የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ተረቶች

0
384

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ዐበይት ከሚባሉት ደራሲያን መካከል አንዱ ናቸው:: የመንግሥት ኀላፊነትን ከምሁራዊ  ተግባር ጋር በማዋሐድ ለለውጥ እና ለትውልድ መገልገያ እንዲሆኑ የደረሷቸው  መጽሐፍት ተጠቃሽ ናቸው:: በድርሰታቸውም ሀገራዊ መልእክትን ከእውቀት ጋር ለዛሬው ትውልድ በማበርከት ይታወቃሉ:: ሥራዎቻቸው ዛሬም   ለጥናትና ምርምር መነሻዎች ሆነው ያገለግላሉ::

ጥቅምት 19 ቀን 1897 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከአባታቸው ጸሐፌ  ትእዛዝ ወልደ መስቀል ታሪኩ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ደስታ አየለ ተወለዱ:: የቡልጋ ሊቁ አባታቸው ክቡር ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ መስቀል ታሪኩ  የራስ ዳርጌ ባለሟልና ጸሐፊ ነበሩ:: በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ ጸሐፊ ትዕዛዝነትን ለመሾም በቅተዋል::

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ የታወቁ የሥነ ጽሑፍ ሰው ከመኾናቸው ባሻገር፤ በፈረንሳይ ሀገር የግብርና ትምሕርት አጠናቀዋል። መጀመሪያ የልዑል አልጋወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ፀሐፊ፤ የእርሻ ምክትልና ዋና ሚኒስትር፤ የገንዘብ ሚኒስትር፤ የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትር እንዲሁም የዘውድ አማካሪ በመሆን ሃገራቸውን አገልግለዋል።

በታሪክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚዘክረውን “ዝክረ ነገር” የተሰኘውን መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። እኚህ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው፣ በታሪክና ባህል፣ በትምህርተ ጥበባት እና በመንፈሳዊ ተግባራት አሥራ አምስት መጻሕፍትን ጽፈዋል።

ታሪክና ባህል፣ ዝክረ ነገር፣  ያባቶች ቅርስ፣ እንቅልፍ ለምኔ፣  አማርኛ ቅኔ፣ ስለ ኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት አስተዳደርና ግብር፣ አማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው፣ ያገር ባህል፣ ባለን እንወቅበት፣ የቀድሞው ዘመን ጨዋ ኢትዮጵያዊ ጠባይና ባህል፣ ቼ በለው? ትምሕርተ ጥበባት፣ ጥበበ ገራህት (የእርሻ መሬት ዝግጅት)፣ ብዕለ ገራህት (ከእርሻ የሚገኝ ብልጽግና)፣ አንክሮ ለእግዚአብሔር፤ ተዘክሮ ለነፍስ (መንፈሳዊ)፣ ዕጹብ ድንቅ፣ ስም ከመቃብር በላይ፣ ሰዋስወ ሰማይ የተሰኙት መጽሐፍትም ጸሐፊ ናቸው።

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል “እንቅልፍ ለምኔ” በሚል ርዕስ በ1952ዓ.ም ባዘጋጁት መጽሐፍ ኢትዮጵያዊ ቀደምት ሀገረሰባዊ ሀብቶች የሆኑትን ተረቶችን አሰባስበዋል:: በዚህም ከ48 በላይ ተረቶችን በማስባሰብ ለአንባቢያን አብቅተዋል:: እነዚህ ተረቶች ቀደምቱ አባቶች የነበራቸውን ጥበብ እና ማስተዋል ለዛሬ በማስተላለፍ፤ ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ ሊቀስም የሚገባውን እውቀት የመጠቆም ጉልበት እና ሚና አላቸው:: ከብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ተረቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት።

 

ሁለት ሌቦች

ጓደኛ ሆነው አብረው ሲሰርቁ የሚኖሩ  ሁለት ሌቦች ከዕለታት አንድ ቀን ከመንገድ ዳር ተቀምጠው ሲጨዋወቱ እንድ ባላገር ለግብር ታዝዞ ማር በገንቦ ተሸክሞ ሙክት እየሳበ ሲመጣ አዩት:: በዚህ ጊዜም ባላገሩን ለመንጠቅ ተማከሩ:: አንዱ ሌባ ተነስቶ ጫካ ገባ:: ሁለተኛው ግን እዚያው መንገድ ዳር ዓይነ ስውር መስሎ ጥቅልል አለና ተኛ:: ያ ባላገርም ሙክቱን እየሳበ ማሩን ተሸክሞ አጠገቡ ሲደርስ  ሌባው ተመለከተና “ስለ ቸሩ እግዚአብሔር ብለህ አትለፈኝ፤ የቀን ጨለማ የወረሰኝ ነኝና እየመራኸኝ ሂድ?” ብሎ ለመነው::

እሱም “እኔ ለግብር ቶሎ አድርስ ተብየ ታዝዤ ሙክት እስባለሁ፤ ማር ተሸክሜያለሁ፤ አንተን እንዴት አድርጌ ነው የምይዝህ?” ቢለው አንተ እኔን ከያዥከኝ  የሙክቱን መሳቢያ ገመድ ሰጥተከኝ፤ እኔ እስበዋለሁ አለ::

ሰውየውም የዋህና የእግዚአብሔር ሰው ነበርና  እሺ ብሎ የመሳቢያውን ገመድ  ለዓይነ ስውሩ አስጨብጦ እርሱ ደግሞ የሌባውን እጅ ይዞ ጉዞ ጀመሩ:: ጥቂት ሄደው ጫካ አካባቢ ሲደርሱ የሌባው ጓደኛ ከኋላ ደርሶ መሳቢያውን ገመድ ፈትቶ ሙክቱን ወሰደው:: ሲሄዱ ሲሄዱ ቆይተው ዓይነ ሰውሩ “ወንድሜ ምነው ገመዱ ቀለለብኝ እስቲ ሙክቱን እይልኝ?” አለው:: ያ የዋህ ሰው ወደ ኋላ ዘወር ብሎ  ቢያይ ሙክቱ የለም:: ማሩን ከትክሻው አውርዶ “እንካ  በእጅህ ይዘህ ጠብቅልኝ፤ እኔ ተመልሼ ሙክቴን ልፈልግ” አለውና  ሄደ:: በዚህ ጊዜ ያ ሌባ ደግሞ ማሩን ተሸክሞ እልም አለ:: እነዚህ ሁለት አታላዮች የዋሁን ባላገር ቀምተው ባዶ እጁን ሰደዱት:: ውስጡን ሳታውቅና ጠባዩን  ሳትመረምር  እምነትህን በሰው ላይ አትጣል የሚለው የዚህ ተረት ዋና ማጠንጠናኛ ሐሳብ ነው::

 

ሦስት ቂል ወንድማማቾች

ሦስት ቂል ወንድማማቾች በአንድ ይኖሩ ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን አብረው ሲሄዱ እልም ካለ ገደል አፋፍ ላይ ለሞፈር የሚሆን ዛፍ አገኙና  መቁረጥ ጀመሩ:: ነገር ግን መቁረጫ መሳሪያቸው ያልሰላ በመሆኑ ቢሉት ቢሰሩት የማይወድቅላቸው ሆነ:: አንደኛው ወንድም ተበሳጨና ሁለቱን ወንድሞቹን “እጫፍ ላይ ወጥታችሁ ክበዱት፤ እኔ ከስር ልቁረጥ” አላቸው:: እነሱም  እሺ አሉና መልካም ሐሳብ ነው ብለው ፈጥነው አናቱ ላይ ፊጥ  አሉና እንዲወድቅ ያወዛውዙት ጀመር:: ያም ዛፍ ክርክሩ ጎድቶት ኖሮ ወዲያ ይዟቸው ገደል ገባ:: ቆራጩ ወንድማቸውም ተናዶ “ኧረ ጉድ ሞፈሩን  ይዘውት ጠፉ”  ብሎ በዚያው በገቡበት ተከትሎ ቁልቁል ዘሎ ወረደ:: በዚህም የተነሳ ሦስቱም ሳይተርፉ አለቁ ይባላል:: እምብዛም ቂልነት ያደርሳል ከሞት:: “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እየተባለ የሚተረተው ይህንን የመሰለ ነገር እንዳይደርስ መሆኑን እንገንዘብ ይላሉ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ::

 

የአንድ መሐይም መነኩሴ ጸሎት

አንድ ትምህርት የሌላቸው መነኩሴ በአንድ ሀገር ይኖሩ ነበር:: የዘወትር ጸሎታቸውም “እንደ ሥራው፤ እንደ ሥራው” ማለት ነበር:: በአቅራቢያቸው እጅግ ሀብታም የሆኑ ሦስት ልጆች የወለዱ  ባልና ሚስት ይገኙ ነበር:: ይህ ባለጸጋ የደሀን ርስት በግፍ የሚነጥቅ፤ ከደንብ የወጣ የብር ወለድ የሚቀበል ተበዳሪዎቹን የሚያስርና የሚነጥቅ ጨካኝ ሰው ነበር:: አንድ ቀን ለሞት የሚያደርስ ሕመም ስለገጠመው ሚስቱ እኝህን መነኩሴ “ባሌ እንዲድንልኝ እግዚአብሔርን ለምኑልኝ” አለቻቸው:: እሳቸውም የዘወትር ጸሎታቸው ነውና  “እንደ ሥራው፤ እንደ ሥራው” እያሉ ይጸልዩ ጀመር:: ወዲያው የባሏን ሥራ ታውቃለችና  “ለምንድን ነው እንደ ሥራው  የሚሉት ደህና አድርገው ይለምኑት እንጂ?” አለቻቸው:: መነኩሴው ግን ሌላ ጸሎት አያውቁምና  እንደ ሥራው እያሉ ሲለምኑለት ሕመሙ ጠነከረበትና ሞተ:: በዚህ ጊዜ ሚስቲቱ “እኒህ ደንቆሮ  መነኩሴ እንደ ሥራው እያሉ ባሌን አስገደሉት፤ቆይ እኔም አደርግላቸዋለሁ” ብላ ዘዴ መፈለግ ያዘች:: አስባም አልቀረች:: ጥቂት በጥቂት ምግብ ትልክላቸው ጀመር:: ከዕለታት አንድ ቀን ባሌ የሞተውን ሞት ይሙቱ ብላ በስውር መርዝ የጨመረችበትን ምግብ ላከችላቸው:: እሳቸውም አምጪውን አሽከር “አቁጣሮውን (ጸሎቴን) ስጨርስ እበላዋለሁና በል እዚያ አኑረውና ሂድ” አሉት::

ሦስት የሟች ልጆች ለአደን ወደ በረሐ ወርደው ኖሮ ሲመለሱ በጣም ስለራባቸው የመነኩሴው ቤት መድረሳቸው ነበርና ፈጥነው ከእሳቸው ዘንድ ገብተው “አባታችን ሆይ አጥብቆ ርቦናልና የሚበላ ነገር ያገኙልናልን?” ሲሉ ጠየቋቸው:: መነኩሴውም “እመቤት የላኩልኝ ድርጎየ እነሆ ተቀምጧልና እሱን ተመገቡ” አሏቸው::

ልጆችም ተርበው ስለ ነበር፤  ፈጥነው ወስደው በሉና  ጥቂት ሳይቆዩ ሦስቱም ሞቱ:: ወዲያው ተጮኸና እናታቸው ሰምታ  ሀዘኗ የመረረ፤ ለቅሶዋም የከበደ ሆነ:: በዚህ ጊዜ የልጆች ዘመዶች መነኩሴውን ለመግደል ይጋበዙ ጀመር:: እናታቸው ግን “አትንኳቸው በገዛ ሥራየ ነው” ብላ ከሞት አስተረፈታቸው ይባላል:: ሥራ ለሠሪው፤ እሾህ ለአጣሪው ነው:: ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል የሚለው የተረቱ ሐሳብ ነው::

 

አንድ መንገድ የሄደ ሰው

አንድ ባለ ትዳር ሰው  በአንድ ሀገር ይኖር ነበር:: አንድ ቀን ሚስቱን፣ ልጆቹን እና ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ወደ ሩቅ ሀገር ይሄዳል:: ብዙ ወራትም ካሳለፈ በኋላ ወደ ሀገሩ ይመለሳል:: ቤቱ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜም ከጎረቤቶቹ ጋር ይነጋገር ጀመር::  በዚህ ጊዜ ሦስት ሰዎች ቤቱ ገብተው ከሚስቱ ጋር ይጨዋወቱ ነበርና ድምጹን ሰምተው ደነገጡ:: አንዱ ተንጠላጥሎ ወደ ጣራው ወጥቶ እዋልታው ስር  ከባላው ላይ ተቀመጠ:: ሁለተኛው ሸሽቶ ወደ ጓዳ ገባ:: ሦስተኛው ደግሞ ሮጦ አልጋ ውስጥ ተሸሸገ:: ባለቤቱም ናፍቆ ነበርና ከቤቱ ገብቶ ሚስቱን፣ ልጆቹን እና ቤተሰቦቹን  ሁሉ በሙሉ ስሞ በደህና ስለመግባቱ “አንተ የላይኛው ሁሉንም ታውቃለህ፤ ላንተ ምን ይሰወርሃል” እያለ ፈጣሪውን ሲያመሰግን እባላው ላይ ያለው “ኧረ እኔ ብቻ አይደለሁም” አለ:: ከጓዳ ያለው ደግሞ “ኋላ ማንን ልትጨምር ነው?” ሲል ተናገረ:: አልጋ ውስጥ ገብቶ የተሸሸገው ደግሞ “ያስለፍልፍ ቀምሳችኋል ወንድሞቼ እንደኔ  አስችሏችሁ ዝም ብትሉ ምን ተቸገራችሁና  የቆጥ የባጡን ትለፈልፋላችሁ” ተባብለው ከተሸጎጡበት እና ከተሸሸጉበት  አምልጠው ሄዱ ይባላል:: ጥፋተኛ ማንም ሳይከታተለው በስራው ይሳደዳል::

ብላቴን ጌታ ማኀተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል እንቅልፍ ለምኔ በሚለው መጽሐፋቸው ባሰፈሯቸው ተረቶች በርከት ያሉ ጠቃሚ ምክሮችን አስቀምጠዋል:: አነጋገርን እና አያያዝን ስለ ማሳመር፤ ስለ መተማመን፤ እናት አባትን እና ቤተሰብን ስለ ማክበር፤ በጥበብ እና በማስተዋል ስለ መኖር፤ ክፋት የሰሩት የእጃቸውን እንደሚያገኙ፤ ኀይል እና ጉልበት ከሞት እንደማያድን ሐሳቦችን በተረት በማዋዛት ተርከዋል::

በተጨማሪም የቅናት አደገኛነትን፣ የበዛ የዋህነት የሚያመጣውን ጉዳት፣ ፈጣሪ ለሚያምኑት ያለውን ቀናኢነት፣ ምክርን ስለ መስማት ጥቅም፣ ውለታን ስለማክበር፤ የእውነትን ጉልበት፣ግፍ የሰሩ የእጃቸውን ስለ ማግኘታቸውም ጽፈዋል::

ብላቴን ጌታ ማኀተመ ሥላሴ በጉልበት መታበይ ስለሚያመጣው ጣጣ፣ ጠላትን በቸልታ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን፣ ቅንነት መልሶ ስለ መክፈሉ፣ ትብብር ያለውን ጥቅም፣ የመታገስን ዋጋ፣ ምስጢር መጠበቅ እና ሰው ለሰው ያለውን ጥቅም አንስተዋል::

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here