ወግ
እንኳን ለአሚኮ 30ኛ ዓመት አደረሰን በማለት ጽሑፌን እጀምራለሁ፤ በ”ስደተኛው ብዕር እና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች” መጽሐፍ አባ ወልዴ ተብለው የተጠቀሱት ገጸ ባሕርይ የዛሬ ሀምሳ ዓመት ገደማ ማንኩሳ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ሰው ናቸው:: እኚህ ሰው በመጽሐፉ ውስጥ አባ ወልዴ ተብለው ይጠቀሱ እንጂ የማንኩሳ ሕዝብ የሚያውቃቸው አባ ረዳቴ በሚለው ስማቸው ነው::
አባ ረዳቴ ዕውቅናን ያተረፉት ብርቄ በተሰኜች ዝነኛ እና ተወዳጅ ሬድዮአቸው ነው:: በዚህ ጽሑፌ ስለ ብርቄ መንገድ ማውራት ስለፈለግሁ ከመጥቀስ ተቆጠብሁ እንጂ አባ ረዳቴ ክራርም ነበራቸው:: ብርቄን እና ክራራቸውን አንግተው አሁን ብር ሸለቆ እየተባለ ወደሚጠራው ያኔ ጥቅጥቅ ጫካ ወደነበረ አካባቢ በመሄድ እንጨት እየለቀሙ እያመጡ በመሸጥ የሚተዳደሩ ታታሪ ሰው ነበሩ::
አባ ረዳቴ እንጨት ለመልቀም ወደ ጫካ የሚሄዱትም ሆነ ማንኩሳ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ብርቄን አንግተው ነው:: ብርቄን አንግተው እንጨት ተሸክመው ከጫካ ሲመጡ እንዲሁም ከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩ ስናያቸው የዚያ ዘመን የማንኩሳ ሕጻናት ዛሬ በያገሩ ተበታትነን የምንገኝ ጎልማሶች እና ሽማግሌዎች ጨዋታችንን እየተውን ግር ብለን እንደ እምቦሳ እየዘለልን ወደ እሳቸው እንሮጥ እንደነበር ትዝ ይለኛል::
እንዲህ እየተሯሯጥን አባ ረዳቴ ካሉበት እንደደረስን “ብርቄን ክፈትልን!…ክፈትልን!…” እያልን እንንጫጫለን:: ትዕግሥታቸው መቼም የሚገርም ነው፤ ያንን ሁሉ ጫጫታ፣ ያንን ሁሉ ጩኸት ችለው “እሽ ልጆቼ! ብርቄ ብዙ የምታስተምረው ነገር አላት” ብለው ይከፍቱልናል:: ያኔ ሬድዮ ይሠራጭ የነበረው ማታ፣ ጧት እና ቀን ለተወሰነ ሰዓት ስለነበር ብርቄ የሥርጭት ሰዓቷ ገና ከሆነ “እሽሽ…” ማለት ትጀምራለች:: ከዚያ የሥርጭት ሰዓቷ ሲደርስ ስታወራ ትቆይና ትዘፍናለች:: ብርቄን ከብበን ቁጭ እንዳልን የምታወራው ምን እንደሆነ ብዙም ባይገባንም አፋችንን ከፍተን፣ ጆሯችንን አቅንተን፣ ዓይናችንን እሷ ላይ ተክለን እናዳምጣታለን:: ቀስ በቀስ ግን አንዳንድ ልጆች ወደ ጨዋታቸው መመለስ ይጀምራሉ:: እኔ ግን ወደ ብርቄ ጠጋ፣ ጠጋ እያልሁ ማዳመጤን እቀጥላለሁ::
ብርቄ ስታወራ ደስ የምትለኝ ቢሆንም ትግርኛ ዘፈኗን ደግሞ ከወሬዋ አስበልጬ ነበር የምወደው፤ የብርቄን መንገድ እንድይዝና በመንገዷ እንድዘልቅ ያደረገኝም ከወሬዋ በይበልጥ ቋንቋውን ባለመቻሌ የተነሳ ትርጉሙን በደንብ የማላውቀው ትግርኛ ዘፈኗ ነው:: አባ ረዳቴ “መሼ” ብለው ከተቀመጡበት ተነስተው ብርቄን አንግተው ወደ ቤታቸው ጉዞ ቢጀምሩ እንኳን በዘፈኗ በጣም ከመሳቤ የተነሳ ከኋላቸው እየተከተልሁ ማዳመጤን እቀጥላለሁ እንጂ ወደ ቤት መሄድ ብሎ ነገር አይነካካኝም፤ እናቴ ወይም አክስቴ መጥተው “መሽቷል” ብለው ተቆጥተው ይዘውኝ ካልሄዱ በቀር::
አባ ረዳቴ በዚያ ዘመን ብርቄን አንግተው በመንቀሳቀስ እንዲሁም ብርቄን በየደረሱበት ከፍተው በማስደመጥ ራድዮን ለማንኩሳ እና አካባቢው ያስተዋወቁ የመጀመሪያው ሰው ይመስሉኛል:: በኋላ ላይ ግን ማንኩሳ ከተማ ውስጥ ራድዮ ወደ ጆሯቸው አስጠግተው የሚያዳምጡ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለት እንደጀመሩ አስታውሳለሁ:: ከአባ ረዳቴ በመቀጠል ማንኩሳ ከተማ ውስጥ ራድዮ ይዘው በመንቀሳቀስ በማዳመጥም ሆነ በማስደመጥ የማንኩሳ አንደኛ ደረጃ መምህራን ተጠቃሾች ናቸው፤ በተለይም የእንግሊዝኛ፣ የግብረ ገብ እንዲሁም የሳይንስ መምህሮቻችን::
ራድዮ ማንኩሳ ከተማ ውስጥ ቀስ በቀስ ቁጥሩ እየጨመረ፣ ብርቄን እየተፎካከረ ሲሄድ እኔም ከራድዮ ራድዮ እያማረጥሁ ጠጋ በማለት ማዳመጤን ቀጠልሁ:: በሬድዮ ፍቅር ወውደቄን ያዩ አንዳንድ ፊደል የቆጠሩ ሰዎች፣ “ይሄ ልጅማ ሲያድግ ጋዜጠኛ ነው የሚሆነው” እያሉ ትንቢት መሰል ነገር ይናገሩ እንደነበርም ትዝ ይለኛል:: እኔ ግን ጋዜጠኛ ምን ማለት እንደሆነ ስለማላውቅ፣ “ጋዜጠኛ አላውቅም፤ እሱ ደሞ ምንድነው?” እያልሁ እጠይቃለሁ::
እነሱም፣ “ጋዜጠኛማ ትምህርታቸውን ጨርሰው እዚህ ራድዮኑ ውስጥ ገብተው የሚናገሩ እና ጋዜጣ በሚባል ወረቀት የሚጽፉ ሰዎች ናቸው” እያሉ ይመልሱልኛል:: በዚህ ጊዜ ‘ጠንክሬ ከተማርሁ ራድዮ ውስጥ ገብቼ መናገር፣ በጋዜጣ መጻፍ እችላለሁ ማለት ነው’ እያልሁ አስብ እንደነበር ትዝ ይለኛል:: በልጅነቴ ይህን ማሰቤ ኋላ ላይ ጋዜጠኛ መሆንን እያለምሁ ትምህርቴን ጠንክሬ እንድማር በእጅጉ ረድቶኛል::
ራድዮ የማዳመጥ ልምድ እያዳበርሁ መሄዴም ሆነ ሳድግ ጋዜጠኛ እሆናለሁ የሚለውን ራዕይ መሰነቄ በእርግጥም መልካም ነገር ነው:: ሆኖም ራድዮ ማዳመጥ አጥብቄ መውደዴን የተረዳ አንዳንድ ሰው፣ “ራድዮ እንድከፍትልህ ይሄን ውሰድልኝ! ያንን አምጣልኝ! እገሊትን ጥራልኝ! ይሄን ገዝተህልኝ ና!…” እያለ ሲያሯሩጠኝ ከዋለ በኋላ ሰበብ እየደረደረ “አልከፍትልህም” ይለኛል:: በዚህ ጊዜ እኔም በልጅነት ልቤ ቂም ቢጤ እየቋጠርሁ፣ “ትምህርቴን ተምሬ ሥራ ስይዝ እኔም ሬድዮ ይኖረኝ ይሆናል” እያልሁ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ::
ራድዮ ይኖረኝ ዘንድ እየተመኜሁ፣ ጋዜጠኛ መሆንንም እያለምሁ ትምህርቴን ስማር ሚኒስትሪን ተፈትኜ በከፍተኛ ውጤት በ1972 ወደ ሰባተኛ ክፍል አለፍሁ:: ሆኖም ያኔ ማንኩሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስተምር የነበረው እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ ስለነበር ትምህርቴን ለመቀጠል ወደ ፍኖተ ሰላም ሄድሁ::
ወደ ፍኖተ ሰላም በሄድሁ በማግስቱ ፖስታ ቤት አካባቢ ስዘዋወር አንድ ሰው ትልቅ ወረቀት ዘርግቶ ሲያነብ አየሁ:: ጠጋ ብየ ወረቀቱን ስመለከት “የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ ዋጋ 15 ሣንቲም” ይላል:: ‘ይሄ ጋዜጣ የሚባለው ወረቀት ነው’ አልሁና ፖስታ ቤት ሄጄ ለሻይ መጠጫ በተሰጠችኝ ሳንቲም ገዝቼ እየገለጥሁ አየሁት:: ከእያንዳንዱ ጽሑፍ ርዕስ ግርጌ የሰው ስም አለ:: ‘ይሄን የጻፈው ይሄ ጋዜጠኛ ነው ማለት ነው፤ ታድሎ!’ አልሁ፤ ራሴ ለራሴ::
ከዚች ዕለት ጀምሮም ራድዮ ከማዳመጥ በተጨማሪ ጋዜጣ እየገዛሁ ማንበብ ጀመርሁ:: ጋዜጣ የማነበው ደግሞ መንገድ ለመንገድ ነበር:: ከትምህርት ቤት እንደወጣሁ ጋዜጣ እገዛና ወደ ቤቴ ለመሄድ ከከተማ ወጣ እንዳልሁ ከዜና ገጽ በመጀመር በራድዮ ሲያነቡ እንደምሰማቸው ጋዜጠኞች ድምጼን ከፍ አድርጌ እስከመጨረሻው ገጽ አነባለሁ፤ ቤት ስደርስም መንገድ ለመንገድ ያነበብሁትን ጋዜጣ ግድግዳ ላይ እለጥፍና እየጮኹ አነበዋለሁ:: ድምጼን ከፍ አድርጌ መንገድ ለመንገድ ሳነብ የሚሰማኝ ሰውም ጤንነቴን በመጠራጠር እየተገላመጠ እያየኝ ይሄዳል:: ቤተሰቦቼም ቢሆኑ ግድግዳ ላይ የለጠፍሁትን ጋዜጣ ሰው በሌለበት እየጮኹ ሳነብ ከደረሱ ይሄን ልጅማ ያ ምናምንቴ ሳይለክፈው አልቀረም እያሉ ይጨነቁ እንደነበር አስታውሳለሁ::
ራድዮ እያዳመጥሁ፣ ጋዜጣ እያነበብሁ፣ ትምህርቴን ስማር ኖሬ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ:: የዩኒቨርሲቲ ትምህቴን በማጠናቀቅም ሥራ ተመደብሁ:: ነገሩ “ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ” እንዲሉ ሆነና በመጀመሪያ ደመወዜ ሬድዮ ገዛሁና “አንድ ቀን ራድዮ ይኖረኝ ይሆናል” የሚለውን የልጅነት ሕልሜን እውን አደረግሁ::
ራድዮ በገዛሁ ባመቱ ለተለያዩ ሬድዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጦች ግጥሞችን እና መጣጥፎችን እያዘጋጀሁ በመላክ መሳተፍ ጀመርሁ፤ ያላንዳች ክፍያ:: ጽሑፎቼ በራድዮ ሲነበቡ ስሰማም ሆነ ታትመው ሳያቸው የሚሰማኝ ደስታ እና የማገኜው የኅሊና እርካታ በገንዘብ የማይተመን ነበር::
