ከ480 ቀናት በላይ ያስቆጠረው የሃማስ እስራኤል ጦርነት ከብዙ ውድመት በኋላ በሁለቱም ወገን ሲገፋ ቆይቶ አሁን ግን ዘላቂ ሰላምን ሊያመታ የሚችል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የተገባ ይመስላል።
መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም በእስራኤል የወደብ ከተማ በሆነችው ኪቡዝ ውስጥ በአይሁድ ባሕል ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ዮምኪፑር በዓልን ለማክበር በሺዎቹ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በደስታ እያከበሩ ነበር። በአካባቢው የነበረው የእስራኤል ሠራዊት ካምፕ የዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ የወትሮ ኃላፊነቱን ለመወጣት በተጠንቀቅ ላይ ነበር።
ነገር ግን በዓለም ወደር የማይገኝለት የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ምንም አይነት ፍንጭ ሳይኖረው ሀማስ በረቀቀ ወታደራዊ ዘመቻ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ገብቶ ነበር። እስራኤላውያኑ ሀገር አማን ብለው በፌሽታ ዓመት በዓላቸውን እያከበሩ ባለበት ሀማስ በድንገት በአየር፣ በየብስ እና በባሕር በተቀናጀ መልኩ አካባቢውን በተኩስ ናዳ ናጠው። ጥቃቱም አንድ ሺህ 200 እስራኤላውያንን በመግደል እና 250 ሰዎችን በማገት ተጠናቀቀ።
በዚህም ምክንያት እስራኤል ሀማስን ለማጥፋት እና የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ በሚል በሃማስ ላይ ሙሉ ጦርነት አወጀች። እየወሰደችው ያለው እርምጃም ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ሕይወት ቀጠፈ፣ በርካታዎችን ለአካል ጉዳት ዳረገ፣ ጋዛም ወደመች።
እስራኤል በምትወስደው እርምጃ ጋዛዉያንን በተለይም ሴቶችንና ህፃናትን በመጉዳቱ እና የከፋ ኢሰብዓዊ ቀውስ በማስከተሉ ዓለም አቀፍ ውግዘት ቢያስተናግድም ጥቃቱን ለማቆም ግን በጂ አላለችም ነበር:: ቀውሱ የቀጣናውን መረጋጋት እያወከ እና ሌሎችን ሀገራት እና ቡድኖች እያሳተፈ በመምጣቱ በአሜሪካ አማካይነት የተኩስ አቁም የስምምነት ሰነድ ለመንግሥታቱ ድርጅት ቀርቦ መፅደቁ ይታወሳል። ነገር ግን በሁለቱም ተፋላሚዎች እየቀረቡ በነበሩ ቅድመ ሁኔታዎች ተፈፃሚ ሳይሆን ቀረ።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተኩሱ በዘላቂነት እንዲቆም ማድረግ እና ተሟጋቾችን እና እስረኞችን የመለዋወጥ ሀሳብ የነበረው ሲሆን ስምምነቱን በታቀደበት ፍጥነት ሳይፈፀም ወራት ነጎዱ። እናም ይህ መዘግየት የታጋቾችን ተስፋ እያመናመነ የመጣ ክስተት ተፈጠረ።
ባለፈው ጳጉሜ ወር 2016 ዓ.ም ስድስት እስራኤላውያን ታጋቾች ተገድለው እንደተገኙ የተሰማው ዜና የቴል አቪቭን ጎዳናዎች በተቃውሞ ሰልፎች ንጧት ነበር:: በጋዛ ከዐሥር እስከ ሀያ ሜትር ጥልቀት ባለው ዋሻ ውስጥ ተጥለው መገኘታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ የሞቱበት ምክንያት በውል ባይታወቅም ተረሽነው ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል::
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሀማስ ለታጋቾቹ ሞት ተጠያቂው የእስራኤል መንግሥት በማሳወቅ ይህ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ባለመቀበሏ ታጋቾቹ የከፈሉት ዋጋ መሆኑን እና አሁንም ጥቃቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
የእስራኤል መንግሥት በጋዛ የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሮ ከቀጠለ ተጨማሪ ታጋቾችን መግደሉን እንደሚቀጥል ያስታወቀው ሃማስ ለሚፈጠር ችግር ሁሉ ተጠያቂው የእስራኤል መንግሥት እንደሚሆን ሲ ኤን ኤን አስታውቋል::
ወዲያው የቴል አቪቭ ጎዳናዎች የእስራኤል መንግሥትን በሚቃወም ሕዝባዊ ተቃውሞ ተሞላች። መንግሥት ወዲያውኑ ስምምነቱን ፈፅሞ ታጋቾችን ከእነ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረጋቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል::
“የታጋቾች ጎዳና” እስከ መባል የተሰየመው የቴል አቪቭ ጎዳና በየቀኑ ሰልፍ በሚያደርጉ ዜጎች እየተስተጋባ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት የማታ ማታ አዲስ ተስፋን አሳዬ። የተኩስ አቁም ስምምነቱም ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እፎይታ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።
ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ውጤታማ ሳይሆን የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት በተለይ የፍልስጤማውያንን መከራ አብዝቶት ነበር ቀጠለው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የተፈጸመው የተኩስ አቁም ስምምነት እስረኞችን እንዲለዋወጡ ከማድረግ ባለፈ ጋዛም መጠነኛ እፎይታ እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ እስራኤል እና ሀማስ መካከል የተረሳው የተኩስ አቁም ስምምነት በቀይ መስቀል አማካይነት መፈፀም እንደጀመረ ሀማስ ከዓመት በላይ ያገታቸውን እስራኤላውያንን እንዲለቅ በምላሹም እስራኤል በተለያዬ ምክንያት ያሰረቻቸውን ፍልስጤማውያንን እንደምትለቅ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተስማምተዋል።
ስድስት ሳምንታትን በሚቆየው የመጀመሪያው ዙር ስምምነት ሀማስ 33 ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን እስራኤልም ከጦርነቱ በፊት በእስራኤል ሠራዊት እና ንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል በሚል ካሰራቸው መካከል 1500 ያክል እስረኞችን እንደሚለቅ ይጠበቅ ነበር። በመሆኑም እስካሁን ሀማስ መጀመሪያ ላይ ከለቀቃቸው አራት ሴት የእስራኤል ወታደሮች በተጨማሪ 18 ታጋቾችን ለቀይ መስቀል አስረክቧል። እስራኤልም በአውቶቡስ ሙሉ እስረኞችን በመልቀቅ ቀይ መስቀል ለየቤተሰቦቻቸው አስረክቧል።
በሌላ በኩል በልውውጥ ሂደቱ ወቅት ሀማስ በቀጥታ ስርጭት ኃይሉን ለዓለም የሚያሳይበት እንደ ጥሩ የፕሮፓጋንዳ አጋጣሚ አድርጎ እንደተጠቀመበት ፍራንስ 24 ቴሌቪዥን ዘገቧል። ቡድኑ የሚለቀቁ ታጋቾችን ለተሰበሰቡ ጋዛውያን በማሳየት አሸናፊነቱን ለማሳየት ተጠቅሞበታል ነው የተባለው። የእስራኤልን መሸነፍ በማስተጋባትም ለታጋቾቹ ሰብዓዊ ርህራሄን ያልነፈገ ድርጅት መስሎ ለመታየት መሞከሩን የዜና ምንጩ ዘግቧል።
ታይም ቱደይ ከተሰኘው ድረ ገጽ የወጣ አንድ ዘገባ ከእነ ህፃን ልጇ የታገተች እና የተላቀቀች እስራኤላዊት ሀማስ በእገታ ወቅት ላሳያት ሰብዓዊ ርህራሄ እና ድጋፍ ያላትን ልባዊ ምስጋና በደብዳቤ ገልጻለች። ይሁን እንጂ የእስራኤል ሚዲያዎች ከእገታ ተመላሾችን ታሪክ ይዘው በመውጣት በአሰቃቂ አያያዝ ውስጥ እንደቆዩ በማጋለጥ የሀማስን ተግባር ለዓለም እያሳወቁ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ባደረጉት ውይይት በጋዛ ላይ ያሳዩት አቋም ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል። ትራምፕ እንዳሉት አሜሪካ ጋዛን ለመቆጣጠር እንደምትፈልግ መግለፃቸው ብዙዎችን (በተለይ ፍልስጤማውያንን) አስቆጥቷል። ፍልስጥኤማውያንን ከጋዛ አስወጥቶ ጋዛን እንደ አዲስ እንደሚገነቧት የተናገሩት ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው የታጋቾችን ልውውጥ ሊያስተጓጉለው እንደሚችል እየተዘገበ ነው።
ቢቢሲ እንደዘገበው ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ትግበራ ከቀናት በኋላ ይጀምራል፤ በዚህም የቀሩ 65 እስራኤላውያን እንደሚለቀቁ ይጠበቃል። ነገር ግን ታጋቾቹ የሚፈቱት ሁለቱ ወገኖች ሁለተኛውን ምዕራፍ ለመፈረም ከተስማሙ ብቻ ነው። አሁን አሜሪካ ካሳየችው ያልተጠበቀ አቋም በኋላ ሁለተኛው ምዕራፍ ይፈፀም ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።
(መሰረት ቸኮል )
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም