ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ክረምቱስ እንዴት ነው? የረፍት ጊዜያችሁን በተለያዩ ጠቃሚ ጉዳዮች እያሳለፋችሁ እንደሆነ እምነታችን ነው፡፡ ልጆች የረፍት ጊዜያችሁን እንደየ ኃይማኖታችሁ ወደ ቤተ ዕምነቶች እየሄዳችሁ መማር እና ማሳለፍ ጥቅም እንዳለው ታውቃላችሁ አይደል?
ልጆች፣ የረፍት ጊዜያቸውን በቤተ እምነቶች በመሄድ የሚያሳልፉ ሁለት ልጆችን እናስተዋውቃችሁ፡፡
የአብሥራ ክንዴ በባሕር ዳር ከተማ ሰላም አርጊው ቅድስ ድንግል ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ የአብሥራ በትምህርቷ ጎበዝ ናት፡፡ ክረምቱ ገብቶ ትምህርት ከተዘጋ በኋላ በሰላም አርጊው ቅድስት ድንግል ማርያም የአብነት ትምህርት ትከታተላለች፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የመዝሙር ልምምድ፣ የሥነ ምግባር፣ ግዕዝ እና ሌሎች ኃይማኖታዊ ትምህርቶችን እንደምትማር ነግራናለች፡፡
የአብሥራ ከሃይማኖታዊ ትምህርት ባሻገር ለቀጣይ ዓመት የምትማራቸውን ትምህርቶች ቀድማ ታነባለች፡፡ ቤተሰቦቿንም በአቅሟ ታግዛለች፡፡ የተለያዩ ጨዋታዎችንም ከሰፈር ጓደኞቿ ጋር ሆና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ትጫወታለች፡፡ ታናናሽ የሰፈሯ ልጆችንም ታስጠናለች፡፡
መሐመድ ሰይድ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ እውቀት ፋና አንደኛ ደራጃ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ መሐመድ በሰፈሩ አቅራቢያ በሚገኝ መስጊድ በመሄድ የቁርዓን ትምህርት ይማራል፡፡ ከዚህ በሻገር ሰውን ማክበር፣ ታላላቆቹን መታዘዝ፣ ታናናሾቹን መውደድ እና ማገዝ እንዳለበት ይማራል፡፡ የእስልምና መዝሙሮችንም እንደሚያጠና መሐመድ አጫውቶናል፡፡
ልጆች የአብሥራ እና መሐመድ ጎበዞች ናቸው አይደል! እናንተም እስካሁን የሃይማኖት ትምህርቶችን መማር ካልጀመራችሁ በመጀመር የስነምግባር ዕውቀቶችን መገብዬት እንዳለባችሁ ከሁለቱ ጎበዝ ልጆች ልምድ መቅሰም ይገባችኋል፡፡ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስክንገናኝ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ፡፡
ተረት
ጥንቸሉ እና ዝሆኑ
በአንድ ወቅት ዝሆንና ጥንቸል ጥሩ ጓደኛሞች ነበሩ:: ከሌሎች እንስሳት ጋር አንድ ላይ ሆነው ለምለም ሳርና ወኃ ወደአለበት ቦታ ይሄዳሉ:: እግር ኳስ መጫወት በጣም ይወዳሉ:: ታዲያ ኳስ ሲጫዎቱ ዝሆኑ ብዙ ጐሎችን ያስገባ ነበር:: ጥንቸሉም ጎል ሲገባበት ያዝን ነበር:: ጥንቸሉ ዝሆኑን “እንዴት ነው ጐበዝ ተጫዋች የሆንከው?” ሲል ጠየቀው:: ዝሆኑም “ትላልቅ እግሮች ስላሉኝ ነው” ሲል መለሰለት:: በሌላ ቀን ደግሞ ዝሆኑና ጥንቸሉ ሩጫ ውድድር ሲጫዎቱ ጥንቸሉ ይቀድም ነበር:: ዝሆኑም ስለተቀደመ አዘነና ጥንቸሉን “እንዴት ነው ፈጣን ሯጭ የሆንከው?” ሲል ጠየቀው:: ጥንቸሉም “ቀጫጭን እግሮች ስላሉኝ ነው” ሲል መለሰለት:: ዝሆኑም ጥንቸሉን “እግሮቼን እንዴት ቀጫጭን ማድረግ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀው:: ጥንቸሉም “እግሮችህ ቀጫጭን እንዲሆኑልህ እሳት ውስጥ ገብተህ መቆም አለብህ” አለው:: ዝሆኑም እንደተባለው እሳት ውስጥ ገብቶ ቆመ:: ትንሽ ሳይቆይም “አቃጠለኝ! አቃጠለኝ!” እያለ አለቀሰ::
ጥንቸሉም ዝሆኑን “እግርህ ቀጫጭን የሚሆኑልህ በዚህ መንገድ ብቻ ነው!” አለው:: ዝሆኑ ግን ሮጠ፤ ከእሳቱ ወጣና መሬት ላይ ተጋድሞ አለቀሰ:: ቀና ብሎም መቆም አልቻለም:: ጥንቸሉ ያደረገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ገባውና ዝሆኑን ይቅርታ ጠየቀው:: ዝሆኑም ይቅርታ አደረገለት:: ሲሻለውም ወደ ቤተሰቦቹ ሄደ::
ልጆች! ከዚህ ተረት እንደ ጥንቸል ተንኮል መሥራት መልሶ ራስን ለፀፀት እንደሚዳርግና ጥፋተኛ መሆናችን ካወቅንም ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብን እንማራለን፤ የማይሆን ነገርን መመኘትም ተገቢ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች
ሞክሩ
- ቁርስ ላይ የማይበላው ምንድን ነው?
- ክብ ስንት ቅርጽ አለው?
- ነጭ ባርኔጣ ጥቁር ባሕር ውስጥ ቢወረወር ምን ይሆናል?
መልስ
- ምሳ እና እራት:
- ሁለት /ፊትና ኋላ/
- ይረጥባል
ነገር በምሳሌ
አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው
ዛሬ የሠራነው ለነገ ይጠቅማል፡፡
ልብ ሳይገዙ፣ ነገር አያብዙ- ድፍረቱ ሳይኖርህ አደርጋለሁ አትበል ማለት ነው::
ሃሰተኛ ሲናገር ይታወቃል ስስታም ሲበላ ይታነቃል፤ ሃሰት ተናጋሪ ገና ከአፉ ይታወቅበታል::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም


