የተቦረቦረ የላይኛውን የጥርስ ክፍል “ኢናሜል”ን “ካልሼየም” እና “ፎስፈረስን” በያዘ ገንቢነት ወይም “ፕሮቲን” በተቀላቀለበት ወፍራም ቅባት መሙላት ጉዳቱን ከመባባስ አግዶ ስስ ንጣፍ ማልበስ ማስቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::
በእንግሊዝ የኖቲንግሀም ፎረስት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በተፈጥሮ መታደስ የማይችለውን የ“ኢናሜል” መቦርቦር “ካልሼየም” እና “ፎስፈረስን” በያዘ ገንቢ ወፍራም ቅባት ውህድ በመሙላት መባባሱን መከላከል ችለዋል::
ከተመራማሪዎቹ አንዱ አልሻሮ ማታ በምርምር ሙከራዎቻቸው በወፍራሙ ቅባት የተቦረቦረ የላይኛውን ጥርስ መሙላት ከሣምንታት ቆይታ በኋላ ጠንካራ ሽፋን ማብቀል ማስቻሉን አረጋግጠዋል:: ከሙሌቱ ስር የሚፈጠረው ስስ ልባስም ከተፈጥሯዊው ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል::
የጥርስ የላይኛው ሽፋን “ኢናሜል” መቦርቦር በዓለማችን ግማሽ ያህሉን ህዝብ ያጠቃል:: ጉዳቱ በሚፈጥረው ክፍተትም የምግብ ቅሪት ገብቶ መበስበስ እና ቁስለት አስከትሎ ሊያመረቅዝ እንደሚችል ነው የተብራራው -በድረ ገጹ::
ምርምሩን ከመሩት ምሁራን ዶ/ር አብሻር ሀሰን “ኢናሜል” በጥርስ ላይ በሀይል ወይም በ “ኬሚካል” ውህድ የሚደርስ ጉዳትን መከላከል የሚያስችል ጥንካሬ ያለው መሆኑን ነው ያረጋገጡት፤ ነገር ግን የተጐዳ ወይም የተቦረቦረን ለመሙላት እና ለማደስ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል::
ተመራማሪዎቹ ወፍራም ውህድ ቅባት የተሞላው የተቦረቦረ ጥርስ በስረኛው ክፍሉ ስስ አብረቅራቂ ሽፋን መልበሱን መሰረት አድርገው እውነታዊውን ሂደት የቀፀለ ምስለ ሙከራዎችን አካሂደዋል:: በሙከራቸው ውህዱን የተሞላው ጥርስ በማኘክ፣ በመቦረሽ ወይም በማፅዳት እና አሲድነት ባለው ምግብ ሳቢያ መጐዳት አለመጐዳቱን ፈትሸዋል::
አዲሱ የሚሞላው ወፍራም ውህድ ያስገኘው ውጤትም ከጤናማ “ኢናሜል” ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን በማረጋገጥ ነው ያደማደሙት -ተመራማሪዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


