“የተበደርኩትን እንደከፈልኩ ነው የምቆጥረው”

0
144

በሀገራችን ሙዚቃ ከ40 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ ከቀበሌ ኪነት ቡድን ተነስቶ፣ በከተማ ኪነት፣ ቀጥሎም በትምህርት ቤት ባንድ እንዲሁም በምሽት ክለብ ሠርቷል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና በባሕር ኃይል ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ሙዚቃ መክሊቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ለታዋቂ ሙዚቀኞች ሙዚቃ ከማቀናበር እስከ ሙዚቃ ማስተማር፣ ከሙዚቃ ማስተማር እስከ የሙዚቃ ዳኛነት ድረስ በሙያው ቆይቷል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የአማተርነት ጉዞውን ከስቃኘናችሁ ከሙዚቃ መምህር እና ባለሙያ ሰመረ ከበደ ጋር ያደረግነው የመጨረሻ ክፍል ቆይታ እነሆ፡፡

ከአማተርነት ወጥተህ ወደ ባንድ የገባህበትን አጋጣሚ ምን ነበር?

ከመሬት ተነስቶ ሙዚቀኛ መሆን አይቻልም፤ በዕውቀት እና በትምህርት መደገፍ ያሻል፡፡ ብዙ ጊዜየን ያሳለፍኩት ስለሙዚቃ በመማር ነው፡፡ ደረጃ በደረጃ ጊዜው እየፈቀደ ሲመጣ የምሽት ክለቦች መሥራት ጀመሩ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ጁዲ ክላሲካል የሚባል ቤት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በጁዲ ክላሲካል ቤት ውስጥ በመጀመሪያ ያገኘኋት ሕይወት አያሌውን ነው (የአያሌው መስፍን ልጅ)፡፡ እሷን ሳገኛት በጣም ነበር ደስተኛ የሆንኩት፤ በወቅቱ ከፍተኛ ዝና ነበራት፡፡ እየሰፋ ሲሄድ በክለብም በሰርጎችም እንዲሁም በባንድም ደረጃ ከተለያዩ ድምጻዊያን ጋር እየተገናኘሁ  መሥራት ጀመርኩ፡፡

በተለይ ጃአካልስ የሚባል ባንድ ተቋቁሞ ነበር፡፡ በተለያዩ ኩነቶች ላይ እየተጋበዝን ሙዚቃ እናቀርባለን፡፡ የተለያዩ ድምጻዊያን እየመጡ አብረውን ይጫወቱ ነበር፡፡ ለአብነት አረጋኸኝ ወራሽ፣ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ ሀመልማል አባተ፣ ተፈራ ነጋሽ፣ እያዩ ማንያዘዋል፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ታደለ ሮባ እና ሌሎችም ድምጻዊያንን አጅበናል፡፡

ሼክ መሐመድ አላሙዲን ሸልመውሀል፤ እስኪ አጋጣሚውን ንገረን?

ጁዲ ክላሲካል የሚባል የምሽት ክለብ ውስጥ እየሠራሁ ነው፡፡ ጊዜው ደግሞ 1997 ዓ.ም ነበር፡፡ አንድ ቀን ደምበኛ አልገባም ነበር እና ዝም ብለን ተቀምጠን እያለ ሱፍ የለበሱ ሰዎች ገቡ፡፡ በክለቡ ውስጥም ዙሪያውን ራቅ ራቅ ብለው ቆሙ፡፡ እረ ይሄ ነገር ምንድን ነው? ብለን በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ መጫወት ጀመርን፡፡ የመጡት ሰዎች ዙሪያውን አይተው ተመልሰው ወጡ፡፡ በኋላ በጣም ብዙ ሰው እና መኪና ወደ ክለቡ ተሰልፎ መጣ፡፡ የክለቡ ውስጥም በሰው ተጨናነቀ፡፡ በዚህ መሀል ሼክ መሐመድ አላሙዲን ሰውን ሰነጣጥቀው መጡ፡፡ ከዚያም እሪኩም የሚለውን ዘፈን ተጫወቱልኝ አሉን፡፡ ድምጻዊ ሕይወትም ነበረች፡፡ ሕይወት እሪኩም የሚለውን ዘፈን እኛ አጅበናት በደንብ አድርጋ ተጫወተችው፡፡ ልክ ስንጨርስ ለእያንዳንዳችን 10 ሺህ ብር ሰጥተውን ሄዱ፡፡ ያኔ በወር 150 እና 200 ብር ለነበረ ደሞዝ ተከፋይ 10 ሺህ ብር እጅግ ብዙ እና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ብሩን ስንቀበል ያለንበት ጠፋን (ሳቅ)፡፡

ድምጻዊያንን ስታጅብ ምን የተለየ ገጠመኝ አለህ?

ሙዚቃውን በስህተት አበላሽቼ በደንብ የተጨበጨበልኝን ቀን አልረሳውም፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ኪቦርድ እየተጫወትኩ የሆነ ሰው ሰክሮ ከምት (ዜማ) ውጪ ይደንሳል፡፡ ሰውየውን ማየት አልፈለኩም፡፡ ቤቱን ቃኝቼ ስመለስ ዝምብሎ ሲውረገረግ እና ሲንገዳገድ አየዋለሁ፡፡ አሁንም አይኔን ወደ ሌላ ቦታ ልኬ ስመልስ እሱን አየዋለሁ፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ወደ እሱ ተመልሼ ሳየው የሆነ ነገር አንሸራቶት ወደቀ፤ በድንጋጤ ኪቦርዱን ነካሁት፤ ሌላ ድምጽ አመጣ፤ ሰው በአድናቆት አጨበጨበ፡፡ ለስህተትም ይጨበጨባል ለካ አልኩ፤ ለብልሽት ጭብጨባ አላውቅማ፡፡ ሰው ይጮህብኛል ብየ ፈርቼ ነበር፤ በምትኩ አድናቆት ተቸረኝ፡፡

የኢትዮጵያን አይዶልን ጨምሮ በሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድሮች ዳኝነት እንዴት ልትሳተፍ ቻልክ?

ከምሽት ክለብ ቀጥሎ አብዛኛውን ጊዜየን የማሳልፈው ሰዎችን በሙያዬ በማስተማር፣ በማገዝ እና በማብቃት ነው፡፡ ለምሳሌ በተለያዩ የሙዚቃ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አማተር ሙዚቀኞችን አግዝ ነበር፡፡ ውጤታማም ሆነዋል፡፡ እነ ታደሰ መኮንን (ቀብራራው)፣ እነ አማረ ተስፋዬ እና ሌሎችም ሙያዊ ድጋፍ ሳደርግላቸው ነበር፡፡

በአጋጣሚ የኢትዮጵያን አይዶል ፕሮዳክሽን ማናጀር (የዝግጅት ሥራ አስኪያጅ) የነበረው ሰው በሙዚቃ ረጅም ዓመት ማሳለፌን ያውቃል፡፡ አዘጋጆቹ እና ቡድናቸው ለውድድር ከአዲስ አበባ ውጪ በየክልል አካባቢዎች መምጣት ጀመሩ፤ ወደ ደሴ ከተማም መጡ፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከሰርጸ እና ከየሺ ጋር ሦስተኛ ዳኛ አድርጎ መድቦኛል፡፡ በወቅቱ ሰርጸ እና የሺ እኔንም አያውቁኝም፤ ዳኛ መሆኔንም አያውቁም ነበር፡፡ እስከ ውድድሩ ዕለት ለሁለቱ ዳኞች እኔ አብሬያቸው እንደምዳኝ አልተነገራቸውም ነበር፡፡ ለእኔ ብቻ ተዘጋጅቼ እንድቀርብ ተነግሮኛል፡፡

የውድድሩ ዕለት ከሰርጸ እና ከየሺ ጋር ቀረብኩ፡፡ ሁለቱም እኔን ለመፈተን ሙከራ ያደርጉ ነበር፡፡ እናም እነሱ አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት እስኪ ምን ትላለህ? በማለት ቅድሚያ እድሉን ለእኔ ይሰጡኝ ነበር፡፡ ከምሰጠው አስተያየት ተነስተው “አሃ ይሄ ሰውየ ይችላል፤ ትክክለኛ ሙዚቀኛ ነው፤ የሚናገረው ነጥብ ነጥቧ ላይ ነው” አሉ፤ በዛውም በደንብ ተግባባን፡፡ ከዚያ በኋላም ሰመረን ያክል ትልቅ ሙዚቀኛ እያለ እየተጠቀምንበት አይደለም የሚል አስተያየት እንደተሰጠ ሰምቻለሁ፡፡

ሰመረ ከሙዚቃ ውጪ ግጥም ይሞክራል?

ሰዎች ግጥም ሲጽፉ ሳይ አይቅርብኝ ብየ መጻፍ ጀምሬ ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ያናድደኛል (ሳቅ)፡፡ እጽፍ እጽፍ እና ቀድጄ እጥለዋለሁ፡፡ የራሴ ግጥም አያስደስተኝም፡፡ ይህም የሆነው የሌሎችን ግጥም ማንበብ ስለምወድ ነው፡፡ የእኔን ግጥም ከሌሎች በሳል ገጣሚያን ግጥም ጋር ሳነጻጽረው የማይረባ ይሆንብኛል፡፡ በራሴ ግጥም አልደሰትበትም፤ የእነ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንን ግጥም አንብቤ የእኔን ግጥም ሳስበው ምን አይነት ደረጃ እንደምሰጠው መገመት ይቻላል፡፡

ዜማዎች ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ የሠራኋቸውን ዜማዎች በሙሉ መግለጽ አልችልም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብዙ መዝሙሮችን ደርሻለሁ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የደሴ ከተማን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እና ሁኔታ የሚገልጽ መዝሙር ይለቀቃል፡፡ ዜማው እና ሙዚቃ ቅንብሩ የእኔ ነው፡፡

በወሎ ኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ምን እየሠራህ ነው ያለኸው?

የግሌ ስቱዲዮ አለኝ፤ ነገር ግን በወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዳለው ሙሉ እና ያማረ አይደለም፡፡ በሁለቱም ግን እሠራለሁ፤ አስተምራለሁ፡፡ በተለይ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሙዚቃ መሣሪያ፣ የሙዚቃ ቅንብር እና የኮምፒውተር ሶፍትዌር ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን አደርጋለሁ፡፡

ክፍያ አለው?

ለእኔ ይሄን የመሰለ ቤት ማግኘት ከክፍያም በላይ ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ መሥራት ለእኔ ከክፍያ በላይ ነው፡፡ ክፍያ የሚያስጠይቀኝም ነገር አይኖርም፡፡ ሀገሬን እና ወገኔን እንዳገዝኩ፣ የተበደርኩትን ዋጋ እንደከፈልኩ ነው የምቆጥረው፡፡

የወሎ ባሕል አምባ ብዙ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ያፈራ ነው፤ አንተም በዚሁ ነው ያደከው፤ ምን ትዝታ አለህ?

ወሎ ባሕል አምባ እነ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ሒሩት በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ታምራት ሞላ፣ ምኒልክ ወስናቸው እና ሌሎች አንጋፋ ድምጻዊያን መጥተው ሥራቸውን የሚያቀርቡበት ነው የነበረው፡፡ እጅግ ትልቅ እና ታዋቂ ነበር፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን እና ሌሎች ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችን በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ የአወኳቸው በወሎ ባሕል አምባ ነው፡፡ ማስታወቂያ አስነግረው ከዚያም መጥተው ሕዝቡን አዝናንተው የሚመለሱበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ እነ ራስ ፣ ማዘጋጃ፣ ብሔራዊ እና ሌሎች ቲያትር ቤቶች ትልልቅ የመድረክ ሥራዎቻቸውን ይዘው መጥተው በወሎ ባሕል አምባ ያቀርቡ ነበር፡፡ ታዳሚውም እጅግ ብዙ ነው የነበረው፡፡ ሕዝቡ የእረፍት ጊዜውን እዚህ ነበር የሚያሳልፈው፡፡ ፊልም ባይኖር ቲያትር አለ፤ ቲያትር ባይኖር ሙዚቃ ድግስ አይጠፋም፡፡

ወደፊት ምን ለመሥራት አቅደሀል?

ከላይ እንዳልኩት የግሌ ስቱዲዮ አለኝ፡፡ በዚህም በርካታ ነሽዳዎች፣ መዝሙሮች፣ የባሕል ዘፈኖች እና ሌሎችን እሠራለሁ፡፡ የሙዚቃ ፍቅር ያላቸው ልጆች ሥራ ለመሥራት ሩቅ ሀገር መሄድ ሳይጠበቅባቸው ከእኔ ጋር መሥራት እንዲችሉ ለማድረግ እየሠራሁ ነው፡፡

በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በባሕል ቡድኖች እንዲሁም በባንዶች ያለኝን ልምድ እና እውቀት በሰፊው ለማካፈል አስባለሁ፡፡ የተሻሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲወጡ በስፋት አግዛለሁ የሚል ትልቅ ተነሳሽነት አለኝ፡፡ ከፈጣሪ ጋር ይሳካል ብየም አምናለሁ፡፡

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here