ኅዳር 27 ቀን 1984 ዓ.ም. ረፋድ ላይ እንደተለመደው ፖስታ ቤት በመሄድ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣን ገዝቼ ከፖስታ ቤቱ ግቢ ሳልወጣ እየገለጥሁ ርዕስ ርዕሱን ሳነብ ዓይኖቼ፣ “የአጭር ልቦለድ ድርሰት አጻጻፍ” በሚል ርዕስ ላይ አረፉ፤ ከርዕሱ ግርጌ ስሜ ተጠቅሷል:: ዓይኖችህን ክጽሑፉ ከነቀልህ ርዕሱ በርሮ ይጠፋብሀል የተባልሁ ይመስል ርዕሱ ላይ አፍጥጬ ብዙ ቆየሁ:: የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ማስተማሪያ መጻሕፍትን በማጣቀስ ያዘጋጀሁት ጽሑፍ በብዙ ሺህ ቅጂ በሚታተመው እና ባገር አቀፍ ደረጃ ተነባቢ በሆነው የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ወጥቶ ሳየው በደስታ ሰከርሁ:: እግሮቼ እየተራመዱ፣ ዓይኖቼ ጽሑፉ ላይ እንዳረፉ መሥሪያ ቤት ስደርስ ሠራተኞች፣ “የምን ጽሑፍ ነው ይህን ያህል የመሰጠህ?” በማለት ሲከቡኝ “ጽሑፌ ጋዜጣ ላይ ወጣልኝ!” አልኋቸው:: እነሱም ጋዜጣውን ነጠቁኝና እየተሻሙ አነበቡት:: ከዚያ በኋላ ጽሑፎችን ለራድዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ለጋዜጦች መላኬን አጠናክሬ ቀጥያለሁ::
በብዙኃን መገናኛዎቹ ስሜ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የሚያዳምጡም ሆነ ተጽፎ የሚያነቡ ሰዎችም ጋዜጠኛ እመስላቸው ስለነበር ከእናንተ ራድዮ ወይም ጋዜጣ ክፍት ቦታ ካለ ብታስገቡን የሚል ጥያቄ ያቀርቡልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ:: አንዳንዶችም ጽሑፍ ልከው ሳይቀርብላቸው ወይም ሳይታተምላቸው ሲቀር ጽሑፌን የቅርጫት እራት አደረጋችሁት እያሉ ወቀሳ ያቀርቡልኝ ነበር::
የበኲር ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኜ ከመመደቤ ካንድ ዓመት ቀደም ብሎ ያጋጠመኝን ነገር እዚህ ላይ ብጠቅሰው ተገቢ ይመስለኛል:: ሚያዝያ 1987 ዓ. ም. አመሻሽ፤ አሁን “ዘምባባ መናፈሻ” ተብሎ ከተሰየመው የጣና ዳርቻ ቁጭ ብየ በተጠቀሰው ወር እና ዓ.ም. በወጣ የበኲር ጋዜጣ የታተመልኝን መጣጥፍ እያነበብሁ ቁጭ ብያለሁ:: አንዲት በመልክ የማውቃት ወጣት ከእኔ ራቅ ብላ ተቀምጣ በኲርን ታገላብጣለች:: ጋዜጣዋን አገላብጣ አገላብጣ መጨረሻው ገጽ ላይ ስትደርስ ድንገት ተንሰቅስቃ አለቀሰች:: በሁኔታዋ ተደናግጬ፣ “ምን ሆነሽ ነው?!” ስል ጠየቅኋት:: ጋዜጣዋን ባንድ እጇ ይዛ ባንድ እጇ እምባዋን እየጠራረገች፣ “ቆይ ግን ለምንድነው በኲሮች የምልክላቸውን ጽሑፍ የማያወጡልኝ?” በማለት ጠየቀችኝ::
“ለዚህ ነው ያለቀስሽ?” አፌ እንዳመጣልኝ ጠየቅኋት፤ ነገሩን ቀለል አድርጌ በማየት:: “ለእናንተማ ተሳታፊ የሚልከውን ጽሑፍ አይረባም ብሎ ቅርጫት ውስጥ መወርወር ቀላል ነው፤ ለእኛ ተጨንቀን ተጨምቀን ለምንጽፈው ተሳታፊዎች ግን የጽሑፋችን አለመታተም ትልቅ መርዶ ነው” በጥያቄየ ተበሳጭታ መለሰችልኝ፤ እምባ ባዘሉ ዓይኖቿ እያስተዋለችኝ:: ልጅቷ ዘወትር በኲርን ይዤ ስለምታየኝ የዝግጅት ክፍሉ ባልደረባ ሳልመስላት አልቀረሁም:: እናም ‘ምነው እንዳፍሽ ባደረገልኝ’ ስል አሰብሁና፣ “እናቴ እኔ የበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ መስየሽ ከሆነ ተሳስተሻል” አልኋት:: “ጽሑፎችህ በተደጋጋሚ ጋዜጣዋ ላይ ታትመው አያለሁ፤ በዚያ ላይ ሁሌም ጋዜጣዋን ስታነብ ነው የማይህ:: ታዲያ…” ንግግሯን አንጠልጥላ ተወችው::
“ካዘጋጆቹ አንዱ ለመሆን አጥብቄ የምመኝ ሆኖም ምኞቴ እውን ያልሆነ የበኲር ተሳታፊ እና አንባቢ ነኝ” ስል የበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ አለመሆኔን አረጋገጥሁላት:: እሷም በመገረም እያስተዋለችኝ፣ “እንኳን እኛን ተቀብለው ሊቀጥሩን እኛ የምንልክላቸውን ጽሑፎችም ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁዎች አይደሉም፤ የሚቀናቸው ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት መወርወር ነው!” በማለት ምሬት የወለደው አስተያየት ሰነዘረችልኝ:: ልጅቷ አዘጋጆች የተሳታፊዎችን ጽሑፍ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት እንደሚጥሉ ስትገልጽልኝ አባባሏ እውነት አልያም ሀሰት ነው ብየ ለመደምደም የሚያስችለኝ መረጃ አልነበረኝም:: እናም በወቅቱ ላስተያየቷ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መረጥሁ::
በልጅነቴ ራድዮ አጥብቄ መውደዴን ያዩ ሰዎች ስታድግ ጋዜጠኛ ትሆናለህ እንዳሉትም በብርቄ መንገድ ስሄድ ኖሬ ከሀያ አምስት ዓመታት በኋላ ራሴን ከጋዜጠኞች ቤት አግኝቼዋለሁ፤ የበኲር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን:: በዚህ ጊዜ ታዲያ በኲሮች የተሳታፊዎችን ደብዳቤ የሚጥሉበት ቅርጫት እንደሌላቸው አረጋግጫለሁ:: ለሠላሣ ዓመታት አንድ ፈሪም በዚህ ቤት ኖሬያለሁ፤ በደስታ እና በእርካታ!
ክብር እና ምስጋና ለአባ ረዳቴ! (አባትሁን ዘገየ)
በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም