የተቀናጀ ጥረት የወባ ስርጭትን ለመግታት!

0
128

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር ከሁለት ሺህ  ጀምሮ በነበሩት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ የወባ ስርጭት በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ታይቷል፡፡ መረጃው ጨምሮ እንደጠቆመው በእነዚህ ዓመታት የበሽታው የስርጭት መጠን  በወረርሽኝ ደረጃ ብዙም ተከስቶ አያውቅም፡፡ በተለይም በ2019 የተመዘገበው የሕሙማን ቁጥር  ዘጠኝ መቶ ሺህ የነበረ ሲሆን  ይህም በተጠቀሱት ዓመታት ከተመዘገበው አነስተኛው ቁጥር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ከ2022 በኋላ በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የወባ በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ አገርሽቷል፡፡ በዚህም መሠረት በ2022 ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት በ3 ሚሊዮን 300 ሺህ ጨምሮ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን፣ በ2023 ደግሞ በ3 ሚሊዮን 200 ሺህ ከፍ ብሎ አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር ተመዝግቧል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ ከሐምሌ 2016 እስከ ኅዳር 2017 ባሉት ወራት በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮኝ 95 ሺህ በላይ የወባ ሕሙማን ቁጥር ተመዝግቧል፡፡

ሆኖም በቀደሙት ጊዜያት በተለየ መልኩ  የበሽታው ስርጭት ከሰሞኑ መጠነኛ መቀነስ አሳይቷል፡፡ ለአብነትም በኅዳር ወር ሦስተኛ ሳምንት 74 ሺህ ያህል የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር ተመዝግቧል፡፡ ይህ ቁጥር ከኅዳር ወር ሁለተኛ ሳምንት አኳያ ሲታይ መጠነኛ መቀነስ ተስተውሎበታል፡፡

የበሽታው ስርጭት ሊቀንስ የቻለው ስርጭቱን ለመከላከል ጥረት በመደረጉ ነው፡፡ ከተደረጉት ጥረቶች መካከልም ስርጭቱን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቋሚነት ውይይቶች መደረጋቸውና የመከላከል ስልቶች ተቀይሰው መተግበራቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ በመከላከል ጥረቱ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ መቻሉ ስርጭቱ እንዲቀንስ ረድቷል፡፡

በዚህም መሠረት፣ “የዐርብ ጠንካራ እጆች የወባን ስርጭት ይገታሉ!” በሚል መሪ ሀሳብ ከ480 በላይ በሆኑ ጤና ጣቢያዎች ዘወትር ዐርብ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች ተከናውነዋል፤ በተጨማሪም በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር  የወባ ስርጭትን መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፤ በሀያ ሁለት ወረዳዎች ለ233 ቀበሌዎች ተደራሽ የሆነ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭትም ተከናውኗል፡፡

በእነዚህ ተግባራት ምክንያት የወባ በሽታ ስርጭት መጠነኛ መቀነስ ቢያሳይም አሁንም  የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ከአማራ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው የቆዳ ስፋት ለወባ መተላለፊያ ምቹ እና 80 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ ለወባ የተጋለጠ ነው፡፡ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ያለው ወቅት ደግሞ ዋነኛ የወባ በሽታ መተላለፊያ ሲሆን ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜም ስርጭቱ በመለስተኛ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ በእነዚህ ወቅቶች የሚጥለውን የክረምት እና የበልግ ዝናብ ተከትሎ ወባ አስተላላፊ ትንኞች ምቹ የመራቢያ ሁኔታን ስለሚያገኙ ቁጥራቸው በጣም ይጨምራል፤ ይህም የወባ በሽታ ስርጭት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

ስለሆነም ስርጭቱን ለመግታት ለወባ ስርጭት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እንዲሁም የመራቢያ ወቅትን መሠረት በማድረግ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ርብርብ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡  ይህ የወባ ስርጭትን የመከላከል ተግባር ላንድ ወገን የሚተው አለመሆኑን በማጤንም ቅንጅታዊ ሥራን ይበልጥ በማጠንከር ወረርሽኙን ለመግታት መረባረብ ያስፈልጋል፡፡፡፡

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here