የተሳካ ህልም

0
280

አያልነህ ማሩ ይባላል፤ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው። በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው አያልነህ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከብቶችን ማገድ፣ መንከባከብ እና ከእነርሱ ጋር መዋል ሐሴት ይሰጠው እንደነበር ያስታውሳል::

የበፊቱ ሕጻን የዛሬው ወጣት እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ሊሰማራበት የሚፈልገው የሥራ ዘርፍ ከእንስሳት ሀብት ውጭ የተለየ ማሰብ አልቻለም:: ህልሙን እውን ለማድረግም ትምህርቱን ከ11ኛ ክፍል አቋርጦ  በወተት ሀብት ለመሰማራት ወሰነ:: ፍላጎቱን ለማሳካት ግን ላሞችን የሚገዛበት  በቂ ገንዘብ አጣ።

አያልነህ  ለጊዜው በወተት ሀብት መሰማራቱን በይደር በመተው  በነበረው ጥቂት ገንዘብ በንብ ማናባት ሥራ ላይ ተሰማራ። ”እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል” እንደሚባለው  ህልሙን ለማሳካት  ከማር ምርቱ ያገኘውን ገቢ ከማጠራቀም  ጎን ለጎን አንዲት ላም በመግዛት የወተት ሀብት ሥራውን ጀመረ:: ወጣቱ ከማር ምርት ጎን ለጎን በ2007 ዓ/ም  የጀመረውን የወተት ሀብት ልማት ሥራ  ቀስ በቀስ  የላሞቹን ቁጥር በማሳደግ የገቢ ምንጩን ከፍ ማድረጉን ያነሳል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት ሌት ከቀን  እየሠራ ባለበት ወቅት  አያልነህ ችግር ገጠመው:: ጊዜው 2011 ዓ/ም  ነው:: ባልጠበቀው መንገድ 12 የወተት ላሞቹ እና 200 የንብ ቀፎዎቹ ተዘረፉበት:: የተወሰደበትን ንብረት ለማስመለስ  ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለት:: በገጠመው ችግር ተስፋ ያልቆረጠው ወጣት አያልነህ የተረፉ የወተት ላሞችን በመያዝ  የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ በሰጠው የሥራ ቦታ  ርባታውን አጠናክሮ ቀጠለ::

ወጣቱ ህልሙን እውን ለማድረግ በገጠመው የገንዘብ እጥረት እና በላሞቹ መዘረፍ ተስፋ ሳይቆርጥ  መፍትሔ በመስጠት ከሥራው ለአፍታም ሳይነጠል በመቀጠሉ  ባሁኑ ወቅት የላሞቹን ቁጥር ከአንድ ወደ 30 ማድረስ ችሏል:: ከዚህ ባለፈ 27 ጥጆች እና 30 ጊደሮች እንዳሉትም ወጣቱ ተናግሯል።  እንደየወቅቱ ሁኔታ ከአንዲት ላም በቀን ከ12 እስከ 14 ሊትር ወተት እንደሚያገኝ የገለፀልን አያልነህ  በቀን 400 ሊትር የሚደርስ ወተት ያገኛል።

”ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ባዶ ነው” የሚለው ወጣቱ አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በሥራው ላይ ጫናውን አሳርፎበታል:: የሚያመርተውን ወተት  ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሶ መሸጥ አለመቻሉን ሲናገር፤ ”ወተት በባህሪው ለተጠቃሚዎች በወቅቱ ካልደረስ የመበላሸት አጋጣሚው  ከፍተኛ ነው:: በከተማ አስተዳደሩ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት በኩልም በቂ የገብያ ትስስር እየተፈጠረ አይደለም:: በዚህም የልፋታችን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም” በማለት ነው።

ወጣቱ ህልሙን እውን ከማድረግ አልፎ ለ27 ወጣቶች ቋሚ እና ጊዚያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል::  በቦታው በተገኘንበት ወቅትም ባለታሪካችን ሠርቶ የሚያሠራ ታታሪ መሆኑን አረጋግጠናል:: እርሱም ሆነ ሌሎች ወጣቶች ከዚህ በተሻለ ሥራቸውን ማጠናከር እንዲችሉ ግን የመንግሥት ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኀይሉ ዓለሙ እንደሚሉት በዶሮ ርባታ፣ በማር ምርት ፣ በዓሳ እና በወተት ሀብት ልማት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል:: ዘርፎቹ  የሥራ እድል መፍጠሪያ ብቻ ሳይሆኑ ለወጣቶች የሀብት ምንጭም ሆነዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶችን በስድስት ማህበራት በማደራጀት በወተት ሀብት ልማት ዘርፍ ማሰማራት መቻሉንም አቶ ኀይሉ አንስተዋል። በዚህም ከማህበራቱ በቀን ከ10 ሺህ ሊትር በላይ የወተት ምርት እየተገኘ እንደሆነ አረጋግጠዋል:: ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ዘርፉን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ኀይሉ ለዚህ ደግሞ ተቋማቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች የሚያነሱትን የገበያ ትስስር ችግር ለመቅረፍ ከትምህርት ቤቶች እና መሰል ተቋማት ጋር እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል::  ለዚህም በከተማዋ በሚገኙ 11 ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሀ ግብር በመጀመር የወተት ግብይቱ እንዲሳለጥ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት:: በቀጣይ ከመስከረም ወር ጀምሮ ደግሞ በ76 ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሀ ግብር በመጀመር የገበያ ትስስሩን ለማጠናከር ውጥን መያዙን አንስተዋል።

በጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሉ በ11 የገጠር ቀበሌዎች በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትን እና ግለሰቦችን በሙያ ለመደገፍ ታሳቢ ተደርጎ የክትባት እና የክትትል ሥራዎች የላሞችን እና የወተት ምርቱን ጤንነት በመጠበቅ በኩልም  እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው  አመላክተዋል።

አያልነህ ህልሙን ለማሳካት የገጠሙትን መሰናክሎች አሸንፎ  ዛሬ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሥራ እድል ፈጥሯል:: ታዲያ ሌሎች ወጣቶችም ሥራን ሳይንቁ አያልነህ  ያለፈበትን መንገድ ተከተሉ መልእክታችን ነው::

 

(አዲስ አለማየሁ)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here