የብዙኃን እጆች ለለውጥ

0
161

በባሕር ዳር ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ አንዳርጌ ደጉ መንገድ ላይ በየጊዜው በዘፈቀደ የሚደረጉ እና በጊዜ የማይነሱ የግንባታ እቃዎች  ያለከልካይ ተበትነው በመገኘታቸው በመንገዱ ለመንቀሳቀስ ችግር እንደፈጠረ እና በግል አንሱ  ተብለው ሲጠየቁ ደግሞ ወደ ጠብ እየሄዱ መቸገራቸውን ይገልፃሉ፡፡ ግንባታው እየተካሄደ ከሆነ እና ቶሎ ቶሎ ከተነሳ ቅሬታ የማይፈጥር ቢሆንም አብዛኛው የግንባታ አሸዋ፣ ጠጠር እና ድንጋይ ለረዥም ጊዜ የሕዝብ መገልገያ መንገዶችን እየዘጉ መቸገራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በግል ሄደው ግለሰቦች እንዲያነሱ ሲጠይቁ እንደምቀኛ መታየት እና መሰደብ እንዳለ የገለፁት አቶ አንዳርጌ ቶሎ ቶሎ ሠርቶ እንደማንሳት ሰዎችን እንደ ክፉ አመለኛ ቆጥሮ መጣላት እየሰለቸው እየተቸገረ ያለ ነዋሪ ብዙ ነው ይላሉ፡፡

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወ/ሮ የሰሩ ዮሃንስ መንገዶች ላይ የግንባታ  ዕቃዎች በነጻነት ልጆቻቸው በሰፈር ወጥተው እንደልባቸው እንዳይጫወቱ አድርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዕቃዎቹ መንገዱን ስለሚይዙ በልጆቻቸው ላይ የትራፊክ አደጋ ይደርስባቸዋል የሚል ስጋት በማሳደሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአምስት ወር በፊት ልጅ መውለዳቸውን የሚገልፁት ወይዘሮዋ ከሰፈሩ መንገዱን ግማሽ የያዘ አሸዋ በመኖሩ ረጅም መንገድ በምጥ እየተሰቃዩ በእግር ለመጓዝ መገደዳቸውን አንስተው የመንገድ መሰረተ ልማት በተዘረጋበት አካባቢ በቸልተኞች ምክንያት ለችግር እንኳን አምቡላንስ መግባት አለመቻሉ እንዳሳዘናቸው ይገልፃሉ፡፡

የቀበሌ 11 ነዋሪዋ ወ/ሮ ነፃነት ስማቸው በበኩላቸው መኪና ይዘው ወጥተው ሲመለሱ፣ ቀድሞ ሔደውበት የሚያውቁት ሰፈር፣ ዋናው አስፓልት … ሳይቀር ሲሄዱ መንገዱ በጠጠር ተዘግቶ ሲዞሩ መዋል እየተለመደ መጥቷል ይላሉ፡፡

በየመንገዱ የሚቀመጠው አሸዋ በጊዜ ብዛት ሳር ሲያበቅል መንገዱን የሠራው አካል ዝም ማለቱ ይገርማል ያሉት ወ/ሮ ነፃነት  የመፋሰሻ ቦታዎችንም ዘግቶ በጎርፍ መቸገር እና እንስሳት በየአሸዋው እየተፀዳዱ ለበሽታ መዳረግ ሰፋ ሲል ደግሞ የተከመረውን ጠጠር፣ አሸዋ፣ ድንጋይ እየሸሹ ለመኪና አደጋ መጋለጥ፣ ሌላም ሌላም … ችግሩ ተዘርዝሮ የማያልቅ  ነው ብለዋል፡፡

ሌላው በሕዝብ በእግረኛ መንገድ የሚደረግ ንግድ እና በየሰፈሩ ባሉ መንገዶች እና አስፓልቶች የግንባታ ተረፈ ግብዓቶችን ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ የማህበረሰቡን  በመንገድ የመገልገል መብት መንፈግ በመሆኑ የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊመለከተው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር  ህንፃ ሹም  ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጄ ንጉሴ የቢሮው ሥራ ዲዛይን ማፅደቅ እና በፀደቀው ዲዛይን መሠራቱን መከታተል እና ቁጥጥር ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን የህንፃ  ዲዛይን በሚፀድቅበት ወቅት በራሳቸው ቦታ ላይ ማስቀመጫ የተወሰነ ቦታ መኖሩን አይቶ ነው የሚፈቀደው፡፡ ይሁን እንጂ ተረፈ ግብዓት ብቻ ሳይሆን ከዛ ውጭም ህንፃ ሳይሠራ ሲያስቀምጡ ይስተዋላል፡፡

ይህንን ተከታትሎ ደንብ ማስከበር ሥራው በምክር ቤት ፀድቆ ለደንብ ማስከበር ስለተሰጠ አስገዳጅ ሕግ የለም፤ ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጥቶ የተሠራ ሃብት ሲወድም ዝም ላለማለት በትብብር እንሠራለን፡፡ ምክንያቱም “ፈቃድ የሠጠነው ሕንፃው እንዲሠራ እንጂ ተረፈ ግብዓቱን መንገድ ላይ እንዲያስቀምጥ ስላልሆነ” ነው ያሉት አቶ ደረጀ፤  ሰዎች ገንብተው ከጨረሱ በኋላ ትርፍ ምርታቸውን አንሱ ሲባሉ በተደጋጋሚ ተነግሮ አላነሳም በማለት የሚያመላልሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለሚካኤል አርአያ ከራሳቸው ቦታ ውጭ በሕዝብ እና በመንግሥት ቦታ አሸዋ፣ ብሎኬት፣ ብረት፣ እንጨት እና ጠጠር የሚያስቀምጡ ሰዎች መኖራቸውን ይናገራሉ፤ በግንባታ ሰበብ ቢሆንም አሸዋው ወደ አፈር እስኪለወጥ ድረስ ተቀምጦ ለመንገድ መሰናክል ይሆናል፡፡ በ2013 ዓ.ም ተሻሽሎ በፀደቀው ደንብ እና ተግባር አንዱ

ካለው ወቅታዊ ችግር አንፃር ዝም ብለን ያሳለፍነው አለ፡፡ ማሕበረሰቡ ራሱ እንደ መብቱ ነው የሚቆጥረው፤ በደንቡ እንሥራ ከተባለ መንገድ ላይ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ጠጠር፣ አሸዋ ፣ ድንጋይ እና ብሎኬት ማከማቸት ወይም መነገድ የመጀመሪያ ቅጣት 15 ሺህ ብር፣ ተነግሮት እንቢ የሚል ከሆነ ሁለተኛ ቅጣት 30 ሺህ ብር፣ ቀጥሎ ደግሞ 45 ሺህ ብር፣ መጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ንብረቱ እደሚወረስ በ2013 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀውን ደንብ እና ተግባር ዋቢ አድርገው አብራርተዋል፡፡

“ቅጣት ብዙ ሰዎች ይቀጣሉ፤ ለምሳሌ ፓፒረስ ጎን ስድስት ጭነት (ቢያጆ) አሸዋ፣ ሁለት ጭነት (ቢያጆ) ድንጋይ፣ አንድ ጭነት ጠጠር ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚገመት ወርሰን ግለሰቡንም በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡ ሕግ የሚቀመጠው ሰው እንዲያከብረው ቢሆንም ሰው ሕጉንም እያከበረ አይደለም፤ በቅጣቱም አልተማረም” ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለሚካኤል እንደሚሉት “ከተማዋ የራሱ መኖሪያ መሆኗን ብዙ ነዋሪ እየዘነጋ ነው፤ ዲች ቦይ ላይ ሽንትቤት ቀላቅሎ የሚለቅ፣ ቆሻሻ በየቦታው የሚጥል፣ የበረንዳ ቅጥያ (ሕገ ወጥ ማስፋፋት) የሚያደርግ፣ የአማራ እሴት ባልሆነ መልኩ በእግረኛ እና ዋናውን መንገድ ዘግቶ ቀኑን ሙሉ መጠጥ ቁጭ ብሎ ሲጠጡ መዋል ችግር አለ፡፡ ቀበሌ 04 እና 14 በተደጋጋሚ ግሮሰሪዎችን ቀጥተናል፤ መስተካከል ባለመቻሉ ቀጣይ እርምጃችን የሚሆነው ከንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር ተነጋግሮ ማሸግ ነው” ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

“ቅጣቱን ተለማምዶ በማን አለብኝነት ሲያጠፋ ህብረተሰቡ ደግሞ ‘ተው ሠርተው ይኑሩበት’ እያለ ለሥራ የሄደውን ባለሙያ መከራውን ይበላል” ይላሉ አቶ ኃይለሚካኤል፡፡

“እንደ ቢሮ ቁርጥ ያለ አቋም ይዞ አለመሥራቱ አንዱ ችግር ነው፡፡ የሠሩት ባለሙያዎች ግን ተደብድበዋል፡፡ መንገድ፣ የከተማ ውበት እና ፅዳት ሥራ  በባለሙያ ጥረት ብቻ የሚመጣ ነገር ባለመሆኑ ይህንን አውቆ አጥፊው ከድርጊቱ ሊቆጠብ እና ማሕበረሰቡም ሊያግዝ ይገባል” ብለዋል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here