ጦርነት (ግጭት) እና የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ድርቅ የ2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራን ክፉኛ ፈትኖታል:: ለተጽእኖው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃዎችን እንመልከት:: በተያዘው የትምህርት ዘመን ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማርን ዕቅዱ አድርጎ ተነስቷል:: ይሁን እንጂ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶባቸው አልተመለሱም በሚል አካል እና በመንግሥት የጸጥታ ኀይላት መካከል በተፈጠረ ግጭት አሁንም ድረስ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል:: ሦስት ሺህ 500 የአንደኛ ደረጃ እና 225 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሁንም አልተከፈቱም። የግጭቱ ዳፋ በዚህ ብቻ አልተወሰነም፤ 298 ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ለጉዳት ተዳርገዋል::
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከ58 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ በቅርቡ አስታውቋል:: ይሁን እንጂ ተማሪዎች ክልሉ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበረበት ጊዜ ብቃታቸውን ያረጋግጣሉ ተብሎ አይታሰብም:: የትምህርት ግብዓትን በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ለማሟላት በየአቅጣጫው የመንገድ በተደጋጋሚ መዘጋት እና የጸጥታ ስጋት አሁንም እክል መፍጠሩ ለዚህ አብነት ተደርጎ ይወሰዳል::
ተማሪዎች አሁንም ድረስ ያልበረዱ የጥይት ድምጾችን እየሰሙ መማራቸው በሥነ ልቦናቸው ላይ የሚያሳድረው የመረበሽ ስሜት ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ እንዳያደርጉ በማድረግ ብቁነታቸውን እና ተወዳዳሪነታቸውን በእጅጉ ይገድበዋል:: በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች የተከሰተው ድርቅም ሌላው የመማር ማስተማር ሥራው ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን እና ግጭቱ በትምህርቱ ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል:: በተለይ የድርቁ ተጽእኖ ከፍተኛ በሆነባቸው በዋግኽምራ እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ ተማሪዎች ከበጎ አድራጊዎች በተገኘ 82 ሚሊዮን ብር የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅትም የአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ደብተር ለማቅረብ እየታተመ መሆኑን አረጋግጠዋል::
ግጭት እና ድርቅ ተማሪዎች አዘውትረው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከማድረግ ባለፈ የጀመሩትን ትምህርት እንዲያቋርጡ እንደሚያስገድዳቸው መረጃዎች ያሳያሉ::
ታዲያ በዚህ ወቅት የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው:: ለድርቅ ተጋላጭ ሆነው ከተለዩ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ አንዱ የሰሜን ጎንደር ዞን ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን አስታውቋል:: የክልሉ ትምህርት ቢሮ የዓመቱን የስድስት ወራት አፈጻጸም የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በገመገመበት ወቅት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክቡር አሰፋ እንደገለጹት የትምህርት ቤት ምገባን በዞኑ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ ስድስት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው:: በአሁኑ ወቅትም በ56 ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ24ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ ፕሮግራም ለመጀመር እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል:: የቢሮው ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ከክልሉ መንግሥት በተመደበ 75 ሚሊዮን ብር እና ከዓለም የምግብ ፕሮግራም በሚለቀቅ በጀት የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው::
የኮምቦልቻ፣ የደሴ፣ የደብረ ብርሐን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደሮች እንዲሁም የማዕከላዊ እና የደቡብ ጎንደር ዞኖች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል:: ክልሉ ቅድሚያ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል::
ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊዋ፣ በአሁኑ ወቅት የድርቁ ተጽእኖ ከፍተኛ በሆነባቸው ዋግኽምራ፣ ሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች የሚገኙ ከ56ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ:: ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ግን ከባለሀብቶች እና ከግብረሰናይ ድርጅቶች ተጨማሪ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል::
የምገባ መርሀ ግብሩ /ፕሮግራሙ/ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ በቀጣይ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ለማስፋት ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል::
በፈረንጆቹ ጥቅምት 9 ቀን 2023 ሜድረክሲቭ (medrxiv.org) ድረ ገጽ ላይ የተጋራው ጥናታዊ ጽሑፍ ዓለም ለትምህርት ቤት ምገባ የሰጠችው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ አሁን ላይ የተመጋቢ ተማሪዎች ቁጥር ከ418 ሚሊዮን በላይ ተሻግሯል። በ66 ሚሊዮን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ትምህርትን ፈልገውት ሳይሆን ተገደው እንዲከታተሉ ሆነዋል ሲል አስፍሯል::
ጥናቱ በአፍሪካ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ሲቃኝ በአህጉሪቱ 23 ሚሊዮን ሕጻናት በቂ ምግብ አያገኙም። በምግብ እና በአቅም ማጣት ምክንያትም 121 ሚሊዮን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ያትታል::
ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባን የጀመረችው በ1994 ዓ.ም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ነው። የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎች የትምህርት ተነሳሽነት እንዲጨምር፣ መጠነ ማቋረጡ እንዲቀንስ እና የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እንዲሻሻል የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው:: በረሀብ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች እንዲቀንሱ፣ የድብርት ስሜቶች ጠፍተው በንቃት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማስቻሉም ባሻገር በወላጆች ከትምህርት እንዲቀሩ የሚደረገውን ጫና የመቋቋም አቅማቸው እንዲዳብርም አድርጓል::
በትምህርት ቤቶች የሚተገበር የምገባ ፕሮግራም የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ እንዲቀንስ ማድረጉን ጥናቱ አረጋግጧል::ጥናቱ እውነታውን የሚያስረዳው በትምህርት ቤቶች የምገባ ሥርዓት ባልተጀመረበት ወቅት ቤተሰብ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ይሰማሩ ነበር። ይህም ለጉልበት ብዝበዛ፣ ያልተገባ ቦታ እንዲውሉ በማድረግ የሱስ ተጋላጭነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን አንስቷል::
የምርት አቅርቦት ውስንነት፣ የምርቶች ዋጋ መጨመር፣ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ ለምገባ ዓላማ ተብሎ የተገነባ መሰረተ ልማት አለመኖር የምገባ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ዋና ተግዳሮት በመሆን ተመላክተዋል:: በመሆኑም ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራምን ለመጀመር ወደ እንቅስቃሴ ሲገቡ ለዘላቂነቱ እነዚህን ጉዳዮች መመርመር እንደሚገባቸው ይታመናል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም