች የሚፈፀሙበት ነው።

ከወረኢሉ ከተማ ሰሜን አቅጣጫ አራግፊኝ የተባለችውን ከተማ አንድ ኪሎ ሜትር ወጣ ብለን ወደ ቀኝ በመታጠፍ ስባት ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ ወደ ስፍራው እንደርሳለን፣ ባቄላ መስጅድ። በእግር እስከ 1:30 ይወስዳል። የመስጅዱ መስራች ሸህ ሙሃመድ ሰኢድ  ከቀድሞው የጁ አውራጃ ከዳንዮች እና ከመርሳ አባ ጌትየ መኸለቂያ ምድር ከወልድያ ወጣ ብሎ ከሚገኘው እና ጓጉር ከሚባል ቦታ ተነስተው እንደመጡ ባቄላ መስጅድን እንደመሰረቱት ይነገራል።

ዘመኑን በዋጀ አስደናቂ ጥበብ የተገነባው መስጅዱ አሁን ድረስ ቀልብን የመግዛት የአሰራር ጥበብን የሚያንፀባርቅ እፁብ ድንቅ የሀገራችን ቅርስ ነው። በደቡብ ምሥራቅ የወይብላ ማርያምን ከፍታማ ስፍራ፣ ወደ ስሜን ምሥራቅ አልብኮን እና ገመገሙን፣ ወደ ስሜን የየወልን ተራራ እና  በምዕራብ የሚያምር ከፍታ ቦታን አዋስኖ መሀል ላይ የሚገኘው ባቄላ መስጅድ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ በራሱ ደስታን የሚፈጥር ልዩ ቦታ ያደርገዋል።

ግድግዳው በድንጋይ የተገነባ፣ ጣሪያው አስገራሚ ወርድ እና ቁመት ባላቸው የፅድ እንጨቶች እና በጠፍር ማሰሪያ ገመድ ተዋዶ የመቆሙ ትንግርት ጥንታዊነቱን ይመሰክራል። ወደ መስጅዱ  ሲገቡ በሰሜን በኩል አንድ የተለየ ክፍል ይመለከቷል። በዚህ ጠበብ ባለው ክፍል ማንም እንዲገባ አይፈቀድም። ይህ ስፍራ ዛሬ ላይ በቦታው የሚገኙት የሸህ ሙሀመድ ሸሪፍ አያት ጌታውን የሸህ ሙሃመድ ኪያር ቅዱስ ቁርአን የሚቀሩባት ስፍራ እና ቅዱስ የቁርአንን ጨምሮ ሌሎች የእምነቱ መፃህፍት መቀመጫ ስፍራ ሆኖ ያገለግላል። ባቄላ መስጅድን አስደናቂ የሚያደርገው አንድ ሌላ እንግዳ ነገር ያስተውላሉ። ይኸውም  በሚያምር በብራና የተሽቀረቀረ ከላዩ ላይ በልዩ ሀረጋዊ ቅርፅ የመስቀል ምልክት ያለበት ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅዱስ ቁርአን የሚገኝ መሆኑ ነው።

የመስጅዱ መስራች ሸህ ሙሃመድ ሰኢድ  ቀኑን በፃም የሚያሳልፉ፣ ሌሊቱንም እንቅልፍ የሌላቸው፣ ከመኝታ ይልቅ ለአላህ በኢባዳ ላይ ሆነው የሚያሳልፉ ታላቅ አባት እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል። ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒሊክ በተጨማሪ ንጉሥ ሚካኤልም በጣም ይቀርቧቸው እንደነበር ይነገራል። ዝናቸውን እና መልካምነታቸውን የሚያውቁት እምዬ ምኒልክም ለእኝህ ታላቅ አባት በርከት ያለ አቡጀዲ እና ቡና በስጦታ መልክ እንዳበረከቱላቸው የፅሁፍ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ ጥር 10 የመውሊድ /ዝየራ/ ቀን ይከበርበታል። ከዚህ በተጓዳኝ በረመዳን የፆም ወቅት እና በጁምአ ሶላት ላይ በርከት ያሉ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በልዩ ሁኔታ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበትም ነው። ሌላው አሁንም ድረስ በቦታው  ከሚከናወኑ ትውፊታዊ ሥነ ሥርአቶች አንዱ እና ዋነኛው የእርቅ ሥነ ሥርዓት ነው። የቀደሙት አባት ከቀላሉ የርስ በርስ ግጭት እስከ ነፍስ ማጥፋት የደረሰ ወንጀል የሟች እና የጉዳይ ወገንን ፊት ለፊት አገናኝተው የማስታረቅ ፀጋን የታደሉ ታላቅ አባት ነበሩ። ይህ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ትውፊታዊ ተግባር ዛሬም በባቄላ መስጅድ የሚከወን ሆኖ እናገኘዋለን።

በጥል ውስጥ ያሉ ሁለት ተቃራኒ ወገኖች በመረጡት ገለልተኛ ስፍራ ላይ ታላቁ አባት ዳስ ተሰርቶላቸው አለበለዚያም ድንጋይ ተተክሎ አንካሴያቸውን እና ሙስብሃ ይዘው በተለይ ታራቂዎቹ የደም ከሆነ ከሳምንት በላይ በዳሳቸው ሆነው ታራቂዎቹ እስከሚሰባሰቡ ድረስ ፀሎት እያደረጉ በዚያው ይቆያሉ። እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከመንግሥት አካል ፖሊስ በተገኘበት የእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ይከናወናል።

እንዲህ ያለው ተግባር የሚከናወነው ለወረዳው ኗሪዎች ብቻ ሳይሆን ከወረዳው ውጭ ያሉ እና እርሳቸውን ብለው በአስታራቂነታቸው አምነው ለሚመጡ ጭምር ነው። የእርቅ ሥነ ሥርዓቱ እስከሚከወን ድረስ ታራቂዎች በመጋረጃ ይለዩ እና በቀኝ እና በግራ እንዲቀመጡ ይደረጋሉ። የሚናገሩትም ሳይተያዩ በመጋረጃ ውስጥ ሆነው ነው። የእርቅ ሥነ ሥርዓቱ  ከሰፈር ሁለቱም ወገኖች ከግርዶሽ ወጥተው አብሮ ሊያኖራቸው የሚችል መሃላ እና ሌሎች ተግባራት በአስታራቂው አባት፣ በሽማግሌዎቹ እና በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ያከናውናሉ።

ምንጭ፡- ወረኢሉ ማህደረ ወሎ- በከብር ጌታቸው ከተፃፈ መፅሐፍ የተወሰደ

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here