የብሔራዊ አንድነት አርማ – ሕዳሴ

0
11

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ግንባታው በይፋ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም (በመንግሥት፣ በመላው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን) ርብርብ የተገነባ ነው፤ ይህ የአንድነት አርማ የሆነው ግድብ  ጷጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል፡፡

በዓለም ካሉ 20 ግዙፍ ግድቦች አንዱ እና ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መድረስ ፋይዳው ለአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤቶቻችን በተለይም ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጭምር ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ግድቡ፣ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፤ ግድቡ ባለፉት ዓመታት 74 ትሪሊየን ሌትር ውኃ ይዟል። የግድቡ ርዝመት (ከፍታ) 145 ሜትር እና ወደ ጎን ያለው ርዝመት ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ነው።

ግድቡን በተመለከተ የእንግሊዝ የዜና ማሠራጫ የሆነው ቢቢሲ በግዙፍነቱ በአፍሪካ ቀዳሚ  ነው በማለትም ዘግቧል። የግብፁ አስዋን ግድብ ከሚያመነጨው ኃይል ከእጥፍ በላይ የማመንጨት አቅም እንዳለውም ጠቅሷል። ይህ የሕዳሴ ግድብ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም በመሆኑ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ ያደርጋል ሲልም ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለአየር ንብረት መጠበቅ የሚኖረውን አወንታዊ አስተዋጽኦ አስፍሯል። ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ቦንድ በመግዛት እና በስጦታ መልክ ገንዘብ በማዋጣት መገንባታቸውንም በአድንቆት አስፍሯል።

ላለፉት 14 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል የተደረገበት የኢትዮጵያዊያን አንድነት የታየበት እና የአፍሪካዊያን ጭምር ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መብቃቱ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ብስራት ነው።

የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ሀብት እና ልምድ ያመጣ ፕሮጀክት ነው። ከ14 ዓመታት በኋላ በመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ለስኬት የበቃው ሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ ተብሏል።

በትውልዶች ቅብብል ዕውን የሆነው ሕዳሴ ግድብ ከዚህ እንዲደርስ መላው ኢትዮጵያዊያን ሀብታቸውን እና ላባቸውን አፍስሰውበታል። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ካላት 130 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 60 ሚሊዮኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም፤ የግድቡ ዕውን መሆን ታዲያ በተለይ በጭስ እና በጨለማ ለሚሰቃዩ እናቶች ታላቅ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ቀን ዕውን እንዲሆን በዱር በገደሉ ከአዞ ጋር ታግለው የዓባይን ተፋሰስ ካጠኑ ባለሙያዎች ጀምሮ፣ የጉባን ሀሩር ተቋቁመው ግንባታውን ያሳኩትን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

አመራር ከሰጡ መሪዎች ጀምሮ በየዘርፉ ያለስስት ዕውቀታቸውን እስካበረከቱት ባለሙያዎች ድረስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ለግድቡ ግንባታ ከመቀነታቸው እየፈቱ የለገሱ እናቶች እና አረጋዊያን፣ በሰው አገር እየኖሩ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የታገሉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ሁሉም በየደረጃው የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በሕዳሴ ግድብ ላይ በተፈጠረው ንጋት ሐይቅ ላይ አዳዲስ መርከቦች ወደ ሥራ እንደሚገቡ እና የመርከብ መሠረተ ልማቶችም እየተገነቡ መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ነው። ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ንጋት ሐይቅ በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ነው፡፡ ይህን የውኃ አካል ለትራንስፖርት እና ለሌሎች ጥቅሞች ለማዋል እየተሠራም ነው፡፡

መርከቦቹ ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለሕብረተሰቡ ትራንስፖርት፣ ዓሳ  ለማጥመድ  እንዲሁም ለጎብኚዎች መዝናኛ የሚውሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም፣ በዓሳ እርባታ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፎች አንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መድረስ ለኢትዮጵያዊያን የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የልማትና አካባቢ እንክብካቤ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው ሙሉ ናቸው። ግድቡ ከፍተኛ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው እንዳሉት ግድቡ የሀገራችን የአንድነት ምልክት፣ ትልቅ የሕዝብ መነሳሳትን የፈጠረ፣ ከህፃን እስከ ሽማግሌ፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከተማሪ እስከ ዲያስፖራ፣ ከወታደር እስከ ወዝአደር፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ብሔር፣ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለየው በአንድነት አሻራ ያሳረፈበት ነው። በደለል እንዳይሞላ ታዲያ በበጋው ወራት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሥራት እንዲሁም በክረምት ወራት ደግሞ ተራሮችን በችግኝ መሸፈን ይገባል፤ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንዳብራሩት ዓባይ ጉዞውን ሲጀምር በየዓመቱ ከ10 ሚሊዮን ቶን በላይ አፈር እንዲሁም ማዕድናትን ይዞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይጓዝ ነበር። ይህ ሁሉ ክስተት አሁን ላይ አከተመ ብለዋል። “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለው ታሪክ ማብቃቱን  አስረድተዋል።

ምሁሩ እንዳብራሩት ይህን ግድብ ለመገደብ ሲታቀድ ኢትዮጵያን ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለማውጣት ነው። እጅግ በጣም ከፍተኛ መሰናክሎችን እና ችግሮችን አልፎ ለዚህ የደረሰ መሆኑን አስታውሰው “ኢትዮጵያ ጥበብ በተሞላበት ዲፕሎማሲ ዓባይን ለፍሬ ያበቃች ስኬታማ ሀገር ናት” ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ማብራሪያ 86 በመቶ የዓባይ ድርሻ የኢትዮጵያ ነው፤ ይሁን እንጂ ያለአንዳች ጥቅም ነው ዘመናትን ያሳለፍነው። ግብጽ እና መሰል ሀገራት “ዓባይ ከፈጣሪ የተቸረን የኛ ብቻ ሃብት ነው የሚል አመለካከት ተጸናውቷቸው ኖሯል”ም ብለዋል።

የቀደሙት የግብጽ መሪዎች ማንኛውም የግብጽ ዜጋ 18 ዓመት ከሞላው በኋላ ውትድርና መሠልጠን እንዳለበት ያዝዙ እንደነበር የታሪክ ምሁሩ አውስተዋል። ለሀገር ዳር ድንበር ሳይሆን ለዓባይ መሞት እንዳለባቸው ይነገራቸው እንደነበርም ያስረዳሉ።

የግብጽ እመቤት ሕጻን ወልዳ ጡቷን ስታጠባ “ይህ የማጠባህ በዓባይ አማካኝነት ከፈጣሪ ላንተ የተመደበልህ ትሩፋትህ ነው” እያለች እያጠባች ነው የምታሳድገው ይላሉ። ይህ አመለካከት ደግሞ የኔ ብቻ የሚል ትርክትን ወልዶ እንደኖረ ነው የገለጹት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት፣ በዓሳ እርባታ እና በንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ፍይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል። የዓለም ሀገራት የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ ኢትዮጵያ የምትባለውን የዓባይ (የታላቁ ሕዳሴ ግድብ) ባለቤት ሄደን መጎብኘት አለብን በሚል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

“ግድቡ ከ70 በላይ ደሴቶች ያሉበት ነው። ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚሰደደው ዜጋ በሀገሩ የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት እንዲሠራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ከውጭ የምናስገባቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ዕድል ይሰጣል። ኢትዮጵያ ከሰማይ ውኃ ጠብቃ የምታመርተው ምርት አዋጭ ባለመሆኑ ግድቡ በዓመት አራት ጊዜ እንድናመርት ዕድል የሚሰጥ ነው” ብለዋል። የመስኖ ሥራን እጅግ በዘመነ መንገድ እንድናለማ ያግዛል። ይህም የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ብሎም ለዓለም ምርቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የምናገኝበት ዕድልም ከፍተኛ ነው።

ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት በመሆኑ ሁሉም በነቃ ተሳትፎ እንዳስገነባው ሁሉ ግድቡን የመጠቀም፣ የመንከባከብ እና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በሚሰጠው ጠቀሜታ ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የሀገርን ገቢ ያሳድጋል ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ መሐመድ ለበኩር እንደገለፁት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለዓሳ ሀብት ልማት፣ ለቱሪዝም እና ለሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በብዙ መልክ ያግዛል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለአብነትም በኃይል፣ በምርት አቅርቦት እንዲሁም እንደ ሀገር የኢንቨስትመት ተወዳዳሪነታችንን የማሳደግ ትልቅ አቅም አለው ብለዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ግድቡ የጎረቤት ሀገራትን ከማስተሳሰር ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ከፍተኛ ገቢን ያስገኛል። ይህም በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ  ይኖረዋል። ፋብሪካዎችን እና ኢንዱስትሪዎችን በማንቀሳቀስ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን በማዘመን ከፍተኛ ጥቅምም አለው።

ኢንዱስትሪዎች ከተንቀሳቀሱ ደግሞ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፣ ብዙ ምርት ይመረታል፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ይጨምራሉ። በዚህም የሕዝቡ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል ነው ያሉት።

ከ300 እስከ 400 ዓመታት ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል የተባለው በአፍሪካ ግዙፉን   ግድብ መጠበቅ ደግሞ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ተናግረዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here