የዴንማርኩ ደራሲ ሃንስ ክርስቲያን አንደርሰን “ሙዚቃ ቃላት መናገር ሲያቅታት ንግግርን ትጀምራለች” ብሏል። እውነትም ሙዚቃ ሰዎች በመጽሐፍ እና በቃላት ንግግር ማቅረብ የማይችሉትን፣ የሚከብዳቸውን፣ የሚያስፈራቸውን፣ ወግ እና ባህሉ የሚከለክላቸውን ሐሳብ ለመግለጽ ትልቅ መሳሪያ ናት።
በአፍሪካ የዴሞክራሲ ልምምድ ገና ጨቅላ ነው። ጽንሰ ሐሳቡ ወደ ተግባር ለመሻገር ገና እየተንቀራፈፈ ነው። ልማድ፣ ባህል፣ እምነት እና ሞራል ስር የሰደደ የልጓምነት ሚና አላቸው። በዚያውም ልክ የሚያጠፉት ብዙ ነው። ብዙ ጎጂ እምነት፣ ባህል እና ልማድ አለ። ሕዝቦች ይህንን ጉዳት የሚናገሩት በሙዚቃ ነው።
የኢትዮጵያ ማህበራዊ መስተጋብር በሙዚቃዎቻችን ውስጥ በብዙ ተፈትሿል። ሰዎች በገሃድ የማይሞግቱትን በሙዚቃ መሳሪያነት ሞግተዋል። ሙዚቃ የጭቁን አንደበትነቷ በብዛት ታይቷል። ጸጋዬ እሸቱ እና ገጣሚ ጸጋዬ ደቦጭ ከአበበ ብርሃኔ ጋር ሆነው የሰሯቸው ሦስት ሙዚቃዎችን ዛሬ እንመለከታለን። ሙዚቃዎቹን ጸጋዬ እሸቱ በድምጽ፤ አበበ ብርሃኔ በዜማ፤ ጸጋዬ ደቦጭ ደግሞ በግጥም ሰርተዋቸዋል። እነዚህ ዘፈኖች በተከታታይነት አንዲት ሴት እና ወንድ ላይ ትኩረት አድርገው የተሰሩ ፈጠራዎች ናቸው። በጸጋዬ እሸቱ ሦስት አልበሞች ውስጥ ተካተዋል። ተከለከለ አሉ በ1981 ዓ.ም፤ ለሰርጓ ተጠራሁ በ1983 ዓ.ም፤ ተጎሳቁላ ሳያት በ1987 ዓ.ም ለአድማጭ ደርሰዋል። ዘፈኖቹ አንድ ወጣት ልጅ የሚያፈቅራትን አብሮ አደግ ልጃገረድ ቤተሰቦቿ ከቤት አላስወጣት ብለው ሲናፍቃት፤ ከዓመታት በኋላ ለሌላ ሰው ሲድሯት ያሳያል። በመጨረሻም ያች ቆንጆ ሴት ውበቷ ረግፎ ተጎሳቁላ ሲያያት ማዘኑን እንመለከታለን።
ተከለከለ አሉ 1981 ዓ.ም
“ተከለከለ አሉ በርሽ ያለ አመሉ
ምነው መዘጋቱ ምነው መከልከሉ
ለወደደሽ ሁሉ”
ይህ ወጣት የጎረቤት ሰው ይመስላል፤ የልጅነት አብሮ አደግ። ሴቷ ጋር እቃቃ ይጫዎት ነበር። ልጅቷ ማደግ ስትጀምር ቤተሰብ ቁጥጥር ማድረጉ አልቀረም። እርሷን ማግኘት አልቻለም። ከቤት እንዳትወጪ የሚል ማስጠንቀቂያ ወላጆች ያበዙባታል። በሁለቱ መካከል መዋደድ እና መፋቀር አለ። አንተን ነው ማገባህ፤ አንቺን ነው ማገባሽ ተባብለዋል። ይህን ደግሞ ባህሉ አይፈቅድም። በዘመኑ ሴት ልጅ ስታድግ ባል ይመጣላታል፣ ትታጫለች እንጂ በራሷ ምርጫ የላትም። ወንዱ ግን ፍቅር አለበትና እንጋባለን ብሎ ያስባል። እርሷም ከፍቅሯ የተነሳ እሱን ማግባት ትፈልጋለች። አንቺ ጋር ለመኖር እየተዘጋጀሁ ነበር፤ ድንገት ግን ሌላ ማተብ አሰርሽ ወይ ይላል፤ ማተብ የቃል ኪዳን ቀለበት ነው። አንቺ አለሽኝ ብዬ ሁሉን ትቼ ምነው ሰው ተካሽብኝ ወይ እያለ ያዜማል ጸጋዬ።
“ይዋል ይደር እንጂ ሆዴን እያመመው
ትዝብት ነው ትርፉ ተተካብኝ ሰው”
የልጃገረዷ ከዓይኑ ዕይታ መሰወር እረፍት ነስቶታል። ምናልባት ከቤት የማትወጣው ለሌላ ሰው ታጭታ ነው ብሎ አስቧል። ይህንን ነው ‘ትዝብት ነው ትርፉ’ የሚለው። እውነት ከድተሽኝ ከሆነ እኔም ከሰው ለማደር የምችልበት አፍቃሪ አላጣም ሲል ይዝታል። የእርሷ ፍቅረኛ ነው ተብዬ ስገመት እንዳልነበር ዛሬ እንዴት በሰው እቀየራለሁ፤ እንዴት እበለጣለሁ ብሎ ይቆጫል።
“እድሌ ቢከፋ እንዲያው ባይሞላልኝ
ያላመድኳትን ርግብ ሌላ መረጠብኝ”
አብሮ አደጉ አፍቃሪ የጓሮ ጎመን መሆኑ የሚያም ነገር ነው። የሚወዳትን ልጅ አሳድጎ ለሰው መስጠቱ የተሸናፊነት ስሜት ፈጥሮበታል። ለእኛ ለአድማጮች ግርምቱን ይነግረናል። ውበቷ አጥር ውስጥ እንድትውል አደረጋት፤ እናቷ ባላጋራዋ፤ አባቷ ባላንጣዋ ሆኑባት ይላል። በውበቷ ምክንያት ታስራለች፤ የምትወደውን ወጣት አግኝታ እንዳትደሰት ይከላከሏታል። በባህል እና ልማድ ታስራለች። በወጉ ቆንጆ ልጅ ከጥሩ ሰው ጋር በጋብቻ መተሳሰሪያ ነበረች፤ ይህቺ ግን ከቤት የማትወጣ ስስት ሆነች። ሁሉም የሚጣላባት ሆነች፤ ድብቅ መሆኗ ተፈላጊነቷን አበዛው ይላል። እኔ ነኝ የማገባት ብሎ ብዙ ሰው በጸብ ምክንያት ተራራቀባት ነው የሚለን። ከነገረን በኋላ ምን ይሻለኛል ብሎ ይጠይቀናል። የራበው ሰው እህል ይጎርሳል፤ የበረደውም ለገላው ጋቢ ይደርባል፤ የደከመውም በእንቅልፍ ጉልበቱን ያድሳል፤ የፍቅር አባዜዬን ምን ላድርግ ብሎ ይጠይቀናል።
“አይከለክሉትም የቆየን ወዳጅ
ባይሆን ወንድም አርገው ያጽናኑታል እንጂ”
ይህ ሰው ቤት እንዳይገባ፣ እንዳያያት የተደረገበት ክልከላ ነው ይህን ሁሉ የሚያብሰለስለው። ከመዋደዳቸው በቀር ምንም የሰማው ነገር የለም። ብዙ ወንድ እንደሚፈልጋት ያውቃል። ቢያንስ እንዴት ቤት እንዳልመጣ እከለከላለሁ፤ ወንድም አይደለሁ ወይ ይላል። የሚሰማው ሰው አልተገኘም እንጂ። ወደ ወላጆች ደግሞ ይዞራል። ውበት ሲያጓጓ ክልከላና አጥር ማብዛት ምንድን ነው? እናቷስ ምነው ወደ ምንጭ ወይ ገበያ አይልኳት? ብሎ ያዜማል። ከዚህ ቀደም የአካባቢው ሰው የሁለቱን ፍቅር የሚያውቅ ይመስላል። “ከእንግዲህ ሰው ብሎ ማን ይሆን የሚያምናት፤ አላት ያሉት ጠፍቶ ሁሉም ሲሰማባት” ብሎ ጸጋዩ የሚገልጸው ፍቅራቸው ገሃድ እንደነበር የሚጠቁም ነው። ቀድሞ ሁለቱ በልጅነታቸው የገቡትን ቃል በማፍረስ አዝኖ ዝም ይላል። የመጀመሪያው ዙር ሙዚቃ “ተከለከለ አሉ” ብሎ በዚህ መልኩ የማህበረሰቡን መስተጋብር ያሳይና ያልቃል። የፍቅር እስከ መቃብሯን ሰብለ ወንጌልን መሳይ ታሪክ በልጅቱ በኩል እናያለን። በቁንጅና ከእንቅስቃሴ መከልከል እና ምርጫ ማጣትን።
ለሰርጓ ተጠራሁ 1983 ዓ.ም
ጸጋዬ ደቦጭ ሁለተኛውን ዙር ሙዚቃ ለመስራት ያሰበው ተከለከለ አሉ የሚለውን ሙዚቃ ደጋግሞ ካዳመጠው በኋላ ነው። በመጀመሪያው ሙዚቃ ልጅቷ ከቤት አልወጣ ማለቷ፤ ወላጆች ቁጥጥር ማብዛታቸው፤ ውበቷ ማጓጓቱ፤ ፈላጊዋ መብዛቱ ለባል ልትዳር እንደምትችል ይጠቁማል። ወጣቱም ልቡ በስጋት እና ጥርጣሬ እንደተወጠረ በትዝብት እና ናፍቆት ላይ ቆሞ ነበር። መጨረሻው ምን ይሆን የሚል ጉጉትን ይፈጥራል። ይህቺ ሴት ባል ታግባ ብሎ አሰበ ጸጋዬ ደቦጭ። ለሰርጓ ተጠራሁ ሙዚቃ ተሰራ። ያ አብሮ አደግ ገጸ ባህሪ ሁለተኛው ሙዚቃ ላይ መጣ።
“ሸጌ የሰርግሽ እለት ጥሪው ደርሶኛል አመስግኛለሁ
ምን ባዝን ቢሰማኝ ምን አቅም አለኝ ምን እፈጥራለሁ
ሲዘፈን ሲደለቅ አልቅሼ ከደጅ እሸኝሻለሁ”
የፈሩት ይደርሳል እንደሚባለው፤ ወትሮውንም ወጣቱ የማህበረሰቡን ባህል ያውቃልና ስጋቱ አልቀረም። ስጋቱ ሌላ ወንድ እንዳታገባበት ነበር። እነሆ አብሮ አደግ እንደመሆኑ መጠን ሌላ ወንድ ስታገባ ሰርግ እንዲበላ ተጠራ። ይህ ወጣት በወላጆች ዓይን ለስፍር የጎደለ ነው። አቅም አልባ እና ደካማ ነው። ልጅቱ ምን ብትወደው ከወላጆች ፍላጎት እና ከማህበረሰቡ ልማድ አትወጣም።
ምናልባት ጥሪውንም ያደረገችለት እርሷ ላትሆን ትችላለች። ወላጆች ናቸው አብረው ከቤተሰቡ ጋር የጠሩት። ቢሆንም ግን ምርጫ አልባ ነውና ሰው ሁሉ ሲዘፍን እኔ እያለቀስሁ በእንባ አሸኝሻለሁ ይላል። ቢሆንለት ጥይት ኖሮት ጠልፎ በወሰዳት፤ ከሰርጉ ለማስቀረት ወገን እና ዘመድ በኖረው ነበር። ጉልበትም ያንሰዋል። ሁለቱ ልጆች አብረው ያደጉ፤ በቃል የተማመኑ ነበሩ። ለሌላ ወንድ ስትዳር መጠራቱ አሳዝኖታል። “ሰው እና ገንዘብ የለኝ” የሚለው ነው ደጋግሞ እንባውን የሚያመጣበት።
ሰርግ ላይ እርሷ እየተመረቀች ነው። እየተዘፈነ ነው። እርሱ ግን ያለቅሳል። “ባለንጀሬ አይክፋሽ ተብሎ ሲዘፈን፤ የኔን ማን አየልኝ የፍቅሬን ሰቀቀን” ይላል። እርሷንስ አጽናናችኋት፤ አይዞሽ አላችኋት፤ እኔ አለሁ እንጅ በውስጤ የፍቅር እሳት የሚለበልበኝ ይለናል። አይዞህ ባይ እና አጽናኝ የሌለኝ ብሎ ይተክዛል።
“ወይ ይዤሽ መክረሜ ላትሆኚኝ ላልሆንሽ
አልሰፋም ዙሪያዬ ባስጠይቅ አነስሁሽ”
ይህ ወጣት ምናልባት ልጅቷ ከመዳሯ በፊት ሊያገባት ጠይቋል። ሆኖም ግን ጋብቻ በማህበረሰባችን ፍቅር አይደለም። ኢኮኖሚ ይቀድማል። ምን አለው፣ የእነ ማን ነው? ይባላል። ወንዱ በተለይ ሴቷን ከሞቀ ቤቷ፣ ከእናት አባቷ ጉያ አውጥቶ የሚወስዳት ስለሆነ በኢኮኖሚ እና በስነ ልቦና ጠንካራ መሆን አለበት። ይህ ወጣት ማህበረሰቡ የሚጠብቅበትን አያሟላም። በወግ በልማዱ ዓይን በቂ አይደለም። ከገንዘብ ይልቅ ፍቅርን አስቀድሟል። ባሏ ማቅረብ የሚችለውን ጥሎሽ አያቀርብም። ፍቅሯን ብቻ ነው በልቡ የያዘው። ፍቅር ደግሞ ራት ምሳ አይሆንም። የቀደመው ዘመን መጀመሪያ መተዳደሪያውን ገንዘብ አጠራቅሞ ነው ወደ ትዳር የሚገባው። ፍቅሩ በሂደት በመላመድ ነው የሚገነባው። ያም ሆኖ ረጅም ዓመት በትዳር ይኖራሉ። ወጣቱ የዘመናዊ እሳቤ ሰለባ ነውና “ዋናው ፍቅሩ ነው ሰርተን እናድጋለን” ብሎ ሊያስብ ይችላል። ቀደምቱ ባህል ግን “ራስ ሳይጠና ጉተና” ብሎ በኩርኩም ዝቅ ያደርገዋል። ባስጠይቅ አነስሁብሽ የሚለው ይህንን ነው። ሁብት ከሌለው ማንም ጆሮ አይሰጠውም።
“ከዚህ በላይ ምን ሊያሳዝን የሰው ነገር
እድሜ የሰጠው ብዙ ይችላል ምን ቢቸገር፤
በትዝታ ስኮራመት ያላዛኝ ጣለችኝ
ትዳሯን ያሙቀው የምላትም የለኝ”
እያለ ትዳሯ የሞቀ እና የደመቀ እንዲሆን ይመኛል። ከእኔ ከነጠሉሽ ወዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ ብሎ ራሱን ያጽናናል። ውስጡን እሳት ቢያቃጥለውም እንኳን መልካም ትዳር ይመኝላታል። ጅምሩ ፍቅራቸው በመለያየት አብቅቷል። እስካሁን ድረስ ለሰርጓ ቀን እንዲገኝ የተደረገለትን በማሰብ ነው ሲብከነከን የሰማነው። ቤቱ ሆኖ ነው በሐሳቡ የሚባዝነው። ሰርግ ላይ መገኘት የሚያመጣበትን ችግር ቀጥሎ ባሉት ስንኞች ይናገራል።
“አልገባም ከዳሱ ድግሱም እርሜ ነው
ትክሻየም አይሞቅ አይጥመኝ እስክስታው
‘ሆ’ ማለት እልልታ ላገኘ ብቻ ነው
ተነጥቆ ላጣ’ማ መች እዬዬ አነሰው”
… ይቀጥላል።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም