የብራዚል የግብርና ስኬት

0
114

የዓለም ባንክ እ.አ.አ በ2024 ባወጣው ሪፖርት ከ217 ሚሊዮን በላይ የሚገመት የሕዝብ ቁጥር አላት። በሕዝብ ብዛቷ ከዓለም  ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች – ብራዚል፡፡

ብራዚል ከስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን  ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋት አላት።  ይህም በዓለም አምስተኛዋ ትልቅ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። ከጠቅላላው  የቆዳ ስፋቷ የግጦሽ መሬትን ጨምሮ አጠቃላይ ለግብርና አገልግሎት የሚውለው  30 በመቶ ይደርሳል።

የሀገሪቱ  የግብርና ዘርፍ ከ1970ዎቹ በፊት የምርት ዕድገትን በሚገቱ በርካታ ከባድ ተግዳሮቶች ሲፈተን ቆይቷል። አብዛኛው የብራዚል የእርሻ መሬት እጅግ በጣም አሲዳማ (acidic) እና ለሰብል ልማት የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች የጎደሉት፣ በየጊዜው ከፍተኛ  የደን ጭፍጨፋ ሚፈፀምበት፣  የአየር ንብረቱም ቢሆን ሞቋታማ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የሀገሪቱ አርሶ አደሮች እና አልሚ ባለሀብቶችም የግብርና ምርትን ማምረት የሚችሉት በሀገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ በሚገኙ ትናንሽ ለም አፈር ባለባቸው ቦታዎች ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። ይህም የሀገሪቱ ዜጎች የምግብ ፍጆታ ለመሸፈን ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሮባት ቆይቷል።

እ.አ.አ በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ሀገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ገጥሟት እንደ ነበርም መረጃዎች አስታውሰዋል።  ይህም የረጅም ጊዜ የግብርና ኢንቨስትመንቶችን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል። መንግሥታት ሲለዋወጡ የግብርና ፖሊሲዎችም ይለዋወጡ ነበር። ይህም በግብርና ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ አልፏል። እነዚህ ፈተናዎች በአንድ ወቅት የብራዚልን የግብርና ምርታማነት ከዓለም አቀፍ ደረጃ በታች አድርገውት ነበር።

በብራዚል የግብርናው ዘርፍ  ከ1970ዎቹ በፊት  ሀገሪቱ የምታመርታቸው ዋና ዋና ምርቶች  በባህላዊ የእርሻ ዘዴዎች፣  በዓለም አቀፍ ፍላጎት… የሚወሰኑ ነበሩ። መሳሪያዊችንም ከሰሜን አሜሪካ እና ከአውሮፓ ታስመጣ ነበር።

ዛሬ ብራዚል በግብርናው ዘርፍ ከአንድ ወቅት ከነበረችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ዓለም አቀፍ ኀያልነት መምጣት ችላለለች፤ ለለውጥ የበቃችውም  በዘረጋችው ዘላቂ የግብርና ፖሊሲዋ ነው።  ሀገሪቱ በግብርና ፖሊሲዋ ቀርጻ ከመሠረተቻቸው ተቋማት ኢምብራፓ የተሰኘው የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን አንዱ ነው።  በ1973 የተቋቋመው ይህ የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን ለሀገሪቱ የግብርና ዕድገት ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ለብራዚል ሞቃታማ  የአየር ንብረት እና የአፈር ሁኔታዎች ተስማሚ የሆኑ የግብርና መፍትሔዎችን በማፍለቅ እና ሀገሪቱ ዛሬ ለደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።  የኢምብራፓ የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን ከፈጠራቸው ትልልቅ ስኬቶች መካከል የሴራዶ (Cerrado) ክልልን ከፍተኛ አሲዳማ አፈርን  ለም እና ለሰብል ተስማሚ ማድረግ ነው።

የምርምር ተቋሙ በሀገሪቱ ሞቃታማ የአየር ንብረት ባለባቸው አካባቢዎች የሚስማሙ የሰብል ዝርያዎችን በቴክኖሎጅ በማበልጸግ ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል። ለአብነትም የአኩሪ አተር፣ የበቆሎና የስንዴ ሰብሎችን  በማሻሻል እና በአካባቢው በማላመድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

የሴራዶ አፈር በተፈጥሮው ከፍተኛ አሲዳማነት ያለውና ለሰብል ልማት የማይመች እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።  የሀገሪቱ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይህንን ችግር ለመፍታት ኖራ (limestone) በመጠቀም የአፈሩን አሲዳማነት ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ይህም ለበርካታ ዓመታት ለልማት ማይውል የነበረው መሬት ለሰብል ልማት እንዲውል አስችሏል። በሀገሪቱ ለእርሻ መሬት መስፋፋት መሠረት ከመጣል ባለፈ  በዓለም ትልቁ የአኩሪ አተር እና የበቆሎ አምራች ሀገር እንድትሆን  ስችሏታል።

ብራዚል በሽታን በቀላሉ መቋቋም የሚችሉ፣ የአካባቢውን የአየር ንብረት የሚላመዱ እንዲሁም ከፍተኛ  ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን በቴክኖሎጅ በማበልጸግ ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ረገድ ለሌሎች ሀገራት ምስሌ በመሆኗም የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ተብላለች።

በምርጥ ዘር ምርምር እና በዘመናዊ የእርሻ አስተዳደር ዘዴዎች መሻሻል ምክንያት፣ አርሶ አደሮች አሁን ላይ  በአንድ የእርሻ መሬት ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ሰብል ማምረት ችለዋል። ለምሳሌ አኩሪ አተር ከተሰበሰበ በኋላ ወዲያውኑ በቆሎ ይመረታል። በመቀጠልም የእንስሳት መኖን ያለማሉ። የብራዚል አርሶ አደሮች በዚህ ሁኔታ ሰብልን አፈራርቀው በማልማታቸው የመሬትን ለምነት መጠበቅ ችለዋል፡፡

ብራዚል በግብርናው ዘርፍ የላቀ ውጤት ካስመዘገበችባቸው መንገዶች ሌላው ዘላቂ የሆነ  መሠረተ ልማትን መዘርጋቷ እና የግብርና ቴክኖሎጅን  ጥቅም ላይ ማዋሏ ነው። ሀገሪቱ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም  ከሰሜን አሜሪካ እና ከአውሮፓ ሀገራት  ጋር ተወዳዳሪ መሆን ችላለች።

የብራዚል መንግሥት ሰፋፊ የመስኖ ግድቦችን እና ማሽኖችን እንዲሁም  መንገድ እና ለግብርናው አጋዥ የሆኑ ሌሎች  መሠረተ ልማቶችን ዘርግታለች። ሁሉም የሀገሪቱ አልሚ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች   ዘመናዊ  የእርሻ  ትራክተር፣ የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር፣ የጸረ ተባይ ኬሚካል መርጫ ማሽኖችንና ሌሎች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጅዎችን በእርሻ ማሳቸው  በስፋት ይጠቀማሉ።

የሀገሪቱ መንግሥትም ለአርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት በማመቻቸት እና የእርሻ ኢንቨስትመንትን በማበረታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫዎታል። ይህም የሀገሪቱ የምርት መጠን  በከፍተኛ ሁኔታ እድገት እንዲያሳይ አስችሏታል።

ብራዚል ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጅን በመጠቀም በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚከሰተውን የምርት ብክነት እና የምርት ጥራት ጉድለት ማስቀረትም ችላለች። አልሚ ባለሀብቶች ዘመናዊ የእርሻ ማረሻ ትራክተሮችን እና የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን እንዲሁም  ዘመናዊ የመስኖ ማሽነሪዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ ማድረጓ የሀገሪቱ የምርት ዕድገት በእጥፍ እንዲጨምር አግዟታል፡፡ በየትኛውም የእርሻ ማሳ ሥራ ላይ የሚገኙ  ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች  በጂፒኤስ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

የብራዚል አርሶ አደሮች የሰብላቸውን ደህንነትና ቁመና  የሚከታተሉት ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች በእግራቸው እየዞሩ አይደለም።

የሀገሪቱ አርሶ አደሮች  የአየር ንብረት ሁኔታን ለመተንበይ፣ የእርሻ መሬታቸውን  ለመቃኘት፣ ሰብሉ  በጸረ ተባይ እንዳይጎዳ  በቀላሉ ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሰብሉን ቁመና ለመገምገም የሚያስችሉ ዘመናዊ ድሮኖችን ይጠቀማሉ።

የብራዚል አልሚ ባለሀብቶች እና አርሶ አደሮች የማዳበሪያ፣ የዘር፣  እና የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ሳይንሱ በሚፈቅደው መጠን እና  በትክክለኛው ቦታ ላይ ብቻ ለመጠቀም የሚያስችሉ  ማሽነሪዎችን ይጠቀማሉ። ከትናንሽ እስከ ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ዘመናዊ የግብርና ግብዓት በአግባቡ መጠቀማቸው ደግሞ በሀገሪቱ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ብራዚል እ.አ.አ በ2024  ብቻ ወደ ውጭ ከላከችው የግብርና ምርቶች 140 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ችላለች። ይህም የሀገሪቱን መሠረተ ልማቶች ለማሻሻል ዕድል ፈጥሯል። አብዛኞቹ ትላልቅ አልሚ ባለሀብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ የግብርና ኩባንያዎች ሆነዋል።

ብራዚል በዓለም ትልቁ የአኩሪ አተር ላኪ እና አምራች ሀገር ሆናለች። ይህ ሰብል ለውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ቁልፍ ከመሆኑም በላይ ለእንስሳት መኖነትም ያገለግላል። በተለይም ከቻይና እና ከሌሎች የኤዥያ ሀገራት  የሚመጣው የግብርና ምርቶች ፍላጎት መጨመር የብራዚልን የውጭ ንግድ  በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። የምርምር ማዕከሉ የአኩሪ አተር፣ በቆሎ እና የከብት ሥጋ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ብራዚልን የዓለም ግብርና ኀያል አደረጋት።

እንደ ዩናይትድ ስቴት ደቨሎፕመንት ኤጀንሲ ዘገባ  ብራዚል ከዓለም ከፍተኛ የምግብ አምራቾች እና ላኪዎች አንዷ ነች። ከአኩሪ አተር በተጨማሪ  ሸንኮራአገዳ፣ ቡና፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝንና ብርቱኳካን በብዛትና በጥራት በየዓመቱ ከሚያመርቱና ወደ ውጭ ከሚላኩ ሀገራት ተጠቃሽ ናት።።

በ2024/2025 በወጣው የሀገሪቱ የግብርና ሪፖርት መሠረት በቆሎ ፣ ሸንኮራአገዳ ፣ቡና ፣ ስንዴ ብርቱካን  እና ሩዝ በማምረት  ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለውጭ ትልካለች፡፡

ከሰብል በተጨማሪ ብራዚል በስጋ ምርት ትታወቃለች፤ የበሬ እና የዶሮ ሥጋ አምራችና ወደ ውጭ ለገበያ ከሚልኩ  ሀገራት መካከል አንዷ  መሆኗንም የሀገሪቱ የስታስቲክስ ኤጀንሲ በሪፖርቱ አመላክቷል።

ግብርናው  ለኢትዮጵያም   ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይነገራል፡፡   ግብርና ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ እድገት ምጣኔ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ የውጭ ምንዛሪ  ማስገኛ ነው።  ከ80 በመቶ በላይ የአገሪቷ ዜጎች የሚተዳደሩበት ግብርና  ዛሬም ድረስ ግን ባህላዊ  የአመራረት ዘዴን በመጠቀሟ  ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል ሲል የዘ ጋርዲያን የደቡብ አፍሪካ ዘጋቢ በሐተታው ጠቅሶታል።

ኢትዮጵያ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና አበባን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ብትገኝም ከዘርፉ በሚገባት ልክ እየተጠቀመች አለመሆኗንም ጠቁሟል፡፡

ግብርና ሚኒሥቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው  መረጃ በኢትዮጵያ ለግብርና አገልግሎት የሚውል 38 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት  እንዳለ አሳውቋል፡፡ ይህም በሚታረስ መሬት ከአፍሪካ 15ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንዳስቻላት አመላክቷል። ይሁን እንጅ የሀገሪቱ አርሶ አደሮች ዛሬም ድረስ የሚያለሙት በእንስሳትና በሰው ኀይል ነው። ዘመኑ ያፈራቸው የግብርና መሳሪያዎችንና የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጅዎችን ባለመጠቀሟም እንደ ሀገር  ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አልተቻለም።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገ  ጥናት እንደሚያመላክተው ከሚታረሰው መሬት 40 ከመቶ አሲዳማ ነው። አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም የተሻለ መፍትሔ ቢሆንም  እንኳ ብዙ ኖራ ገዝቶ ለመጠቀም በአርሶአደሩ አቅም መፍታት አይቻልም ብሏል።፡

ለምግብ ፍጆታ እና ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት የሚውሉ ምርቶችን  ዛሬም ድረስ ከውጭ ሀገር በከፍተኛ ዶላር እያስመጣች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ልክ እንደ ብራዚል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ  ብሎም በኢኮኖሚ የፈረጠመች ሀገር ለመሆን የግብርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የግብርና ፖሊሲዋን መቃኘት፣ የግብርና መካናይዜሽንን በስፋት መጠቀም የምርምር ተቋማትን ማስፋትና ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡

ምንጭ፦ፋራንስ 24፣ ቢቢሲ፣ ቲአርቲ ወርል፣ አልጀዚራ፣ ዓለም ባንክ፣ አግሪ ወርልድ ዲስከቨር፣ ሎዋ ሶያቢን አሶሴሽን፣ የብራዚል ስታስቲክስ ኤጀንሲ( ibge) ፣ዩናይትድ ስቴትስ ደቨሎፕመንት ኤጀንሲ፣ ዳውን ኦን ብራዚል ፋርም፣  የብራዚል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ፣ አፍሪካን ኢኮኖሚ ሪባውንድ፣ ሴንተራል ፎር ስትራቴጅክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ ሌሎችን ተጠቅመናል።

 

መረጃ

የብራዚል ስታትስቲክስ ኤጀንሲ (IBGE) መረጃ እንደሚያመላክተው ብራዚል በዓመት ከ140 እስከ 155 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን አኩሪ አተር ታመርታለች።

በፈረንጆቹ  2023 የምርት ዘመን ብቻ 153 ሚሊዮን ቶን የአኩሪ አተር ምርት ማምረት ችላለች። ከዚህ ውስጥም 102 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑን ወደ ውጭ በመላክ 54 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች። ይህ የአኩሪ አተር ምርት ለሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

 

(ቴውድሮስ ደሴ)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here