የብዙኃን መገናኛ አጀማመር

0
138

ጋዜጣን፣ ራዲዮን፣ ቴሌቪዥንን  እና ዲጅታል መረጃዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የብዙኃን መገናኛ የኅብረተሰቡ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ናቸው። ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ባህላዊ ክንውኖችን ለዜጎች ያሳውቃሉ፣ ያስተምራሉ፣ አመለካከትን ይቀርጻሉ እንዲሁም ያዝናናሉ። በአጠቃላይ ብዙኃን መገናኛ ማኅበረሰብን  በማሳወቅ፣ የሕዝብ አመለካከትን በመቅረጽ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎቱ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል:: ታዲያ እነዚህን ሁሉ ጥቅም የሚያስገኘው ብዙኃን መገናኛ መቼ ተጀመረ? የሚለውን ማወቅ ተገቢ ነው::

የተለያዩ የመረጃ ምንጮች  እንደሚያሳዩት የብዙኃን መገናኛ ታሪክ ብዙ  ዘመናትን አስቆጥሯል::  ተረትን  ከመንገር እስከ ዘመናዊ ዲጂታል መድረኮች ድረስ ያለውን፣ የማተሚያ ማሽን መፈልሰፍን፣ የራዲዮ እና የቴሌቭዥን መጀመርን እና የበይነ መረብ መምጣትን ጨምሮ ቁልፍ ክንውኖችን ያጠቃልላል::

ስተዲ ስማርተር (studysmarter) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የመጀመሪያዎቹ የብዙኃን መገናኛ  ታሪኮች እና መረጃዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉባቸውን የቃል ወጎችን እና የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን ያካትታሉ። መንገደኞች እና ነጋዴዎችም መልዕክቱን አድራሽ  ነበሩ:: በዋሻ ግድግዳዎች ላይ የተቀረጹ ሥዕሎችም የመገናኛ ዘዴዎች እንደሆኑ መረጃው ያትታል::

ብዙ ጊዜ በቤተ መቅደስ ግድግዳዎች ላይ የሚሳሉ ሥዕሎች መልዕክት አስተላላፊዎች ነበሩ:: ለዚህም አብነት የሚሆኑት የጥንታዊ  ግብጻዊያን ታሪክን መመልከት በቂ ነው። በግድግዳ ላይ የተቀረጹት እነዚህ መልዕክቶች ክንውኖችን በጽሑፍ ለማስፈር እና ባሕላዊ ልማዶችን ለማስተላለፍ ወሳኝ ነበሩ።

በ15ኛው ክፍለ ዘመን በነጋዴዎች  መካከል ይሰራጩ የነበሩ በእጅ የተጻፉ ጋዜጦች ስለተለያዩ ክስተቶች መረጃዎችን የያዙ ነበሩ። እ.አ.አ 1439 የጀርመናዊው  ጆሐንስ ጉተንበርግ (Johannes Gutenberg) የማተሚያ ማሽን ፈጠራ ጋዜጦች በብዛት እንዲመረቱ ፈር ቀዳጅ ነበር። የሕትመት ውጤቶች ወይም ጋዜጦች የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ የብዙኃን መገናኛ አይነት እንደሆኑ ይነገራል::

በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ራዲዮ  እና ቴሌቪዥን  እንደ ቅደም  ተከተላቸው በድምጽ  እና  ምስላዊ  ይዘትን  በማቅረብ በአዲስ የብዙኃን መገናኛ አውታርነት ብቅ አሉ። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ብዙ አድማጮችን እና ተመልካቾችን በማዳረስ መረጃን እና መዝናኛን በቅጽበት ለማሰራጨት ምቹ ሆነዋል። ራዲዮ በመላው ዓለም የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር እና የመዝናኛን ኢንዱስትሪ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ይጠቀሳል::

ጣሊያናዊው የኤሌክትሪክ መሐንዲስ ጉግሊልሞ ማርኮኒ ነበር ራዲዮን የፈለሰፈው:: የማርኮኒ አዲስ ግኝት በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማሕበራዊ እና ባሕላዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ረዥም ርቀት ድረስ መረጃዎችን ለማስተላለፍ አስችሏል:: የመጀመሪያው የራዲዮ ስርጭት የተከናወነውም በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር:: የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ስርጭት ደግሞ እንደ studysmarter.co.uk ድረ ገጽ መረጃ እ.አ.አ በ1927 ነበር የጀመረው:: እ.አ.አ በ1950 አካባቢ ቴሌቪዥን  በዓለም ዙሪያ የተስፋፋበት ጊዜ ነበር::

ሌላው የዲጂታል ዘመን ተብሎ በሚጠራው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ የተጀመረው የበይነ መረብ የብዙኃን መገናኛ ገጽታን ለውጦታል።  በይነ መረቡ በግለሰቦች እና በድርጅቶች ይዘትን መፍጠር እና መጋራትን አመቻችቷል:: ይህም በድረ ገጽ ላይ የሚለቀቁ ዜናዎች ወይም መረጃዎች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል::

ማሕበራዊ ሚዲያ (Social Media) በዓለም ላይ እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከበይነ መረብ መፈጠር ጋር ተያይዞ ነበር የተጀመሩት። ማሕበራዊ ሚዲያዎች በርካታ ሲሆኑ በብዙዎች ዘንድ መወደድን ያተረፉ እና ብዙ ተጠቃሚ ያላቸው ግን ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ፣ ትዊተር (x)፣ ኢንስታግራም፣ ቲክ ቶክ እና ዋትስ አፕ ናቸው::

ፌስ ቡክ (Face book) (እ.አ.አ 2004) በኮሌጅ ማሕበረሰቦች በዋነኛነት በማርክ ዙከርበርግ (Mark Elliot Zuckerberg) ተጀምሮ ወደ ዓለም በመስፋፋት ዛሬ ላይ በጣም ትልቁ የማሕበራዊ መስተጋብር መድረክ ሆኗል።  ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ፌስ ቡክ እ.አ.አ. በ2025 በዓለም ላይ ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን  በላይ ተጠቃሚዎች አሉት። እነዚህ ተጠቃሚዎች በቀን ውስጥ 30 ነጥብ ዘጠኝ ደቂቃ ገጹን በመጠቀም ያሳልፋሉ:: በዚህም አጠቃላይ ከማሕበራዊ መገናኛዎች መካከል 59 ነጥብ በመቶውን ይወስዳል::

በወንድማማቾች ፓቭል እና ኒኮላይ ዱሮቭ እ.አ.አ በ2013 የተጀመረው ቴሌግራም መልዕክትን በከፍተኛ ፍጥነት ያስተላልፋል:: ቴሌግራም በበርካታ ሀገራት ለአብነትም በሕንድ፣ በሩሲያ፣ በብራዚል፣ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያም የፖለቲካ፣ የማሕበራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማጋሪያ በመሆን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቴሌግራም ይጠቀማሉ:: እ.አ.አ. የ2025 የወርልድ ፖፑሌሽ ንሪቪው (worldpopulationreview.com) መረጃ እንደሚያሳየው በአንድ ወር ከ700 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት::

በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር 2005 የተጀመረው ዩቲዩብ (YouTube) በዓለም ላይ ትልቁ የቪዲዮ ማጋሪያ አውታር ነው። ግሎባል ሚዲያ ኢንሳይት (globalmediainsight.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በዓለም ላይ ከሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ በላይ ሰዎች ዩቲዩብ ይጠቀማሉ::

ዲማንድ ሳጌ (demandsage.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው አሁን ላይ ኤክስ /X/ በሚባል የሚታወቀው ትዊተር (Twitter) እ.አ.አ በ2006 የተፈጠረ ሲሆን ፈጣን መልዕክት እና የዜና ማስተላለፊያ የማሕበራዊ ሚዲያ መተገብሪያ መሳሪያ ነው:: እ.አ.አ. 2025 በየቀኑ 245 ሚሊዮን፣ በወር ውስጥ ደግሞ 611 ሚሊዮን ሰዎች ሳያቋርጡ ትዊተርን በአሁኑ ስያሜው ደግሞ  ኤክስ /X/  ይጠቀማሉ::

በየቀኑ 500 ሚሊዮን እና በአንድ ወር ውስጥ  ሁለት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ደግሞ እ.አ.አ በ2010 የተጀመረው ኢንስታግራም  (Instagram) ነው:: ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን የሚጋሩበት እና የሚያጋሩበት የማሕበራዊ መተግበሪያ ሥርዓት ነው::

በቻይና እ.አ.አ በ2016 የተጀመረው ቲክ ቶክ “tikTok” ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በፍጥነት በርካቶች የሚጠቀሙበት አዲስ ማሕበራዊ መድረክ ሆኗል። በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው ቲክቶክ በዓለም አቀፍ  ደረጃ በአንድ ወር ውስጥ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ሰዎች ይጠቀሙበታል:: 148 ሚሊዮን ዜጎቿ ቲክቶክን በመጠቀማቸው አሜሪካ ከዓለም ሀገራት በቲክቶክ ቀዳሚ ናት::

በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ2009 የተጀመረው ዋትስ አፕ (WhatsApp) በአንድ ወር ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ሰዎች ይጠቀሙታል:: በጽሑፍ መረጃን ያለዋውጥ የነበረው ዋትስ አፕ በአሁኑ ጊዜ በድምጽ እና በምስል (በቪዲዮ) ጭምር መረጃዎችን እያደረሰ ይገኛል:: ሁለት ነጥብ ዘጠኝ የሚደርሱ ሰዎችም ተጠቃሚዎች አሉት::

በአፍሪካ ውስጥ የብዙኃን መገናኛ  እድገትን በምናይበት ጊዜም   ታሪክ በቅድመ-ቅኝ ግዛት፣ በቅኝ ግዛት እና በድህረ-ቅኝ ግዛት በሚል ተከፋፍሎ የሚታይ ነው።

አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት በፊት፣ በቅኝ ግዛት ዘመን እና ከቅኝ ግዛት በኋላም ቢሆን እንደ መገናኛ መንገዶች የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች (ሚዲያዎች) አሏቸው። ለአብነትም ከበሮ፣ ደወል እና ቀንዶች በብዙ አፍሪካዊያን ዘንድ መረጃን ለብዙኃኑ ለማሰራጨት  ይጠቀሙባቸው ነበር።

ቅኝ ገዢዎች አምባገነናዊ የፕሬስ ጽንሰ-ሀሳብን በማስተዋወቅ እና የሀገር በቀል ፕሬስ እድገትን በመገደብ በአፍሪካ አህጉር የሚዲያ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ኒያምጆህ የተባለ ጸሐፊ (እ.አ.አ.2005) እንዳብራራው በአፍሪካ የመጀመሪያ ተብለው ለሕትመት የበቁ ጋዜጦች የሚባሉት እ.አ.አ በ1797 በግብፅ፣ በ1800 በደቡብ አፍሪካ፣ በ1801 በሴራሊዮን እና በ1826 በላይቤሪያ የታተሙ ጋዜጣዎች ናቸው::

በድህረ-ቅኝ ግዛት ዘመን፣ በአፍሪካ የብዙኃን መገናኛዎች   በቴሌኮሙኒኬሽን  በተለይም በሞባይል ስልኮች እና በበይነ መረብ መሻሻሎች ምክንያት በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የኢንተርኔት፣ የማሕበራዊ ሚዲያ እና የሞባይል ቴክኖሎጂ መፈጠር አፍሪካዊያን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ በጣም ብዙ የሚዲያ ምንጮችን እና ይዘቶችን የማግኘት ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ራዲዮ በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ተመልካች ስለሚደርስ የአፍሪካ “የልብ ምት” ተብሎ ሲነገርለት መቆየቱን እንዲሁም ዜናዎችን እና ትምህርታዊ ይዘቶችን በማቅረብ እና ማሕበራዊ ትስስርን በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫዎቱን ወርድ ፕረስ ድረገጽ (wordpress.com) ላይ ያገኘነው መረጃ  ያስረዳል::

ወደ ሀገራችን ስንመጣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጋዜጣ አዕምሮ የሚባል ሲሆን መታተም የጀመረው ጥር 17 ቀን 1901 ዓ.ም መሆኑን ጋዜጠኛ መዝሙር ሃዋዝ የብዙኃን መገናኛ እድገት በኢትዮጵያ በሚል ካሳተመው  መጽሐፉ መረዳት ይቻላል:: በወቅቱም ለቤተ መንግሥት ባለሟሎች ይከፋፈል ነበር:: ከዛ በፊት ግን ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን መለከት በመንፋት፣ ዜና መዋሎችን በማዘጋጀት መረጃን ያስተላለፉ ነበር::

በኢትዮጵያ ቋንቋ እና ጽሕፈት ባልዳበረበት በጥንት ጊዜ መረጃዎችን በስዕል፣ በምልክት እና በመሳሰሉት ዘዴዎች ይተላለፉ እንደ ነበርም በባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር አየለ አዲስ (ዶ/ር) በ academia.edu ላይ ያሰፈረው ጽሑፍ ያትታል:: ጋዜጠኛ አየለ አዲስ እንደዳሰሰው ዘመናዊ የብዙኃን መገናኛ  ከመፈጠሩ በፊት ለሕዝብ መረጃ የሚደርሰው በዘፈን፣ በግጥም እና በሥነ ቃል  ነበር:: በወቅቱ ወሬውን ለማሕበረሰቡ የሚያጋሩት ደግሞ አዝማሪዎች እና እረኞች ነበሩ:: ነጋሪት እና ጥሩንባም የብዙኃን መገናኛ መሳሪያዎች ሆነው አገልግለዋል::

የኢትዮጵያ ራዲዮ ስርጭት የጀመረው በ1928 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ንግግር እንደሆነ ጋዜጠኛ መዝሙር ሃዋዝ ከትቧል:: የራዲዮ ጣቢያው የመጀመሪያ ጋዜጠኛም ክቡር ከበደ ሚካኤል ነበሩ:: በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ በርካታ ክልላዊ የራዲዮ እና የኤፍ.ኤም ጣቢያዎች ተስፋፍተው ይገኛሉ::

በአፍሪካ ቀደም ብላ የቴሌቪዥን ቴክኖሎጂን ያስገባችው ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ላይ የማሳወቅ፣ የማስተማርና የማዝናናት ዓላማን አንግቦ በ1957 ዓ.ም ሥራውን መጀመሩን የኢቲቪ የሃምሳኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ከተሠራ ዘገባ ማወቅ ይቻላል::

የሙከራ ስርጭቱን የጀመረው ግን በ1948 ዓ.ም በእንግሊዙ የቴሌቪዥን ኩባንያ ቢቢሲ በመታገዝ የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የንግሥና በዓል በሚከበርበት ወቅት ነበር:: በአሁኑ ወቅት እንደ ክልላዊ ራዲዮ ስርጭቶች ሁሉ በኢትዮጵያ በርካታ ክልላዊ እና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተቋቁመዋል::

ከተመሠረተበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች፣ ዜናዎችን፣ ፕሮግራሞችን እና መጣጥፎችን እያደረሰ የሚገኘው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የተደራሽነት ሽፋኑን በማሳደግ ላይ ይገኛል።

በበኵር ጋዜጣ የተጀመረው የ30 ዓመታት ጉዞውም በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በኤፍ ኤም፣ በአራት ጋዜጣ እና በዲጂታል ሚዲያ አድማሱን በማስፋት ግዙፍ የብዙኃን መገናኛ ለመሆን ችሏል። አሁን ላይ ሁለት የውጭ ቋንቋዎችን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጠው አሚኮ ለክልሉ ብሔረሰቦችም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ለኽምጣና፣ ለአዊኛ እና ለኦሮሞ ብሔረሰብ ቋንቋዎችም የቴሌቪዥን፣ የራዲዮ፣ የጋዜጣ እና የዲጂታል ሚዲያ ሽፋን በመስጠት መረጃ በሰፊው እያደረሰ ይገኛል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የነሐሴ 19  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here