የቦሊውድ ኮከብ

0
116

የሕንዱ ፊልም ኢንዱስትሪ ቦሊውድ በዓለም ከሚገኙት ሦስት ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ ነው። አሜሪካ ሆሊውድ፣ ናይጀሪያ ኖሊውድ፣ ሕንድ ደግሞ ቦሊውድ አላት።

የሕንድ ቦሊውድ በዓለም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ የፊልም አምራች ድርጅቶች መካከል ብዙ በማምረት እና በእድገቱ የአሜሪካው ሆሊውድን ይበልጠዋል።

ቦሊውድ በዘመድ አዝማድ ተዋናዮችን ይመለምላል፣ ፊልም ሰሪዎች በቤተሰብ እና በትውውቅ ነው የተሰባሰቡት የሚል ክስ ይቀርብበታል። ከዚህ ስብስብ ውጪ የሆኑ ሰዎች ቦሊውድ ውስጥ ፊልም መስራት እንዳማራቸው የሚቀሩ ናቸው።

ይህንን ለዓመታት ስር የሰደደ ሐሜት እና መጥፎ ልምምድ በችሎታቸው ሰብረው ገብተው ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የፈጠሩ ፊልም ተዋናዮች አሉ። ሻሩካ ካህን፣ አክሻይ ኩመር፣ ፕሪያንካ ቾፕራ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።

ዛሬ “የቦሊውድ ኮከብ፣ የፍቅር ንጉሥ”  እያሉ ሕንዶች ስለሚያወድሱት ተወዳጅ የፊልም ሰው ሻሩካ ካህን ላስነብባችሁ ነው።

ከሕንዷ ኒው ደልሒ ከተማ ጎዳናዎች እስከ ተወዳጁ የፊልም ኢንዱስትሪ ቦሊውድ  ያደረገው አስገራሚ ጉዞ ለብዙዎች መነሳሳትን የሚፈጥር ነው። መልከ መልካም፣ ፈገግታው ደስ የሚያሰኝ፣ ቁመናው ሎጋ ነው። ብዙ አድናቂዎች በፍቅር የወደቁለት፣ ለዓመታት ፊልም አፍቃሪዎች  ልብ ውስጥ ያለ ተወዳጅ የፊልም  ተዋናይ ነው። ጨዋ እና በስነ ምግባሩ የተወደደ ነው ይባልለታል። “ኮከብ እም ከዋክብት ይሄይስ ክብሩ” እንደሚባለው የህንዱ ኮከብ ከሌሎች ከዋክብት በልጦ የተገኘበት የራሱ መንገድ አለው። ዝና እና ክብሩን የጠበቀበት፣ ያስቀጠለበት ምስጢር አለው። ብዙዎችን በስራ እና በክብር በልጦ በመገኘቱ በልዩነቱ እንድናነሳው አድርጎናል።

ዜ ዘስት ድረገጽ የዚህን ዝነኛ ተዋናይ ታሪክ ሲጽፍ ከዝናው በስተጀርባ ያለፈበት መስመር አባጣ እና ጎርባጣ የበዛበት ነበር፤ ዝነኛ የመሆን ጉዞው ሕመም እና ስቃይ ነበረው ሲል ጽፏል።

ከሕንድ የነጻነት ታጋይ አባቱ ሚር ታጅ ሙሀመድ ካህን እና እናቱ ላቴፍ ፋጡማ ሕዳር ሁለት ቀን 1965  እ.አ.አ ተወልዷል። ልጅነቱን በተወለደባት ኒው ደልሒ አሳልፏል።  በኒው ደልሒ ትምህርቱን ሲከታተል በቴያትር፣ ሙዚቃ፣ ስፖርት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጎበዝ ተሳታፊም ነበር። ለዚህ ጉብዝናውም የክብር ኒሻን ተሸልሟል። በኮሌጅ  ቆይታውም ሃንሲራጅ ኮሌጅ ገብቶ በኢኮኖሚክስ ዲግሪ ተመርቋል።

በሕንድ በወቅቱ ዝነኛ የፊልም ተዋናይ እና አዘጋጅ የነበሩትን ዲሊፕ ኩመር እና አሚታባ ባቻቻን ከልቡ ያደንቃቸው ነበር። በኮሌጅ ቆይታውም በቴያትር ቡድን ውስጥ በቴያትር እና ትወና ላይ ይሳተፍ ነበር። በሒደትም ወደ ሐገሪቱ የድራማ ትምህርት ቤት ተቀላቀለ። የቴሌቪዥን ድራማዎችን እና ቴያትሮችን በመስራት ራሱን ከጥበብ ጋር አላመደ።

የምንጊዜም ዘናጩ ተዋናይ በሚል አድናቆት፣ ፍቅር እና ሙገሳ ያስገኙለትን ከ80 በላይ ፊልሞች ሰርቷል። ከዚህ ዝና በፊት አነሳሱ ምቹ አልነበረም። ገና በለጋ እድሜው እናቱን በማጣቱ በሕይወቱ ከባዱን ስቃይ የተሞላበት ሕይወት አልፏል። በሕንድ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች እንደመወለዱ የገንዘብ ችግርን እየተሰቃየበት አልፏል።

ከዚህ ችግር ወጥቶ ግን ሚሊዮኖች የሚቀኑበትን የተመቻቸ ሕይወት መኖር ችሏል። ድንቅ የትወና ብቃት ነበረው። ብዙዎች ግን በቀላሉ አምነው ጎልቶ የሚወጣበትን የድራማ ሚና አልሰጡትም። ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ፊልም ለመስራት ተንከራቷል።

ወደ ሙምባይ ባቀናበት ጊዜ ፈላጊዎች ዓይን ውስጥ መግባት ቻለ። አትችልም ያሉት ራሱን በማብቃቱ ተቀብለውታል። ዝቅ አድርገው የተመለከቱት ከፍ አድርገውታል። የዛሬው ኮከብ ድንገት አልወጣም። ዓመታትን ማለፍ ነበረበት።

ጊዜው እ.አ.አ  1988 ነበር። ወጣቱ ሻሩክ 23 ዓመቱ ነበር። በጊዜው ዲል ዳሪያ በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፈ። ፋውጂ እና ሰርከስ በተሰኙት ድራማዎችም ከሁለት ዓመታት በኋላ ሰርቷል። እነዚህ ድራማዎች የሻሩክን የዝና መንገድ የጠረጉለት እና ዓይን ውስጥ ያስገቡት ሆኑ። በፊልሞች ውስጥ መሳተፍም ጀመረ።

ዋግል ኪ ዱኒያ እና ዩሚድ በተሰኙት ፊልሞች ላይ መስራቱ የፊልም አዘጋጆችን ቀልብ እንዲስብ አድርጎታል።  ሻሩክ በፊልሞቹ ሲተውንም ይሁን ሲጫዎት በልጅነቱ የሚያደንቀውን ዲሊፕ ኩመርን መምሰሉ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ አደረገው።

በእነዚህ ስራዎቹ ረክቶ መቆም አልቻለም። የፊልም አምሮቱን የሚያጣጥምበት ሁነኛ ስፍራ ይቀረዋል። የሕንድ መልክ የሆነው ቦሊውድ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ መቀላቀል ይፈልግ ነበር። ቀደም ሲል የሰራቸው ፊልሞች እርሾ ሆነውት ለታላቅ ኢንዱስትሪ ተዋናይ ለመሆን በቃ። እ.አ.አ በ1992 ሻሩክ ቦሊውድ ውስጥ ገብቶ የመጀመሪያውን ዴዋና የተሰኘ ፊልም ሰራ። ዲሊፕ አሻና ሄ ቀጣዩ ፊልሙ ሆነ። ከዓመት በኋላ የሰራው ባዚጋር ፊልም የቦሊውድን የደረጃ ሰንጠረዥ በሁለተኛነት የመራበት ሆነለት። በዴዋና ፊልም የዓመቱ ምርጥ ጀማሪ ተዋናይ በሚል ርዕስ አሸናፊ ሆነ።

የሻሩክ ፊልም ስራዎች በቦሊውድ ውስጥ በትወና እና ተወዳጅነት ታሪክ እየጻፈባቸው ያለፈባቸው ናቸው። የምንጊዜም አቅሙ ታይቶባቸዋል ሲል ኢንዲያ ታይምስ  አጃም እና ካቢ ሃን ካቢ ና የተሰኙትን ይጠቅስለታል። እነዚህ ፊልሞች የዝና እና ተወዳጅነት ጎርፍ ያጎረፉለት ነበሩ። ምርጥ ተዋናይ በሚልም ተሸልሞባቸዋል። በመቀጠልም ዲልዋል ዱልሃኒያ፣ የስ ቦስ፣ ኩቹ ኩቹ ሆታሄ፣ ፓርደስ፣  ዲልቶ ፓጋል ሄ  ፊልሞች በዝናው ላይ ዝና የደራረቡለት ነበሩ። ቻክ ዲ ኢንዲያ፣ ማይ ኔም ኢዝ ካህን፣ ስዋድስ፣ ዲር ዘንደጊ፣ ዴቭዳስ፣ ድል ሲ፣ ሜን ሆን ና እና ሌሎችም ተወዳጅ ፊልሞች ይጠቀሱለታል።

የዝና ዘመን አብሮ የሚቀጥል አልሆነም። ሻሩክ እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ የጤና ችግሮች እና ከፊልም ውጪ ሌሎች ጉዳዮች በተጠበቀው ልክ እንዳይቀጥል አድርገውታል። የቦክስ ኦፊስ የደረጃ ሰንጠረዥን በፊልሞቹ ይሞላል ቢባልም የሻሩክ ትኩረት ግን ሌላ ሆነ። ዱፕሊኬት፣ አሶካ፣ ባድሻ ፊልሞች በዚህ በቀዘቀዘው የዝናው ዘመን ተሰርተው ለዕይታ የበቁ ፊልሞች ናቸው።

በዚህ ዘመን ድሪምስ አን ሊሚትድ የተሰኘ የፊልም ማምረቻ ኩባንያ መስርቷል። ይህም ድርጅት ያን ያህል ውጤታማ አልነበረም።

ሻሩክ የሕንድ ጀግና ተዋናይ ነው። በየዓመቱ ልደቱን ለማክበር ቤቱ በመቶዎች አድናቂዎች የሚጨናነቅበት ዝናን ይዟል። ባለቤቱ ጋውሪ ካህን ጋር በመሆን ከዚህ ቀደም የመሰረተውን የድሪምዝ አን ሊሚትድ ኩባንያ ወደ ሬድ ቺልስ ኢንተርቴመንት ቀይሮታል። በዚህ ድርጅት ሜን ሆን ና  እና  ቬር ዛራ እና ሌሎችም ተሰርተው ለገበያ ቀርበዋል።

በሻሩክ የትወና ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቀዳሚ ፊልም ስዋድስ የተሰኘው ነው። በሕንድ ፊልሞች ታሪክ በናሳ ግቢ ውስጥ የተቀረጸ የመጀመሪያው ፊልም ነው። በድሮው ልክ ባይሆንም በቅርብ ዓመታትም ፊልሞችን ሰርቷል። ዶን 2፣ ሃፒ ኒው ይር፣ ቻናይ ኤክስፕረስ፣ ማይ ኔም ኢዝ ካህን፣ ዲል ዋል፣ ጃብ ታክ ሄይ ጃን ፊልሞች የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡለት ፊልሞች ናቸው።

የ59 ዓመቱ የቦሊውድ ፊልም ኮከብ በምርጥ ባህሪው፣ በመልካም ሰብዕናው እና ጎበዝ የትወና አቅሙ እንደተወደደ ቀጥሏል። ዝና ይዟቸው የሚመጡ የሕይወት ቀውሶች አልነኩትም። በውዝግብ እና ብጥብጥ፣ በማጭበርበር ወይም ዝናን ለጥፋት በመጠቀም አንድም ቀን ስሙ ተጠቅሶ አያውቅም። ሰውነቱ ዛሬም ጠንካራ፣ ጎረምሳ እና አማላይ ወጣት እንደመሰለ ቀጥሏል። ክብሩን፣ ሰውነቱን እና ዝናውን በሚገባ ጠብቋል።

ኢንዲያን ኤክስፕረስ በሕንድ በተያዘው የፈረጆች 2025 ዓመት ምርጥ አስር ሀብታም ተዋናዮችን ዘርዝሯል። በዚህም መሰረት የሕንድ ቀዳሚ የዘርፉ ሀብታም አርቲስት ሻሩካ ነው። ገንዘቡን የሰራው በትወና ብቻ አይደለም። ይልቁንስ ብዙ የሀብት ማግኛ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ነው እንጂ ይላል የመረጃ ምንጩ። በሕንድ እና በሌሎች አካባቢዎች ሪል ስቴት ያለማል። የፊልም አምራች ኩባንያም አለው።እነዚህ ተግባራት  የሀብት መጠኑን ጨምረውለታል። በኢንስታግራም 47 ሚሊዮን፣ በኤክስ 44 ሚሊዮን፣ በፌስቡክ 43 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። እነዚህ ኩባንያዎች በሚሰራቸው ማስታወቂያዎች ጠርቀም  ያለ ገንዘብ ይከፍሉታል።

ብሉምበርግ በዘገባው በዓለም ቀዳሚ ባለጸጋ አርቲስቶችን ዘርዝሯል። ታይለር ፔሪ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር፣ ኮሜዲያን ጄሪ ሴንፊልድ አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ዲዋይን ጆንሰን 890 ሚሊዮን ዶላር፣ ሻሩካ ካህን 870 ሚሊዮን ዶላር ሀብት አላቸው በማለት የሕንዱን ኮከብ በአምስተኛ ደረጃ አስቀምጦታል።

ሻሩክ በፊልም ስራዎቹ 14 ያህል ሽልማቶችን አግኝቷል። ከእነዚህ ሽልማቶች መካከል ስምንት ያህል ምርጥ ተዋናይ በሚል ዘርፍ የተሸለመባቸው ናቸው።  የሕንድን ዓለም አቀፍ ፊልም ሽልማት አግኝቷል። ዘጠኝ የስታር  የስክሪን ሽልማቶች፣ 3 የቦሊውድ ሽልማቶችን፣ 8 የ ዘ ሲን ሽልማቶችን እና 2 የግሎባል ኢንዲያን ፊልም ሽልማት አግኝቷል። የፈረንሳይ መንግሥትም የክብር ሽልማት አበርክቶለታል። ባሉት አድናቂዎች ብዛት፣ በገቢ፣ ዝናን ጠብቆ በመቀጠል በዓለም ከተሳካላቸው ምርጥ ፊልም ሰሪዎች መሐል ይጠቀሳል።

ዓለም አቀፉ ዝነኛ የፊልም ሰው የረጂም ጊዜ ፍቅረኛውን በ1991 እ.አ.አ አግብቷል። ሦስት ልጆችንም ወልደዋል። አርያን እና አብራም ወንዶች ናቸው። ሱሃና ደግሞ ሴት ልጃቸው ናት። ቤተሰቡ የሂንዱዝም እና እስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።

“ስኬት ገንዘብ መስራት ሳይሆን ልዩነት መፍጠር ነው” የሚለው ሻሩክ የእናቱ ሞት ዛሬም በውስጥ አሉ። ስሞት ሄጄ አገኛታለሁ ይላል። እናቱ ስኬቱን ባለማየቷ በጣም ይቆጫል። ይህ ኮከብ አምስት ዓመታትን አያቱ ጋር ነበር ያደገው። “ሀብታም ሳትሆን አትፈላሰፍ” የሚለው ሻሩክ “ጠንክረህ አጥና፣ ጠንክረህ ስራ፣ ጠንክረህ ተጫዎት። በሕጎች አትታጠር፤ ማንንም አትጉዳ፤ እናም የሌላ ሰውን ሕልም አትኑር” በሚለው አባባሉ ይታወቃል። በልጅነቱ ወታደር የመሆን ምኞት ነበረው። ተሰጥዖን ከተግባር ጋር አቆራኝቶ ዛሬ ቢሊዮኖች ልብ ውስጥ አለ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here