ቤት ለቤት በመዞር በር እያንኳኩ አካል ጉዳተኛ ታዳጊዎችን መልምለዋል፤ ብዙ አካል ጉዳተኞች ስፖርቱን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆነዋል፤ በፓራለምፒክ ስፖርት በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ መድረኮች የተሳተፉ በርካታ አትሌቶችን አፍርተዋል፤ በርካታ የፓራለምፒክ ስፖርተኞችን በማብቃት ለሀገራችን የተለያዩ ክለቦች አበርክተዋል፤ ለስፖርቱ ፍላጎት ያላቸውን አካል ጉዳተኞች ፍላጎታቸውን እና ችሎታቸውን መሰረት በማድረግ ባለፉት 12 ዓመታት አሰልጥነዋል- አሰልጣኝ ጋሹ ይስማው።
የፓራለምፒክ ስፖርት አሰልጣኙ ጋሹ ይስማው በጎጃም አገው ምድር ኮሶበር ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። ለአትሌቲክስ ስፖርት ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር በ1970 ዓ.ም የአትሌቲክስ ስፖርትን ጀምረዋል። እስከ 190ዎቹ መጀመሪያ ድረስም በተለያዩ የአማራ ክልል እና ሀገር አቀፍ መድረኮች በሩጫ ተሳትፈዋል። በእነዚህ የተለያዩ መድረኮችም በተደጋጋሚ በማሸነፍ እና ውጤት በማምጣት ክልሉን አስጠርተዋል።
በ1991 ዓ.ም በሥራ ምክንያት ከደብረ ማርቆስ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የአሰልጣኝነት ሥራ መጀመራቸውን ከአሚኮ በኲር ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። በ2004 ዓ.ም ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በወቅቱ ወደ ነበረው የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች እና ባህል ስፖርት መምሪያ ተዘዋውረዋል። የወጣቶች እና ስፖርት መምሪያን ከተቀላቀሉ በኋላም ፓራለምፒክ ስፖርት እንዲያሰለጥኑ መደረጋቸውን ያስታውሳሉ። ምንም እንኳ ሥራው ቀላል ባይሆንም በደስታ መቀበላቸውን ያስታውሱታሉ። ሥራውን በጀመሩበት ማግስትም በዘርፉ ውጤታማ ሥራ መሥራት ጀምረዋል።
በወቅቱ ማኅበረሰቡ አካል ጉዳተኞችን ወደ ስፖርቱ የማምጣት ችግር ስለነበረበት የፓራለምፒክ አሰልጣኙ ነበር ቤት ለቤት በመዞር እና በር በማንኳኳት ስፖርተኞችን የሚመለምሉ። በተለይ መስማት የተሳናቸው ልጆች ስፖርቱን እንዲቀላቀሉ አጼ ሰርጸ ድንግል እና ሽምብራ ትምህርት ቤቶችን ብዙ ደጅ ጠንተዋል።
በቤት ውስጥ የተደበቁትንም ቢሆን ከወላጆቻቸው ጋር በመነጋገር ወደ ስፖርቱ ለማምጣት ጥረት አድርገዋል። ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በሊስትሮነት፣ በሎተሪ አዟሪነት እና መሰል የቀን ሥራዎች የተሰማሩ አካል ጉዳተኞችንም በስፖርቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተቻላቸውን አድርገዋል።
ይህ ጥረት በመጨረሻ የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ እና ግንዛቤ መሻሻል እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል። ከዐስር ዓመታት በፊት በዚህ መንገድ የፓራለምፒክ ስፖርተኞችን ለማምጣት ጥረት ያደረጉት አሰልጣኝ ጋሹ አሁን ላይ በአንፃራዊ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችም ለፓራለምፒክ ስፖርት ያላቸው ፍላጉት ማደጉን ይናገራሉ። ይህ በመሆኑም በርካታ ወላጆች፤ አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን አሰልጣኙ ቤት ድረስ ይዘው ማምጣት ችለዋል። ታዲያ ይህ ለውጥ እና መሻሻል በዘርፉ ስኬታማ ሥራ እንዲሠሩ አስችሏቸዋል፡፡
ባለፉት 24 ዓመታትም በአትሌቲክሱ እና በፓራለምፒክ ስፖርት በርካታ አትሌቶችን አፍርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረታቸውን በፓራለምፒክ ስፖርት ላይ በማድረግ አስደናቂ ሥራ ሠርተዋል፤ አሁንም እየሠሩ ይገኛሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የተለያዩ ውድድሮች በተደጋጋሚ በማሸነፍ እና ውጤት በማምጣት አማራ ክልልን አስጠርተዋል።
የእጅ እና እግር ጉዳት ያለባቸውን፣ መስማት የተሳናቸውን እና ዐይነ ስውራን ስፖርተኞችን በመም እና በሜዳ ተግባራት በዋናነት የሚያሰለጥኑ ቢሆንም ጎን ለጎን መደበኛ አትሌቶችንም ያሰለጥናሉ። ከፓራለምፒክ ስፖርተኞች ጋር እየሰለጠኑ የሚገኙት መደበኛ አትሌቶች ለፓራለምፒክ አትሌቶች አሯሯጭ (peace makers) ሆኖው ጭምር እንደሚያገለግሉ ነው አሰልጣኝ ጋሹ የነገሩን። በመም ከመቶ ሜትር እስክ አንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት ስልጠና የሚሰጥባቸው ርቀቶች ናቸው። አሎሎ ውርወራ፣ መዶሻ ውርወራ፣ ዲስከስ ውርወራ እና ጦር ውርወራ ደግሞ በሜዳ ተግባራት አሰልጣኙ ስልጠና የሚሰጥባቸው የስፖርት ዓይነቶች ናቸው።
አሰልጣኙ በፓራለምፒክ አሰልጣኝነት ህይወታቸው 22 አትሌቶችን ለሀገራችን ክለቦች ያበረከቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ዐስሩ በተለያዩ የአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ስኬታማ ሆነዋል። ወርቁ፣ ፀጋዬ፣ የፀዳው እና የመሳሰሉት በአሰልጣኝ ጋሹ ይስማው ጎልብተው የሀገራችንን ስም ካስጠሩ የፓራለምፒክ ስፖርተኞች መካከል ይጠቀሳሉ።
የፓራለምፒክ አሰልጣኙ በዘርፉ ማሰልጠን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች በሀገር አቀፍ በተደረጉ ውድድሮች 15 ጊዜ በበላይነት አጠናቀዋል። ስድስት ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ሲጨርሱ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት። በሀገር አቀፍ ደረጃም ስኬታማ ከሚባሉ የፓራለምፒክ አሰልጣኞች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ይቀመጣሉ። በአትሌቲክሱ ዘርፍ ደግሞ አዳዲስ ተተኪ የፕሮጀክት አሰልጣኞችንም ያፈሩ ሲሆን ይመር ተቀባ፣ ዮሐንስ ምህረት እና አማረ ሙጬ ከአሰልጣኝ ጋሹ ዕውቀት ሸምተው ወደ አሰልጣኝነት የመጡ ለአብነት የሚጠቀሱት ናቸው።
የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የሆኑት አሰልጣኝ አማረ ሙጬ ከፓራለምፒክ ስፖርት አሰልጣኙ ጋር የተገናኙት በ1994 ዓ.ም መሆኑን ያስታውሳሉ። በወቅቱም የትሌቲክስ ስፖርቱን በመቀላቀል ሯጭ የሆኑት፤ በአሰልጣኝ ጋሹ ይስማው አማካኝነት እንደነበረ ይናገራሉ። “ከልምምድ በኋላ ለበርካታ አትሌቶች አምባሻ እና ወተት በመግዛት ያበረታታን ነበር፤ በርካታ ወጣቶች ስፖርቱን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል” ይላሉ አሰልጣኝ አማረ።
ለስፖርቱ ያደሩ፣ ታታሪ፣ እና ለሥራቸው ያላቸው ፍላጎት እና ፍቅር ለወጣት አሰልጣኞች አሪያ እንደሚሆኑ ምስክርነታቸውን ሰተዋል። ለራሳቸው እና ለግል ህይወታቸው ሳይጨነቁ ሥራቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ህይወታቸውን ለፓራለምፒክ ስፖርት የሰጡ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል- አሰልጣኝ አማረ ሙጬ። የፓራለምፒክ አሰልጣኝ ጋሹ፤ ክፍያው እና ሽልማቱ የአዕምሮ እርካታ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለአራት ዓመታት አብረዋቸው በፓራለምፒክ አሰልጣኘነት ያገለገሉት፤ ብርሃኑ ምናለ በመሰላቸት ሥራቸውን ሲያቆሙ፤ ለዘርፉ ጥልቅ ፍቅር እና ፍላጎት ያላቸው አሰልጣኝ ጋሹ ግን ዛሬ ድረስ ለብዙ አካል ጉዳተኞች በባሕር ዳር ከተማ ብቸኛው የስፖርት መንገድ ሆነዋል።
ይሁን እንጂ ተገቢውን እውቅና እና ክብር ግን አላገኙም። በጡረታ ብቻ የሚተዳደሩት አሰልጣኙ እርሳቸው በዘርፉ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ሌሎች ባለሙያዎች እርሳቸውን ተክተው እንዳይቀላቀሉ አድርጓል።
ችግሩን ለመቅረፍም የሚመለከታቸው የመንግሥት እና የግል ተቋማት የፓራለምፒክ ስፖርትን መደገፍ ይኖርባቸዋል፤ ልክ እንደ ሌሎች ስፖርቶች ትኩረት ተሰቶት መሥራትም ይኖርበታል፤ የሚል አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።
በዕድሜ ማምሻ ላይ የሚገኙት አሰልጣኙ ዛሬም የማይደበዝዝ ተስፋ እና ዕቅድ አላቸው። ምንም እንኳ እርሳቸው በስፖርቱ ተጠቃሚ ባይሆኑም የፓራለምፒክ ስፖርተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። እናም በቀጣይ የተሻለ ሥራ በመሥራት በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚታዩ ስፖርተኞችን ለማፍራት አልመዋል። ልክ እንደ ሌሎች የስፖርት ዘርፎች የፓራለምፒክ የስፖርት ዘርፍም ተጠቃሚ እንዲሆን ተግተው ለመሥራት አቅደዋል።
አሰልጣኝ ጋሹ አሁን ላይም 30 አትሌቶችን እና 42 የፓራለምፒክ ሰልጣኞችን በመያዝ በአፄ ቴዎድሮስ ስቴዲየም እያሰለጠኑ ይገኛሉ።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም