የተራዘመው ግጭት እና እልባቱ

0
189

ኮንሰርን (concern.net) በሰብዓዊ ርዳታ ላይ ተወስኖ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ በዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እጃቸውን ለምጽዋት ስለመዘርጋታቸው በወርሀ መስከረም 2023 ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ግጭትን ተከትሎ የተፈጠረው ረሀብ እና ድህነት ደግሞ ለዚህ ገዥ ምክንያት ሆኖ ተነስቷል፡፡ ድርጅቱ ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት በዓለም ላይ እየተደረጉ ያሉ 12 ግጭቶች በአብነት ያነሳ ሲሆን ኢትዮጵያን በሰባተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ በበኩሉ ኢትዮጵያን አስመልክቶ በ2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ሀገሪቱ ያጋጠማት ድርቅ እና ተደጋጋሚ ግጭት 28 ሚሊዮን ሰዎች ርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በግልጽ እየታዩ ያሉ ግጭቶች እያስከፈሉት ያለው ሰብዓዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን አሳጥቷል፡፡ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትም እያስከተለ ያለው ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ከፍተኛ ነው፡፡ በግጭቱ እየደረሰ ካለው ሁሉን ዓቀፍ ጉዳት ለመዳንም ለአስር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ክልሉ ከመደበኛው ሕግ ውጪ እየተዳደረ ይገኛል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ማስቻሉን መንግሥት በየጊዜው ቢያሳውቅም ለንጹሀን ዜጎች ግድያ ግን ዋስትና እየሰጠ አለመሆኑን በሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አካላት በተደጋጋሚ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት፣ ሁሉን አካታች መዋቅር አለመኖር፣ ለዘመናት የተሠራው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት፣ ፍትሐዊ የልማት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች አለመኖር፣ የተቀዛቀዘ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና መፍትሄ ርቆት የዘለቀው የኑሮ ውድነት ግጭቶች በተደጋጋሚ እንዲከሰቱ ስለማድረጋቸው በተለያዩ መድረኮች ተነስተዋል፡፡ በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች የተከሰተው እና መፍትሄ ርቆት ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ቀውስ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት አድርሷል፡፡

አሁንም አልፎ አልፎ ግጭቶች መኖራቸውን ተከትሎ አስተማማኝ እንቅስቃሴ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ይህም የተቀዛቀዘው የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የምርት ዝውውር፣ የማኅበራዊ  እና የተለያዩ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት እንዳይመለሱ ስጋት ፈጥሯል፡፡

ወቅቱ በተለይ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ የበላይ ጠባቂ የግብርና ግብዓት ለመኸር ወቅቱ ፈተና በማይሆንበት ደረጃ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ክልሉ ከማስገባት ጀምሮ ወደ አርሶ አደሩ ለማሰራጨት ፈተና መሆኑን በተለያዩ መግለጫዎች ሲያሳውቅ ቆይቷል፡፡

የዘንድሮው መኸር በተለይ ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት፣ በአፈር ማዳበሪያ እጥረት እና በድርቅ የታጣውን ለማካካስ ወሳኝ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ለበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በስልክ  ያስታወቁትም የዘንድሮው የግብርና ግብዓት አቅርቦት ስርጭት ቀደም ብሎ መጀመሩን እና በዋጋም የተሻለ መሆኑን ነው፡፡

ለአብነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁነሴ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፍሬው ንብረቴ በዘንድሮው ዓመት በዘር ለሚሸፍኑት ማሳቸው 19 ኩንታል የተለያየ አይነት የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋሉ፡፡ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንደሌለ በመንግሥት በኩል እየተገለጸ መሆኑ በዓመቱ ለመግዛት ያቀዱትን ሁሉንም እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቆላቸዋል፡፡

ጦርነትም ሆነ ግጭት ምርት እንዳይመረት በማድረግ ሕዝብን ለተረጂነት የሚዳርግ በመሆኑ ሁሉም በግጭት ውስጥ ያለ አካል ለሰላም አማራጮች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የሃይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ ሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ከፋርጣ ወረዳ የሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቷል፡፡ የሃይማኖት አባቶችም መንግሥት ለግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለይቶ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቱ በተሳሳተ መንገድ እንዳይሄድ አባቶች የበኩላቸውን ኃላፊት እንደሚወጡም በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ በበኩላቸው ዛሬ ላይ ያሉ ችግሮች እልባት አግኝተው እየደረሰ ካለው ጥፋት ለመውጣት  የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ጥያቄን በኅይል ሳይሆን በጥበብ እና በብስለት መፍታትን ማስቀደም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩትም ነፍጥ ማንሳት ግን የከፋ ጉዳት ከማስከተል ያለፈ መፍትሄ ይዞ እንደማይመጣ እስካሁን የደረሰው ጉዳት ማሳያ እንደሚሆን ያስታወቁት ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ናቸው፡፡ አቶ ዋለ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ  ያረጋገጡት የተፈጠረው ግጭት በዞኑ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ማድረሱን ነው፡፡

የተፈጠረውን የሰላም እጦት በመፍታት ዞኑን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታው ለመመለስ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቁመዋል፡፡  ለተገኘው ሰላምም ሕዝቡን አመስግነዋል፤ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በተመለከቱበት ወቅት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ፣ ከበደ የባሕር ዳር ከተማ ሰላሟን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ከፍተኛ የልማት ሥራ እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ሰላም ለልማት እና ልማትም ለሰላም ትልቅ ቅድመ ሁኔታ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ለመጀመር ለሰላም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ግጭቶችን በሰላም መቋጨት የመንግሥት የቅድሚያ ፍላጎት መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ በግጭት ተሳታፊ ለሆኑ ወገኖች የተላለፈው የሰላም ጥሪ በግጭቱ ለተሳተፉ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በሰላም ለመኖር አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ ቃል እየመረጡ በመወርወር ሕዝብን ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም አካሄድ አደገኛ መሆኑን በመረዳት ከድርጊቱ መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት አሁንም የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ  ሕግ የማስከበር ኀላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ርእሰ መስተዳደሩ አረጋግጠዋል፡፡ የክልሉ አመራሮችም የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡም በየአካባቢው  የራሱን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ ምንም እንኳ በአንጻራዊነት እየተሻሻለ ቢመጣም በዘላቂነት ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ አማራጮች ለመቋጨት እያሳየ ያለውን ፍላጎት በቁርጠኝነት ወደ መሬት ማውረድ ይገባዋል፡፡ “መንግሥት ለሰላም ዝግጁ ነኝ” ከማለት በዘለለ ሀገርን እና ሕዝብን በበላይነት የሚያስተዳድር በመሆኑ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ወደ ንግግር፣ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here