የቤት ባለቤት ለመሆን…

0
104

“በሕይዎት ለመኖር  በመሠረታዊነት አስፈላጊ የሆኑትን   ይጥቀሱ?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብልዎት ቅደም ተከተሉ ቢለያይም ከምላሽዎት አንዱ መጠለያ /ቤት/ ማለትዎ አይቀሬ ነው፡፡ እኛም የቤትን ጉዳይ አስቀድመን ማንሳታችን ያለምክንያት አደለም፤ ከሰሞኑ  የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ  በመገናኛ ብዙኃን አብስሯል፡፡ ባሁኑ ወቅትም ከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ   ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች  አሳውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ምዝገባውን ጀምሯል፡፡

ዜጎች የመኖሪያ ቤት  ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ በኵር የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሐም ወርቁን አነጋግራለች፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የቤት መሥሪያ ቦታ  ፈላጊዎች በተቋሙ አቅጣጫ እና መመሪያ ሰጪነት፣ በራሳቸው አመራር እና  ሒሳብ ኃላፊ በአንድ ቡድን ከ14 እስከ 24 ሰዎች ይደራጃሉ፡፡ አደረጃጀቱ (ቡድኑ)   ሴቶችን  ከአባልነት ባለፈ በአመራርም ያሳተፈ አሠራር መከተል አለበት፡፡

ሕብረት ሥራ ማኅበሩ  ዜጎችን የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ጉዳዮችን መነሻ አድርጎ ለይቷል፡፡ የመጀመሪያው  ከተማ አስተዳደሩ በመልካም አስተዳደር የሚነሳበት ቁጥር አንድ  ችግርም የመኖሪያ ቤት እጦት መሆኑን የጽ/ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች፣ የጸጥታ መዋቅር አባላት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች  የገጠማቸውን ከፍተኛ የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት በማሰብ ነው፡፡

ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግም   ሦስት መንገዶች በአማራጭነት መቀመጣቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡  ከእነዚህም ለዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን ሠርቶ መስጠት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡  በጋራ ቤት መገንባት የሚፈልጉ ነዋሪዎች ካሉ ከእጣ ውጭ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይስተናገዳሉ፡፡  ሌላው  አማራጭ ደግሞ ዜጎች ተደራጅተው በተናጠል የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በመውሰድ   ችግሮቻቸውን ይፈታሉ ተብሎ ታስቧል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ከዚህ  በፊት በማኅበር ለተደራጁ ነዋሪዎች  የቤት መሥሪያ ቦታ የተላለፈበት መንገድ ከፍተኛ ችግር እንደነበረበት  አቶ አብርሐም አንስተዋል፡፡ በተለይም በፍቺ እና በተለያዩ  መንገዶች  ከአንድ በላይ ቦታ እንዲሁም  ሌላ ቦታ እየኖሩ በተጭበረበረ መንገድ በተገኘ  ሀሰተኛ  የባሕር ዳር ከተማ መታወቂያ ተደራጅቶ ቦታ የመውሰድ ችግሮች ነበሩ፡፡ ችግሩ ከተቋሙ ይጀምርና ደላሎች ይመሩታል፤ በዚህም ሳያበቃ  ግንኙነቱ እስከ ኅብረተሰቡ እንደሚደርስ ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከንቲባ ኮሚቴ ነዋሪዎች በቤት ማሕበር እንዳይደራጁ ካገደ በኋላ በ2012 እና 2013 ዓ.ም የተደራጁ 25 ሺህ አባላትን የያዙ 936 ማህበር እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው በስድስት መታወቂያ  ስድስት ቦታ ተደራጅቶ መገኘቱ፣ ኑሯቸው እና  ሥራቸው ሌላ አካባቢ ያሉ ዜጎች በመታወቂያቸው ብቻ በመደራጀታቸው…ነው፡፡ አሁን የነበረውን አሠራር ሙሉ ለሙሉ አምክኖ በአዲስ እንዲጀመር መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ግን የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚደረገው  ሂደት በተለይ  ከደላላ ነፃ የሆነ አሠራር ለመከተል ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡  ለዚህም የከተማ ነዋሪው  ማንም የማይገዛው/በሕገወጥ መንገድ የማያገኘው/  አንድ የነዋሪነት መታወቂያ ብቻ እንዲኖረው ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም ጋር ከተማ አስተዳደሩ ውል ይዟል፡፡ ይህም ከመረጃ ክፍተት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ይፈታል ነው የተባለው፡፡

ዋናው ነገር የቤት መሥሪያ ቦታን ለተጠቃሚዎች  ከደላላ ነጻ ማድረግ ስለሆነ ማንኛውም ቤት ፈላጊ ወደ ተቋሙ በመሄድ መስፈርቱን ካሟላ ተቋሙ በተለያየ መንገድ አጣርቶ ይሠጣል፡፡

እንደ አቶ አብርሐም ማብራሪያ ከአሁን በኋላ የማደራጀት ሥራ የሚፈፀመው በከተማው ኅብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት እና ተቋሙ ባደራጀው መንገድ ብቻ ነው፡፡ የቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት  ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ  ባለ  ተቋም የሚሠራ፣ በከተማዋ ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ የኖረ የሚሉትን መስፈርቶች ማሟላት የግድ ይላል፡፡  በባልና ሚስት ቦታ ማግኘት እንደማይቻል በማንሳትም በተጭበረበረ መንገድ ሙከራ ማድረግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ለሚደራጁ እንዲሁም ቦታ ለመስጠት ቅድሚያ የሚሠጠው  የጋብቻ ሰርተፍኬት ላላቸው ይሆናል፤ ላላገቡት እስከ ታች ድረስ ኮሚቴ ተዋቀሮ ቤት ድረስ የሚጣራ እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ምዝገባ የሚካሄደው በተቋም ስለሆነ ተቋሙ ኃላፊነት እንደሚወስድ ይጠበቃል፤ ይሁንና ያገባ፣ ያላገባ.. የሚለውን ተቋሙ ኃላፊነት ከወሰደ በኋላ በሂደትም ይጣራል፡፡ ይህን መመሪያ ተላልፈው  የተገኙ ሰዎች  ግን በፍትሐብሔር እና በወንጀል ይጠየቃሉ፡፡ ካለአግባብ ያገኘው ጥቅምም ይነጠቃል፤ የሰጠው አካልም ይጠየቃል፡፡ ዜጎች ጥቆማ የሚሰጡበት አሠራርም ተዘርግቷል፡፡

እንደ አቶ አብርሐም ገለፃ በ2015 ዓ.ም በሕገወጥ መንገድ ቦታ ከተሠጡት ውስጥ ጽ/ቤቱ ከነዋሪዎች በደረሰው ጥቆማም በባል እና ሚስት መውሰዳቸው  የተረጋገጠ 22 ሰዎች ቦታቸው ተነጥቋል፤ አሁንም ይቀጥላል  ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባው የሚመሩት ኮሚቴ ከተማ አስተዳደሩ ለ500 ማህበራት በአራቱም አቅጣጫ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉ ተገልፆል፡፡

አቶ አብርሐም አያይዘውም ትልልቅ ተቋማት ለአብነት /ፀጥታ፣ ባንክ … / ለሠራተኞቻቸው ቦታ ተቀብለው ቤት ከገነቡ በኋላ በደመወዝ ወ|ይም በብድር ሥርዓት ተጠቃሚ እናደርጋለን ካሉ ቅድሚያ የሚሠጥ መሆኑን ነው የገለፁልን፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here