በዓየር ንብረት ቀውስ የሚደርሰውን ተፅእኖ መቀነስ ወደሚያስችል ከብክለት የፀዳ የኃይል አማራጭ ለመሸጋገር የሚደረግ የማእድን ቁፋሮ የብዝሃ – ሕይወት ውድመትን ሳያስከትል ሊሠራ እንደሚገባ ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በእንግሊዝ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው ከብክለት ወደ ፀዳ የኃይል ምንጭ መሸጋገር ግድ መሆኑ ታምኖበታል:: ሆኖም ሽግግሩን እውን ለማድረግ መሥሪያ የሆኑት መሰረታዊ ቁሶች ሊቲዬም እና ኮባልትን የመሣሰሉ ማዕድናትን ለማውጣት የሚደረገው ቁፋሮ በቀጣናው የሚገኝ ብዝሃ ሕይወት ላይ ውድመት እንደሚያደርስ ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል::
በአዲስ መልኩ በተካሄደ ጥናት እና ምርምር ከአራት ሺህ የሚበልጡ አከርካሪ ያላቸው የዓእዋፍ እና የዓሣ ዝርያዎች የመጥፋት ስጋት እንዳዣበበባቸው ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል- ተመራማሪዎቹ:: በተጨማሪም ስጋቱ በማዕድን ማውጫው ቦታ ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ያብራሩት ተመራማሪዎቹ ርቀው የሚኖሩ ዝርያዎችም የጉዳቱ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት:: ለዚህ ደግሞ በተበከሉ የውኃ መፋሰሻዎች፣ በሚሠሩ አዳዲስ መዳረሻ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የደን መጨፍጨፍ አይቀሬ መሆኑን ነው በትኩረት ያነሱት::
ከማእድን ማውጣት ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን የብዝሃ – ሕይወት ውድመት ለመቀነስ መንግሥታት እና የማእድን ኢንዱስትሪው በቅንጅት ተናበው መሥራት እንደሚገባቸውም ነው የጠቆሙት – ተመራማሪዎቹ::
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ መሪ ተመራማሪው ኘሮፌሰር ዴቪድ ኤድዋርድ በዓየር ንብረት ብክለት የሚደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ ከብክለት የፀዳ ኃይል ማምረት አማራጭ የሌለው መሆኑን አስምረውበታል::
ይህንኑ እውን ለማድረግም የማእድን ፍለጋው በርካታ ብዝኃ ሕይወት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ጉዳት ያደርሳል:: ሆኖም የጉዳቱን ደረጃ መቀነስ ወይም ማመናመን ተገቢና ግድ መሆኑን ነው በአፅንኦት ያሳሰቡት::
ተመራማሪው እንዳመላከቱት በማዕድን ቁፋሮ ምክንያት ዓሣዎች፣ ተሳቢ እንስሳት፣ አእዋፍ ከሁሉም በላይ በአነስተኛ ክልል ብቻ የሚገኙ ዝርያዎች በከፍተኛ ደረጃ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው:: ለዚህም ወደ ሌላ አካባቢ ፈልሰው መኖር አለመቻላቸውን ነው በምክንያትነት የጠቀሱት::
ሌላው በአብነት ከተጠቀሱ እውነታዎች ማዕድን ለማውጣት የሚደረግ ቁፋሮ ከወንዞች ወይም ከውኃ መስመሮች ጋር ተገናኝቶ ረዢም ርቀት ተጉዞ ሰፊ ስነ ምህዳር ሊበክል መቻሉ ከፍተኛ ስጋት መሆኑ ነው በማደማደሚያነት ያስፈሩት – ተመራማሪዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም