የተሰዋው ውበት

0
133

ካለፈው የቀጠለ

በዚህ ፅሑፍ ቀዳሚ ክፍል የኢትዮጵያ ማህበራዊ መስተጋብር በሙዚቃዎቻችን ውስጥ በብዙ መልኩ መፈተሹን ጠቁመናል።

ፀጋዬ እሸቱ እና ገጣሚ ፀጋዬ ደቦጭ ከአበበ ብርሃኔ ጋር በመሆን የሰሯቸውን ሶስት ሙዚቃዎች ይዘትም በመተንተን ማስነበብ ጀምረናል። ቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የወደዷት ልጅ  ሌላ ወንድ ስታገባ ሰርጓ ላይ መገኘት ይቅርና ወሬውን መስማት በጣም የሚረብሽ ነገር ነው። ወጣቱ በዘፈኑ ውስጥ አንዴ ይቅናሽ ሲላት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በደሉን ሲናገር እንሰማዋለን። ደግሞ እንደገና ዓለም ጎዶሎ ናት ብሎ በእድሉ ሲያዝን እናደምጠዋለን። ይቅናሽ እንጂ ሌላ ክፉ ቃል ምንም አልናገርም ብሎ በተሰበረ ልብ ሲናገር እናያለን። ሰርግ የደስታ መግለጫ ነው። እሱ ደግሞ ኀዘን እና እንባ ይዞ ዳስ ውስጥ መገኘቱ ተገቢ አይደለም። እሷንም ይረብሻታል። እሱንም የበለጠ እንዲያለቅስ አድርጎ ሰርጉን ይረብሻል። ድብቁ ፍቅራቸው አደባባይ መውጣቱ ለቀጣይ ትዳሯ እና ለአዲሱ ባሏ ያልተገባ መልእክትም ያስተላልፋል። በዚህ ደረጃ ይጠነቀቅላታል።  የሰርጉ ቀን እንዴት እንደዋለም በሚቀጥለው ግጥም ይናገራል።

“ሸጌ የሰርግሽ እለት እኔው ልቅር እንጂ ተጠርቻለሁ

በወግ ማዕረግሽ ቤትሽ  ሲዘፈን ሳለቅስ ውያለሁ

አድባር  ትቀበልሽ እንግዲህ ባዳሽ ነኝ ርቄሻለሁ”

በሰርጓ ቦታ መገኘት እንደማይበጀው ከላይ ነገረን። አሁን ደግሞ “አልመጣሁም ነበር፤ ሳለቅስ ነው ቤቴ ኩርምት ብዬ የዋልሁት” ብሎ ለእሷ ለሙሽሪት ይነግራታል። በማህበረሰባችን ጋብቻ ዘር፣ ሃይማኖትን እና ሌሎች ጉዳዮችን መስፈርት ያደርጋል። በሁለቱ አብሮ አደጎች መሃል ግን የእምነትም ይሁን የሃይማኖት ልዩነት እንደሌለ አፍቃሪው ይናገራል። “የዘር ዘራዝርቷ ከዘሬ ቂም የለው፤ ሳትወድ ከእኔ ለዩዋት ምርጫውን ተጭነው” የሚለው አፍቃሪ ክስተቱን “ዱብ እዳ ነው ሳናስብ  የለየን” ይበል እንጂ መሰረቱ ባህላችን ነው። የተሰናበታት ቢመስልም እንኳን ቤቷ ሄዶ መጠየቅ ይፈልጋል። ግን ደግሞ ባሏ ይህን ወጣት እንደ አብሮ አደግ ጓደኛ እንደማይቀበል በማሰብ ይሰጋል። ባልዬው የምን አባትህ አብሮ አደግ ቢለኝስ፤ ቢከፋብኝስ እያለ ያስባል። አብረው ለመኖር ብዙ ያቀዱ አብሮ አደጎች ውጥናቸው በዚህ ሰርግ ተሰናክሏል። እንደሱ ደግሞ ጠብቆ ያቆየውን፣ ያሳደገውን ለሰው አሳልፎ የሰጠ ይኖር ይሆናል ብሎ ብቸኛ አለመሆኑን፤ ይህ ክስተት በእሱ ብቻ እንዳልተጀመረ እያሰበ ይጽናናል። “እንደዚህ አድርጋኝ ብዬ አላወራም” ይላል። ምክንያት አለው ልጁ። “ያጣ ለማኝ ተሳድቦ ይሄዳል” እንደሚባለው  እሱም “ያጣ አያምር አድማጭ የለው ምን ቢናገር” ብሎ ስሟን በክፉ ላለማንሳት ቃል ይገባል።

ተጎሳቁላ ሳያት 1987 ዓ.ም

ጸጋዬ ደቦጭ ለጸጋዬ እሸቱ የእነዚህን አብሮ አደጎች ሕይወት ከሰርግ በኋላም ማሳየት እንዲችል ግጥም ጽፎለታል። ሦስተኛው የአብሮ አደጎች ታሪክ በ “ተጎሳቁላ ሳያት” ሙዚቃ ተዳሷል። ውበት ሴት ልጅ ላይ  ጉዞው በጣም ፈጣን ነው። ሴት ልጅ በ16 ዓመቷ ሁሉም ወንድ ትኩረት ውስጥ ትገባለች። አሁን ቀረ እንጂ እንዲያውም ድሮ በ10 ዓመት ልጆች ይዳሩ ነበር። 16 ዓመቷ ላይ’ማ ቆማ ቀረች ነበር የሚባለው። ይህ ሐሳብ  ሴት ልጅ ከወንድ ጋር ቅድመ ጋብቻ ግንኙነት ሳትፈጽም ማግባት ከመፈለግ ነው፤ በድንግልና እያለች። ወንዱ ደግሞ በጊዜ ሂደት ነው ዕይታ ውስጥ የሚገባው። የዓለም ስርዓት ሴትን እንጂ ወንድን በውበቱ አይለካውም። ወንድ ልጅ በራሱ መኖር ሲጀምር፣ ሲያገኝ፣ ራሱን ሲጠብቅ ነው ዓይን ውስጥ የሚገባው። መስህብ የሚያገኘው ራሱ በሰራው ቁስ ነው። ሴት ግን ፈጣሪዋ በሰጣት ውበት ወንዱን ታነሆልለዋለች። በትንሽ ዕድሜዋ ብዙ ወንዶች የሚመኟት ትሆናለች። ወንዱ ጥሩ መኖር ከቻለ እድሜው ሲጨምር ያምርበታል። የሴት ግን ዕድሜዋ በጨመረ መጠን ውበቷ ይረግፋል። ውበትን ለልጆቿ እያጋራች ትቀጥላለች። ባትወልድም በውበቷ ትቆያለች እንጂ ብዙ አትዘልቅም፤ ተፈጥሮ ነውና።

አብሮ አደጉ ከዓመታት በፊት እንዲያ ሲያፈቅራት፤ ሲሳሳላት የነበረች ሴት ከጋብቻ በኋላ በሚያሳዝን ሁኔታ አገኛት። ያን ጊዜም

“ተጎሳቁላ ሳያት ፊቷ ኀዘን ለብሶ

ዓይኔም አላምን አለ እያያት መላልሶ

ውስጤ ተረበሸ ተሰበረ ደርሶ

አለኝ ኀዘን ኀዘን አለኝ ለቅሶ ለቅሶ”  ይላል።  እሱ በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ነው። እሷ ደግሞ ኑሮ ከፍቶባታል። ቀና ብላ ለማየት እንኳን አልደፈረችም፤ ውስጧ ጸጸት ይኖራል፤ ከእሱ ጋር ብሆን ኖሮ የሚል። ለባህል መስዋእት ሆና የከፋ ኑሮን በመጋፈጧ ትሳቀቅ ይሆናል። ምርጫዋን ለቤተሰብ ስትል አሳልፋ መስጠቷ ይቆጫት ይሆናል። ያ ሁሉ ኩራት ቀርቷል። ልቧ ትዕግስትን ገንዘቡ አድርጓል። ስታገኘው እንኳን በመሸማቀቋ አንገቷን አቀርቅራ አለፈችው። የሚያውቃት በግሩም ውበት ነበርና “እኔ ላግባሽ ስልሽ እምቢ ብለሽ” ብሎ የሚያሸማቅቃት ሲመስላት በማቀርቀር አለፈችው። “አንቺ ቃል አባይ” ብሎ የሚሰድባትም መሰላትና አንገቷን ደፋች። እንዲህ የሆነችው ምን አግኝቷት ይሆን ብሎ ይገረማል።

“በኑሮ ፈተና በችግር ላይ ወድቃ

አቀርቅራ አየኋት አንገቷን ዘቅዝቃ

ስንቱን ልሙትልሽ ያሰኘው ውበቷ

ምን አግኝቷት ሸሸ ምን ይሆን ጉዳቷ

አልገለጽ አለኝ የችግሯ ሰበብ

ሰው የላይ ገጹ እንጂ የውስጡ አይነበብ”

ይህች ሴት ውስጧ ምን እንደሆነ ለማወቅ ማንም አይችልም። በደፈናው ኑሮ አልተስማማትም ከማለት በቀር። አብሮ አደጓም ይህንን ነው  የሚያስተጋባው። የሚያዝነውም ከፍቅሩ የተነሳ ነው። እኛም በኑሯችን ከ10 ዓመት በፊት አብረውን የተማሩ ቆነጃጅትን በማየት እንደነቃለን። በተለይ ወንዶች ጩቤ የሚማዘዙላቸውን ሴቶች ውበት አይተን ምን ሆና ነው እንላለን። “ከወለደች በኋላ ውበቷ ረገፈ” እየተባባልን እናዝናለን። በመንገድ ጎረምሳው “አናግሪኝ እንጂ” ፤ “ፍቅሬን አስጨርሽኝ” ይላቸው የነበሩ ውብ ሴቶችን አሁን ሳያቸው እኔም አዝናለሁ። ከዓመታት በፊት ምድርን ለመርገጥ የሚጠየፉትን ሴቶች ሳይ በአካል አያመሹ የሚሉት ብሂል ትዝ ይለኛል። ቢያንስ አረማመዳቸው እንኳን የት ሄደ? እላለሁ። “ሜሮን ባለሀብት አግብታ ሦስት ወልዳለች፣ ቃል ኪዳን አረብ ሀገር ሄዳ ተመልሳለች፤ ሮዛ የሆነ ቢሮ ነው ምትሰራው” እያልን የወጣትነት ዘመናችንን ቆነጃጅት ውበት መርገፍ አንስተን እናወራለን። ሴቶች ውበታቸው እየጠወለገ ነው፤ ፉንጋ የነበርን ወንዶች ደግሞ መለምለም ጀምረናል። የጸጋዬዋም ሴት የረገፈችው እንዲሁ ነው፤ በኑሮ ፈተና እና በተፈጥሮ ኡደት።

“ወቅቱ እንዳለፈ እሸት አበባው ረግፎ

የሚያስደንቅ ደሟ ለዛ ወዟ ነጥፎ

እድሜዋ ሳይገፋ ፈተና በዝቶባት

ይህች የማትሞላ ዓለም አየሁ አጉድላባት

ፊቷ ማዲያት ወርሶት ጥቁርቁር አርጓታል

የመኖር ፈተናው ስንት መልክ ያስወጣል”

የዚህች ሴት ጉዳት ከሁሉም የከፋ ይመስላል። በዕድሜ መሄድ ነው እንዳንል የመኖር ፈተና እንጂ እድሜዋስ አልገፋም ነበር ይላል። ገጽታዋን፣ መልኳን፣ ሁኔታዋን፣ አኗኗር የገጠመውን ችግር፤ ከእሸት መድረስ ጋር አመሳስሎ በስዕል እንድናየው ያደርገናል።  በመልካም ልቦና ሲታሰብ እንኳንስ የሚያፈቅሯት ልጅ ማንም ሰው ሕይወቱ ተጎሳቆሎ ለማንም ደስታን አይሰጥም፤ ያሳዝናል እንጂ። የዚህ ልጅ ኀዘን ግን እንባም የተቀላቀለበት ነው፤ ለቅሶ ለቅሶ የሚል ነው።

“ተወልዶ አድጎ እስኪያረጅ እድሜ እስከሚከብደው

ኑሮውን ይመስላል ሰው መልኩ ብዙ ነው

የእሷም ወረት አልቆ አየሁ አንገት ደፍታ

የአንዱ እድል ጠዋት ነው የአንዱ አዱኛ ማታ”

የእድል መፈራረቅ በሁለቱ አብሮ አደጎች በኩል ታይቷል። እሱ ትናንት ኀዘን የበዛበት፣ ፍቅረኛውን ከጎኑ ሰው ነጥቆ የወሰደበት ነበር። “ያላመድኳት ርግብ”፤  “ጠብቄ ያቆየኋትን ተቀማሁ” ብሎ በሰርጓ ቀን ሲያለቅስ የዋለ ሰው ነበር። እሷም የወግ የባህል ነውና ልቧ ባይፈቅድም “አይክፋሽ ባለንጀሬ” ተብላ የተዳረች ልጅ ነበረች። እንደ እሱ ዘወር ብላ ለማልቀስ እንኳን ጊዜ እና ሁኔታው አልተመቻትም። ልቧ አብሮ አደጓ ጋር ሆኖ ነው ለሌላ ወንድ የተዳረችው። ከዛሬ አፍላ የፍቅር ስሜት ይልቅ ለነገ መልካም ትዳር ከተመረጠላት ጥሩ ሰው ጋር ትኖር ዘንድ ተድራለች።  በስሜት መኖር እንደማይቻል ታውቃለች። ማህበረሰቧም ይሁን ቤተሰብ ይህን በመረዳት ነው “የተሻለ ሰው” ብለው መርጠው ለማትወደው ሰው የዳሯት። አብሮ አደጓ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን አፍርሳ መልካም ትዳር ለመኖር ነበር የሄደችው። ለወግ ለማእረጉ በቅታለች። የወላጆቿን ትዕዛዝ ፈጽማለች። ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ እንደተባለው፤ እሷም ይሆናል ብላ እንደጠበቀችው አልገጠማትም። እሷ ቃላት ሳትናገር ማዲያት የወረሰው፣ ወዟ የነጠፈው፣ ደም ግባቷ የደረቀው ፊቷ ይናገራል። እሱ ጠዋት ኀዘንተኛ ነበር። ማታ ግን ደስተኛ ነው። እሷ ጠዋትም ደስታ አልነበራት፤ የምትወደውን ሰው ከልክለዋታልና። የማታ ደስታውን ለማግኘት ነበር ምርጫዋን የቀየረችው። እንዳሰበችው አልሆነምና ማምሻዋ ጉስቁልና ሆነባት። የድሮ ወዳጇ ደግሞ ይህንን በማየት ያዝናል። ይተክዛል።  ከተፈጥሮ ጋር በማነጻጸር ሲያዝንላት  የጊዜን ፍትሐዊነት በግጥሞቹ እንመለከታለን።

“ጨረቃና ፀሐይ በጋና ክረምት

አንዱ ሲሸኝ ሌላ ሲፈራረቅ ወቅት

የሰው ልጅም ኑሮ ቦታው ይለወጣል

አንዱ ላይ ሲጨልም ለሌላው ይነጋል

ከወረተኛ ዓለም ሰብስባ ትዝብቷን

ታማርረዋለች ጠልታ ሰውነቷን

ጊዜ አይጠነጠን የጥንቱ አይመለስ

ሲያናንቋት አየሁ ነገር ሲቀለበስ

አለ ጊዜው ወድቃ ሳያት ክው አልሁላት

የእሷስ ተለየብኝ ምን አፈጠነባት ”

በሦስቱም ሙዚቃዎች ውስጥ ከርኅራኄ በስተቀር በቀል የሚባል ሐሳብ አንድም ቦታ ላይ አንመለከትም። እውነተኛ ፍቅር የተሰበከባቸው፤ የማህበረሰባችን መስተጋብር የተነገረባቸው፤ የሙዚቃ አቅም የታየባቸው ናቸው፤ ዘፈኖቹ። ድሮ በሰውነቷ ምክንያት ሁሉም ያደንቃት ነበር፤ ዛሬ ገላዋ ሲከዳት ዓለምን ትታዘባለች። ካለጊዜዋ የወደቀች አበባ ናት። የማህበረሰብ እና ቤተሰብን ምርጫ እና ፈቃድ ለመፈጸም ስትል የተሰዋች የመስዋእት ቆንጆ ነች።

ሃንስ ክርስቲያን አንደርሰን እንዳለው ቃላት የማይደፍሩትን የማህበረሰብ ልማድ እና ባህል ሙዚቃ እንዲህ ተናግራዋለች።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here