መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም
በዓለማችን አዝናኝና አስደሳች ከሚባሉ እንዲሁም በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድም ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል እግር ኳስ ቀዳሚ ነው። ምናልባት እዚህ ጋር የሰዎች የተለያየ ፍላጎትና የየሀገራት ባህልና ወግ ታሳቢ እንዲደረግልኝ እፈልጋለሁ። ወደ እኛ ሀገር እንምጣ እና እግር ኳስን የሚወዱ እና በፍቅር የሚደግፉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ) እና ብሔራዊ ሊግ በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው ።
በከፍተኛ ሊጉ ከሚሳተፉት ክለቦች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ እግር ኳስ ቡድን ‘ብርሃኖቹ’ አንደኛው ነው።ብርሃኖቹ ከተመሰረቱ አራት አስርት ዓመታት ተቆጥሯል ።እድሜ ጠገብ ብንላቸው ያስደፍራል።
አሁን ላይ የደብረ ብርሃን ከተማን ፈጣን እድገት እና የእግር ኳስ ቡድኑ ያለበትን ደረጃ ማነፃፀር ያስቸግር ይሆናል።ለዛም ነው ብርሃኖቹን በኢትዮጽያ ፕርሚዬር ሊግ መመልከት ቅንጦት አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው የሚስተጋቡት። ያም ሆነ ይህ ግን ብርሃኖቹ አሁንም ከፍተኛ ሊግ ላይ ናቸው።
ሰለሞን አየለ የደብረ ብርሃን ከተማ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ናቸው። የዚህ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከአሚኮ ጋር ውይይት አድርገው ነበር።
ያኔ ታዲያ ሁሌም ቢሆን ቢሆንልን እና ቢሳካ ሀሳባችን ፕሪሚየር ሊግ መግባት ነው ብለውን ነበር። በርግጥ ያለበት ላይ መቆየት የሚፈልግ ከፍታን የሚጠየፍ ያለ አይመስለኝም ።በርግጥም ሁሉም የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊዎች ራሳቸውን የፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፎ ላይ ማየት ቀዳሚ ፍላጎታቸው ብሎም እቅዳቸው ነው።
ዋናው ነገር ህልሙ እንዲሳካ ምን ምን ሥራዎች ተሰሩ የሚለው ነው።አሰልጣኙ ታዲያ በዚህ የውድድር ዓመት ከእስከዛሬው የተሻለ ነገር አለ ይላሉ ፤እንዴት?ያልን እንደሆን በገንዘብም ፣በተጨዋቾች ብዛትም፣ በተለይ ልምድ ያላቸው እና ብሄራዊ ቡድን የደረሱ ተጨዋቾች መኖራቸው እና የአሰልጣኝ ቡድኑ መጠናከር የታየባቸው መሆኑ ተመላክቷል። ይሄ መልካም ይሁን እንጂ ብርሃኖቹ ልምምድ የሚሰሩበት ሁነኛ ሜዳ አለመኖር እንደልብ መንቀሳቀሻ የራሳቸው ተሽከርካሪ አለመኖር እና አሁንም ለነሱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ እንደችግር የሚነሳው ነጥብ ነው።
እዚህ ጋር እኔም እማኝነቴን ላሳያችሁ፤ ብርሃኖቹ ልምምድ የሚሰሩበት ሜዳ መቸገራቸውን ማሳያው እንደነገሩ በራሳቸው ወጭ ያስጠረጉት ሜዳ ላይ እንዳይቀር ያህል መንቀሳቀሳቸውን ታዝቤያለሁ። ሜዳ ተብዬው ኳስን እንደፈለጉ ለማንሸራሸር የማይመች፣ ያልተባለውን የሚያደርግ ብሎም ተጨዋቾችን ለጉዳት የሚያጋልጥ ስፍራ ነው።እንደዚህም ሆኖ ልምምዳቸውን በፍቅር ይሰራሉ፤ መናበባቸው፣ ተስፋቸው እና ቆራጥነታቸው አስደናቂ ነው ። ይህ ነገር ከምን የመነጨ ይሆን?
የተሻ ግዛው የብርሃኖቹ አምበል ነው።እንዲህ ይመልሳል “በችግርም ውስጥ ሆነን ክለባችንን ትልቅ ደረጃ ላይ ማየት ፍላጎታችን ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሥነ ልቦና ጥንካሬ እና ጠንካራ ወኔ መታጠቅ ግድ ነው። እኛ ቡድን ላይ ያ ነገር አለ።ያለፈው የውድድር ዓመት (የ2015ቱ መሆኑ ነው) በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ግሩም ነበር ለኛ እሱም ትልቅ ተስፋ የሰጠን ነው “ ብለውናል::
ዘንድሮስ? ብለን ላነሳነው ጥያቄ ደግሞ “በዚህ ዓመትም ጥሩ ነን “የአምበሉ መልስ ነው።
አሰልጣኙ ሰለሞን አየለ “ምናልባት የዚህ የውድድር ዓመት ሲጀመር በጥሎ ማለፍ መሆኑ፣ የቡድኖች ቁጥር መቀነሱ ፣ ቁጥሩ ሲቀንስ ደግሞ ጥራቱ መጨመሩ አይቀርም፣የዝግጅት ጊዜ ማነሱ እና በቂ የወዳጅነት ጨዋታ እድሎችን አለማግኘታችን ፈተና ይሆንብናል“ ብለውኝ ነበር ቆይታችን ያበቃው።
የውድድር ዓመቱ ተጀምሮ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ለመገናኘት በቃን።መቼም የመጀመሪያው ጥያቄዬ እንዴት ነበር ቆይታ? የሚለው እንደሆነ ይጠበቃል።አሰልጣኝ ሰለሞን አየለ ይመልሳሉ:- “እንደጠበቅነው አልነበረም፤ የተሳታፊ ቡድኖች ጥራት አስገራሚ ነው ።ሁሉም በሚገባ ተዘጋጅቷል። እኛ ስንሄድ እንደነገርኩህ ነው የዝግጅት ጊዜ አንሶናል፤ ምርጥ 11 እንኳን ከውድድሩ ላይ ነው ለመምረጥ የተገደድነው፤ ምን ያህል እንደተቸገርን ይሄ ማሳያ ይመስለኛል” ነበር ያሉኝ ።ውጤቱ እንዴት ይታያል? የሚለውን አስከተልኩ፤አሰልጣኙ “የከፋ አይደለም” ሲሉ ጀመሩ፤ “ስንጀምር ተደጋጋሚ የውጤት ማጣት እና የስነ ልቦና ጫና ውስጥ ገብተን ነበር፤ የሚገርምህ ተጨዋቾች ደግሞ ዛሬ ምን ያህል ጎል ይቆጠርብን ይሆን እስከማለት ደርሰው ነበር፤ ግን ፈጣሪ ይመስገን ወዲያው ወደማሸነፍ መጥተናል፤ የደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆነን ነው ያጠናቀቅነው፤እንደ አጀማመራችን ቢሆን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብተን ነበር” ብለውኛል።
አምበሉ የተሻ ግዛው በበኩሉ ከፍተኛ ሊጉ ከፕሪሚየር ሊጉ ባልተናነሰ ፉክክር የሚታይበት ከባድ ሊግ ነው። በመሆኑም በዚህ የውድድር ዓመት እቅዳችን የሚሳካ አይመስለኝም፤ በከፍተኛ ሊጉ ለመቆየት ግን ጠንክረን እንሰራለን፤ ተጨዋቾች ጋር ያለውም ስሜት ይሄው ነው፤ ብሎኛል። ከዚህ ባለፈ ግን የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የደጋፊ ማህበሩ እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ቁርጠኝነት ከመቼውም በላይ መሆን አለበት፤ ያንን ማድረግ ከቻልን ፕሪሚየር ሊግ የማንገባበት ምክንያት የለም ባይ ነው።
አሰልጣኙም ቢሆኑ ውድድሩ እየከበደ ነው፤ ባለፈው ጊዜ በሦስት ምድብ 44 ቡድኖች ነበሩ አሁን ግን በሁለት ምድብ 28 ቡድኖች ናቸው ያሉት፤ ይሄ ፉክክሩን ያጦፈዋል። እናም በዚሁ መቆየት በራሱ ስኬት ነው ይሉና በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከመጀመሪያው በመማር እና ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንሰራለን፤ ከሚመለከታቸውም ጋርም ተነጋግረናል ብለውኛል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት “ክለቡ በከተማችን ብቸኛ ከመሆኑ ባሻገር ከተማዋን በማስተዋወቅ ረገድ አበርክቶው ቀላል አይደለም፤በመሆኑም ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ አበክረን እንሰራለን፤በከተማው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ይገኛሉ፣እነሱን ለልምምድ ምቹ ለማድረግም ይሰራል፤ሌሎች መሰል ችግሮችንም ለመቅረፍ እንሰራለን፤ነገር ግን ከችግሮቹ ብዛት አንጻር እና የስፖርት መሰረተ ልማት ከሚፈልገው መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ አንጻር የሁሉንም ባለድርሻ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” ብለዋል::
ከ1975 ዓም ጀምሮ ነበር የደብረ ብርሃን ከተማ እግር ኳስ ቡድን እንቅስቃሴውን የጀመረው። በአማራ ክልል በሚደረጉ የተለያዩ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳትፎም ነበረው። በ1994 ዓ ም የአማራ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና በመሆን ነው ወደ ብሄራዊ ሊግ አቅንቶ የነበረው። አሁን ደግሞ ከፍተኛ ሊግ፤ ነገ እና በመጪዎቹ ጊዜያት ፕሪሚየር ሊግ ከዚያም ወደ በለጠ የስኬት ጉዞ።የብርሃኖቹ የተስፋ መንገድ የተሻለ ቀና እንዲሆን የኛም ምኞት ነው::
(ዮናስ ታደሰ)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም