በታሪክ እንደምንረዳው የብሔር ፌደራሊዝም መንግሥታዊ ውቅርን የሚከተሉ ሀገራት ብዙዎቹ የከፋ አደጋ ገጥሟቸዋል። ለዚህ አብነት ደግሞ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ … ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሀገራት ታዲያ ለገጠማቸው ችግር ፈጣን የእርምት እርምጃ በመውሰዳቸው ከችግራቸው መውጣት ችለዋል። ለአብነትም በጎሳ ግጭት ምክንያት አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿን ያጣችው ሩዋንዳ በሀገር በቀል ዕውቀት፣ በሽምግና፣ በይቅርታ እና ከዚያ አለፍ ሲልም ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃን በመውሰድ የገጠማትን ችግር መሻገር ችላለች። ይህንን በማድረጓም በአሁኑ ወቅትም በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ አይተናል። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በሩዋንዳ ስለ ብሔርተኝነት ማውራት በሕዝቡ ዘንድ የተጠላ ከመሆኑም ባሻገር ከበድ ያለ ቅጣትን ያስከትላል።
በሌላ በኩል ለዘመናት የብሔር ፌደፋሊዝምን የምትከተለው ሀገራችን በተሳሳተ አተገባበር ምክንያት ከባድ አደጋን አስከትሏል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ስዕሉን ዘንግቶ በብሔር ጎጥ እንዲታጠር አድርጎታል። ለአብነትም የሀገራችን ሕገ መንግሥት መግቢያ “… መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና…” ይላል፤ የተዛባ ግንኙነት በሚል የተገለጸው ደግሞ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን የሚያቀነቅን ነው።
ይህ መሆኑ ታዲያ የሀገራችን ብሔረሰቦች አንዱ ሌላኛውን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓል:: ይህም ለበርካታ ዓመታት ሲቀነቀን የቆዬ በመሆኑ ጦሱ በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን እያመሳት ይገኛል። በተለይ ደግሞ አማራው ላይ በተሠራበት የተሳሳተ ትርክት ምክንያት በመላው ሀገሪቱ በማንነቱ ምክንያት የችግሩን ገፈት እየተጎነጨ ነው።
‘ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት’ መጽሐፍ ደራሲ ቹቹ አለባቸው (ዶ/ር) በመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም የበኩር ዕትም የተሳሳተ ትርክትን በተመለከተ ቆይታ አድርገው ነበር። ዶ/ር ቹቹ እንዳሉት የአማራ ሕዝብ ችግሮች ውስብስብ እና ሥር የሰደዱ ናቸው፤ የአማራን ሕዝብ ማዳከም የተጀመረውም ከጣሊያን ወረራ በፊት መሆኑን ነው ያብራሩት። የተለያዩ የውጭ ጸሐፍት አማራን አስመልክተው ይጽፏቸው የነበሩ ጽሑፎች በተለይ አማራን እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን ነጥሎ በማጥቃት ሌላው ዓለምም ይህንን ሕዝብ በመጥፎ እንዲስለው ጥረት ያደርጉ ነበር ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ቹቹ ማብራሪያ አማራው በተሠራበት የፈጠራ ትርክት ምክንያት ላልበደለው በደል መከራን እንዲያጭድ የተደረገ ሕዝብ ነው። ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችም በተሠራበት መጥፎ ትርክት ምክንያት እንደ ጨቋኝ ነው የሚመለከቱት። በዚህ ስሁት ትርከት ምክንያት ታዲያ ያልደረሰበት መከራ እና ግፍ የለም።
ሀገራችን የበርካት ብሔሮች መገኛ ናት፣ በርካታ ብሔሮች ላላቸው ሀገራት ደግሞ የደራሊዝም ሥርዓት ተመራጭ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በሀገራችን ፌደራሊዝም የተዋቀረበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ዶ/ር ቹቹ ይናገራሉ። ለአብነትም የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን መግቢያ አድርጎ የተዋቀረው ሕገ መንግሥት አማራን በሚጎዳ መልኩ የተረቀቀ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፤ ይህንን በተመለከተ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የአማራ ሕዝብ በተሳሳቱ ትርክቶች ምክንያት ግፎች ሲፈጸሙበት እንደቆዩ አውስተዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም እና ለሀገር ግንባታ ሂደቱ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በሕዝብ አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ያሉት አቶ አረጋ፣ የአማራ ሕዝብም የተሳሳቱ የፖለቲካ ትርክቶች ታርመው በምክክር ወደ ተሻለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያነሳ መቆየቱን አክለዋል። በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሐሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽዖ ለማድረግ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የጠቆሙት።
በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ሀገራዊ ታሪክን እና ሰላምን በተመለከተ ምሁራን የተሳተፉበት ምክክር ተካሂዶ ነበር። በምክክሩ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዘዳንት ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ታሪክን የማያውቅ ዜጋ መሠረት እንደሌለው በማንሳት “የወል ትርክትን በመገንባት ሀገርን ማሳደግ ይቻላል” ብለዋል።
በምክክሩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ታሪክን በአግባቡ አለመያዝ እና አለመጠቀማችን በአሁኑ ወቅት ለሚስተዋሉ አለመግባባቶች ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፤ ያደጉ ሀገራት ለዕድገት መሠረታቸው ታሪክን በአግባቡ ሰንደው በመያዛቸው ነው፤ በመሆኑም ሀገርን ወደ ዕድገት ጎዳና ለማሻገር እና ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለመፍጠር ታሪካችንን በአግባቡ እውነታውን ሳይለቅ አክብሮ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ፌዴራላዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አስፈላጊዋ ቢሆንም ሲዋቀር ግን ብዙ ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት ዶ/ር ቹቹ ተናግረዋል። በተለይ የሕዝብን አንድነት የሚያፀና መሆን ይኖርበታል:: በፌዴራል ሥርዓቱ ምክንያት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር መጋጨት እና የቂም ቁርሾ መያዝ የለበትም። ከችግሮቹ በመማር፣ ችግሮቹን ለማስወገድ መሥራት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የሚጠበቅ አንኳር ጉዳይ ነው። መንግሥትም ይህንን ጉዳይ በተገቢው መልኩ መረዳት አለበት። የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም የሕዝብ አንድነት እንዲጠነክር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም