በአማራ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል። ለዚህም በርካታ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ለመኸሩ የሚሆን ሰባት ሚሊዮን 70 ሺህ 759 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ አገልግሎት ላይ ውሏል። 309 ሺህ 109 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ እንደዋለ መረጃው አክሏል።
በምርት ዘመኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። አገልግሎት ላይ ከዋሉ ቴክኖሎጂዎች መካከልም ሁለት ሺህ 122 የእርሻ ትራክተሮች፣ 54 ኮምባይነሮች (የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች)፣ አራት ሺህ 184 የበቆሎ መፈልፈያ እና 232 ሁለገብ (በቆሎን እና ሌሎች ሰብሎችን) ለመፈልፈል የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል።
በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ገብስ፣ አተር፣ ሩዝ፣ ቦሎቄ፣ ሰሊጥ እና ሌሎች በክልሉ በመኸር ወቅት የተሸፈኑ ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች ናቸው። በክልሉ ያለው የሰብል ቁመናም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እንደሆነም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ከሀገሪቱ ለእርሻ ከሚውለው መሬት 35 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው። ምቹ የአየር ንብረት እና ተፈጥሮ የቸረችው የለም መሬት ባለፀጋም እንደሆነ ይነገርለታል። ይሁን እንጂ በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቀው እና ለሀገሪቱ ብሎም ለውጭ ገበያ የተትረፈረፈ ምርት የማቅረብ እምቅ ፀጋ ያለው አማራ ክልል በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች ዘርፉ ክፉኛ እየተጎዳ ነው፡፡
ግጭቱ ለአርሶ አደሩ ፈተና መሆኑ አይዘነጋም። ሆኖም ግጭቱን ተቋቁሞ እያመረተ ይገኛል። አርሶ አደሩ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት በስጋት ውስጥ ሆኖ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞ እና ኮትኩቶ… ለፍሬ ያደረሰውን ሰብል አጭዶ እየከመረ እንዲሁም ወቅቶ ወደ ቤቱ ማስገባት መጀመሩን በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መረጃዎችን በስልክ አጋርተውናል። አርሶ አደሮቹ እንደነገሩን ሲወጡ ሲወርዱ የከረሙበትን አዝመራ ሰብስበው ወደ ጎተራ ለማስገባት ሩጫ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል እስከ 35 በመቶ የምርት ብክነት እንደሚከሰት መረጃዎች ያመላክታሉ፤ አርሶ አደሮች ለምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ብዙ ገንዘብ አውጥተው እንዲሁም ደክመው እና ለፍተው ያመረቱትን ሰብል ብክነት እንዳይገጥመው በወቅቱ እና በጥንቃቄ መሰብሰብ እንዳለባቸው ነው ባለሙያዎች ምክረ ሀሳባቸውን የሚያቀርቡት። በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የምርት ብክነት እና የጥራት ጉድለት እንዳይከሰት ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም እና በተቀናጀ የሰው ኃይል (በደቦ) በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል። እንዲሁም ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጥኖ መሰብሰብ ይገባል። ሌላው የደረሱ ሰብሎችን በዘመቻ እና በትኩረት በመሰብሰብ ዝናብ ከማያገኝበት ቦታ ማስቀመጥ፣ መቼ እንደሚታጨዱ እና የመድረቅ መጠናቸውን መለየት፣ ከታጨደ በኋላ በደንብ እንዲደርቁ ማገላበጥ፣ የሚከመርበት ቦታ ደረቅ መሆኑን መለየት፣ በእንጨት ርብራብ ሠርቶ መከመር፣ የአይጥ መንጋ እንዳይበላው ከቁጥቋጦ እና ከጫካ አካባቢ ማራቅ ከዚያም ፈጥኖ በደረቅ ወቅቶ ወደ ጎተራ እና ቤት በማስገባት ምርትን ከብክነት መታደግ ይቻላል።
የደረሱ ሰብሎችን አጭደው እንደከመሩ እና ፈጥነው ወቅተው ወደ ቤት ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በስልክ ለበኩር ጋዜጣ ሀሳባቸውን ካደረሱን አርሶ አደሮች መካከል የደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አደለኝ እሸቴ አንዱ ናቸው። በምርት ዘመኑ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ግብዓት አግኝተው ማሳቸውን በሰብል ሸፍነዋል። የተሻለ ምርት ለማግኘት እና ጊዚያቸውን ለመቆጠብ የእርሻ ትራክተር እንደተጠቀሙም ነግረውናል።
በዚህ ወቅት የደረሰ የሩዝ ሰብላቸውን የሰበሰቡት አርሶ አደር አደለኝ የሰበሰቡትን የሩዝ ሰብል ብክነት እንዳይደርስበት በጥንቃቄ ከምረው እየጠበቁ መሆኑን አክለዋል። ከመኸሩ ባሻገር በበጋ መስኖ እንደሚያለሙ አስረድተዋል። የሰበሰቡትን አንድ ሄክታር የሩዝ ማሳ ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ ስንዴ እና አጃ ለመዝራት መሬታቸውን አርሰው አለስልሰዋል። በቀጣይ ጊዚያትም የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በወቅቱ ለማከናወን እንዳቀዱ ነው የነገሩን።
ሌላው ሀሳባቸውን ያካፈሉን በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ እርግብ ቀበሮ ሜዳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዘለቀ ወርቄ ናቸው። “እርሻ መተዳደሪያዬ፣ ቤተሰቦቼን የምመራበት እና ልጆቼን የማስተምርበት የህይወት መሠረቴ ነው” ብለዋል። ነገር ግን በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በግብርና ሥራቸው ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን አንስተዋል።
በሰላም እጦቱ ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት ብዙ ርቀቶችን ተጉዘው እና ላልተገባ ወጪ ተዳርገው እንዳገኙም በስልክ ለበኩር ተናግረዋል። ሆኖም ያን ሁሉ ፈተና ተጋፍጠው በሁለት ሄክታር ተኩል መሬታቸው በቆሎ እና ጤፍ በዋናነት ማምረታቸውን ገልፀዋል። የበቆሎ ሰብላቸውን ወቅተው ወደቤት ለማስገባት ተዘጋጅተዋል። ዓመቱ ጥሩ የሰብል ቁመና የታየበት ነው ብለውታል። ያጨዱትን ጤፍ ከፍ ባለ ቦታ እና በጥንቃቄ እንደከመሩ አስረድተዋል። የዳግም ሰብል ሽምብራ ዘርተው በማሸት (በመድረስ) ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ የሺጥላ ፍቃዴ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል።
መምሪያ ኃላፊው እንዳስታወቁት በዞኑ በ2016/2017 የምርት ዘመን 539 ሺህ 872 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል። ከዚህም 19 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ዕቅዱን ለማሳካትም በመኸር ወቅት 671 ሺህ 885 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም ከ17 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ ውሏል። አቶ የሺጥላ አክለውም አርሶ አደሩ ከባሕላዊ የአስተራርስ ዘዴ እንዲላቀቅ ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። ለዚህም በዞኑ 23 የእርሻ ትራክተሮች አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቁመዋል። ግብርና መምሪያ ኃላፊው ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ የግብዓት አቅርቦት እና የተሻሻሉ አሠራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው የተሻለ የሰብል ቁመና ማየት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ኃላፊው እንዳብራሩት በዞኑ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና በቆሎ በስፋት የሚመረቱ ሰብሎች ናቸው። በዓመቱ የተሻለ የግብዓት አቅርቦት በመቅረቡ እና ተስማሚ የአየር ንብረት በመኖሩ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ (የምርት ብክነት እንዳይከሰት) አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ በደረቅ እና በንፁህ ቦታ ማስቀምጥ ይጠበቅበታል ብለዋል። በወቅቱ ወቅቶ ወደ ቤቱ ማስገባት ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
አቶ የሺጥላ እንዳሉት በዞኑ በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ ከ467 ሺህ 882 ሄክታር በላይ የሚሆነው ሰብል ተሰብስቧል፡፡ ቀድመው የተዘሩ አዝርዕርት (እንደ ገብስ፣ ባቄላ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ አተር፣ ሩዝ እና ቦለቄ) የተሰበሰቡ ሰብሎች ናቸው።
የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና መሰል ችግሮች ምርት እንዳይባክን እና እንዳይበላሹ አርሶ አደሮች ጉልበታቸውን እና ሙሉ ጊዚያቸውን በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እና መውቃት እንደሚገባም የዞኑ ግብርና መምሪያ አሳስቧል። አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእህል ማከማቻ ጎተራዎችን በመጠቀም ከብክነት እና ከተባይ መከላከል እንደሚችል አመላክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን በእህሉ ላይ መጨመር በጤና ላይ (የጎንዮሽ ጉዳቱ) የከፋ ነው ብለዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ዘመናዊ ጆንያ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል። ይህም ከነቀዝ እና ከመሰል ችግሮች እንደሚከላከል አስረድተዋል። ዘመናዊ የእህል ማከማቻ ጆንያዎች እንዲቀርቡ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ገዝቶ የመጠቀም ልምዱ እና ግንዛቤው እየተሻሻለ መምጣቱንም አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያው ምትኩ መላኩ እንደተናገሩት የምርት ብክነት በዋናነት በአያያዝ ጉድለት የሚከሰት እንደሆነ ያስረዳሉ። በአግባቡ፣ በወቅቱ እና በጥንቃቄ አለመሰብሰብ እና አለመያዝ፣ የሰብሉን ትክክለኛ የመድረቅ ደረጃ አለመለየት፣ የግዛቤ ፈጠራ አናሳ መሆን፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን አለመከተል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አለመጠቀም እና ሌሎች ጉድለቶች ለምርት ብክነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
አርሶ አደሩ፣ ባለሀብቱ እና ነጋዴው የተለመደውን አካሔድ በመቀየር ዘመናዊ መንገዶችን መጠቀም ይገባዋል ብለዋል። የምርት ብክነትን ለመከላከል ባሕላዊ አሠራሮችን ማስቀረት፣ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን መጠቀም፣ በሰፊው የእርሻ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም ከፕላስቲክ የተሠሩ የእህል ማከማቻ ከረጢቶች (ዘመናዊ ጆንያዎችን) እና ከተባይ የሚከላከሉ ከብረት የተሠሩ የእህል ማከማቻ ጎተራን መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ ሰብሉን በወቅቱ ማጨድ (መሰብሰብ) ሲከምር በደረቅ ቦታ ማስቀመጥ፣ በአግባቡ ማድረቅ፣ ማገላበጥ፣ በጥንቃቄ ማጓጓዝ፣ መውቃት እና ማበጠር ይገባዋል። ምርቱ ለገበያ እና ለምግብነት እስኪውል ድረስ በጥንቃቄ መያዝ ተገቢ መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል።
በክልሉ በዘር ከተሸፈነው አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2017 ዓ.ም አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም