የተሻሻለው የመሬት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ

0
194

የፌዴራል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ላይ   ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን ሕጐችን ያወጣል፡፡  በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ሕግ ያወጣል ይላል፤ በተለይም  የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ድምበር ተሻጋሪ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚያስተሳስሩ ወንዞችና ሐይቆች አጠቃቀምን በተመለከተ ያለውን ሕግ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሰረት በፌዴራል ደረጃ በ2016 የወጣው አዲሱ የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 1324/16 ወደ ክልል ወርዶ በየደረጃው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ይህን ተከትሎም የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በተሻሻለው የመሬት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከከተማ ልማት ክላስተር መሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በመድረኩ ላይ ከዚህ በፊት እያገለገለ የቆየው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር መሬት አሥተዳደር አዋጅ ቁጥር 252 /2009 እና የአሁኑ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ባሻሻላቸው ሕጎች ዙሪያ ነው ውይይት የተካሄደው።

በክልሉ የገጠር መሬት የሕግ ባለሙያ አቶ አዲሱ ሞላ እንዳሉት በፌዴራል ደረጃ የተሻሻለው 1324/2016 ረቂቅ አዋጅ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ሀገሪቱ ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ጋር ለማስተሳሰር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ አዋጁ የገጠር መሬትን በአግባቡ ለማደራጀት ሚናው ጉልህ እንደሆነ እና የመሬት ባለይዞታ መብትን ከበፊቱ በተሻለ   እንዳጎናጸፈው ተገልጿል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መግቢያ በግልፅ እንደሚያትተው  የሀገሪቱን ሥነ ምህዳር ያገናዘበ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ለማውጣት እና ለማደራጀት፣ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የአዋጁ መሻሻል የአርሶ አደሩን፣ የከፊል አርብቶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ የኑሮ ደረጃ ሀገሪቱ ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እድገት ጋር ለማራመድ እንዲቻል ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  አርሶ አደሩን፣ ከፊል አርብቶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በመሬት ይዞታው ላይ ያለውን የንብረት መብት ለማጠናከር የተሻሻለ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት አሰፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ለከፊል አርብቶ አደርና ለአርብቶ አደሩ ባህላዊ የመሬት አጠቃቀም እና አጠባበቅ ሥርዓት ጠቃሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው  ስለሆነ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታ መብት በተመለከተ በሕገ-መንግሥቱ እውቅና የተሰጠው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ እና በማስፈፀሚያ ሕግ ማስደገፍ በማስፈለጉ እና የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማደራጀት እንዲሁም ለተጠቃሚው በአግባቡ ለማሰራጨት የሚያስችል ምቹ የሕግ ማዕቀፍ በመፍጠር በኩልም ረቂቅ አዋጁ ጉልሕ አስተዋጾ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ የባለይዞታዎችን የይዞታ ዋስትናን በማጠናከር በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና አጠቃቀም ላይ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት፣ በመሬት ላይ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ ፣ መንግሥት እና ተጠቃሚዎች አስተማማኝ የሆነ መረጃ የሚያገኙበትን ዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መውጣቱን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የተለያዩ የሀገሪቱን የሥነ ምህዳር ቀጣናዎች ያገናዘበ ዘላቂ የገጠር መሬት አጠቃቀም ዕቅድ በማውጣትና በመተግበር የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ በማስፈለጉ፤ የሴቶች እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት የሚያረጋግጥና የሚያጠናክር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አካታች ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

አቶ አዲሱ እንደሚሉት የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የገጠር መሬትን ስለማግኘት፣ የገጠር መሬት ይዞታና ዓይነቶች፣ ባለይዞታዎች በመሬታቸው የሚኖራቸው መብቶች፣ የገጠር መሬትን ስለመለካት፤ ስለመመዝገብ እና የምስክር ወረቀት ስለመስጠት በዝርዝር ያካትታል። የወል መሬት እና አጠቃቀም፣ በገጠር መሬት ላይ ስለሚነሱ ክርክሮች፣ መፍትሔዎች፣ የገጠር መሬት ምዝገባ ፣ ቅየሳ እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ረቂቅ መሆኑም ተመላክቷል።

አዋጁ ሲጸድቅ ከዚህ በፊት በክልሉ በገጠር  እና በከተማ ይከሰቱ  የነበሩ የሥራ ማነቆዎችን የሚፈታ እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል። በተለይም ይላሉ አቶ አዲሱ በከተሞች መስፋፋት የሚከሰቱትን የወሰን ግጭቶች ለመፍታት እንዲሁም   የባለይዞታዎችን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ካሳ ከፍሎ  ርክክብ ለመፈፀም የሚቻልበት መንገድን በግልጽ ያሰፈረ ነው፡፡

የማህበራዊ ተቋማትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና ባለሃብቶችን  በተመለከተም ረቂቅ ሕጉ የባለይዞታነት እና የመጠቀም መብትን የሰጠ ነው፡፡ ለአርሶ አደሩ መሬቱን  የማከራየት ፣ የመጠቀም እና የማውረስ ሰፊ መብትም ይሰጣል፡፡

ሕገ መንግሥቱ መሬትን  መሸጥ መለወጥ ቢከለክልም  ለባለይዞታው ደግሞ በመሬቱ ላይ  እውቀቱን ፣በጊዜውን እና ገንዘቡን ተጠቅሞ  ላፈራው ንብረት የመሸጥ መብት ይሰጣል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የገጠር መሬትን  በውርስ እና በስጦታ  በማንኛውም የሙያ መስክ ለተሰማራ ሰው የማበርከት መብት ያስጠበቀ እንደሆነም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የክልሉን አርሶ አደሮች እና ባለሃብቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት በከተማ ዙሪያ ያለን መሬት መንግሥት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በማንኛውም ጊዜ ከፈለገ ተመጣጣኝ ካሳ ከፍሎ የማንሳት ሥልጣን ስላለው አዋጁ በከተሞች ዕድገት እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ችግር እንደማያመጣ ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ ከነባሩ አዋጅ በርካታ የተለዩ ነገሮችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ረቂቁ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን እና የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅዱንም ታሳቢ ያደረገ ነው።

ረቂቅ አዋጁ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ፣ የመሬት አጠቃቀምን የሚያሻሽል መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይ አዋጁ የወጣቶችን ተጠቃሚነት እና ለባለሃብቶች የብድር ዋስትና ይበልጥ የሚያረጋግጥ እንዲሆን በትኩረት ማየት እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።

አዋጁ በየጊዜው በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲሻሻል ዕድል የሚሠጥ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 7   ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here