የተነቀለዉ እንቅፋት

0
58

በቻይና – ጂያንግዙ፣ ዢጂያንግ እና ሻንጋይን ግዛትን ለማገናኘት በአምስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሲገነባ በነበረው የባቡር መስመር ላይ የነበረ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ባለንብረት ባቀረቡት የካሳ ጥያቄ እና በተወሰነላቸው መጠን ሳይስማሙ ለሁለት ዓመታት ቆይተው በመጨረሻ የመንግሥትን ውሳኔ መቀበላቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::

በ2020 እንደ አውሮፓውያኑ ዓመት ነበር ቻይና ዢጂንግ እና ሻንጋይ የተሰኙ ግዛቶችን ማገናኘት የሚያስችል ፈጣን የባቡር መስመር መዘርጋት የጀመረችው፡፡ እናም  163 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የባቡር መስመር ተዘርግቶ መጠናቀቂያው ሲቃረብ በጂያንግዙ ግዛት በሀዲዱ ማለፊያ መካከል የነበረ የግለሰብ ቤት ከመጠናቀቅ አሰናክሎታል:: የመኖሪያ ቤት ባለቤቱ ከመንግሥት የጠየቀው ካሳ ካልተከፈለው እንደማይነሳ አስታውቋል፡፡

ሌሎች በቀጣናው የነበሩ ባለንብረቶች በካሳ ክፍያ ተስማምተው ሲነሱ “አውንት ዛንግ” የተሰኙት ባለንብረት አሻፈረኝ ማለታቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል::የባቡር መንገዱ ከሁለት ጐን ተዘርግቶ በቤቱ አቅራቢያ ባለ ወራጅ ወንዝ ላይ ድልድይ ተሰርቶ ቤቱ ብቻ ሲቀር መንገዱን ከመገናኘት ገቶ ለሁለት ዓመታት ምረቃው እንዲዘገይ አስገድዷል:: የቤቱ ባለንብረት ለካሬ ሜትር 14000 ዶላር ወይም 100,000 ዮዋን የቻይና ገንዘብ ነው የጠየቁት፡፡ የግንባታ የበላይ ኃላፊዎች ግን የተጠየቁትን መክፈል እንደማይችሉ ያሰውቋቸዋል፡፡

ግለሰቧ በግትርነታቸው በመግፋታቸው እና የመጠናቀቂያው ጊዜ መራዘሙን ተገንዝበው በድጋሚ ባለብረቷ ሲጠየቁ ይባስ ብለው መጀመሪያ ከጠየቁት የካሳ ጥያቄ በእጥፍ አሳድገውታል፡፡ ይህ ማለት ለካሬ ሜትር በ28 ሺህ ዶላር ስሌት በጠቅላላው ለቤቱ 14 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ነው ለንባብ የበቃው::ምክንያት ከሚቆም የጠየቁትን ይከፍላሉ የሚል እምነት እንደነበራቸው ነው ድረ ገጹ ያስነበበው:: የግዛቱ ባለስልጣናት  ግለሰቧ ሀሳባቸውን ይቀይራሉ በሚል በትእግስት ቢጠብቋቸውም አንድ ዓመት አልፎ ሁለተኛው ሲቃረብ በተለያዩ መገናኛ አውታሮች የግለሰቧን ስግብግብነት፣ ኘሮጀክቱ የፈሰሰበትን ወጪ እና የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በማንሳት ያብጠለጥሏቸው ጀመር፡፡

ይህንን የሰሙት ባለንብረቷ ከየአቅጣጫው በደረሰባቸው ወቀሳ በተወሰነላቸው ካሳ መስማማታቸው በማጠቃለያነት ለንባብ በቅቷል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here